ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮ ገበታ *999# አማካኝነት የድምፅ፣ የኢንተርኔት እንዲሁም አጭር የፅሁፍ መልዕክት አገልግሎቶችን ለክቡራን ደንበኞቹ በቅናሽ ዋጋ ማቅረቡ የሚታወቅ ሲሆን በርካታ ደንበኞችም የጥቅል አገልግሎቱን በመግዛት በቅናሹ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ህጋዊ አካሄድ ወደ ጎን በመተው በህገወጥ ተግባር ላይ ከተሳተፉ ጥቂት የተቋሙ ሰራተኞች እና ተባባሪ ግለሰቦች የሞባይል ጥቅል አገልግሎት በመግዛት ወይም ስጦታ በመቀበል ተሳትፈው የተገኙ ብዛታቸው 5796 የሆኑ ደንበኞች የሞባይል አገልግሎት ጥሪ ማድረግ እንዳይችሉ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ኩባንያችንም በደንበኞች ዘንድ የነበረውን የግንዛቤ ክፍተት ከግምት ውስጥ በማስገባት የጥቅል አገልግሎቶችን በህገወጥ መንገድ ሲገዙ ወይም በስጦታ ሲቀበሉ የነበሩ ደንበኞችን የሞባይል አገልግሎት ቁጥር ከመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ጋር የከፈተ ሲሆን ፤ የጥቅል አገልግሎቱን በመሸጥና ተያያዥነት ባላቸው ተግባሮች ተሳትፎ የነበራቸው የተቋሙ ሠራተኞችና ተባባሪ ግለሰቦችም ጉዳይ በህግ አግባብ እየታየ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ክቡራን ደንበኞች ኩባንያችን በኢትዮ ገበታ *999# ወይንም በሽያጭ ማዕከሎቹ ከሚያቀርባቸው የጥቅል አገልግሎቶች በስተቀር ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሞባይል ጥቅል አገልግሎት መግዛት፣ ስጦታ መላክም ሆነ መቀበል ከአገልግሎት መቋረጥ በተጨማሪ በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን እናስገነዝባለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ ክቡራን ደንበኞች በህዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ የቴሌኮም ማጭበርበር ተግባሮችን በተመለከተ መረጃ በመስጠት የዘወትር ትብብራችሁን እንድታደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡