ኢትዮ ቴሌኮም በአጭር ቁጥር አማካኝነት መረጃና የተለያዩ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ አጋር ድርጅቶች ጋር ሲሰራ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን ከአጋር ድርጅቶች መካከል አንዳንዶቹ ከገቡት ስምምነት ውጭ ያለደንበኛው ፈቃድ ተደጋጋሚና አሰልቺ አጭር የፅሁፍ መልዕክቶችን በመላክ በደንበኞች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ሲፈጥሩ እንደነበረ ይታወሳል ፡፡

በዚሁ መሠረት ኢትዮ ቴሌኮም ለችግሩ ዋነኛ ምክንያት የነበረውን የአሰራር ክፍተት በመለየት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጥ በዚህ ድርጊት ላይ ተሳታፊ የነበሩ አጋር ድርጅቶችን ውል ከማቋረጡም በተጨማሪ ለአዲስ አጋር ድርጅቶች የአጭር ቁጥር ሽያጭ አገልግሎት ለጊዜው እንዲቆም ማድረጉ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም በአጭር ቁጥር አማካኘነት አገልግሎት የሚሰጡ አጋር ድርጅቶች አጭር የፅሁፍ መልዕክቶችን ፈቃዳቸውን ለገለፁ ደንበኞች ብቻ መላካቸውን መቆጣጠር የሚያስችል እንዲሁም ያለደንበኛው ፈቃድ መልዕክት በሚልኩ ድርጅቶች ላይ አፈጣኝ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል በሲስተም የታገዘ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል፡፡

በዚሁ መሠረት የአጭር ቁጥር አገልግሎት ለመግዛት ፕሮፖዛል አስገብታችሁ በመጠባበቅ ላይ የምትገኙ አዲስ አጋር ድርጅቶች በአካል ቀርባችሁ ውል መፈፀም የምትችሉ ሲሆን ቀደም ሲል አገልግሎት ስትሰጡ የነበራችሁና በተፈጠረው ችግር ምክንያት ውል የተቋረጠባችሁ ነባር አጋር ድርጅቶች የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በሟሟላት ውል ማደስ የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን ፡፡