ኢትዮ ቴሌኮም ባለአክሲዮኖቹ አክሲዮናቸውን በሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ እንዲያስተዳድሩ፣ እንዲገዙና እንዲሸጡ ማስቻሉን በታላቅ ደስታ ያበስራል!

CEO at ESX

መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅዱ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን በማድረግ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ ከወሰዳቸው ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች መካከል የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ማቋቋም እንዲሁም ዜጎች በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ማስቻል ይገኝበታል።

ይህን የመንግሥት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የወጡ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ለ132 ዓመታት በትጋት ሲያገለግል የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት ከልማት ድርጅትነት ወደ አክሲዮን ማኅበርነት ተቀይሯል። በዚህም በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን መመሪያ መሠረት የመጀመሪያውን የአክሲዮን ሽያጭ በስኬት ማከናወን ችሏል።

በዚሁ መሠረት የኢትዮ ቴሌኮም የ10 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ሽያጭ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ 47,377 ዜጎች በድምሩ 10.7 ሚሊዮን አክሲዮኖችን በማቅረብ ለሕዝብ ይፋ ማድረጋችን ይታወቃል። ኩባንያችን ባለፉት ወራት ባለአክሲዮኖች የተቋማችን ባለቤት የሚሆኑበትን ማረጋገጫ ለመስጠት የሚያስችሉ መጠነ-ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ በተለይም የባለአክሲዮኖችን መረጃዎች (KYC) በመመርመር እንዲሁም ከባለአክሲዮኖች ጋር በመነጋገር ያልተሟሉ መረጃዎችን የማሟላት ተግባራትን አከናውኗል።

በተጨማሪም ባለአክሲዮኖች በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ መደላድሎችን ለመፍጠር፣ የተሸጡ አክሲዮኖች ድልድል በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እንዲጸድቅና የተደለደሉ አክሲዮኖች በማዕከላዊ የሰነዶች ሙዓለ ነዋዮች ግምጃ ቤት (Central Securities Depository) እንዲመዘገቡ ተደርጓል።

በዚህም መሠረት አጠቃላይ አክሲዮን ከገዙ 47,377 ዜጎች ውስጥ 45,366 (95.8 በመቶ) የሚሆኑት የባለቤትነት ማረጋገጫና አክሲዮኖችን ወደ ዲጂታል የመቀየር (Dematerialization) ሂደታቸውን ሙሉ በሙሉ አጠናቀዋል። እነዚህ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሂደታቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች በገንዘብ ሲሰላ 3.04 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 10.1 ሚሊዮን አክሲዮኖች ባለቤት መሆናቸው ተረጋግጧል።

በመሆኑም በዛሬው ዕለት፣ የኢትዮ ቴሌኮም ባለአክሲዮኖች በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ (ESX) ላይ አክሲዮናቸውን ማንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ዝግጅት መጠናቀቁንና በይፋ ለግብይት ዝግጁ መሆናቸውን በታላቅ ደስታ እናበስራለን።

ባለአክሲዮኖች አክሲዮኖቻቸውን ተፈጻሚነት ባላቸው ህጎች መሠረት የመሸጥ፣ የመግዛት እንዲሁም የማስተላለፍ (Transfer) መብት የሚያገኙ ይሆናል። አክሲዮኖቻቸውን በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ ለመሸጥም ሆነ ተጨማሪ ለመግዛት፤ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ከተሰጣቸው አገበያዮች ወይም የኢንቨስትመንት ባንኮች (Licensed investment bank, Brokers/Dealers) ዘንድ በመቅረብ የንግድ አካውንት መክፈት የሚኖርባቸው መሆኑን እንገልጻለን።

የባለቤትነት ድርሻቸውን ወደ ዲጂታል የመቀየር (Dematerialization) ሂደት ያጠናቀቁ ባለአክሲዮኖች፤ የባለቤትነት መብታቸው ከያዝነው በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ የሚከበርና የሚጠበቅላቸው ይሆናል።

ኩባንያችን የያዝነውን በጀት ዓመት ማጠቃለያ አፈጻጸምና የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት ለደንበኞቹና ለባለአክሲዮኖች ይፋ በማድረግ በመጪው በጀት ዓመት የመጀመሪያውን የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ (AGM) የሚጠራ ሲሆን፤ በዚሁ ታሪካዊ መድረክ ላይ የትርፍ ክፍፍል (Dividend) እና ሌሎች ስትራቴጂያዊ ውሳኔዎች ለባለድርሻዎች ይፋ ይደረጋሉ።

በሌላ በኩል፣ በብሔራዊ መታወቂያ መረጃ አለመሟላት ምክንያት ገና ያልተረጋገጡ 1,646 ባለአክሲዮኖች መረጃዎቻቸውን በአፋጣኝ እንዲያሟሉ ኩባንያችን ጥሪ እያቀረበ፣ በቀጣይም እነዚህን መረጃዎች የማጥራትና የማደራጀት ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል። እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም አክስዮኖችን ለመግዛት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን የማያሟሉ 248 (105 ሺህ አክሲዮኖች) የአክስዮን ግዢ ጥያቄ አቅራቢ የውጪ ዜጎች የከፈሉት ገንዘብ ተረጋግጦ ተመላሽ ይደረጋል።

ባለአክሲዮኖች ስለ ግብይት ሂደቱ፣ ስለ ዕለታዊ የገበያ መረጃዎችና ስለ አክሲዮናቸው ወቅታዊ ሁኔታ በኢትዮ ቴሌኮም ድረ-ገጽ (www.ethiotelecom.et) በሚገኘው የኢንቨስተር ሪሌሽንስ ፖርታል አማካኝነት በቀላሉ መከታተል ይችላሉ። በተጨማሪም፣ ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ ወይም ድጋፍ የሚፈልጉ ባለአክሲዮኖች በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀውን 128 የጥሪ ማዕከል በመጠቀም ወይም በዋና መሥሪያ ቤታችን በሚገኘው የኢንቨስተር ሪሌሽንስ ቢሮ በአካል በመገኘት አስፈላጊውን መረጃ ማግኘት የሚችሉ መሆኑን እናስታውቃለን።

የኢትዮ ቴሌኮም የባለቤትነት ድርሻ ሽያጭ ሀገራዊ የካፒታል ገበያ ሥርዓትን ለማጠናከርና ዜጎችን የሀብት ባለቤት ለማድረግ የተወሰደ ታሪካዊ እርምጃ ሲሆን፤ ይህም ጉዞ በስኬት ተጠናቆ ባለአክሲዮኖች በሁለተኛ ገበያ ላይ አክሲዮኖችን በመግዛት፣ በመሸጥ ወይም ማስተላለፍ መቻል ዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በር የሚከፍት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው። ለዚህ ስኬታማ ጉዞ በሥነ-ምህዳሩ ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት እስካሁን ላደረጉት ድጋፍ እያመሰገንን፤ በቀጣይም የካፒታል ገበያ ሥርዓቱ የታለመለትን ሀገራዊ ስኬት እንዲያመጣ የተቀናጀ የጋራ ርብርብ ወሳኝ መሆኑን እንገልጻለን።

 

ግንቦት 18 ቀን 2018 ..
ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives