ኢትዮ ቴሌኮም በየጊዜው አዳዲስ አገልግሎቶችን በማቅረብ የደንበኞቹን እርካታ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እያደረገ ያለውን ጥረት በመቀጠል ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ (Long Term Evolution-Advanced) የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ የሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀም ከፍተኛ በሆነባቸው ቦታዎች ከጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ አዋለ፡፡

በተጨማሪም ኩባንያው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተወሰኑ የአዲስ አበባ አካባቢዎች እየሰጠ የሚገኘውን የ4G ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት በመላው አዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ደንበኞቹ ተደራሽ እንዲሆን የኔትወርክ ማስፋፊያ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ደንበኞቻችን ከአሁን በኋላ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎትን በሁሉም የአዲስ አበባ አካባቢዎች ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

የኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ከደረሰባቸው የልህቀት ውጤቶች አንዱ ሲሆን ይህ አገልግሎት ከፍተኛ የዳታ መጠን ያላቸውን መረጃዎች ለመላክ፣ ቪዲዮዎችን፣ አፕልኬሽኖችን፣ ምስሎችን፣ ለመጫንና ለማውረድ እንዲሁም የቀጥታ ስርጭቶችን በከፍተኛ ፍጥነት ለማሰራጨት የሚያስችል አገልግሎት ነው፡፡

የኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀም በሚበዛባቸው በቦሌ አየር ማረፊያ፣  ቦሌ ፍሬንድሺፕ፣ ቦሌ መድሃኒዓለም፣ ቦሌ አትላስ፣ መስቀል አደባባይ፣ ስቴዲየም፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና መ/ቤት፣ ካዛንቺስ፣ አራት ኪሎ (አንድነት ፓርክ)፣ ስድስት ኪሎ፣ ልደታ (ኢ.ሲ.ኤክስ)፣ አሮጌው አየር ማረፊያ (Old Airport)፣ አፍሪካ ህብረት፣ እና የዓለም የምግብ ድርጅት (FAO) መ/ቤት የሚገኝባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡

የኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ደንበኞቻችን ቀፎዎቻቸው፣ የዋይፋይ ሞደሞቻቸው፣ ዶንግሎቻቸው፣ ታብሌቶቻቸው እና ሲም ካርዶቻቸው አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚያስችሉ መሆኑን ለማረጋገጥ በአቅራቢያቸው የሚገኙ የሽያጭ ማዕከላትን መጎበኘት ወይም ዝርዝር መረጃዎችን በwww.ethiotelecom.et ማግኘት ይችላሉ፡፡

 

ኢትዮ ቴሌኮም

ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.