የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና የሁዋዌ ሰሜን አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሚስተር ሊ ሸን ከሥራ አመራር ቡድኖቻቸው ጋር በመሆን፣ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ እና የሁለቱ ኩባንያዎች ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት ስትራቴጂአዊ ውይይት አካሂደዋል። ውይይቱ በዋነኝነት ትኩረቱን ያደረገው የኢትዮጵያን የኢንተርፕራይዝ እንዲሁም የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች (SMEs) ገበያን በፈጠራ የታገዙ የዲጂታል መፍትሄዎችን በመጠቀም ማሳደግ ላይ ነው።
ይህ ውይይት የኢትዮ ቴሌኮምን የ“ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂ መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ የሁለቱን ወገኖች አጋርነት ከተለመደው የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት ዝርጋታ ባለፈ ወደ ሰፊ የንግድ፣ የፈጠራና የዲጂታል ሥነ-ምህዳር (Ecosystem) ትብብር ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጓል። ሁለቱም ኩባንያዎች ለንግድ ተቋማት፣ ለማህበረሰቡ እና ለአጠቃላይ የዲጂታል ኢኮኖሚው ዘላቂ እሴት በመፍጠር የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በጋራ ለመምራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ወቅት ከተነሱት መካከል፣ የላቀ ትስስርን (Advanced Connectivity)፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግን (Cloud Computing)፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI)፣ የሳይበር ደህንነትን (Cybersecurity)፣ የነገሮች በይነመረብን (IoT)፣ የዳታ ሴንተር አገልግሎቶችን እና የተለያዩ የዲጂታል ፕላትፎርሞችን በማቀናጀት በቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ ያሉ ተቋማትን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሚያፋጥኑ እና ለተወሰኑ ዘርፎች ተለይተው የተዘጋጁ የተቀናጁ የዲጂታል መፍትሄዎችን በጋራ ማልማት የሚሉት ቁልፍ ጉዳዮች ይገኙበታል።
በተጨማሪም የሁለቱ ተቋማት አመራሮች ፈጠራ የታከለባቸው የንግድ መፍትሄዎችን ከቴሌብር ጋር በማቀናጀት ለኢንተርፕራይዞችና ለአነስተኛና መካከለኛ ንግዶች ምቹ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል። ይህም የዲጂታል ክፍያዎችን፣ የፋይናንስ አገልግሎቶችን፣ የንግድ ሥራ አመራር መሣሪያዎችን፣ የኢ-ኮሜርስ (e-commerce) እና ሌሎች እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶችን በማቅረብ ንግዶች ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ፣ የገበያ ተደራሽነታቸውን እንዲያሰፉ እና ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያስችላቸዋል።
የሀገር ውስጥ የፈጠራ ሥራዎችን ማበረታታት እና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥን ማረጋገጥ ያለውን የጎላ ጠቀሜታ በመገንዘብ፤ በውይይቱ ወቅት የሀገር ውስጥ ሶፍትዌር ልማትን፣ እንደ ፍላጎት የሚበጁ መፍትሄዎችን ማዘጋጀትን (Solution Customization)፣ የስርዓት ውህደትን (System Integration) እና የቴክኒክ ድጋፍን ማጠናከር ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። ይህም የሚከናወነው የሀገር ውስጥ መሐንዲሶችን አቅም በማሳደግ፣ የመፍትሄ አውጭዎች (Solution Architects) ሚናን በማጎልበት እና በምርምርና ልማት (R&D) ትብብር አማካኝነት ነው።
በተጨማሪም ፈጠራ የታከለባቸው የፋይናንስ አማራጮችን (Innovative Financing Models) እና ሰፋፊ የገበያ ዕቅዶችን በመጠቀም፣ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን ስማርት ስልኮች እና የዲጂታል መሣሪያዎችን ተደራሽነት ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው ዕድሎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ሁለቱም ኩባንያዎች ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ስማርት መሣሪያዎችን በሰፊው ተደራሽ ማድረግ፣ የዲጂታል አካታችነትን (Digital Inclusion) ለማፋጠን እና ማህበረሰቡ በኢትዮጵያ እያደገ ባለው የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ ለማስቻል መሠረታዊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ከቴክኖሎጂ እና ከንግድ ዕድገት ባሻገር፣ ሁለቱም ወገኖች በአካባቢ፣ በማህበራዊ ጉዳዮች እና በድርጅታዊ አስተዳደር (ESG) እንዲሁም በማህበራዊ ኃላፊነት (CSR) ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል። በውይይቱም የዲጂታል አካታችነትን፣ ዲጂታል ክህሎትን (Digital Literacy)፣ የገጠር ትስስርን፣ ዲጂታል ትምህርትን፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን እና ዘላቂ የዲጂታል መሠረተ ልማትን በጋራ ለማስፋፋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የተመካከሩ ሲሆን፣ ይህም ትርጉም ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠ ሆኗል።
የሁለቱ ኩባንያዎች አመራሮች አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን አጠቃቀም ይበልጥ ለማፋጠን በግብይት ተግባቦት (Marketing Communications)፣ በደንበኞች ግንዛቤ ማሳደግ እና በዲጂታል ንቃተ-ህሊና ግንባታ ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል። ይህ የጋራ ጥረት ትኩረት የሚያደርገው የፈጠራ ግብይት ዘመቻዎችን፣ የማስተማሪያ ይዘቶችን፣ የማስተዋወቂያ ቁሳቁሶችን እና የደንበኞች ተሳትፎ መድረኮችን በማዘጋጀት ላይ ሲሆን፤ ይህም ቴሌብርን እና የኢንተርፕራይዝ ዲጂታል መፍትሄዎችን ጨምሮ የኢትዮ ቴሌኮም እያደጉ ያሉ የዲጂታል ምርቶች እና አገልግሎቶች ግንዛቤን ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ከፍ ለማድረግ ያስችላል።
ሁዋዌ ኩባንያ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ መሪ የቴክኖሎጂ ዲጂታል አገልግሎት ሰጪነት (TechCo) ለመለወጥ ለሚያደርገው ጉዞ ያለውን የማይናወጥ ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጧል። ኩባንያው በኢንተርፕራይዝ ፈጠራ፣ በአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት (SME) አቅም ግንባታ፣ በዲጂታል ሥነ-ምህዳር ልማት፣ በመፍትሄዎች የጋራ መፈጠር (Solution Co-creation) እና በቀጣናዊ ዕድገት ዕድሎች ዙሪያ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለውን ዝግጁነት የገለጸ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ፈጠራውን ከኢትዮጵያ አልፎ ወደ ጎረቤት ሀገራት እና ወደ አጠቃላይ አፍሪካ ገበያ ለማስፋፋት ያለውን ትልቅ ራዕይ የሚደግፍ ነው።
ውይይቱ የተጠናቀቀው እነዚህን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች በተግባር ወደሚታዩ ተጨባጭ ሥራዎች ለመለወጥ በተደረገ የጋራ ስምምነት ነው። ይህም የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን፣ ለኢንተርፕራይዞችና ለአነስተኛና መካከለኛ ንግዶች አዳዲስ ዕድሎችን ለመክፈት፣ የዲጂታል አካታችነትን ለማጠናከር እና መላውን የአፍሪካ ገበያ ማገልገል የሚችሉ ሰፋፊ የዲጂታል መፍትሄዎችን ለመፍጠር ያስችላል።




