ኢትዮ ቴሌኮም እና ኢንስፐር ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያን የዲጂታል መሠረተ ልማት ሽግግር ለማፋጠን የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ውይይት አደረጉ

Ethio telecom and Inspur Software Technology Explore Strategic Partnership to Accelerate Ethiopia's Digital Infrastructure Transformation

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በቦርድ ሊቀመንበሩ ሚስተር ሊን ሹዋይ ከተመራው የኢንስፐር ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ (Inspur Software Technology Co., Ltd.) ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል። በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የሻንዶንግ ሃይ-ስፒድ ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ (Shandong Hi-Speed Road & Bridge International Engineering) ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጋኦ ዢንጂ መገኘት፤ የላቁ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ግንባታ ጋር የሚያቀናጅ ሁለንተናዊ አጋርነት ለመፍጠር ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ ነው።

የኩባንያችንን “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂ መሠረት ያደረገው ይህ ውይይት፤ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ለማፋጠንና የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማጠናከር የቀጣዩ ትውልድ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር በሚያቀናጅ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። ትብብሩ እጅግ የላቁ የኮምፒውቲንግ አቅሞችን (Cutting-edge computing capabilities) ከጠንካራ ፊዚካል መሠረተ ልማት ጋር በማጣመር፤ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሀገራዊ ልማትን የሚደግፍ የማይበገር፣ ኢንተለጀንት እና ለመጪው ጊዜ ዝግጁ የሆነ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር መፍጠርን ያለመ ነው።

የትብብሩ አንዱ አካል በመሆን ኢንስፐር ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ በዲጂታል መሠረተ ልማት ያለውን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም፤ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዝግጁ የሆኑ የዳታ ማዕከል መፍትሔዎችን፣ የክላውድ ኮምፒውቲንግ መድረኮችን እንዲሁም የላቁ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በመቅረጽና በመዘርጋት ረገድ የበኩሉን አስተዋፅዖ ያበረክታል። እነዚህ አቅሞች የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት (Sovereign digital infrastructure) ያጠናክራሉ፣ ሀገራዊ የኮምፒውቲንግ አቅምን ያሳድጋሉ፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚመሩ ፈጠራዎችን ይደግፋሉ እንዲሁም የቀጣዩን ትውልድ የዲጂታልና የኢንተርፕራይዝ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ያስችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ውይይቱ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የዲጂታል አጠቃቀምን ለማፋጠን በማለም፤ ከኢትዮጵያ ገበያ ጋር የተጣጣሙ የሀገር ውስጥ የዲጂታል መተግበሪያዎችን (Localized digital applications) እና ዘርፍ-ተኮር መፍትሔዎችን በጋራ ለማልማት ባሉ ዕድሎች ላይም መክሯል። በተጨማሪም ኩባንያዎቹ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ኮምፒውቲንግ መሠረተ ልማት፣ በክላውድ አገልግሎቶች፣ በኢንተርፕራይዝ ዲጂታል ሽግግር፣ በዘመናዊ የኢንዱስትሪ መፍትሔዎች፣ በክህሎት ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በምርምርና ፈጠራ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተወያይተዋል። እንዲሁም በየዘርፉ ያሏቸውን ጥንካሬዎች በመጠቀም ትብብራቸውን ከኢትዮጵያ ወሰን ውጭ በማስፋፋት፣ በመላው አፍሪካ ስትራቴጂያዊ ዕድሎችን በጋራ ለመጠቀምና ለቀጠናዊ የዲጂታል ሽግግር፣ ለዲጂታል አካታችነትና ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ለማበርከት ያላቸውን ፍላጎት ዳስሰዋል።

በውይይቱ ወቅት ሚስተር ሊን ሹዋይ እና ሚስተር ጋኦ ዢንጂ የኢትዮ ቴሌኮምን አርቆ አሳቢ አመራር፣ አስደማሚ የለውጥ ጉዞ እና ከተለመደው የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ወደ አፍሪካ መሪ የዲጂታል አገልግሎቶች እና ቴክኖሎጂ ኩባንያነት ለመሸጋገር ያስመዘገባቸውን ስኬቶች አድንቀዋል። ኩባንያው ለተከተለው ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ፣ ላስመዘገበው ፈጣን የዲጂታል ሽግግር፣ በላቁ ቴክኖሎጂዎች ላይ ለሚያደርገው ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት እና የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ በመምራት ረገድ እየተጫወተ ላለው ሚና ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። በኢትዮ ቴሌኮም የወደፊት ጉዞ ላይ ያላቸውን እምነት በማረጋገጥም፣ ከአፍሪካ ገበያ አንጻር የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለመመሥረት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ገልፀዋል።

በመጨረሻም ዋና ሥራ አስፈጻሚያችን ፍሬሕይወት ታምሩ የሚመለከታቸው የቴክኒክ ቡድኖች አጠቃላይ የትብብር ማዕቀፍ እና የትግበራ ፍኖተ-ካርታ (Implementation Roadmap) ዝግጅትን እንዲያፋጥኑ ስትራቴጂያዊ መመሪያ ሰጥተዋል። ይህ የቅድመ-ዝግጅት ሥራ አጋርነቱን በይፋ ለማፅደቅና የኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን የዲጂታል መጻኢ ዕድል የሚቀይሩ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸውን ስትራቴጂያዊ ኢኒሼቲቮች ወደ ትግበራ ለማስገባት በቀጣይነት በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ለሚደረገው ውይይት መንገድ የሚጠርግ ይሆናል።

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives