የኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከአፍሪካ ልማት ባንክ (AfDB) ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር ሚስተር ሰለሞን ኳይኖር እና ከባንኩ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ጋር ስትራቴጂያዊ ውይይት አድርገዋል። ውይይቱ የኩባንያችንን “ቀጣዩ አድማስ: ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂ ትግበራ እና የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለመደገፍ የታለሙ የሁለትዮሽ አጋርነቶችን እና የትብብር መስኮችን ለመገምገም ያለመ ነው።
በውይይቱም ሁለቱም ተቋማት የኢትዮጵያን የዲጂታል እና የቴሌኮም መሠረተ ልማት ለማስፋፋትና ለማዘመን፣ የዲጂታል ፕላትፎርሞችና ሥነ-ምህዳሮችን ለማጠናከር እንዲሁም በመላው አገሪቱ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን፣ የቢዝነስ ድርጅቶችንና ተቋማትን አቅም የሚያሳድጉ የፈጠራ ዲጂታል አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማስፋፋት የተጀመሩ የፋይናንስና የስትራቴጂ ውይይቶችን ሂደት ገምግመዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚያችን ለአፍሪካ ልማት ባንክ አመራሮች በ“ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂ እየተመዘገቡ ስለሚገኙ ጉልህ ስኬቶች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይም ስለኩባንያችን ቀጣይ ሁለንተናዊ ዕድገትና በሁሉም የቢዚዝነስና ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ዘርፎች የታየውን ለውጥ አብራርተዋል። ኩባንያያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር ወደ መሪ ዲጂታል ሶሉሽኖችና ፕላትፎርም አቅራቢነት ያደረገውን የተሳካ ሽግግር በአድናቆት ገልጸዋል።
ይህም ቀጣይነት ባለው ዘመናዊ የቴሌኮም መሰረተ ልማት፣ የክላውድ አገልግሎቶች፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዙ ቴክኖሎጂዎች፣ የፊንቴክ (fintech) ስነ-ምህዳር እና ዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ እየተካሄደ ባለው ኢንቨስትመንት የታገዘ መሆኑ እየተመዘገበ ለሚገኘው ውጤት የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ውይይቱ ኩባንያችን በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን ከኮኔክቲቪቲ ባሻገር ስነ-ምህዳር በስፋት የዳሰሰ ሲሆን፤ ይህም እንደ ቴሌብር፣ ዘመን ገበያ እና ዘኔክሰስ (znexus) ያሉ ስትራቴጂያዊ የዲጂታል ፕላትፎርሞችን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህም ለፋይናንስ ተደራሽነት፣ ለዲጂታል ቢዝነስ፣ ለስራ ፈጠራ፣ ለፈጠራ ስራዎች እና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ተመልክቷል።
ዋና ስራ አስፈጻሚያችን ኩባንያችን በቀጣይ ትውልድ የዲጂታል መሰረተ ልማት ላይ እያደረገ ያለውን ኢንቨስትመንት ያብራሩ ሲሆን፤ ይህም የ4ጂ እና 5ጂ ማስፋፊያ፣ የገጠር ኮኔክቲቪቲ/ ተደራሽነት፣ የክላውድ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት አቅም ግንባታ፣ የአረንጓዴ እና የሃይል ቆጣቢ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም እንደ የሆራይዘን ፋይበር ፕሮጀክት ያሉ ድንበር ተሻጋሪ ኢኒሼቲቮችን እንደሚያካትት አብራርተዋል፡፡ ኢኒሼቲቮቹ ኢትዮጵያ በቀጣናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን በጎ ተጽህኖ እና እድገት የሚያጠናክሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ክቡር ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን ኳይኖር እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ከፍተኛ አመራሮች የኩባንያችንን አስደናቂ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እና የሥራ ክንውን እድገት አድንቀዋል። ከፍተኛ አመራሮቹ ኩባንያችን በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስኬት ታሪኮች መካከል አንዱ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፣ አመራሮቹ የአፍሪካ ልማት ባንክ ስትራቲጂያዊ ትብብርን ለማጠናከር እንዲሁም ግዙፍ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታን፣ ሁሉን አቀፍ የዲጂታል አካታችነትን፣ ፈጠራን እና የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘላቂ የፋይናንስ ማዕቀፎችን ለመዘርጋት ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ይህ ውይይት የአፍሪካን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ፣ ቀጣናዊ የዲጂታል ትስስርን እና አካታች የሆነ የአፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚን የመገንባት ሰፊ ራዕይን ጨምሮ አህጉራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማሳካት ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ያንጸባረቁበት ነው፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ኩባንያችን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የጀመሯቸውን የጋራ የትብብር ስራዎችን ለማፋጠን፣ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማሳለጥ እና የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚያስቀጥሉ፣ በዜጎች ህይወት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር እንዲሁም በመላው አህጉሪቱ ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ እድገት አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።




