Smart Mobility, Seamless Payments: Powering Ethiopia’s Expressway with telebirr
የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማፋጠን ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ዘመናዊ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት በዛሬው ዕለት ተግባራዊ አድርጓል። ይህ የተቀናጀ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና ባለው የአዲስ አበባ – አዳማ የፈጣን መንገድ ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማለትም የመንገድ አገልግሎት ክፍያዎችን፣ የቅጣት ክፍያዎችን እና ቶሎ (TOLO) የተሰኘና በቴሌብር ሱፐር አፕ ላይ የተመሠረተ የሂሳብ መሙያ ሚኒ አፕ አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ በማቀናጀት የተጠቃሚዎችን ተሞክሮ ለማላቅ የሚያስችል ሶሉሽን ነው፡፡
ይህም የ“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂን ከማሳካት ባለፈ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን ግልጽነት፣ የአሠራር ቅልጥፍና እና አካታችነት የሰፈነበት የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው።
አዲሱ የአገልግሎት እና የቅጣት ክፍያ አስተዳደር ሥርዓት ቀደም ሲል የነበረውን አድካሚና በእጅ የሚከናወን አሠራር ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ የአውቶሜሽን አሠራር የሚተካ ሲሆን፤ በቴሌብር ሱፐር አፕ (telebirr SuperApp) ውስጥ የሚገኘው እና በ RFID ሲስተም በመታገዝ TOLO Mini App ክፍያዎችን በራስ-አገዝ ቴክኖሎጂ ተቀናሽ በማድረግ ተሽከርካሪዎች ለክፍያ ሳይቆሙ በቀጥታ እንዲያልፉ (Non-stop passage) በማድረግ ጉዞውን ፈጣን፣ ምቹና እንከን-የለሽ የሚያደርግ ነው፡፡
- የአገልግሎት እና የቅጣት ክፍያ አሠራር ሥርዓትን ማዘመን
ቀደም ሲል የኢንተርፕራይዙ ክፍያዎች በጥሬ ገንዘብ፣ በባንክ ዝውውር እና መረጃዎችን ወደ ሲስተም በእጅ በማስገባት (manual entry) ሂደቶች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለሥራ መጓተት፣ ለገቢ ብክነትና በክፍያ በሮች ላይ ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ይህ አዲሱ የቴሌብር የተቀናጀ ሥርዓት እነዚህን ነባር አድካሚ የአሠራር ሂደቶችን በማዘመን የሚከተሉትን አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ለማከናወን ያስችላል፡፡
- መሠረታዊ የመንገድ አገልግሎቶች፦ የንብረት ውድመት ካሳ፣ የክሬን (Towing) እና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ክፍያዎችን ያለምንም እንግልት በዲጂታል መንገድ ማከናወን፣
- አጠቃላይ የቅጣት ክፍያዎች፦ የጭነት ክብደት ገደብ መጣስ፣ ያለፈቃድ ወደ ፈጣን መንገድ መግባት እና ሌሎች የትራፊክ ደንብ ጥሰት ክፍያዎችን በቀላሉ መፈጸም ያስችላል፣
- የላቀ የአሠራር ብቃት፦ የኢንተርፕራይዙ ማኔጅመንት የገቢ አሰባሰቡን በቅጽበት (Real-time) ለመከታተል፣ መረጃዎችን በአግባቡ ለመቆጣጠር እና ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራርን ለማስፈን ያስችለዋል።
- የቶሎ ሚኒ አፕ (የቶሎ አካውንት ክፍያ መሙያ)
ይህ አጋርነት ልዩ ልዩ አገልግሎት እና የቅጣት ክፍያዎችን ከማሳለጥ ባሻገር፣ በቴሌብር ሱፐር አፕ አማካኝነት ለቶሎ (TOLO) የኤሌክትሮኒክ ክፍያ (Electronic Toll Collection – ETC) አካውንት ፈጣን የዲጂታል ክፍያ መሙያ ሶሉሽን ያስጀመረ ሲሆን፣ ይህ አሠራር አሽከርካሪዎች ሳይስተጓጎሉ በቅጽበት ክፍያን በመፈጸም እንዲጓዙ ያስችላል፡፡ በተለይም፦
- ስማርት ትስስር (Smart Integration)፦ አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪዎቻቸው ላይ የ RFID ታግ (መለያ) በመለጠፍ እንዲሁም ምዝገባው ሲከናወን የተሽከርካሪው አካውንት መለያ (Account ID)፣ የቶል ካርድ መለያ እና የሰሌዳ ቁጥር በዲጂታል ዘዴ ለማስተሳሰር ያስችላቸዋል፡፡
- ቀላልና የተቀናጀ ትስስር (Seamless Binding)፦ አሽከርካሪዎች በቶሎ ሚኒ አፕ አማካኝነት የተሽከርካሪዎቻቸውን ዝርዝር መረጃ (Profile) ከቴሌብር አካውንታቸው ጋር በቀላሉ በማስተሳሰር እስከ 10 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን በቴሌብር ሱፐር አፕ አማካኝነት ለማስተዳደር እና ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች አሽከርካሪዎች ክፍያ ለመሙላት (Top-up) ያስችላቸዋል፡፡
- አውቶማቲክ የቶል ክፍያ አሰባሰብ፦ አሽከርካሪዎች ከቴሌብር ጋር በተሳሰረው የቶሎ ሚኒ አፕ ካውንታቸው ላይ በቂ ሂሳብ በመሙላት፣ ስርዓቱ የRFID ታጉን ከርቀት በመለየት ክፍያውን በቀጥታ በመቀነስ ተሽከርካሪው በቶል ጌቶች (መውጫዎች) ላይ መቆም ሳይጠበቅበት በፍጥነት እንዲያልፍ ያስችላል፡፡
የአሠራር ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና ልህቀትን ለማምጣት
ይህ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በቶል መንገዶች አስተዳደር ላይ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችል ሲሆን፣ በተለይም በማኑዋል የሚደረጉ የጥሬ ገንዘብ ክፍያዎችን እና የወረቀት ሥራዎችን በማስቀረት የሚከተሉትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ያስችላል፡-
- መጨናነቅ፦ በቶል ጌቶች /መግቢያ በሮች/ ላይ የሚፈጠርን የመጠበቂያ ጊዜ እና የትራፊክ መጨናነቅን ይቀንሳል፣
- ደህንነት፦ ከጥሬ ገንዘብ አያያዝ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ እንደ ስርቆት እና ማጭበርበር ያሉ ሥጋቶችን ያስቀራል፣
- ውጤታማነት፦ በእጅ/በማኑዋል የመረጃ ምዝገባ ወቅት የሚፈጠሩ የመረጃ ግድፈቶችን ከማስቀረቱም በላይ የሪፖርት መዘግየቶችንም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል፣
ለኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ (ETRE) የሚሰጣቸው ቁልፍ ጠቀሜታዎች
- በሁሉም የገቢ ምንጮች ላይ ቅጽበታዊ (real-time) በሆነ መንገድ እና ግልጽነት በተሞላበት ሁኔታ ማዕከላዊ ቁጥጥር ለማድረግ፣
- የቴሌብርን ሰፊ የደንበኛ መሠረት በመጠቀም የዲጂታል ክፍያ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለመጨመር፣
- በአውቶሜሽን አማካኝነት የአሠራር ቅልጥፍናን እና የገቢ ፍሰትን ለማሳደግ፣
- የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር፣
ለደንበኛው የሚሰጣቸው ቁልፍ ጥቅሞች
- አገልግሎቱን በቀን 24 ሰዓት፣ በሳምንት 7 ቀን፣ በማንኛውም ቦታና በማንኛውም ጊዜ ለማግኘት፣
- ምቹ፣ ፈጣን እና ለመጠቀም ቀላል መሆኑ፣
- ተጨማሪ የክፍያ አማራጮችን ማካተቱ፣
ኩባንያችን በ‘ቀጣዩ አድማስ‘ ስትራቴጂ በመመራት፣ ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ (ETRE) ጋር ያደረገው ይህ አጋርነት የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ዘመናዊ እና በመረጃ ወደታገዘ የዲጂታል አገልግሎት ለማሸጋገር የሚያስችል ሲሆን፣ በተለይም ኩባንያችን የቴሌብርን ሥነ-ምህዳር በመጠቀም የአሠራር ማነቆዎችን ከማስወገድ ባለፈ፣ የፋይናንስ እና የተቋማት አገልግሎቶች ተቀናጅተው የዜጎቻችንን ሕይወት የሚያሻሽሉበትን “ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር“ የተሰኘውን ኢኒሼቲቫችንን ዕውን ለማድረግ ያስችላል፡፡
ይህ ኢኒሼቲቭ የኢትዮጵያን ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ለማገዝ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን፣ ዲጂታል ፕላትፎርሞች አገራዊ መሠረተ-ልማቶችን እንዴት ማዘመን እንደሚችሉ እንደ ማሳያ የሚጠቀስ ነው። የኩባንያችን ትኩረት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ፍጥነት እና ቅልጥፍናን የሚያንፀባርቅ ምቹ የደንበኛ ተሞክሮ መፍጠር ላይ ሲሆን፣ ይህ አጋርነት ኢትዮጵያ በዲጂታል ወደተሳሰረች፣ አካታች እና በዲጂታል ወደበለጸገች ሀገር የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን ኩባንያችን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
ኢትዮ ቴሌኮም
ሚያዝያ 1 ቀን 2018 ዓ.ም.




