ኢትዮ ቴሌኮም የአረንጓዴ ኦፕሬተርነት ጉዞውን ይበልጥ በማጠናከር እንዲሁም በሃገር አቀፍ ደረጃ “ተስፋን እንትከል” እንዲሁም በኩባንያችን “ለአረንጓዴ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በኩባንያችን ደረጃ 250 ሺህ ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን ዕቅድ መሰረት በማድረግ በዛሬው ዕለት በመላው የሃገራችን ክፍሎች በሚገኙ የኩባንያው ጽ/ቤቶች የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሮችን በይፋ አስጀምሯል፡፡ ይህም ኩባንያችን በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የማህበረሰባችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስትራቴጂ ነድፎ (Sustainable Strategy) ከሚያከናውናቸው ቁልፍ የልማት ዘርፎች መካከል አንዱ ነው፡፡
በ8ኛው ዙር አገር አቀፍ አረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ መርሃ ግብር ኩባንያችን በኮርፖሬት፣ በዞን እና ሪጅን ደረጃ ከ3,500 በላይ የኩባንያው ሠራተኞችን እና አጋሮቻችን በማሳተፍ የችግኝ ተከላ ዘመቻ አካሂዷል፡፡ በዚህም መሰረት በኮርፖሬት እና ዞን ደረጃ እንጦጦ (ቁስቋም ማዞሪያ) አካባቢ በተዘጋጁ ቦታዎች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያከናወነ ሲሆን፣ 18 ሪጅኖች ደግሞ ሪጅኖቹ ከሚገኙባቸው መስተዳድሮች በተረከቧቸው ቦታዎች ላይ የችግኝ ተከላ ዘመቻ አካሂደዋል፡፡
ኩባንያችን የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን፣ የዲጂታል አካታችነትን፣ የሥራ እድል ፈጠራን፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ለሀገራችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም ኩባንያችን በአህጉራዊ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳደግ ያለመ የሶስት አመት “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” ቀርፆ ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ በማድረግ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
በተለይም ከአለም አቀፍ የዘላቂነት ግቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ የአየር ንብረት ጥበቃ ተሳትፎ ላይ ሀገራችን ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የምታደርገውን ግስጋሴ በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችሉ የአረንጓዴ መሰረተ-ልማቶችን (Green Infrastructure) በመገንባት ዘመን ተሻጋሪ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡: በዚህም ኩባንያችን የአረንጓዴ ኦፕሬተር (Green Operator) መርህን በመቀላቀል፣ በታዳሽ የኃይል ኢንቨስትመንቶች፣ ተጨማሪ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የኔትወርክ መሰረተ ልማት በመዘርጋት፣ የቅይጥ (Hybrid) ኃይል ስርዓቶችን እና ኃይል ቆጣቢ አረንጓዴ የዳታ ማዕከላትን በመገንባት የአካባቢ ጥበቃ ሚናውን እያጠናከረ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህም ውጤታማ የኃይል አጠቃቀም እና የካርቦን ልቀት ቅነሳን ማሳካት ችሏል።
ለአብነትም ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በስፋትና በፍጥነት በመተግበር 190 በፀሐይ ብርሃን ብቻ (Pure Solar) የሚሠሩ የቴሌኮም ጣቢያዎችን፣ 867 ቅይጥ የኃይል ሥርዓቶችን (Solar and Battery) እና 1,114 የሊቲየም-አዮን ባትሪ ማከማቻዎችን የገነባ ሲሆን፤ ይህም የናፍጣ ጀኔሬተሮችን የሥራ ሰዓት እስከ 40% ድረስ መቀነስ አስችሏል። በተጨማሪም 215 አዳዲስ የፀሐይ ኃይል (ሶላር) ጣቢያዎችን በመገንባት እና 774 ነባር ጣቢያዎችን በማሻሻል የታዳሽ ኃይል አሻራውን ያሰፋ ሲሆን፣ በዚህም በተለመዱ የኃይል ምንጮች ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ 12.72 MW ተጨማሪ የሶላር አቅም በመፍጠር አጠቃላይ የሶላር አቅማችንን 39.72 MW በማድረስ ለኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ኩባንያችን በአንድ ጊዜ 108 ተሽከርካሪዎችን መሙላት የሚያስችሉ ከ9 በላይ እጅግ ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች መገንባት የቻለ ሲሆን፣ እነዚህ ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ከጀመሩበት ከየካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ሀምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ፣ ከ481,112 በላይ ለሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት ችሏል፡፡ በዚህም 11,241,659.03 ኪሎዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ ይህም 15,447,411 ኪሎግራም ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቅ መከላከል ተችሏል፡፡ ይህም አበርክቶ ከ76,340 በላይ ዛፎችን ከመትከል ጋር ይነፃፀራል።
ኩባንያችን ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት (Green Development Project) በርካታ ስራዎችን ማከናወን ችሏል፡፡ በዚህም ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በታዋቂው Brand Africa 16ኛው ዓመታዊ የብራንድ አፍሪካ 100 ሽልማት ላይ ለማኅበረሰቡና ለአካባቢ ጥበቃ በጎ አስተዋጽኦ በማድረግ እጅግ ተወዳጅ የኢትዮጵያ ብራንድ (The Most Admired Ethiopian Brand Doing Good for Society and the Environment) ሽልማትን እና ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ደግሞ የ2025 የኢትዮጵያ አረንጓዴ ሽልማት (Ethiopian Green Award 2025) ዕውቅናን ማግኘት ችሏል፡፡
ኩባንያችን በማህበረሰባዊ ልማት ላይ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ስምንተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለችግኝ ተከላ፣ እንክብካቤ እና ጥበቃ ስራዎች ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የስራ ዕድል ይፈጥራል። ባለፉት ሰባት ዓመታትም በአጠቃላይ ከ24.8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በተጨማሪም እስካሁን የተተከሉ ችግኞችን በማፅደቅ ረገድ በአማካይ የ82.7 በመቶ ስኬት በማስመዝገብ፣ የተራቆቱ አካባቢዎችን በማልበስ እና በረሃማነትን በመከላከል ረገድ የሚደነቅ ስራ እያከናወነ ይገኛል።
ባለፉት ተከታታይ ሰባት ዓመታት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 889 አካባቢዎች ከ4.6 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራውን ሲያሳርፍ የቆየው ኩባንያችን፣ ዘንድሮም ስምንተኛውን ዙር መርሃ ግብር በመላ ሀገሪቱ 250,000 ችግኞችን ለመትከል፣ ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ ከ42.4 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የመደበ ሲሆን፣ ባለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታትም ለአካባቢ ጥበቃ እና ለአረንጓዴ ልማት ስራዎች በአጠቃላይ ከ159.9 ሚሊዮን ብር በላይ መዋለ ንዋይ አፍስሷል።
ሃገራችንን ለ132 ዓመታት በቁርጠኝነት በማገልገል ላይ የሚገኘው ኩባንያችን፣ የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ለመደገፍና የአስቻይነት ሚናውን ለመጫወት በየጊዜው አዳዲስ አገልግሎቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ ባሻገር ለማህበረሰባችን እና ለሃገራችን ፋይዳ ያላቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ፣ ሃገራዊና ማህበራዊ የጥምር ኃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም




