የኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በዜድ.ቲ.ኢ ኮርፖሬሽን ኤክስክዩቲቭ ቫይስ ፕሬዝደንት እና ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ሚስተር ዢ ጁንሺ ከተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር ስትራቴጂያዊ ውይይት አድርገዋል። ውይይቱ በተለይም በባርሴሎና በተካሄደው የሞባይል ወርልድ ኮንግረስ 2026 (MWC2026) ላይ የተፈረመውን ወሳኝ የኔትወርክ ማስፋፊያና ማዘመኛ ስምምነት አፈጻጸም ሂደትን ለመገምገም ያለመ ሲሆን ኩባንያችን በ”ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂው የዲጂታል መሠረተ ልማትን ለማፋጠን ያስቀመጠውን ራዕይ የሚያረጋግጥ ነው።
በውይይቱ ላይ እንደተገለጸው፣ በዜድ.ቲ.ኢ የፕሮጀክት ማዕቀፍ (ZTE circle) ሥር በሚገኙ 879 ጣቢያዎች (Sites) ላይ ሙሉ በሙሉ በተካሄደው የኔትወርክ ማዘመን ሥራ፤ በ462 የራን (RAN) ማዘመኛ ጣቢያዎች ላይ (ማለትም በ180 ጣቢያዎች ላይ የ-LTE ሌየሪንግ፣ በ248 ጣቢያዎች ላይ የ-LTE ማሻሻያዎች እና በ102 ጣቢያዎች ላይ ሙሉ በሙሉ የቅየራ (SWAP) ሥራዎችን ያካተተ)፣ የ237 የላቁ ማይክሮዌቭ (MW) ሊንኮች ማሻሻያ እና የ103 የአይፒ ራን (IP RAN) ጣቢያዎች ማስፋፊያ ሥራዎች በስኬት መጠናቀቃቸው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የዚሁ የኔትወርክ ማዘመኛ ፕሮጀክት አካል የሆኑት የ124 አዳዲስ ጣቢያዎች ግንባታ፣ በ272 ጣቢያዎች ላይ የ-U2100 መልሶ ማዘመን ሥራ እንዲሁም የ115 የገጠር ዲጂታል መፍትሔ ጣቢያዎች (Rural Solution Sites) ትግበራ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተብራርቷል።
ይህ የኔትወርክ ዝርጋታ የከፍተኛ ፍጥነት ኢንተርኔት ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ ያሰፋ ሲሆን፣ በዜድ.ቲ.ኢ ሰርክል የሚገኘውን የ4ጂ (4G) ሞባይል ኔትወርክ የሕዝብ ተደራሽነት ሽፋን ወደ 92% የሚያደርስ ነው። እነዚህ ጣቢያዎች አሁን ላይ በሁለንተናዊ መልኩ በማደግ ላይ ለሚገኘው የሀገራችን ኢኮኖሚ ጠንካራ የዲጂታል ማዕከል በመሆን በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የግንኙነት አቅም አሳድገዋል።
የኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የፕሮጀክቱን ስኬታማ አፈጻጸም አድንቀው፣ የ«ቀጣዩ አድማስ» ስትራቴጂ የአንደኛ ዓመት ግቦችን ለማሳካት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የኩባንያችን አመራር ዜድ.ቲ.ኢ ላስተዋወቀው ፈጠራ የታከለበት የፋይናንስ ሞዴል፣ ለቴክኒክ ብቃቱ እና የታቀዱትን የኔትወርክ ማዘመኛ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ለማጠናቀቅ ላሳየው ቁርጠኝነት ከፍተኛ አድናቆት ሰጥተዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚያችን ቀጣዩ የኔትወርክ ማዘመኛ እና የማስፋፊያ ምዕራፍ በታላላቅ ግቦች እንደሚቀጥል አጽንኦት የሰጡ ሲሆን፣ የዜድ.ቲ.ኢ ቡድንም ያላሰለሰ ድጋፉን በዘላቂነት እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም፣ ይህ ስትራቴጂያዊ አጋርነት የኔትወርክ ማሻሻያዎች በብቃትና በዘላቂነት እንዲከናወኑ በማድረግ፣ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የሀገሪቱን ከፍተኛ ጥራት ያለው የዳታ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካት አስችሏል።
የዲጂታል ተጠቃሚነት ክፍተትን ለማጥበብ ሁለቱም ተቋማት ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ስማርት ስልኮችን ተደራሽ የሚያደርጉ አዳዲስ የዲቫይስ ፋይናንሲንግ (Device Financing) አማራጮች ላይ በአጋርነት ለመሥራት ተስማምተዋል። ደንበኞችን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ ማብቃት፣ አዲስ የተዘረጋውን የ4ጂ ኔትወርክ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና በፍጥነት ለሚገነባው ዲጂታል ማህበረሰብ ድጋፍ ለመስጠት እንደ ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ የሚወሰድ ይሆናል።
ሌላው ቁልፍ ትኩረት የኢትዮ ቴሌኮምን የ”አረንጓዴ ኦፕሬተር” (Green Operator) ኢኒሼቲቭን ማፋጠን ሲሆን፣ በዘላቂ የአረንጓዴ ኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ በጋራ በመሥራት ከቴሌኮም ኦፕሬሽናል ሥራዎች የሚወጣውን የካርቦን ልቀት (Carbon Footprint) በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ታቅዷል። ይህ ተነሳሽነት ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ መስፈርቶች እና ከኢትዮ ቴሌኮም የዘላቂነት ግቦች ጋር የሚጣጣም፣ ጠንካራ እና አካባቢን የማይበክል ኔትወርክ ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
በመጨረሻም የዜድ.ቲ.ኢ ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር (COO) የኢትዮ ቴሌኮምን አስደናቂ ዕድገት እና ስትራቴጂ ያደነቁ ሲሆን፣ ዜድ.ቲ.ኢ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቴሌኮም ኦፕሬተር ከሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በከፍተኛ ደረጃ የመሥራት ዕድል በማግኘቱ የተሰማቸውን ክብር ገልጸዋል። ሁለቱም ተቋማት አጋርነታቸውን በማጠናከር፣ የኢትዮጵያን ዲጂታል መፃኢ ዕድል ለማሳካት እና የቴክኖሎጂ ብቃትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሁለቱንም ተጠቃሚ የሚያደርግ (win-win) አጋርነትን ለመቀጠል ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ገልጸዋል።




