ይህ ሪፖርት የ “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” ዘመን ከሐምሌ 2017 እስከ ሰኔ 2018 ያለውን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡
“ቀጣዩ አድማስ” የመጀመሪያ ዓመት፡ ስትራቴጂን ወደ ተጨባጭ ውጤት የመለወጥ ስኬት!
ኩባንያችን የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን፣ የዲጂታል አካታችነትን፣ የሥራ እድል ፈጠራን፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ለሀገራችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም ኩባንያችን በአህጉራዊ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳደግ ያለመ የሶስት አመት “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” (Next Horizon: Digital & Beyond 2028 Strategy) ቀርፆ ከበጀት ዓመቱ መባቻ ጀምሮ እየተገበረ ይገኛል።
በዚህም በየጊዜው የሚለዋወጠውን ቴክኖሎጂ በፍጥነት በመላመድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ፣ በቀጠናው ልዩ እና በዲጂታል የጎለበተ ኩባንያ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎችን በመክፈት ከትሩፋቱም ለመቋደስ የሚያስችል ሥራዎችን ለማከናወን ሁሉንም የኩባንያውን ማህበረሰብ በማቀናጀት በከፍተኛ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ስትራቴጂውን ሲተገብር ቆይቷል፡፡
የ2018 በጀት ዓመት የኢትዮ ቴሌኮም “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” የመጀመሪያው ዓመት ስኬታማ ትግበራ የታየበት ምዕራፍ ነው። የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን ስትራቴጂያዊ ዓላማዎችን ወደሚለኩ እና ከፍተኛ ፋይዳ ወዳላቸው ተጨባጭ ውጤቶች በመለወጥ ረገድ ስኬት የተመዘገበበት ነው። በሁሉም የሥራ ክንውን እና የፋይናንስ መለኪያዎች፣ ስትራቴጂያችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ዲጂታል አካታችነትን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያነቃቁ ድሎችን አስገኝቷል።
ይህንን ስትራቴጂ በስርዓት እና በዲስፕሊን ለመተግበር እንዲሁም የነበረውን እድገት ለማፋጠን፣ የስትራቴጂካዊ ኳድራንት ማዕቀፍን በመከተል እርስ በርስ በተሳሰሩ አራት ዋና ዋና አዕማድ ማለትም እድገት (Growth)፣ትራንስፎርሜሽን (Transformation)፣ ውጤታማነት (Efficiency) እና ጽናት (Resilience) በተሰኙ ማዕቀፍ ውስጥ ስትራቴጂው ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ስትራቴጂካዊ ኳድራንቶች የኩባንያችንን የረጅም ጊዜ ዘላቂነት በማረጋገጥ፣ የበጀት ዓመቱን ስትራቴጂካዊ ግቦች ስኬት ለማፋጠን እና ለማሳካት የተቀረጹ ናቸው።
ኩባንያችን በዚህ ስትራቴጂ ማዕቀፍ ውስጥ፣ ከመደበኛ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ወደ ሁሉን አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋም (Telco-to-TechCo) የመሸጋገር መቅራዊ ጉዞውን በተሳካ ሁኔታ ጀምሯል። ከመሠረታዊ የግንኙነት አገልግሎት ባለፈ ወደ ክላውድ መፍትሔዎች፣ በቴሌብር አማካኝነት ወደ ዲጂታል ሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት፣ ወደ ኢንተርፕራይዝ መፍትሔዎች እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ወደታገዙ ፕላትፎርሞች በመስፋፋት ስትራቴጂያዊ ውጥኖችን የማህበረሰቦችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ለማቅለል እንዲሁም ቢዝነሶችን እና የመንግሥት ተቋማትን አሰራር ወደሚያዘምን ውጤቶች ለውጠናል።
የኩባንያችን ስትራቴጂ ለሀገራዊው “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ራዕይ ስኬት ወሳኝ ሲሆን፤ ይህም ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን፣ የዲጂታል መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ እና በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚጫወተውን ሚና ያጠናክረዋል። እንዲሁም የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማሻሻል፣ የንግዱን ማኅበረሰብና የመንግሥት ተቋማትን ለመደገፍ፣ እንዲሁም በቴሌኮም መሠረተ ልማት፣ በዲጂታል መድረኮች እና በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ላይ የሚያደርገውን ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት በማጠናከር ንቁ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር መሠረትን ለማጽናት በትጋት እየሠራ ይገኛል።
በተጨማሪም አገልግሎቶችን ወደ ተለያዩ ዲጂታል ፕላትፎርሞች፣ ሥነ-ምህዳሮች እና የኢንተርፕራይዝ መፍትሔዎች በማስፋፋት ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነን። ከሀገር ውስጥ ባለፈም፣ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ አዳዲስ ዕድሎችን በመፍጠር፣ ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎቶችን በመስጠት እና አህጉራዊ ትብብርን በማጎልበት የ”ዲጂታል አፍሪካ 2063″ ጉዞን ለማፋጠን እና የቀጠናው ተምሳሌት ለመሆን እየሠራን እንገኛለን።
የቀጣዮቹ ገጾች ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌኮም እና በዲጂታል መሰረተ ልማቶች ላይ እንዴት በስትራቴጂካዊ መንገድ ኢንቨስት እንዳደረገ፣ እንዲሁም እነዚህ መሰረታዊ ሀብቶች ህብረተሰቡ ሰፊ የኢንተርኔት ተደራሽነት እና የበለፀጉ የዲጂታል አገልግሎቶችን እንዲያገኝ እንዴት እንዳስቻሉት በዝርዝር ያብራራሉ። ይህም ክፍል እነዚህ የመሰረተ ልማት እድገቶች ኩባንያችን የደንበኞችን ቀጥተኛ አስተያየት በመቀበል—የተለያዩ ምርቶች እና አገልግሎቶችን ገበያ ላይ በማዋል እንዲሁም የሀገሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሰረት የሆኑትን ከፍተኛ አቅም ያላቸውን የኢንተርፕራይዝ መፍትሄዎችን (Enterprise Solutions) ለማቅረብ እንዴት እንዳስቻሉት ያብራራል። በተጨማሪም፣ አጠቃላይ የክዋኔ ውጤታችንን ለደንበኞች፣ ለኢንተርፕራይዞች፣ ለመንግስት ተቋማት፣ ለማህበረሰቡ፣ ለባለአክሲዮኖች እንዲሁም ለማህበረሰቡ ካስገኙት ትሩፋቶችና በጎ ተጽዕኖዎች ጋር የሚያቀርብ ሲሆን፤ ለተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) እና ለአካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና አስተዳደራዊ (ESG) መመዘኛዎች ያደረግነውን ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ያሳያል።
- የኔትወርክ ማዘመን፡ ለዲጂታል ኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል የማይናወጥ አቅምን መገንባት
የኩባንያችን የ2018 በጀት ዓመት የመሠረተ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እና የፋሲሊቲ ልማት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ለወደፊት ዝግጁ የሆነ (future-ready) የዲጂታል መሠረት ለመጣል የተወሰዱ ወሳኝ እርምጃዎች መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በሞባይል ኔትወርኮች፣ በማስተላለፊያ ሥርዓቶች እና በኮር መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደረጉ የማዘመን ሥራዎችን ከማስፋፊያ ጥረቶች ጋር በማቀናጀት፤ ኩባንያችን ከተለመደው ጥቃቅን የኔትወርክ ማሻሻያዎችን ወጥቶ ወደ ሁለንተናዊ የትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብር ተሸጋግሯል።
በበጀት ዓመቱ በሁዋዌ፣ በዜድ ቲ ኢ እና በኤሪክሰን የኔትወርክ ሰርክሎች መጠነ ሰፊ የኔትወርክ ማዘመኛና ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል። እነዚህ ስትራቴጂያዊ ጣልቃ-ገብነቶች የኔትወርክ አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደጉ፣ የኔትወርክ መጨናነቅን የቀረፉ፣ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የዳታ አገልግሎት በሚጠይቁ አካባቢዎች የ4ጂ አገልግሎት ጥራትን ያሻሻሉ እና አጠቃላይ የደንበኞችን ተሞክሮ ከፍ ያደረጉ ናቸው። እነዚህ መሻሻሎች ከደንበኞች በተገኘ አዎንታዊ ግብረ-መልስ የታጀቡ ሲሆን፣ ይህም በመከናወን ላይ ያሉ የማዘመኛና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ምን ያህል ውጤታማ መሆናቸውን በተግባር አረጋግጧል።
1.1 ሀገር አቀፍ የ4ጂ፣ 5ጂ እና የፋይበር ኮኔክቲቪቲን ማሳደግ
በበጀት ዓመቱ የኔትወርክ አቅምንና ሽፋንን በገጠር፣ በከተማና በንግድ ማዕከላት ለማጠናከር በድምሩ 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል። ከተገነቡት 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች መካከል 195ቱ አዳዲስ የገጠር ጣቢያዎች ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ 22ቱ የገጠር ሶሉሽን ጣቢያዎች ናቸው፤ ቀሪዎቹ 408ቱ ደግሞ አዳዲስ ማክሮ ጣቢያዎች ናቸው።
በዚህም መሠረት ጠቅላላ የሞባይል ጣቢያዎች ቁጥር ከ10,010 ወደ 10,613 ከፍ እንዲል ተደርጓል። ከእነዚህም ውስጥ 10,159 ማክሮ ጣቢያዎች ሲሆኑ፣ 454 ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በሌለባቸው ወይም ውስን በሆነባቸው የገጠር አካባቢዎች ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች የግንኙነት አገልግሎት ለማቅረብ ተደርገው የተነደፉ የገጠር ሶሉሽን ጣቢያዎች ናቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ የ10.2 ሚሊዮን የኔትወርክ የመሸከም አቅም የተፈጠረ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የኩባንያችንን የኔትወርክ አቅም ከ104.8 ሚሊዮን ወደ 115.1 ሚሊዮን አሳድጎታል።
መጠነ-ሰፊ የ4ጂ ኔትወርክ ማሻሻያ እና ማስፋፊያ ሥራዎች የ4ጂ የሕዝብ ቁጥር ሽፋንን 82.23% አድርሰውታል!
አዳዲስ የኔትወርክ ጣቢያዎችን ከመገንባት ጎን ለጎን፣ የኔትወርክ አቅምን፣ ሽፋንን እና የተጠቃሚዎችን ተሞክሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ መጠነ-ሰፊ የ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ ማሻሻያና ማስፋፊያ ተግባራት በበጀት ዓመቱ ተከናውነዋል። በዚህም በበጀት ዓመቱ 264 አዳዲስ ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የ4ጂ ሽፋን ያላቸውን ከተሞች ቁጥር ወደ 1,200 አድርሶታል። በዚህም መሠረት የ4ጂ የሕዝብ ቁጥር ሽፋን ከ70.83% ወደ 82.23%፣ እንዲሁም የጂኦግራፊያዊ ሽፋን ከ21.06% ወደ 36.29% ከፍ እንዲል ተደርጓል።
የ5ጂ ኔትወርክ ማስፋፊያ ለዘመናዊ ከተሞች ግንባታ (Smart City) ፣ ለኢ-ኮሜርስ፣ ለዲጂታል መንግሥታዊ አገልግሎቶች እና ለፊንቴክ መድረኮች አዳዲስ ዕድሎችን ፈጥሯል
የ5ጂ ማስፋፊያ ሥራው ተጨማሪ ሰባት ከተሞችን በማካተት በአጠቃላይ በ33 ከተሞች ተደራሽ መሆን የተቻለ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ በተገነቡ 25 አዳዲስ የ5ጂ ጣቢያዎች አማካኝነት ጠቅላላ የጣቢያዎቹ ቁጥር 340 ደርሷል። ይህም የ5ጂ የመሸከም አቅምን ወደ 1.4 ሚሊዮን ያሳደገ ሲሆን፣ የተፈጠረው ተጨማሪ የ80.9 ሺህ አቅም ለዘመናዊ ከተሞች (Smart city) ግንባታ፣ ለኢንተርፕራይዝ ደረጃ አገልግሎቶች እና ለፈጠራ ሥነ-ምህዳር ግንባታ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
እያንዳንዱ የጣቢያ ግንባታና የአቅም ማሳደጊያ ተግባር በቀጥታ ለአገልግሎት አስተማማኝነት፣ ለላቀ ፍጥነትና ለሰፊ ተደራሽነት መረጋገጥ የጎላ ፋይዳ ያለው ሲሆን፤ በተመሳሳይ ጊዜ የ5ጂ ስርጭት ለዲጂታል ንግድ፣ ለመንግሥታዊ የዲጂታል አገልግሎቶችና ለፋይናንስ ቴክኖሎጂ መድረኮች አዳዲስ የዕድገት በሮችን ከፍቷል።
በአጠቃላይ እነዚህ ጥረቶች አስተማማኝ ሀገር አቀፍ ትስስርን በማረጋገጥ፣ ዲጂታል አገልግሎቶችን በማብቃት እና ኢትዮ ቴሌኮምን በሀገሪቱ የዲጂታል ጉዞ ውስጥ የፈጠራና የተወዳዳሪነት ዋነኛ ሞተር በማድረግ የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ራዕይን ዕውን የሚያደርጉ ናቸው።
የፋይበር እና የማስተላለፊያ ኔትወርክ፡ ለአገልግሎቶቻችን ዋነኛ የጀርባ አጥንት
የባክቦን ፋይበር ኔትወርክ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች ዋነኛ ምሰሶ ነው። በበጀት ዓመቱ በተከናወነው የማስፋፊያ መርሃ ግብር 793 ኪሎ ሜትር አዲስ የፋይበር ኦፕቲክ ገመድ የተዘረጋ ሲሆን፣ ይህም የ1,100 ኪሎ ሜትር ዓመታዊ ዕቅዱን 72 በመቶ በማሳካት ጠቅላላ ሀገራዊ የባክቦን ፋይበር ኔትወርክን ወደ 23,442.1 ኪሎ ሜትር ከፍ አድርጎታል። እነዚህ ዝርጋታዎች የፋይበር መስመር ጥግግትን (densification)፣ የተጠባባቂ/ተቋራጭ የፋይበር ኔትወርክ ጥበቃን (Ring Protection) እና የኔትወርክ አማራጭ መስመሮችን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድገዋል።
በተጨማሪም በአጠቃላይ 231.46 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባክቦን ፋይበር በኩባንያችን የውስጥ አቅም የታደሰ ሲሆን፣ ይህም በውጭ ተቋራጮች ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ የኔትወርክ ተገኝነትን፣ የማስተላለፊያ ጥራትን እና በፍጥነት የመንሰራራት አቅምን (resilience) አጠናክሯል። ከዚህም ባሻገር በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በተከናወኑ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ወቅት 445.6 ኪሎ ሜትር የፋይበር ዝውውር የተከናወነ ሲሆን፣ ይህም በሥራው ወቅት ምንም ዓይነት የአገልግሎት መቋረጥ ሳይከሰት መጠናቀቁ የላቀ የኦፕሬሽን ልህቀትን በተግባር ያሳየ ነው።
በበጀት ዓመቱ እያደገ የመጣውን የትራንስፖርት ኔትወርክ ፍላጎት ለማሟላት በ104 ጣቢያዎች ላይ የኦቲኤን (OTN) ማስፋፊያ ሥራዎች በንቃት ተከናውነዋል። ይህንን ማስፋፊያ ዕውን ለማድረግ በጣቢያ ደረጃ ዝርዝር የምህንድስና ዲዛይኖች (LLDs) የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ይህም ኔትወርኩ እያደገ የመጣውን የአቅም ፍላጎት እንዲሸከም እና ለወደፊት መስፋፋት (scalability) ዝግጁ እንዲሆን አስችሎታል።
የሜትሮ ኔትወርክ ማስፋፊያ
በበጀት ዓመቱ 1,275 ኪሎ ሜትር አዲስ ዝርጋታ በማጠናቀቅ የሜትሮ ኔትወርክ አቅምን ወደ 15,615 ኪሎ ሜትር ማሳደግ ተችሏል። ይህም የኔትወርኩን በፍጥነት መልሶ የመቋቋም አቅም (Resilience) ለማሻሻልና መጨናነቅን ከመቀነስ ባለፈ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የብሮድባንድ ትራፊክ ፍላጎት በላቀ ሁኔታ ለመደገፍ የጎላ ፋይዳ አለው።
የሞባይል ጣቢያዎችን በፋይበር የማገናኘት ሥራ (Fiberization)
በበጀት ዓመቱ 841 የሞባይል ጣቢያዎችን በፋይበር የማገናኘት ሥራ በስኬት የተከናወነ ሲሆን፣ ይህም በፋይበር የተገናኙ አጠቃላይ የሞባይል ጣቢያዎችን ቁጥር ወደ 3,279 አድርሶታል። ከእነዚህም ውስጥ 1,548ቱ ጣቢያዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በየክልሉ የሚገኙ የገመድ አልባ ጣቢያዎች ናቸው። ይህም በአዲስ አበባ 96 በመቶ፣ በሪጅን ደግሞ 19 በመቶ የሚሆኑትን የሞባይል ጣቢያዎች በፋይበር የማገናኘት ሥራ መከናወኑን የሚያመላክት ነው።
ይህ ማስፋፊያ የኔትወርክ አቅምን፣ አስተማማኝነትንና የአገልግሎት ጥራትን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠናክራል። ከማይክሮዌቭ ግንኙነቶች ጋር ሲነጻጸር፣ የፋይበር ትስስር እጅግ የላቀ የመረጃ ማስተላለፊያ አቅምን (Bandwidth)፣ ዝቅተኛ የመረጃ መመላለሻ ጊዜን (Lower Latency) እና ጠንካራ መረጋጋትን (Stability) በመስጠት የላቀ የሞባይል ዳታ አፈጻጸምን ያረጋግጣል። በስትራቴጂካዊ እይታም፣ የሞባይል ጣቢያዎችን በፋይበር ማገናኘት ለላቁ የ4ጂ ማስፋፊያዎች፣ ለMassive MIMO ዝርጋታ፣ ለ5ጂ ስርጭት እና ለወደፊቱ የ6ጂ ቴክኖሎጂ ዝግጁ የሆነ (Future-ready) የትራንስፖርት ኔትወርክ ለመገንባት እንደ ዋነኛ መሠረት ያገለግላል።
ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መውጫ
የመደበኛ ብሮድባንድ፣ የ4ጂ፣ የ5ጂ እና የኢንተርፕራይዝ ኔትወርኮች መስፋፋትን ተከትሎ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች የዳታ ፍላጎት ለማርካት፣ የተጠቃሚዎችን ተሞክሮ ለማሻሻል፣ መጨናነቅን ለመቀነስ እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለውን የብሮድባንድ ፍላጎት ለመደገፍ የዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መውጫ (Internet Gateway) አቅማችን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ተደርጓል። ይህም ለኢንተርፕራይዝ እና ለዲጂታል አገልግሎቶች አስተማማኝ ግንኙነትን ያረጋግጣል። አጠቃላይ የዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መውጫ አቅማችን 4.3 Tb/s የደረሰ ሲሆን፤ የሲዲኤን (CDN) የሀገር ውስጥ ጊዜያዊ መረጃ ማከማቻ አቅም (Cache) በ820 Gbps በማደግ በ5 የሲዲኤን አጋሮች አማካኝነት 2,062 Gbps ደርሷል። እንዲሁም የዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መውጫ (IGW) አቅም በ750 Gbps በማደግ ወደ 2,040 Gbps ከፍ ብሏል። ይህ መጠነ-ሰፊ የአቅም ጭማሪ ዓለም አቀፍ የማስተላለፊያ (Backhaul) ጽናትን የሚያጠናክር፣ የመረጃ መመላለሻ ጊዜን (Latency) የሚቀንስ እና በመላ ሀገሪቱ እየታየ ያለውን የዳታ ፍላጎት እና የዲጂታል አገልግሎቶች ዕድገት በብቃት ለመደገፍ የሚያስችል ነው።
አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ
በበጀት ዓመቱ፣ ኢትዮ ቴሌኮም አስተማማኝ ባልሆነ የኤሌክትሪክ መስመር አቅርቦት ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ በሞባይል ጣቢያዎች (BTS) ላይ 867 የሀይብሪድ የኃይል ሥርዓቶችን (Hybrid Power Systems) የዘረጋ ሲሆን፤ ይህም የአገልግሎት ዝግጁነትን ለማሻሻልና የሞባይል ኔትወርክ ተገኝነትን ለማረጋጋት የላቀ ሚና ተጫውቷል። በተጨማሪም 215 አዳዲስ የፀሐይ ኃይል (ሶላር) ጣቢያዎችን በመዘርጋት እና 774 ነባር ጣቢያዎችን በማሻሻል የታዳሽ ኃይል አሻራውን ያሰፋ ሲሆን፤ በዚህም በተለመዱ የኃይል ምንጮች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ 12.72 MW የሶላር አቅም በመገንባት አጠቃላይ የሶላር አቅማችንን 39.72 MW የደረሰ ሲሆን ይህም በተለይም ዲጂታል እና የሞባይል አገልግሎት በሌለባቸው የገጠር አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ለመሆን በእጅጉ ከማገዙ በላይ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ሽግግር የሚደግፉ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል፡፡ የአገልግሎት ጥራትን (QoS) ለማረጋገጥ እና የአገልግሎት መቆራረጥን ለመቀነስ 225 ጄነሬተሮች እንደ መጠባበቂያ የኃይል ምንጭ ሥራ ላይ ውለዋል።
የፀሐይ ኃይል (ሶላር) ማስፋፊያ፣ የተቀናጁ/ሃይብሪድ የኃይል መፍትሔዎች፣ የላቁ የባትሪ ቴክኖሎጂዎች፣ በኤአይ (AI) የተደገፈ የኃይል አጠቃቀም ማሻሻያ እና ዘላቂ የዳታ ሴንተር መሰረተ ልማቶች የአካባቢ ተፅዕኖን ይቀንሳሉ፤ የኔትወርክ አስተማማኝነትን ያሳድጋሉ፤ እንዲሁም የረጅም ጊዜ የተግባቦት ጽናትን ይደግፋሉ።
1.2. የዲጂታል መሠረተ ልማት፡ የዳታ ማዕከል እና ክላውድ (Data Center & Cloud)
የዳታ ማዕከል እና የክላውድ አገልግሎቶች
ኢትዮ ቴሌኮም በሞዱላር እና በሃይፐርስኬል (hyperscale) ዳታ ማዕከላት፣ በክላውድ ፕላትፎርሞች እና በላቁ የሳይበር ደህንነት ሥርዓቶች ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የዳታ ማዕከል መሠረተ ልማቱን በማዘመን እና በማስፋፋት ላይ ይገኛል። እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ሊሰፋ የሚችል (scalable) ዲጂታል መሠረተ ልማት ለማቅረብ የታለሙ ሲሆን፤ ይህም የክላውድ አገልግሎቶችን፣ የኢንተርፕራይዝ መፍትሔዎችን፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የታገዙ መተግበሪያዎችን እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የዲጂታል ሽግግር ያፋጥናሉ።
በበጀት ዓመቱ ውስጥ ከ20 በላይ አዳዲስ በክላውድ የታገዙ የኢንተርፕራይዝ አገልግሎቶች የተጀመሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ኢንተርፕራይዝ ኢሜይል፣ የኪራይ አስተዳደር፣ Tele ERP Lite፣ BMS፣ Workspace፣ Znexus እና ቴሌ ኮንታክት ሴንተር ይገኙበታል። ይህም ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ታማኝ የዲጂታል መሠረተ ልማት እና ሶሉሽን አቅራቢነት ያለውን ደረጃ አጠናክሮለታል። ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለአዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ለDARS የተከናወኑ የTeleSign ውል ስምምነቶች በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀው ከ110 በላይ ደንበኞችን የሚያገለግሉ በ14 የአገልግሎት ማዕከላት የሚገኙ የድጋፍ ኦፕሬሽን ሥራዎች ተጀምረዋል።
የዳታ ማዕከላት ማስፋፊያ ሥራችን ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ (Milestone) ላይ የደረሰ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በሚገኙ ስድስት በቲየር 3 (Tier III) ደረጃ በተረጋገጡ ዳታ ማዕከሎቻችን የ 5 ሜጋ ዋት (MW) የኦፕሬሽን አቅም እና 640 የሰርቨር ማቀፊያዎች (racks) ማዘጋጀት ተችሏል። በአሁኑ ወቅት የዳታ ማዕከሎቻችን የአጠቃቀም አቅም 87% የደረሰ ሲሆን፤ ከ 880 በላይ የመንግሥት ተቋማትን፣ 340 ድርጅቶችን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትን እና የኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ፕላትፎርሞችን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ። በአጠቃላይ የዳታ ማዕከሎቻችን የኮምፒዩቲንግ አቅም 12,400 ቨርቹዋል ማሽኖችን (VMs)፣ 8.4 ፔታባይት (PB) የመረጃ ማከማቻ እና 240 ጊጋቢት በሰከንድ (Gbps) የኢንተርኔት ትስስር አቅምን አካቷል።
ሁለት ቦታዎች ላይ የተዘረጉት አስተማማኝና ፅናት ያላቸው ዳታ ማዕከሎች (dual-site architecture) መረጃዎችን በቅጽበት ወደ ሁለተኛው ማዕከል የማሸጋገር (real-time replication) አቅም ስላላቸው፣ ምንም ዓይነት የመረጃ መጥፋት (zero data loss) እንዳያጋጥም የሚያደርጉ እና በድንገተኛ አደጋ ወቅት በ 15 ደቂቃዎች ውስጥ አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት የመመለስ አቅም ያላቸው ናቸው። ማዕከላቱ በየአካባቢው ከሚያጋጥሙ መቋረጦች ነፃ ለመሆን እርስ በእርሳቸው በ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ተራርቀው የተገነቡ ሲሆን፣ አገልግሎቱ ሳይቋረጥ ቀልጣፋ ሆኖ እንዲቀጥልም የ 8 ሚሊሰከንድ (ms) እጅግ ዝቅተኛ የመረጃ መዘግየት (latency) ፍጥነትን ያረጋግጣሉ።
የአካባቢ ጥበቃን ያገናዘቡ የአረንጓዴ ዳታ ማዕከል (Green Data Center) አሰራሮችን ዘመናዊ የማቀዝቀዣ ሥርዓቶችን በመጠቀም ማጠናከር የተቻለ ሲሆን፣ የአመቱን 67% ጊዜ የተፈጥሮ አየርን እንደ ማቀዝቀዣ (free-air cooling) በመጠቀማችን የኤሌክትሪክ ሃይል አጠቃቀምን በ34% መቀነስ ተችሏል።
በሁሉም ዳታ ማዕከሎቻችን ላይ የተዘረጉት ባለሁለት አማራጭ የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ሥርዓቶች (dual-grid systems) የኃይል ስርጭትን በማሻሻል የሥራ ቅልጥፍናን የበለጠ አሳድገዋል፤ ይህም የኃይል አጠቃቀም ውጤታማነትን (PUE) 1.3 ማድረስ ያስቻለ ሲሆን፣ ይህም ከዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ አማካይ ውጤት (1.6) ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነው። ዳታ ሴንተሮቹ ቀደም ሲል ከነበሩት ቴክኖሎጂዎች ጋር ሲነፃፀሩ ለእያንዳንዱ የኮምፒዩቲንግ አሃድ የሚጠቀሙትን የኤሌክትሪክ ኃይል በ 41% የቀንሱ በመሆኑ፣ የኦፕሬሽን ወጪን ከመቀነሳቸውም በላይ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል።
የዲጂታል መሠረተ ልማትን ማስፋፋትና ማሻሻል
ኩባንያችን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓቶችን ደረጃ በማሳደግና በማሻሻል፣ በዘመናዊ የአገልግሎት ጥራት አማካኝነት የላቀ የደንበኞች ተሞክሮን እያረጋገጠ ቀጣይነት ያለው የሥራ ዕድገት እና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ብቃትን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። በዚህም ለማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት አኗኗር እና ለተቋማት የሥራ ቅልጥፍና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች በሰፊው ተደራሽ እየሆኑ ይገኛሉ። በተለይም አሠራሮችን የሚያዘምኑ እና ለደንበኞች ፈጣንና ምቹ አገልግሎት የሚሰጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ዲጂታል መፍትሔዎች (Solutions) ሥራ ላይ እየዋሉ ይገኛሉ።
ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ፡ የኦፕሬሽን ደጋፊ ሥርዓት (OSS) Cloud ትግበራ፣ የደንበኞችን የመቀበል አቅም ያሳደገው የቀጣይ ትውልድ ቢዝነስ ሰፖርት ሲስተም (NGBSS SNS) ማሻሻያ፣ ቴሌክላውድ (teleCloud) እና ፕራይቬት ክላውድ (Private Cloud)፣ የአደጋ ጊዜ መረጃ መልሶ ማግኛ (DR) ማስፋፊያ፣ አዲስ የኢ-ኮሜርስ (E-Commerce) ፕላትፎርም ግንባታ፣ የ-DNS ሥርዓት ማሻሻያ ሶሉሽን፣ የዌብሆስቲንግ (Webhosting) ማሻሻያና ሽግግር እንዲሁም የማረጋገጫ፣ የፈቃድ አሰጣጥ እና የሂሳብ አያያዝ (AAA) ሥርዓቶች ይጠቀሳሉ።
የሳይበር ደህንነት (Cybersecurity)
የሳይበር ጥቃቶች በፈጣን ሁኔታ እያደገ ላለው የዲጂታል አገልግሎት ዋነኛ ፈተና በመሆናቸው፤ የኩባንያችንን የሰው ኃይል አቅም በመገንባት፣ አሠራሮችን በማዘመን እና ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ የኩባንያችንን ዋና ዋና ሀብቶች ከመረጃ ስርቆት፣ ከአገልግሎት መቋረጥ እና ከገቢ ኪሳራ መጠበቅ ተችሏል። በቀን 24 ሰዓት በሳምንት 7 ቀናት (24/7) የሚሠራ የሳይበር ደህንነት ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋቱ፣ የኩባንያችንን ዋና ዋና ሲስተሞች ደህንነት ለመጠበቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ተግባራዊ በመደረጉ እና የጥቃት ሙከራዎችን አስቀድሞ ለመለየት የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ በመዋላቸው የተሰነዘሩ ጥቃቶች ሁሉ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያደርሱ እንዲመከቱ ተደርጓል።
በበጀት ዓመቱ በኢንተሊጀንት ኦፕሬሽን ማዕከል አማካይነት 242,459 የደህንነት ስጋቶችን ለይቶ በመተንተን መከላከል የተቻለ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 78,845 የርቀት ኮድ ማስፈጸም ሙከራዎች (remote code execution)፣ 67,537 የማልዌር (malware) ጥቃቶች፣ 67,042 የፊሺንግ (phishing) ጥቃቶች፣ 19,421 አጠራጣሪ የተጠቃሚ ባህሪዎች፣ 4,423 ኢንጄክሽን-ተኮር (injection-based) ጥቃቶች፣ 2,274 የኤክስፕሎይት (exploit) ሙከራዎች፣ 2,210 የአገልግሎት መቋረጥ (DDoS) ጥቃቶች እና 707 ቅድመ-ጥቃት መረጃ የመሰብሰብ (reconnaissance) እንቅስቃሴዎች ይገኙበታል።
የመረጃ ምስጢራዊነት እና የተደራሽነት ደህንነትን ለማጠናከር አጠቃላይ የልዩ ፈቃድ ተደራሽነት አስተዳደር (privileged access management) እና የማንነት ቁጥጥር ሥርዓቶች ተዘርግተዋል። ዋና ዋና ሲስተሞች ተደራራቢ የግንባታ መዋቅር (redundant architecture) እና ቅድመ-መከላከል ቁጥጥር በማድረጋቸው 99.99% የሥራ ላይ ዝግጁነት (uptime) ነበራቸው። ብሔራዊ ኩነቶች በሚከናወኑበት ወቅት ምንም ዓይነት ከፍተኛ የአገልግሎት መቋረጥ አለማጋጠሙ የኩባንያችንን ጽኑ የአሠራር የመቋቋም አቅም (operational resilience) ያሳያል።
ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ባህልን ለመገንባት ኩባንያችን የሠራተኞችን የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በስፋት ከውኗል። በኩባንያችን የግንዛቤ ደረጃ ለመፈተሸ በተደረገ የፊሺንግ ሙከራ (phishing simulation) ጥቃት የመሰንዘሪያ ሊንኮችን የመጫን ምጣኔ ወደ 5.4% ዝቅ እንዲል የተደረገ ሲሆን፣ 74.5% ሠራተኞች የፊሺንግ ፈተናውን በስኬት አልፈዋል። የሠራተኞች የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ብስለትም ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል፤ ባለፈው ዓመት 44.8% የነበረው ሙሉ ውጤት ያመጡ ሠራተኞች ቁጥር በዘንድሮው ዓመት ወደ 79.5% አድጓል።
- ተደራሽነትን ማስፋፋት
ሀገራዊ የአገልግሎት ተደራሽነትን ማጠናከር
ኢትዮ ቴሌኮም ክልላዊ ተደራሽነቱን እያሰፋ ባለበት በዚህ ወቅት ሀገር አቀፍ የቢዝነስ እና አገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋት በሀገር ውስጥ ገበያ ያለውን መሪነት ማጠናከሩን ቀጥሏል።
በበጀት ዓመቱ ኩባንያችን 110 ማዕከላትን ለመክፈት አቅዶ 217 አዳዲስ ቀጥታ የሽያጭ እና የአገልግሎት ማዕከላትን በመክፈትና ወደ ሥራ በማስገባት የቢዝነስ ተደራሽነቱን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል። ይህም የእቅዱን 197% አፈጻጸም የሚያሳይ ሲሆን በእቅዱ ላይ 107 ተጨማሪ ማዕከላትን መክፈት ችሏል።
ይህ ማስፋፊያ የኩባንያችንን የአገልግሎት ተደራሽነት ወደ ደንበኞች የበለጠ ያቀረበ፣ ሀገር አቀፍ ተደራሽነትን ያሻሻለ እንዲሁም በከተሞች፣ በከተማ አቅራቢያ እና ቀደም ሲል ተደራሽ ባልሆኑ ሌሎች አካባቢዎችም የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የዲጂታል እና የፋይናንስ አገልግሎቶችን የማቅረብ አቅምን አጠናክሯል።
በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ላይ ኢትዮ ቴሌኮም የሚከተሉትን ያካተተ በአጠቃላይ 1,145 የአገልግሎት ማዕከላትን እና የደንበኞች አገልግሎት ጣቢያዎችን እውን አድርጓል፦
- ፕሪሚየም የአገልግሎት ማዕከላት (Premium service centers)
- ግራንድ የአገልግሎት ማዕከላት (Grand service centers)
- ሃየር የአገልግሎት ማዕከላት (Higher service centers)
- ሚዲየም የአገልግሎት ማዕከላት (Medium service centers)
- ኪዮስኮች እና የኪዮስክ ማዕዘናት (Kiosks and kiosk corners)
- በኢትዮ ቴሌኮም ባለቤትነት ሥር ያሉ ተንቀሳቃሽ ኪዮስኮች (Ethio telecom-owned movable kiosks)
- ከአጋሮች ጋር የተዘጋጁ ተንቀሳቃሽ ኪዮስኮች (partnered movable kiosks)
- የፍራንቻይዝ የአገልግሎት ማዕከላት (Franchise service centers)
- የአንድ መስኮት ዘመን ገበያ የዲጂታል ቻናል (One Zemen GEBEYA digital channel)
ይህ የተሳለጠ የአገልግሎት ተደራሽነት የደንበኞችን ምቾት ያሻሻለ፣ የመጨረሻውን ማይል ተደራሽነት ያጠናከረ እና ኩባንያችን ለተለያዩ የደንበኞች እና የገበያ ፍላጎቶች የበለጠ ውጤታማ ምላሽ እንዲሰጥ ያስቻለው ሆኗል።
አካታችነት እና ደንበኛ ተኮር እድገት
ይህ የማስፋፊያ ሥራ ከአካላዊ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያነት በተጨማሪ የመጨረሻውን ደንበኛን በመቅረብ አካታች ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ዘላቂ የገበያ እድገትን ለማምጣት የተደረገ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት ነው። ኩባንያችን የአገልግሎት ማዕከላትን ከፍራንቻይዝ እና ከአጋሮች ጋር በተገነቡ የአገልግሎት መስጫ ቻናሎች በማቀናጀት የደንበኞችን ቁጥር ማሳደግን፣ የአገልግሎት አሰጣጥን እና የድህረ-ሽያጭ ድጋፍን ያጠናከረ ሲሆን፤ ከዚህ ጎን ለጎን የሞባይል፣ የብሮድባንድ፣ የቴሌብር እና የሌሎች ዲጂታል አገልግሎቶች አጠቃቀም እንዲፋጠን አድርጓል።
ይህ የኔትወርክ መስፋፋት ኢትዮ ቴሌኮም በሀገሪቱ የኮኔክቲቪቲ፣ የዲጂታል እና የፋይናንስ አገልግሎቶች ግንባር ቀደም አቅራቢነቱንና ያለውን መሪ ደረጃ የበለጠ አጠናክሮታል።
- የደንበኞች ተሞክሮ እና የአገልግሎት ጥራትን ማሸጋገር
የምርት እና አገልግሎት ማሻሻያ
በበጀት ዓመቱ 475 አዳዲስ እና የተሻሻሉ ምርቶችና አገልግሎቶች ለ ግል ደንበኞች፣ ኢንተርፕራይዝ፣ ፊንቴክ፣ ዲጂታል ላይፍስታይል እንዲሁም በአለም አቀፍ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ ለገበያ የቀረቡ ሲሆን፤ ኩባንያችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተደገፉ መፍትሔዎችን፣ ፈጠራ የታከለባቸውን የፋይናንስ አገልግሎቶችን እና የላቁ የኢንተርፕራይዝ ቴክኖሎጂዎችን አስተዋውቋል። ይህም 193 አዳዲስ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን፣ 197 ማሻሻያዎችን እና 85 የፕሮሞሽን ቅናሽ ጥቅሎችን ያካተተ ነው።
በተመጣጣኝ ዋጋ በሚቀርቡ ዲቫይዞች እና የደንበኞች ግንዛቤ ማስጨበጫ አማካኝነት የዲጂታል አካታችነትን ማፋጠን !
የዲጂታል አካታችነትን ለማሻሻል እና የፋይናንስ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ኩባንያችን ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን በCloud የሚሰሩ znexus ዲቫይዞችን፣ Cloud Workspace መፍትሔዎችን፣ የዲቫይዞች የተራዘመ የክፍያ አማራጭ (installment based) ሽያጭ አሰራሮችን አስተዋውቋል። እነዚህ ፕሮግራሞች በርካታ ደንበኞች የዲጂታል እና የቴሌኮም አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስችለዋል። በቀጥታ የአቅርቦት ተደራሽነት እና ከስማርትፎን አምራች ብራንዶች ጋር በተደረጉ አጋርነቶች የስማርትፎን ስርጭት (smartphone penetration) 45.2% የደረሰ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ውስጥ 832,656 የዲቫይዞች ሽያጭ ተከናውኗል (ይህም የአመታዊ እቅዱን 88.8% ያሳካ ነው)።
የደንበኞች ግንዛቤ ማሳደጊያ ፕሮግራሞች በከፍተኛ ሁኔታ ተግባራዊ በመደረጋቸው 30.5 ሚሊዮን ደንበኞችን ተደራሽ ያደረጉ ሲሆን፤ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የአገልግሎት አጠቃቀምን በማጎልበት እና የዲጂታል መላመድን በማፋጠን ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። እነዚህ ጥረቶች የዲጂታል ቻናሎች አጠቃቀም እንዲጨምር፣ በዲጂታል ግብይቶች ላይ ያለው እምነት እንዲጎለብት እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች አጠቃቀም እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
የኔትወርክ አፈጻጸም (Network Performance)
በኩባንያችን የተከናወኑትን የኔትወርክ ማዘመን እና ማስፋፊያ ስራዎች ተከትሎ በበጀት ዓመቱ የኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ አፈጻጸም ጠንካራ የመቋቋም አቅምና ቀጣይነት ያለው መሻሻል አሳይቷል።
የኔትወርክ ውጤታማነት ምጣኔ (NER – Network Effectiveness Ratio) በተከታታይ የ90% ግብ በከፍተኛ ሁኔታ አልፎ የቀጠለ ሲሆን፤ የኔትወርክ ዝግጁነት ምጣኔ (NAR) ጥቂት መዋዥቆች ቢኖሩበትም በአብዛኛው የበጀት ዓመት ከ94% በላይ ሆኖ በመቆየት እስከ 95.2% ጫፍ ደርሷል፤ ይህም ጠንካራ የኔትወርክ አቅምን የሚያንፀባርቅ ነው።
በዚህም የአገልግሎት ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ የተሻሻለ ሲሆን የ4G ተጠቃሚዎች የዳታ ፍጥነት (throughput) በ6.7 እና 8.06 Mbps መካከል ተረጋግቶ በመቆየት አስተማማኝ እና ፈጣን የዳታ አቅርቦትን አረጋግጧል። በጋራ ሲታዩ እነዚህ ውጤቶች ኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማትን በማዘመን፣ የኔትወርክ አፈጻጸምን በማሻሻል እና የደንበኞችን ተሞክሮ በማሳደግ ረገድ የነደፈውን “ቀጣዩ አድማስ” ስትራቴጂ ስኬታማነት ያመላክታሉ።
- የዲጂታል አጠቃቀም ክፍተትን ማጥበብ፡ የገጠር ኮኔክቲቪቲን እና አካታችነትን ማፋጠን
ኩባንያችን የገጠር ኮኔክቲቪቲ ፕሮግራሞችን በስትራቴጂያዊ ዕቅዱ በማከተት፣ በዕቅዱ መሰረት የተተገበሩት ስራዎች ለገጠር ማህበረሰቦች ሁለገብ ለውጥ እና እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። በቂ አገልግሎት ባላገኙ አካባቢዎች የቴሌኮም መሠረተ ልማት እና የሞባይል አገልግሎቶችን በማስፋፋት፣ ፕሮግራሙ የኮሙኒኬሽን እና የዲጂታል ኮኔክቲቪቲ ተደራሽነትን እያሻሻለ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም የገጠር ማህበረሰቦች በዲጂታል አገልግሎቶች ላይ ተቋዳሽ እንዲሆኑ እያስቻለ ይገኛል።
የገጠር ኔትወርክ ማስፋፊያው 1.64 ሚሊዮን የኔትወርክ አቅም ያላቸው 195 አዳዲስ የገጠር የቴሌኮም ጣቢያዎችን እውን ያደረገ ሲሆን፤ ይህም 117 ወረዳዎችን እና 492 መንደሮችን/ቀበሌዎች በመሸፈን ወደ 1.53 ሚሊዮን የሚጠጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ አስችሏል። እነዚህ ስኬቶች የዲጂታል ክፍተቱን ለመቀነስ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ጨምሮ ዲጂታል አካታችነትን ለማሳደግ እንዲሁም በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የገጠር ማህበረሰቦች ውስጥ የኮሙኒኬሽን እና የዲጂታል አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በአጠቃላይ እነዚህ ዘርፈብዙ ጥረቶች የዲጂታል አጠቃቀም ክፍተቱን ለማጥበብ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማሳደግ እና በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የገጠር ማህበረሰቦችን የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል የላቀ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ።
- የቢዝነስ ድርጅቶችን እና የመንግስት ተቋማትን በኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖች ማብቃት
ደህንነቱ የተጠበቀ ኮኔክቲቪቲን፣ ዲጂታል ፕላትፎርሞችን፣ በመረጃ ላይ የተመሰረቱ አሰራሮችን እና የተቋማት የዲጂታል ሽግግር በማስፋፋት ፣ የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖቻችን በተለያዩ ድርጅቶችና ዘርፎች የአገልግሎት አሰጣጥን፣ የአሰራር ቀጣይነትን፣ ምርታማነትን እና የተጠቃሚዎችን እርካታ በማላቅ ላይ ይገኛሉ። ይህ አዎንታዊ ተፅዕኖ ፈጣንና ይበልጥ ግልፅ በሆኑ አገልግሎቶች፣ በተሻሻለ የተቋማት ብቃት፣ ጠንካራ በሆነ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን በሚደግፉ፣ ሊያድጉ በሚችሉ ዲጂታል ሞዴሎች ላይ እየተስተዋለ ነው።
የመንግስት አገልግሎቶችን፣ የግል ድርጅቶችን፣ ቱሪዝምን፣ ጤናን፣ ዘመናዊ ከተሞችን፣ ኢንዱስትሪን፣ ግብርናን እና ማዕድንን ጨምሮ በስትራቴጂያዊ ዘርፎች ሁሉ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች በአውቶሜሽን፣ በተሻሻለ ተደራሽነት፣ አሁናዊ ክትትልና በተሻሻለ የስራ ቁጥጥር አማካኝነት የሚለካ እሴት እየፈጠሩ ይገኛሉ። ይህም ይበልጥ ቀልጣፋ የሕዝብ አገልግሎቶችን፣ የተሳሰሩ ኢንዱስትሪዎችን፣ ዘመናዊ የከተማ አስተዳደርን፣ የተሻሻለ የጤና አገልግሎት ቀጣይነትን፣ የዲጂታል ግብርና ስነ-ምህዳርን እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ የሀብት ልማት ተግባራትን ለማከናወን ያስችላል። የኢንተርፕራይዝ ቢዝነስ ዘርፋችን 126 የታቀዱ ኢኒሸቲቮችን በመተግበር 60 የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን፣ 94 የተቋማት ትስስሮችን እና 8 አበይት ግዙፍ ፕሮግራሞችን በማቀናጀት ወደ አንድ የጋራ የዲጂታል አሰራር ብቃት እንዲሸጋገሩ አድርጓል።
- የአፈጻጸም አጠቃላይ እይታ፡ የዕድገት፣ የበጎ ተፅዕኖ እና ትራንስፎርሜሽን
የደንበኞች ቁጥር
ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች የደንበኛ መሠረቱን በማስፋፋት በገበያ ውስጥ ያለውን ቁመና ማጠናከሩን ቀጥሏል። አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 90.12 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የዕቅዱን 101.7% በማሳካት የ8.3% ዕድገት አሳይቷል። አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉ ንቁ ጠቅላላ የሞባይል ደንበኞች (active mobile subscribers) ቁጥር 72.09 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ በዚህም የዓመታዊ ዕቅዱን 94.4% ለማሳካት እና የ8.1% ዓመታዊ ዕድገት ለማስመዝገብተችሏል።
አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉ ንቁ የሞባይል ዳታ እና የድምጽ ተጠቃሚዎችም በቅደም ተከተል 51.53 ሚሊዮን እና 66.95 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የዕቅዱን 10.7% በማሳካት የ11% ዕድገት አሳይቷል። ከዕቅዳቸው አንጻር 91.0% እና 95.6% በቅደም ተከተል አሳክተዋል፡፡ የአጭር የጽሁፍ መልዕክት (SMS) ንቁ ተጠቃሚዎች ቁጥር 65.65 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ7.8% ዕድገት እና የ93.9% የዕቅድ አፈጻጸም ያሳያል።
ደንበኞች በአገልግሎት ዓይነት
በአገልግሎት ዓይነት ሲታይ፣ የሞባይል ድምጽ ደንበኞችች ቁጥር 86.91 ሚሊዮን (101.7% አፈጻጸም) በመድረስ ዓመታዊ ዕቅዱን ያሳካ ሲሆን ፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ8.2% ዕድገት አሳይቷል። የሞባይል ዳታ ተጠቃሚዎችም በበጀት ዓመቱ 51.53 ሚሊዮን የደረሱ ሲሆን፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10.7% ዓመታዊ አማካይ ዕድገት (CAGR) ያሳየና ከዘንድሮው የ56.63 ሚሊዮን ዕቅድ አንጻር የ91.0% አፈጻጸም ያስመዘገበ ነው። የፊክስድ ብሮድባንድ 1 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት አዲስ ምዕራፍ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ 52.5 ሚሊዮን ደርሷል።
የገቢ አፈጻጸም
ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት ለኮኔክቲቪቲ፣ ለዲጂታል አገልግሎቶች እና ለኢንተርፕራይዝ መፍትሄዎች ቀጣይነት መረጋገጥ 215.82 ቢሊዮን ብር ገቢ ማመንጨት የቻለ ሲሆን፤ ይህም የዓመታዊ ዕቅዱን 99.7% በማሳካት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ33.2% የላቀ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡
ለተመዘገበው ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ካበረከቱ የአገልግሎት ዓይነቶች መካከል የዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎት 31.1% ድርሻ ሲኖረው፣ የሞባይል ድምፅ አገልግሎት ደግሞ 23.5% ድርሻ ይዟል፡፡ በተጨማሪም የተጨማሪ እሴት አገልግሎቶች (VAS) 9.1% እና ዓለም አቀፍ አገልግሎቶች 8% ለጠቅላላ ገቢው የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የኢንተርፕራይዝ መፍትሄዎች 7.1% ድርሻ ያበረከቱ ሲሆን፤ ብሔራዊ መታወቂያ፣ የዲቫይዞች ሽያጭ እና ቴሌብር በቅደም ተከተል 3.3%፣ 4.0% እና 3.6% ድርሻ እንዲመዘገብ አድርገዋል፡፡
የዲጂታል ተጠቃሚነትን ማፋጠን
የዳታ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ከጠቅላላ ገቢው 31.1% ድርሻ በመያዝ የኩባንያው ዋነኛው የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ሆነው የወጡ ሲሆን፤ ይህም እ.አ.አ ከሰኔ 2018 ጀምሮ የ35.9% ድምር አማካይ ዓመታዊ ዕድገት (CAGR) ማስመዝገባቸውን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል የሞባይል ድምፅ አገልግሎት ለአጠቃላይ ገቢው 23.5% ድርሻ ያበረከተ ሲሆን፤ ከ2018 ጀምሮ ያስመዘገበው ዓመታዊ አማካይ ዕድገት 9.5% ነው፡፡
ይህ ውጤት ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየተደረገ ያለውን የተፋጠነ ሽግግር የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ኩባንያችን ከተመሠረተበት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ለሚሆን ጊዜ የድምፅ አገልግሎት ቀዳሚው የገቢ ምንጭ ሆኖ የቆየ ቢሆንም፤ የድምፅ አገልግሎት ገቢ የዕድገት ጉዞውን ቢቀጥልም የዳታ አገልግሎት በመጠነ-ሰፊ መስፋፋቱ የዳታ ገቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ከድምፅ አገልግሎት ገቢ የላቀ ድርሻ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ ይህም የደንበኞቻችንን እያደገ የመጣ የዲጂታል ተጠቃሚነት እንዲሁም የኩባንያችንን ስኬታማ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በግልጽ የሚያሳይ ታሪካዊ ስኬት ነው፡፡
የውጭ ምንዛሬ ግኝት እና ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እሴትን ማጠናከር
በበጀት ዓመቱ ዓለም አቀፍ አገልግሎቶችም ጠንካራ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ ሮሚንግን፣ የጅምላ የትስስር አገልግሎትን (wholesale connectivity) እና ስትራቴጂካዊ ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን በማጠናከር 139.9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አስገኝተዋል። በዚህም በበጀት ዓመቱ የተገኘው ጠቅላላ የውጭ ምንዛሬ መጠን 188.48 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል፡፡
ጠንካራ እና ዘላቂ የፋይናንስ አፈጻጸምን ማረጋገጥ
ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት በከፍተኛ የገቢ ዕድገት፣ በተሻሻለ የወጪ ቁጠባ እና በዲሲፕሊን የታገዘ የፋይናንስ አስተዳደር አማካኝነት ጉልህ ውጤት አስመዝግቧል። በዚህም መሠረት የኩባንያው ያልተጣራ ትርፍ (EBITDA) የ51.9% ወይም የ38.7 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት 113.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤ የሥራ ማስኬጃ ትርፍም (Operating Profit) የ47.5% ወይም የ30 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማስመዝገብ 92.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
የወጪ ቁጠባ እና የአሠራር ቅልጥፍና፡ በእያንዳንዱ ሀብት የላቀ እሴት መፍጠር
ኩባንያችን ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. (July 2021) ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው፣ የወጪ ቁጠባ ባህል “Do2Save” ኢኒሸቲቭ፣ ተከታታይ ለውጥን፣ የሀብት አጠቃቀም መሻሻልን እና በሁሉም የኩባንያችን እንቀስቃሴ ውስጥ እሴት መፍጠርን በማስረጽ ኩባንያ-አቀፍ የአሠራር ልቀት ዋና ማዕቀፍ መሆን ችሏል፡፡ በሪፖርት ዓመቱ ይህ ኢኒሸቲቭ 14.61 ቢሊዮን ብር የአሰራር ቅልጥፍና ትርፍ ማስገኘት የቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 96 በመቶው ከወጪ ማሻሻል እና 4 በመቶው ደግሞ ከገቢ ማሳደግ የተገኘ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው የኔትወርክ አቅምን በማሳደግ፣ የፊክስድ ኔትወርክን በማዘመን፣ የኃይል አጠቃቀም ውጤታማነትን በማላቅ፣ የዓለም አቀፍ ኮኔክቲቪቲን በመጨመር፣ ዲጂታል ሽግግርን በማፋጠን፣ የቢዝነስ (commercial) እና የሥርጭት ማሻሻያዎችን፣ የቢሮዎችና የተሽከርካሪዎች ስምሪትን በማዘመን፣ የግብይት ቅልጥፍና እና የአቅርቦት ሰንሰለት ልህቀትን በማካተት በተከናወኑ መጠነ ሰፊ ስራዎች አማካኝነት ነው።
እነዚህ ሁለገብ ጥረቶች ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ እድገትን፣ የደንበኞችን እርካታ፣ የኔትወርክ ጥራትን፣ ዲጂታል ሽግግርን እና የንብረት አጠቃቀምን ከማሻሻል እና ከማረጋገጥ ባሻገር፤ የአመራር ተጠያቂነትን፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥን እና በተለያዩ የሥራ ክፍሎች መካከል ያለውን የጋራ ትብብር ባህል በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። ይህም የአሠራር ቅልጥፍናን ለትርፋማነት፣ ለተወዳዳሪነት እና ለዘላቂ ስትራቴጂያዊ ዕድገት የጎላ ሚና አእንዲኖረው አስችሎታል፡፡
- ቴሌብር፡ የፋይናንስ አካታችነትን እና የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ላይ
ቴሌብር በቀላል የሞባይል ገንዘብ ማንቀሳቀሻነት (mobile wallet) ብቻ ሳይወሰን፤ ክፍያዎችን፣ የመክፈያና የገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን፣ የነጋዴዎች (merchant) አገልግሎትን፣ የመንግሥት ክፍያዎችን፣ ቁጠባን፣ ብድርን፣ የሐዋላ አገልግሎትን፣ ዲጂታል ንግድን እና ሌሎች ተጨማሪ እሴት የሚፈጥሩ አገልግሎቶችን (value-added services) ያቀፈ ሁለንተናዊ የዲጂታል ፋይናንስ ሥነ-ምህዳር መሆን ችሏል። ይህም ዕድገት ቴሌብር የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር እንዲሆን አስችሎታል።
ቴሌብር ከ33 ባንኮች፣ ከአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት እና ከቁጠባና ብድር የህብረት ስራ ማህበራት ጋር ያደረገው ትስስር፣ ከሰፊው የኤጀንቶች እና የነጋዴዎች ኔትዎርክ ጋር ተዳምሮ፣ በጋራ የመስራትና የመናበብ አቅምን ያጠናከረ ከመሆኑም በላይ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽነትን በማስፋት የኢትዮጵያን የዲጂታል ፋይናንስ መሠረተ ልማት ማጠናከር ችሏል።
የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር
ቴሌብር ደንበኞችን በማፍራት እና የዲጂታል ሥነ-ምህዳሩን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። በአጠቃላይ 60.6 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ በዚህም የዕቅዱን 96.9% ማሳካት ተችሏል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 8.54 ሚሊዮን ደንበኞች በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ አዳዲስ ደንበኞች ናቸው። በሌላ በኩል፣ 12 ሚሊዮን አዳዲስ አካውንቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ የመረጃ ጥራትን እና የፕላትፎርሙን ቅልጥፍና ለማሻሻል ሲባል 6.85 ሚሊዮን የማይንቀሳቀሱ (inactive) አካውንቶች እንዲወገዱ ተደርገዋል። የደንበኞች ተሳትፎም የጎለበተ ሲሆን፣ ባለፉት 90 ቀናት ውስጥ ንቁ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች (active users) ቁጥር 19.48 ሚሊዮን፣ የሱፐርአፕ (SuperApp) ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ ከ11.57 ሚሊዮን በላይ መድረስ ችሏል። ይህም ቴሌብር በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መሪ የዲጂታል ፋይናንስ ፐላትፎርምነቱን ደረጃ በድጋሚ እንዲያረጋግጥ አስችሎታል።
የቴሌብር ግብይቶች
ቴሌብር 2.61 ቢሊዮን ግብይቶችን በማስተናገድ በጠንካራ የዕድገት ጉዞ ላይ እየቀጠለ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም የበጀት ዓመቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለማሳካት የታቀደውን 2.09 ቢሊዮን ግብይት በማለፍ የዕቅዱን 124.6% ማሳካት ችሏል። ይህም የደንበኞች ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና በፕላትፎርሙ ላይ የሚደረጉ ተደጋጋሚ ግብይቶች (transaction frequency) መጨመራቸውን የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ145.3% ከፍተኛ ዕድገት ያሳያል። የግብይቱ የገንዘብ መጠን 4.19 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ76.2% ዕድገት በማሳየት የበጀት ዓመቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግብይት ለማከናወን የታቀደውን የ4.51 ትሪሊዮን ብር ዕቅድ 92.8% ማሳካት ተችሏል። ቴሌብር አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአጠቃላይ 9.13 ትሪሊዮን ብር የሚገመት ግብይት ተከናውኖበታል። ይህም በአገራችን ያለውን የገንዘብ ዝውውር በዲጂታል መንገድ ከማሳለጥ ባለፈ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተደራሽ እና ሁሉንም ያካተቱ እንዲሆኑ የላቀ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
የቴሌብር አገልግሎቶችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ፣ የኩባንያችንን አጋሮች ቁጥር ለመጨመር እንዲሁም በቴሌብር አማካኝነት የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ ለማስቻል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም መሠረት 410.7 ሺህ ወኪሎች እና 440.1 ሺህ ነጋዴዎች የቴሌብር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ወኪሎች ደንበኞችን መመዝገብ፣ ገንዘብ ገቢ ማድረግና ወጪ ማድረግ ማሳለጥ፣ የአየር ሰዓት መሸጥ እንዲሁም የአገልግሎት ክፍያዎችን ማስተናገድ ይችላሉ። በተጨማሪም ከ33 ባንኮች ጋር የማስተሳሰር ሥራዎች የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ይህም ከባንክ ወደ ቴሌብር እንዲሁም ከቴሌብር ወደ ባንክ ቀላል የገንዘብ ዝውውር ለማድረግ ያስችላል።
የቴሌብር የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት አፈጻጸም
በበጀት ዓመቱ ከባንኮች ጋር በመተባበር፣ በማኅበረሰባችን አጠቃላይ ለውጥና መሻሻል ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከማግኘት ባለፈ ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ አነስተኛ ቁጠባ እና ተያያዥ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማቅረብ ተችሏል። በዚህም ያለዋስትና በሚሰጥ የዲጂታል ብድር አማካኝነት የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ 19.51 ቢሊዮን ብር ለ5.65 ሚሊዮን ደንበኞች ተደራሽ ተደርጓል፤ ይህም የዓመታዊ ዕቅዱን 87.7% ያሳካ ነው። በተጨማሪም የዲጂታል ቁጠባ መጠን ከ1.3 ሚሊዮን ደንበኞች 18.75 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ66.9% ከፍተኛ ዕድገት ያሳያል።
የዘመን ገበያ (ኢ–ኮሜርስ) አፈጻጸም
ኩባንያችን የሀገራችንን የንግድ ሥርዓት ለማዘመንና ለማሳደግ “ዘመን ገበያ“ የተሰኘ የዲጂታል ገበያ (ኢ-ኮሜርስ) ፕላትፎርም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የዘመን ገበያን ተደራሽነትና ተቀባይነት ለማሳደግ በማድረሻ ዋጋዎች (delivery prices) ላይ ማስተካከያ የተደረገ ሲሆን፣ በተለይም የበዓላት ማድረሻ አገልግሎቶችን ነፃ በማድረግና በዕቃዎች ላይ ቅናሾችን በመስጠት የዘመን ገበያ ተጠቃሚዎችንና የዲጂታል ንግድ ተሞክሮን ለማሳደግ የላቀ ጥረት አድርጓል። ይህ በተለይ አብዛኛው ማኅበረሰብ የሚጠቀምባቸው የፍጆታ ዕቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋና በተቀላጠፈ ሁኔታ መቅረብ እንደሚችሉ እንዲሁም አምራቾች ምርቶቻቸውን በተሻሉ አማራጮች ለማኅበረሰቡ ማቅረብ እንደሚችሉ እንደ ማሳያ ሆኖ አገልግሏል።
በዚህም መሠረት ዘመን ገበያ በዓመቱ ውስጥ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ የገበያ የፕላትፎም ጉብኝቶችን አስተናግዷል። በተጨማሪም ከ58.3 ሺህ በላይ ደንበኞች 72.1 ሺህ ግብይቶችን የፈጸሙ ሲሆን፣ የተሸጡ ዕቃዎች ጠቅላላ ዋጋ 377.9 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ይህም እያደገ የመጣውን የደንበኞች እምነት፣ የዲጂታል ንግድ አጠቃቀም መስፋፋትን እንዲሁም የፕላትፎርሙ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን አስተዋፅኦ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው።
- በሰው ኃይል ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ፡ ለወደፊቱ ዝግጁ የሆነ ብቃት ያለው የሰው ኃይል እና ተቋማዊ አቅምን መገንባት
ኩባንያችን የሰው ኃይል ስትራቴጂውን ከኩንያው «ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር 2028» ስትራቴጂ ጋር በቀጥታ በማጣጣም፣ ሰራተኞቹን የዲጂታል ሽግግር፣ ፈጠራ እና ቀጣይነት ያለው እድገት ስትራቲጂያዊ ዋና አንቀሳቃሽ ኃይል እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ይገኛል። በተመረጡና ዘርፈ-ብዙ በሆኑ የልማት ኢኒሸቲቮች አማካኝነት የሰራተኞቻችንን አቅም በተከታታይ እያሳደግን የምንገኝ ሲሆን፣ ይህም ብቁ፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በቀላሉ መላመድ የሚችል እና ለወደፊቱ ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል ለመፍጠር አስችሏል። ከዋና ዋናዎቹ ተግባራት መካከል በኩባንያችን ውስጥ የሚሰጡ እና ከታወቁ የውጭ ተቋማት ጋር በመተባበር የተዘጋጁ ልዩ የስልጠና ፕሮግራሞች ይገኙበታል።
በዚህም መሰረት፣ ኩባንያችን ለ152,126 ተሳታፊዎች ስልጠና የሰጠ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 148,257 ሰራተኞች፣ 3,436 አጋሮች፣ 254 የኢንተርፕራይዝ ደንበኞች እና 179 የኮንትራት ሰራተኞች ይገኙበታል። ከዚህም በላይ 86 በመቶው ስልጠና በዲጂታል ፕላትፎርሞች አማካኝነት የተሰጠ ነው። ይህ በኩባንያችን ታሪክ ውስጥ ትልቁ እና በሥርዓት የተዋቀረ የስልጠና ተግባር ሲሆን፣ በዲጂታል አመራር፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ በሳይበር ደህንነት እና በኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖች ላይ ያተኮሩ ክህሎቶችን በማሳደግ የኩባን ያችን የሶስት ዓመት «ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር 2028» ስትራቴጂን በቀጥታ ለማሳካት የሚያስችል ነው።
በተጨማሪም ሴቶችን ወደ አመራርነት ቦታዎች ለማምጣት የተነደፈውን ስትራቴጂ በተግባር እያዋልን የምንገኝ ሲሆን፣ ሁሉን አቀፍ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናትን መሰረት በማድረግ፣ በቴክኒክ እና በኮሜርሻል የስራ ዘርፎች ውስጥ ለሚገኙ ሴት ስራ አስኪያጆች ልዩ የአቅም ማሳደጊያ ፕሮግራሞችን በመተግበር ላይ እንገኛለን። በተጨማሪም በቅርቡ በተደረገው ተቋማዊ መዋቅር ማሻሻያ ወቅት ብቁ የሆኑ ሴቶችን በጥንቃቄ ለይቶ በማውጣትና ወደ ቁልፍ የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች በማሳደግ ለጾታ እኩልነት ቅድሚያ የሚሰጡ ስራዎችን መስራት ችለናል።
- ከኮኔክቲቪቲ ባሻገር፡ የዲጂታል ምርቶችንና አገልግሎቶችን ማስፋፋት
ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አፈጻጸም
ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ደህንነቱ የተጠበቀ ማንነትን፣ እምነት የሚጣልባቸው የዲጂታል ግብይቶችን፣ የተሻሻሉ የሕዝብ አገልግሎቶችን እና የዘርፎች እርስ በርስ መናበብን (interoperability) በማሳደግ የ“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ራዕይን ለማሳካት የሚያስችል ዋነኛ የዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት ኢኒሸቲቭ ነው። ኩባን ያችን የሀገሪቱ መሪ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አሳላጭ እንደመሆኑ መጠን ሀገር አቀፍ መሠረተ ልማቱን፣ የደንበኞች ተደራሽነቱን፣ የዲጂታል አቅሙን እና የሥራ ማስፈጸም ብቃቱን በመጠቀም የብሔራዊ መታወቂያ አጠቃቀምና ተደራሽነትን ለማፋጠን ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኩባንያችን በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት፣ በፍራንቻይዝ በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት እና በተንቀሳቃሽ የምዝገባ ቡድኖች አማካኝነት በሁሉም 12 ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚሰራ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ትላልቅ የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ኔትዎርኮች አንዱን የዘረጋ ሲሆን፣ ይህም 119 ዞኖችን (98%)፣ 986 ወረዳዎችን (79%) እና 1,376 ከተሞችን ከ3,340 በላይ የምዝገባ መሣሪያዎችን (kits) የሚያጠቃልል ነው፡፡
ኩባንያችን እ.ኤ.አ ሚያዝያ 24 ቀን 2024 (ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም) ወደ ፕሮግራሙ ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ ወደ 32 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን መመዝገብ የቻል ሲሆን፣ ይህም ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ 69 በመቶውን የሚሸፍንና 27.1 ሚሊዮን መሠረታዊ የማንነት መለያ ቁጥሮችን (FINs) ያስገኘ ነው። በበጀት ዓመቱ ብቻ 20.19 ሚሊዮን ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ 17.17 ሚሊዮን መሠረታዊ የማንነት መለያ ቁጥሮች (FINs) ተሰጥተዋል።
በተጨማሪም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከ4 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን እንዲሁም ከUNHCR እና ከNRC ጋር በተደረገ አጋርነት 28,000 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን (IDPs) በመመዝገብ አካታች የዲጂታል ማንነት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ቅድሚያ ተሰጥቶ ተሰርቷልል። ተጨማሪ የታለሙ ኢኒሸቲቮች የሴፍቲኔት (PSNP) ተጠቃሚዎችን፣ ተመላሾችን፣ ተማሪዎችን እና ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ወገኖች የደገፉ ሲሆን፣ ይህም የመንግሥትን ሁለንተናዊ የዲጂታል ማንነት ተደራሽነት ግብ ለማሳካት ያስቻል ነው።
የብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ዝግጅትና ሥርጭት አገልግሎትን ለማሻሻል የተቻለ ሲሆን፣ ከቀረቡት 9.4 ሚሊዮን ትዕዛዞች ውስጥ 9.35 ሚሊዮን ካርዶች (99%) እንዲታተሙ ተደርጓል፡፡ በበጀት ዓመቱ በ19 የክልል ማተሚያ ማዕከላት፣ በ27 አታሚዎች፣ ከ500 በላይ የካርድ መቀበያ ቦታዎች እና በአንድ ጊዜ በሚላክ የይለፍ ቃል (OTP) ላይ በተመሠረተ አስተማማኝ የካርድ ሥርጭት የታገዘ 7.45 ሚሊዮን ካርዶች ታትመዋል። ይህም ከ4,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ለፍራንቻይዝ አጋሮችም የቢዝነስ ዕድሎችን ማስፋት ችሏል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ (EV) የኃይል መሙያ ጣቢያዎች
በበጀት ዓመቱ አምስት እጅግ ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ተገንብተዋል። ይህም ኩባንያችን እስካሁን የገነባቸውን የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ቁጥር ወደ 9 ያደረሰው ሲሆን፥ እጅግ በጣም ፈጣን እና ፈጣን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአንድ ጊዜ 108 ተሽከርካሪዎችን የመሙላት አጠቃላይ አቅም ፈጥሯል። ይህ የመንግሥትን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲና አቅጣጫ ከመደገፍ ባለፈ፥ በሀገራችን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀምንና ሽግግርን ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
- የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ዲጂታል ተሳትፎን ማጠናከር
በኩባንያችን “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂ ውስጥ ከተቀመጡት ግቦች አንዱ ከአገር ውስጥ ባለፈ በሌሎች አገራት ውስጥ በመንቀሳቀስ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የዲጂታል ሶሉሽኖች አቅራቢ ተቋም መሆን ነው። በዚህም መሠረት በበርካታ አገራት ውስጥ ከሚገኙ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ጋር የቢዝነስ ግንኙነቶችን እየመሠረተ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የካሜሩን መንግሥታዊ የቴሌኮም ተቋም ከሆነው ካምቴል (CAMTEL) ጋር የተደረገው ስምምነት አንዱ ነው።
የዚህ አጋርነት መሠረት ኩባንያችን ከመደበኛ የቴሌኮም አቅራቢነትን አልፎ ወደ ቴክኖሎጂ ኩባንያነት (TechCo) ለማደግ የነደፈው ስትራቴጂ ነው። ስትራቴጂው በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርገው የዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽነትን ማስፋፋት፣ ከመደበኛ የድምፅ እና የዳታ ግንኙነት ባለፈ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የዲጂታል ፕላትፎርሞችን ማቅረብ፣ እንዲሁም ስኬትን ባስመዘገበው የቴሌብር ዲጂታል ስነ-ምህዳር ላይ በመመሥረት የፋይናንስ፣ የማህበራዊ እና የመንግሥት አገልግሎቶችን በማስተሳሰር እያሳለጠ ይገኛል።
የሆራይዘን ፋይበር እና ስትራቴጂያዊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች
የሆራይዘን ፋይበር እቅድ (Horizon Fiber Initiative) ጅቡቲን፣ ኢትዮጵያን፣ ሱዳንን እና ሳዑዲ አረቢያን (ጅዳን) የሚያገናኝ ለውጥ አምጪ እና ከፍተኛ አቅም ያለው የየብስ ኮሪደር በመሆን እያገለገለ ይገኛል። ይህም ለሃፐርስኬሎች (hyperscalers) እና ለአለም አቀፍ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት አቅራቢዎች ተስማሚ የሆነ፣ አስተማማኝ፣ የመረጃ መዘግየት ጊዜው የቀነሰ እና ከባህር ወለል ኬብል ጥገኝነት የሚገላግል መልቲ-ቴራቢት (multi-terabit) አማራጭ የሚያቀርብ ነው።
እ.ኤ.አ. ታህሳስ 3 ቀን 2024 በአዲስ አበባ በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ስትራቴጂያዊ አጋርነቱ ይፋ ከሆነበት እና እ.ኤ.አ. የካቲት 4 ቀን 2026 የትግበራ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ፣ ፕሮጀክቱ ጠንካራ የአፈጻጸም ፍጥነትን በመያዝ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በጥብቅ ክትትል እየተከናወነ ይገኛል።
ከጫፍ-እስከ-ጫፍ (E2E) የመፍትሄ ዲዛይን መዋቅር (architecture) ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን እንዲሁም ሁሉም የግዢና የጣቢያ (site) ቁሳቁሶች አቅርቦት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ እቅዱ በተሳካ ሁኔታ ወደ ተግባራዊ የመዘርጋት ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር፣ ሆራይዘን ቀጣናዊ የመረጃ ፍሰትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳልጣል፣ የመረጃ መዘግየት ጊዜንና የማስተላለፊያ ወጪን ይቀንሳል፣ ቀጣናዊ የዲጂታል ንግድና የኢኮኖሚ እድገትን ያነቃቃል እንዲሁም ለወደፊቱ ድንበር ተሻጋሪ የቴሌኮሙኒኬሽን ማስፋፊያ ሊያድግ የሚችል ጠንካራ መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል።
- የጋራ ዕሴት መፍጠር፡ ለደንበኞች፣ ለመንግሥት እና ለማህበረሰብ የምናበረክተው አስተዋፅዖ
ኩባንያችን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በአገር አቀፍ ደረጃ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ተግባራትን በተቋማዊ ማህበራዊ ኃላፊነት (CSR) ዕቅዶች ሥር በማደራጀት እና ከዘላቂ የልማት ግቦች (SDGs) ጋር በማስተሳሰር የአገሪቱን እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል። እነዚህ ተግባራት በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርጉት በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ልማት እና በከተማ ውበት ፕሮጀክቶች ላይ ሲሆን፣ ዓላማቸውም የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ፣ የዲጂታል ግንዛቤ ክፍተትን ማጥበብ፣ አካታችነትን ማረጋገጥ እና የማህበረሰቡን ዘላቂ ልማት ማጠናከር ነው።
በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ከ492 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ ይህ ድጋፍ ትምህርትን፣ ጤናን፣ ሰብአዊ ድጋፍን፣ የአካባቢ ጥበቃን፣ አረንጓዴ ልማትንና ውበትን እንዲሁም አገራዊ ፕሮጀክቶችን ያካተተ ነው። ኩባንያችን የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል፣ ጽዱ እና ለኑሮ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር እንዲሁም ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ባለው ቁርጠኝነት መሠረት፣ የተቋማችን ሠራተኞችና አጋሮች በተሳተፉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመላ አገሪቱ ችግኞች እንዲተከሉ በማድረግ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል።
ኩባንያችን ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ፣ ሠራተኞቹ በፈቃደኝነት በገንዘብ 3.6 ሚሊዮን ብር እና በዓይነት የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለተለዩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ፣ የደም ልገሳ እና ሌሎች የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎቶችን በማበርካት አበረታች እና ዓርአያነት ያለው ተግባር ፈጽመዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የገቢ ምንጭ
ኩባንያችን ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት የዲጂታል ኢኮኖሚ ስነ-ምህዳርን በመገንባት ረገድ የሚጫወተውን ቁልፍ የአስቻይነት ሚናን ከመወጣት ባሻገር፣ ለዜጎች ዘላቂ የሥራ እና የገቢ ምንጭን በመፍጠር አገራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ሁኔታ እየተወጣ ይገኛል።
በዚህም መሠረት ለ44,757 ሠራተኞች (15,912 ቋሚ እና 28,845 በውል/ጊዜያዊ) ከተፈጠረው ቀጥተኛ የሥራ ዕድል በተጨማሪ፣ በምርት እና አገልግሎት ስርጭት፣ በወኪሎች እና በተለያዩ የአጋርነት ሞዴሎች አማካኝነት መጠነ-ሰፊ የሥራ እና የገቢ ማስገኛ ዕድሎች ተመቻችተዋል። በተለይም ይህ ስነ-ምህዳር 519,810 የአገልግሎት ስርጭት አጋሮችን እና የቴሌብር ወኪሎችን፣ 2,205 የአገር ውስጥ አቅራቢዎችን፣ 1,213 የተጨማሪ ዕሴት አገልግሎት (VAS) አጋሮችን፣ 138 የፍራንቻይዝ አጋሮችን እና 693 ዓለም አቀፍ አጋሮችን ያካትታል።
በአጠቃላይ ኩባንያችን በደህንነት፣ በኔትወርክ ዝርጋታ፣ በጥገና፣ በትራፊክ ቁጥጥር፣ በግንባታ፣ በአካባቢ ጥበቃ (የችግኝ እንክብካቤ) እና በሦስተኛ ወገን ስምምነቶች በተፈጠሩ የሥራ መደቦች አማካኝነት በስነ-ምህዳሩ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ እና የገቢ ማስገኛ ዕድሎችን ለመፍጠር ችሏል። ይህም ኩባንያችን ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር እና የዜጎችን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ ያለውን ወሳኝ ሚና የሚያሳይ ነው።
በሌላ በኩል፣ የኩባንያችንን ምርታማነት ለመጨመር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና የቢዝነስ ሞዴሎችን በፍጥነት ለመተግበር እንዲሁም ፈታኝ ሁኔታዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር አዳዲስ ዕድሎችን ለመጠቀም ወቅታዊ የአደረጃጀት ለውጥ እና የሰው ኃይል ምደባ ሥራዎች በቀጣይነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ለአገር አቀፍ ልማት አስተዋፅዖ በማድረግ ረገድ
በበጀት ዓመቱ የታክስ ክፍያ 73.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን (36 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ እና 37.5 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ ሆኖ ከዚህ ውስጥ 2.4 ቢሊዮን ብር ለብሔራዊ የአደጋ ማገገሚያ ፈንድ /National Disaster Recovery Fund/ የተደረገ አስተዋፅዖ ነው)። ይህም ከ2018 ጀምሮ የተከፈለውን አጠቃላይ ታክስ 244.5 ቢሊዮን ብር በማድረስ ኢትዮ ቴሌኮም ለአገር ግንባታ የሚያደርገውን እያደገ የመጣውን ጉልህ አስተዋፅዖ ያሳያል።
ዘላቂ ትስስርን በአረንጓዴ እና ጠንካራ መሠረተ ልማት ማረጋገጥ
ኢትዮ ቴሌኮም የኮሜርሻል ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ (EV) ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን በመዘርጋት አገራዊ የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮችን ለመደገፍ የቻለ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ሁለት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጂንግ ጣቢያዎች ተገንብተው አጠቃላይ ቁጥራቸው አምስት nደርሷል፤ ይህም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ትራንስፖርት ንቅናቄ ኢኒሼቲቭን የሚደግፍና የቴሌኮም መሠረተ ልማትን ከአገራዊ የዘላቂነት ግቦች ጋር የሚያስተሳስር ነው። የላቁ የሊቲየም-አዮን ባትሪዎች እና የፀሐይ ኃይል ሲስተሞች ትስስር የመጠባበቂያ ኃይል አስተማማኝነትን ከማሻሻሉም በላይ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ኢትዮ ቴሌኮም ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ቁርጠኝነት ለማጠናከር ችሏል።
የማዘመን እና የኢነርጂ ብቃት እርምጃዎቻችን—በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ከሚታገዙ የሲሊፕ ሞዶች (sleep modes ማለትም ኃይልን ለመቆጠብ ሲባል አገልግሎት በማይሰጥበት ወቅት) እና ተለዋዋጭ የካሪየር የአገልግሎት መቋረጦች (shutdowns) ጀምሮ እስከ ነባር/ሌጋሲ መሣሪያዎችን መተካትና በክላውድ ማዕከላዊነት (cloud centralization) ረገድ—የኦፕሬሽናል ሥራዎች ማሻሻያዎች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ዲጂታል አጀንዳ የሚያፋጥኑ ስትራቴጂያዊ አስቻዮች ናቸው። እነዚህ ኢኒሼቲቮች ጠንካራ፣ ዘላቂ እና ለወደፊት ዝግጁ የሆኑ ኔትወርኮች ላይ ከሚያተኩረው የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ራዕይ ጋር በቀጥታ የሚጣጣሙ ናቸው። የኢነርጂ ፍጆታን በመቀነስ፣ የመሣሪያዎችን የአገልግሎት ዘመን በማራዘም እና የጥገና ወጪን በመቀነስ፣ ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌኮም ተደራሽነት ቀልጣፋ፣ አካታች እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆኑን በማረጋገጥ አገሪቱ ዘመናዊና ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት እያገዘ ይገኛል።
የዘላቂነት እና የESG አፈጻጸም
ኢትዮ ቴሌኮም የአካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና አስተዳደራዊ (ESG) መርሆችን በኮርፖሬት ስትራቴጂው ውስጥ ማዋሃዱን የቀጠለ ሲሆን፣ ለደንበኞች፣ ለሰራተኞች፣ ባለአክሲዮኖች፣ ማህበረሰቦች እና ለሀገር ዘላቂ እሴት እየፈጠረ ይገኛል። ኩባንያችን በ “ቀጣዩ አድማስ ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028“ ስትራቴጂው በመመራት ከሀገራዊና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች እንዲሁም ከአለም አቀፍ የዘላቂነት ግቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ የአየር ንብረት ጥበቃ ተሳትፎ፣ የዲጂታል አካታችነትን፣ ተጠያቂነት ያለው አሰራርን በመከተል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን እያፋጠነ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውጥን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል።
በ2018 (2025/26) የበጀት ዓመት ኢትዮ ቴሌኮም ዘላቂነትን በትግበራዎቹ ውስጥ በማካተት ረገድ ከፍተኛ እድገትን አሳይቷል። ዋና ዋና ከሚባሉት ስኬቶች መካከልም፦
- ታዳሽ የኃይል ኢንቨስትመንቶች፣ የኔትወርክ ማዘመን እና ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የካርቦን ልቀትን መቀነስ፤
- በቴሌብር፣ በተመጣጣኝ የኮኔክቲቪቲ እና ተደራሽ የዲጂታል አገልግሎቶች አማካኝነት የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን ማስፋፋት፤
- የሰራተኞችን ደህንነት፣ ብዝሃነትንና የሰው ሃብት ልማትን ማጠናከር፤
- ተጠያቂነት ባለው የግዥ አሰራር፣ በህግ አክባሪነት፣ በሳይበር ደህንነት፣ በመረጃ ሚስጥራዊነት እና ግልጽ በሆነ የቢዝነስ አሰራር አማካኝነት የኮርፖሬት አስተዳደርን ማጠናከር የሚሉት ይገኙበታል።
አካባቢያዊ (Environmental)፦ ኢትዮ ቴሌኮም ተጨማሪ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የኔትወርክ ግብአቶችን፣ የሃይብሪድ ኃይል ስርዓቶችን እና ኃይል ቆጣቢ አረንጓዴ የዳታ ማዕከላትን በመትከል የአካባቢ ጥበቃ ሚናውን ያጠናከረ ሲሆን በውጤቱም ከፍተኛ የኃይል አጠቃቀም እና የካርቦን ልቀት ቅነሳን አሳክቷል። ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ (EV) የሀይል መሙያ ጣቢያ በመገንባት 212 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ስራ ላይ በማዋል፣ የዳበረ የኔትወርክ ኃይል አማራጭ ትግበራው እና የአረንጓዴ አሻራ መልሶ ማልማት እንቅስቃሴዎቹ ኩባንያችን ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ግቦች የሚያደርገውን አስተዋፅኦ የበለጠ አጠናክረውታል።
በአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት (Green Development Project) ኩባንያችን በ84 ቦታዎች 347,700 የዛፍ ችግኞችን የተከለ ሲሆን፤ በተጨማሪም ለተለያዩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች 19.9 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት በማድረግ የ1,720 ዜጎችን የአረንጓዴ ስራ እድል እውን አድርጓል።
ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በስፋትና በፍጥነት በመተግበር 190 በፀሐይ ብርሃን ብቻ (pure solar) የሚሠሩ የቴሌኮም ጣቢያዎችን፣ 867 ድቅል (Hybrid) የኃይል ሥርዓቶችን (solar,and battery) እና 1,114 የሊቲየም-አዮን ባትሪ ማከማቻዎችን የገነባ ሲሆን፤ ይህም የዲዜል ጄኔሬተሮችን የሥራ ሰዓት እስከ 40% ድረስ መቀነስ አስችሏል።
ተጠያቂነት ባለው የቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ፣ የመሳሪያዎች እድሳት፣ የሀብት ማገገሚያና የመልሶ መጠቀም (recycling) እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በዘላቂ የሀብት አስተዳደር አማካኝነት የሰርኩላር ኢኮኖሚ አሰራሮቹን ያጠናከረ ሲሆን ከአቅራቢዎች ጋር በሚደረግ ተጠያቂነት ያለው ግንኙነትና ሀገራዊ የአካባቢ ጥበቃ መርሆችን በማክበር የአካባቢ ጥበቃ ኀላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል ።
ማህበራዊ (Social)፦ ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ የዲጂታል አካታችነትን በማረጋገጥ የኮሙኒኬሽን እና የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለዜጎቹ ተደራሽ ማድረጉን አጠናክሮ ቀጥሏል። ኩባንያችን በሀገር አቀፍ የኮኔክቲቪቲ ልማት ትግበራው በተመጣጣኝ ልዩ የፓኬጅ አማራጮቹ አማካኝነት ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የገጠሩን ማህበረሰብ ጨምሮ ተመላሽ ዲያስፖራዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። ከ 6.1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞቹ ወደ ፈጣን የብሮድባንድ ቴክኖሎጂዎች የተሸጋገሩ ሲሆን ከ 834,000 በላይ ደንበኞች የዲጂታል ትምህርት ፕላትፎርሞችን ተጠቅመዋል፤ እንዲሁም የዲጂታል ክፍተቱን ለማጥበብ የሚያግዙ ተመጣጣኝ ስማርት ዲቫይዞች ለዜጎቹ አስተዋውቋል። ቴሌብር 4.19 ትሪሊዮን ብር ግብይቶችን በማስተናገድ (ይህም ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት/GDP ወደ 20% ያህል ጋር እኩል ነው) የፋይናንስ አካታችነትን ከፊት ሆኖ መምራቱን የቀጠለ ሲሆን፤ የዲጂታል ክፍያ ሥነ-ምህዳርን፣ የገጠር ወኪል ኔትወርኮችን፣ የነጋዴዎች ምዝገባን እና የመንግስት ዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ሥርዓትን በማዘመን አስፍቷል።
ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ኩባንያችን ከ492 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ በጎ አድራጎቶችን አከናውኗል። ከዚህ ውስጥ 140.8 ሚሊዮን ብር ለ39 አጋር የበጎ አድራጎት ተቋማት ቀጥተኛ የገንዘብና የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የዋለ ሲሆን፤ በተጨማሪም ለልብ ህሙማን እና ፊስቱላ ማዕከላት ነፃ የኢንተርኔት ማቅረብን፣ እንዲሁም ለሴፍቲኔትና WFP ተጠቃሚዎች በዲጂታል መንገድ ክፍያ ማዳረስን ያካተተ ነው።
የዲጂታል አጠቃቀምን ለማፋጠን እና የዲጂታል ልዩነትን (digital divide) ለማጥበብ 2.1 ሚሊዮን ስማርትፎኖችን በድጎማ ማሰራጨት ተችሏል።
ለ80,000 ተማሪዎች የተዘጋጀው 960,000 ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የመማሪያ ደብተሮች ድጋፍ፣ ለእያንዳንዱ ተማሪ 12 ደብተሮች የሚያደርስ ነው። ይህም እያንዳንዱ ልጅ ለአንድ ሙሉ የትምህርት ዘመን ለዋና ዋና የትምህርት ዓይነቶቹ ያለ ምንም የደብተር እጥረት በብቃት እንዲከታተል ያስችለዋል።
ገቨርናንስ (Governance)፦ ኢትዮ ቴሌኮም አሰራሩን ከሀገራዊ ደንቦች እና ከአለም አቀፍ የESG መርሆች ጋር በማጣጣም የአሰራር ማዕቀፉን የበለጠ አጠናክሯል። ኩባንያችን ውጤታማ በሆነ የስጋት አስተዳደር፣ በሥነ-ምግባር እና በህግ ማዕቀፍ ጥንካሬ፣ በሳይበር ደህንነት፣ በመረጃ ሚስጥራዊነት እና ግልጽ በሆነ የፋይናንስ ሪፖርት የተደገፈ ጠንካራ የኮርፖሬት አሰራር መዋቅርን ገንብቷል በተጨማሪም ለተከታታይ ስምንት ዓመታት እንከን አልባ (unqualified) የኦዲት አስተያየት አግኝቷል። በጠንካራ የደንበኞች ማንነት ማረጋገጫ እና በዲጂታል የቁጥጥር ስልት የዲጂታል ማጭበርበርን ለመከላከል ጠንካራ ስራዎች ተሰርተዋል፣ 99.99% የቁልፍ ሲስተሞች ዝግጁነትን (availability) አረጋግጧል በዚህም በበጀት ዓመቱ ምንም አይነት አስጊ የመረጃ ሚስጥራዊነት ጥሰት አልገጠመውም በዚህም አስተማማኝ ተቋማዊ የስጋት አስተዳደርን ገንብቷል። የአቅራቢዎች አስተዳደር በ ESG በተቀናጁ የግዥ አሰራሮች፣ በአፈጻጸም ግምገማዎች፣ ተጠያቂነት ባለው የሀብት አቅርቦት እና ግልጽ በሆነ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የበለጠ ተጠናክሯል።
በነዚህ የስኬት ዐምዶቹ አማካኝነት ኢትዮ ቴሌኮም ዘላቂ የቢዝነስ አሰራሮችን እና የዲጂታል ፈጠራዎችን እርስ በእርስ ማቀናጀት እንደሚቻል ማሳየት ችሏል። በአሰራር ሥርዓቱ ውስጥም የESG መርሆዎችን በማካተት ኩባንያችን ለኢትዮጵያ የበለጠ አካታች፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ የዲጂታል ሥነ ምህዳር እየፈጠረ ዘላቂ አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን እየገነባ ይገኛል።
- ለባለአክሲዮኖች እና ባለድርሻ አካላት እሴት መፍጠር
በበጀት ዓመቱ ኢትዮ ቴሌኮም በጠንካራ የፋይናንስ ማገገም፣ በዘላቂ እድገት እና በስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንቶች አማካኝነት ለባለአክሲዮኖች እና ለባለድርሻ አካላት ከፍተኛ እሴትን መፍጠር ችሏል። ኩባንያችን የአፈጻጸም አቅሙን በማሻሻል፣ የፋይናንስ ብቃቱን በማጠናከር፣ የባለቤትነት ካፒታልን (equity) በማሳደግ እና ያልተከፋፈለ ትርፍን (retained earnings) በማሳደግ የረጅም ጊዜ እሴትን ለባለ አክሲዮኖች ፈጥፘል። ይህም የፋይናንስ የመቋቋም አቅምን እና የኩባንያችንን የውስጥ የገንዘብ አቅምን አጠናክሯል። በዚህም አጠቃላይ ሀብቱ (total assets) በ 27% አድጎ 420 ቢሊዮን ብር መድረሱ የመሰረተ ልማት፣ የቴክኖሎጂ ሀብቶች እና የዲጂታል አቅሞች ላይ ከተደረጉ ኢንቨስትመንቶች የተገኘውን እሴት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፤ ይህም የወደፊት ገቢ የማመንጨት አቅምን እና የተቋሙን እሴት ያጠናክራል።
ለደንበኞቹ እና ለማህበረሰቡም ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌኮም መሰረተ ልማት፣ በዲጂታል ፕላትፎርሞች እና በአገልግሎት አቅም ላይ ያደረገው ተከታታይ ኢንቨስትመንት ተደራሽነትን፣ አስተማማኝነትን እና ለአዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶች ያለውን ዝግጁነት አሻሽሏል። የኩባንያችን ዘርፈብዙ የአገልግሎት ተደራሽነት የዲጂታል አካታችነትን በመደገፍ፣ ንግዶችን በመደገፍ፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በከፍተኛ የታክስ ክፍያዎችና የአቅራቢዎች ተሳትፎ አማካኝነት ሰፊ ኢኮኖሚያዊ እሴትን ፈጥሯል። ለአጋሮች እና አቅራቢዎችም በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እና በአገልግሎት ተደራሽነት ላይ የታየው እድገት የቢዝነስ ትብብርን እና የሥነ-ምህዳር ልማቱን አጠናክሮታል።
በአጠቃላይ ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ ከአጭር ጊዜ የፋይናንስ አፈጻጸም ማሻሻያ ወደ ዘላቂ የባለድርሻ አካላት እሴት መፍጠር መሸጋገሩን ያሳየ ሲሆን፤ ይህም ምርታማነትን፣ የጎለበተ የፋይናንስ ጥንካሬን እና ለቀጣይ እድገት እና ለሀገራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚያዘጋጁ ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማጣመር የተገኘ ስኬት ነው።
- ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች
በበጀት ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ያጋጠሙ ሲሆን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ያጋጠመው የዋጋ ግሽበት (Inflation)፤ የውጭ ምንዛሪ (FX) እጥረት እና ባልተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ምክንያት የሚፈጠሩ የንግድ መዋዥቅ ተጽዕኖዎች የስራ ማስኬጃ እና የካፒታል ወጪዎችን በተለይም ከሃገር ውጭ በግዢ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኔትወርክ እቃዎችን ዋጋ ከፍ እንዲል አድርገውታል። እነዚህ ተግዳሮቶች በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የኔትዎርክ ጣቢያዎቻችን ከሚጠቀሙት ተጠባባቂ የዲዝል ጄኔሬተሮች ከፍተኛ የኃይል ወጪ ጋር ተደምረው የጥሬ ገንዘብ ፍሰት (cash flow) ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። እነዚህን የፋይናንስ ማነቆዎች ለመፍታት ፈቃድ ባላቸው አስመጪዎች ፣ በግልጽ ጨረታ ግዢ እንዲሁም የራስ አቅም አቅርቦትን በመጠቀም የተሳለጠ የሀብት አቅርቦት ማዕቀፍ (diversified) ከአማራጭ የፋይናንስ ዘዴዎች ጋር ተተግብፘል።
የኔትወርክ መሰረተ ልማቶች ለአደጋ ያላቸው ተጋላጭነት በመቀጠሉ ሁን ተብሎ የሚከሰቱ የአደጋ ስጋቶችን ጨምሮ የኔትወርክ ኬብል ስርቆቶች፣ በመንገድ ሥራ ምክንያት በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የፋይበር ኬብል ጉዳቶች ለአገልግሎት መቆራረጥ ምክንያት በመሆናቸው የተነሳ ኩባንያችን ከኮፕር ኬብል ወደ ዘመናዊውና ፈጣኑ የፋይበር ኔትወርክ የሚያደርገውን ሽግግር በማፋጠን እንዲሁም ከከተሞች የኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ በኔትወርክ ደህንነት ሥራዎች ላይ በትብብር በመስራት ላይ ይገኛል።
በስትራቴጂያዊ አጋርነት በኩል በነበረው ግንኙነት ላይ የአለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ፣ የቁጥጥር ማዕቀፍ ለውጦች፣ የሳይበር ደህንነት ስጋቶች እና ከ ኦቨር ዘቶፕ (OTT) አገልግሎቶች የሚመጣ የገበያ ውድድር ቀጣይነት ያላቸውን የአገልግሎት ስጋቶችን ደቅነዋል። በዚህም ፈቃድ ያላቸውን አቅራቢዎች ዝርዝር ማዕቀፍ (ASL) በማስተዋወቅ እና የአቅራቢዎችን ኔትወርክ በማስፋት አለም አቀፍ የግዢ መዘግየቶችንና የግብአት ዋጋ ጭማሪን ለማረጋጋት ተሰርቷል።
- ይፋዊ የአክሲዮን ምዝገባ እና የካፒታል ገበያ መሪነት
ኢትዮ ቴሌኮም ታሪካዊ ምዕራፍ በማስመዝገብ ወደ ህዝባዊ አክሲዮን ማህበርነት (Public Share Company) የተሸጋገረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ሴኪውሪቲስ ኤክስቼንጅ (ESX) የመጀመሪያውን ይፋዊ የአክሲዮን ምዝገባ አከናውኗል። በዚህም የሁለተኛ ደረጃ የአክሲዮን ገበያ ግብይት ከግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም (May 26, 2026) ጀምሮ ከተጀመረ ወዲህ የአንዱ አክሲዮን ዋጋ ከ300 ብር ወደ 852 ብር አድጓል፤ይህም የ184% ከፍተኛ ጭማሪን ያሳያል።
ይህ ፈጣን የአክሲዮን ዋጋ እድገት ባለሀብቶች በኩባንያችን “ቀጣዩ አድማስ” ስትራቴጂ እና በዲጂታል ኢኮኖሚ በሚመራው እድገቱ ላይ ያላቸውን ጥልቅ እምነት ያረጋገጠ ሆኗል። ወደ 47,000 የሚጠጉ የአክሲዮን ግዢ ማመልከቻዎች የመዘገበ ሲሆን ይህንን ተከትሎ 96% የአክሲዮን ዲማቴሪያላይዜሽን (share dematerialization) መጠን ተሳክቷል፤ ይህ ስኬታማ ሽግግር ኢትዮ ቴሌኮም ግልጽ እና እሴት-መር ሀገራዊ መሪ ተቋምነቱን የሚያጠናክር እና በኢትዮጵያ አዳጊ በሆነው የካፒታል ገበያ ላይ እንደ ሞዴል ፍኖት የሚያገለግል ውጤት ነው።
ለተመዘገበው ስኬት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ጉዳዮች
የኩባንያችን የስራ አፈጻጸም እድገት እና ስትራቴጂያዊ ስኬት ሀገራዊ ኃላፊነት ከሚሰማው የዳይሬክተሮች ቦርድ እና ቀልጣፋ አስተዳደር ጀምሮ በበርካታ ቁልፍና አስቻይ ጉዳዮች የተመራ ነው። ይህ አስተዳደራዊ መሠረት በጠራ ስትራቴጂያዊ አሰላለፍ፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥነ ምግባር፣ እንዲሁም በደንበኛ-ተኮር አፈጻጸም የዲጂታል ፈጠራን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ውህደትን በሚያጎላ ተቋማዊ ባህል የተጠናከረ ነው። በቀጣይም እነዚህን ስኬቶች ለማስቀጠል ኩባንያችን ቀጣይነት ባለው የሰው ሀብት ልማት፣ ንቁ የሰራተኞች ተሳትፎ እና በጋራ የውስጥ ማዕቀፎች አማካኝነት በተቋማዊ ቅልጥፍና (organizational agility) ላይ ትኩረት ያደርጋል።
ከተቋሙ ውጭ ባለው የስራ አፈጻጸም ኩባንያችን በቀጠናው ስትራቴጂያዊ አጋርነቶችን በመገንባት፣ የማህበራዊ ኃላፊነቱን (CSR) በማጠናከር ብሎም ዋና ዋና ፕሮጀክቶችን በተሻሻሉ የግዢ ሂደቶች በመፈፀም ላይ የተደገፈ ነው። እነዚህ የተቀናጁ ተግባራዊ ክንውኖች የደንበኞችን ታማኝነት ለማሳደግ፣ ተመጣጣኝ እና አካታች የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲሁም በስልታዊ የወጪ ቁጠባ እርምጃዎች አማካኝነት የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ያግዛሉ።
- እውቅና እና ሽልማት
በበጀት ዓመቱ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም የሚከተሉትን ሀገራዊ እና አህጉራዊ ሽልማቶች እና እውቅናዎች አግኝቷል፡
- የፕላቲኒየም ግብር ከፋይ ሽልማት፦ ቀጣይነት ባለው የታክስ ህግ አክባሪነት እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚያደርገው ዘላቂ አስተዋፅኦ እውቅናን ያገኘ ሲሆን ፤ ለተከታታይ አምስት ዓመታት በሀገሪቱ ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ በመሆን ደረጃውን አስጠብቋል።
- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) እውቅና፦ ለዚህ ሀገራዊ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴ በሚያደርገው የፋይናንስ አስተዋፅኦ እና ንቁ ተሳትፎ እውቅና እና ክብር ተሰጥቶታል።
- የአፍሪካ ምርጥ ብራንዶች ሽልማት፦ በ16ኛው ዓመታዊ የBrand Africa 100 ሽልማት ላይ “Most Admired Ethiopian Brand in Telecommunications” እና “Most Admired Ethiopian Brand Doing Good for Society and the Environment” ተብሎ ተሰይሟል።
- ሀገራዊ የዲጂታል ንግድ ሽልማት፦ የዲጂታል ክፍያ ስርዓቶችን ለማሳደግ እና የአካባቢውን የኢ-ኮሜርስ ሥነ-ምህዳር ለመደገፍ ላደረገው አስተዋፅኦ በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተሸላሚ ሆኗል።
- አህጉራዊ የአመራር እውቅና፦ የኩባንያችን ዋና ስራ አስፈፃሚ ለቢዝነስ ትራንስፎርሜሽን፣ ለዲጂታል ፈጠራ እና ለተቋማዊ እድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና የሚሰጠውን “African Businesswomen in Leadership 2026” ሽልማት የተቀበሉ ሲሆን፤ ይህም በሀገሪቱ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ገበያ ውስጥ ያለንን ተወዳዳሪነት እና ተቀባይነት በከፍተኛ ደረጃ ያጠናክረዋል።
- ቴሌብር GSMA Certification፡ ቴሌብር ታዋቂውን የGSMA ሞባይል ማኒ ሰርቲፊኬሽን (GSMA Mobile Money Certification) አግኝቷል።
በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው ስኬት የጋራ ርብርብ ውጤት በመሆኑ ለውድ የኩባንያችን ቤተሰቦች፣ ለክቡራን ደንበኞቻችን እንዲሁም ስትራቴጂያዊ አጋሮቻችን ለሆናችሁ አከፋፋዮች፣ አቅራቢዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና ለመላው ባለድርሻ አካላት ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን። ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የጀመርነውን የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አጠናክረን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ዛሬም በድጋሚ እናረጋግጣለን።
ኢትዮ ቴሌኮም
ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም




