“ባለሁበት እንደ አንድ የኢትዮ ቴሌኮም አምባሳደር እሰራለሁ…”

ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር

ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ይህንን የተናገሩት ኢትዮ ቴሌኮም የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ላበረከቱት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ነሐሴ 4 ቀን 2ዐ11 ዓ/ም ተቋሙ ባዘጋጀው የእውቅና እና የምስጋና ማዕድ ምሽት ላይ ነው፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ የምስጋና ፕሮግራሙን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት  ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከግንቦት 2ዐ1ዐ ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮ ቴሌኮም የስራ አመራር ቦርድን በሰብሳቢነት በመምራት የስራ አቅጣጫና የተረጋጋ አመራር በመስጠት እና ማኔጅመንቱን በማገዝ እንዲሁም ኩባንያው ከተለያዩ ተቋማት ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረው ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት ማድረገቸውን ገልፀዋል፡፡

ወ/ት ፍሬሕይወት አክለውም ባጠናቀቅነው (በ2ዐ11) በጀት ዓመት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስራዎች ተቋማችን ለረጅም ዓመታት ውሳኔ ሳይሰጥባቸው ከቆዩ ውስብስብ ችግሮችና በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ከነበረበት ስጋት ተላቆ አበረታች የስራ ውጤት እንዲያስመዘግብ የክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የቅርብ ክትትል እና እገዛ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ገልፀዋል፡፡

ወ/ት ፍሬሕይወት አያይዘውም ለዜጎች በርካታ የስራ እድል ለመፍጠር እንዲሁም የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቋማት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው፣ ተባብረው፣ ተጋግዘው እና ተናበው መስራትን የሚጠይቅበት ወቅት ላይ በመሆናችን ኢትዮ ቴሌኮም ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከሚመሩት እና ከሌሎች ክልሎች ጋር በመተጋገዝ የሃገራችንን እድገት እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ባሳለፍነው በጀት ዓመት ከኩባንያው ጎን ለነበሩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እና  አጋሮች ላቅ ያለ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ለአዲሱ የኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝም የእንኳን ደህና መጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡

ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ከኢትዮ ቴሌኮም የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ማኔጅመንት እንዲሁም ከሰራተኛ ማህበሩ እና ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር በጋራና በቅርበት መስራት በመቻሉ ተቋሙ ከነበረበት ስጋት ለማውጣት የገበነውን ቃል ለማሳካት ችለናል በማለት ገልፀዋል፡፡ በማከልም ወደፊት ለሚመጣው የቴሌኮም የገበያ ውድድር ማኔጅመንቱ የሰራተኛ ማህበሩ እና ሰራተኞቹ ብሎም የተቋሙ መልካም የሆነ የስራ ባህል ብቁ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጉት ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ባለሁበት የተቋሙ አምባሳደር እንደሚሆኑ፤ የሚመሩት ክልልም ከተቋሙ ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ አክለውም በተቋሙ የተፈጠረውን በጋራ የመስራት መንፈስም ከአዲሱ የስራ አመራር ቦርድ ሰባሳቢ ጋር እንደሚቀጥል ያላቸውን መተማመን ገልፀዋል፡፡

አዲሱ የኢትዮ ቴሌኮም የስራ አመራር ቦርድ ሰባሳቢ ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝም በበኩላቸው መልካም ነገር እንደ ሀገርም የማስቀጠል አደራ ስላለብን  ተቋሙ የተሰሩትን መልካም ስራዎች እና የተፈጠረውን በጋራ የመስራት ስሜትና ከፍተኛ መነቃቃት ለማስቀጠል የተሰጠኝ አደራ እወጣለሁ ብለዋል፡፡ በእለቱም ከኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡

ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮ ቴሌኮም የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢነት ቆይታቸው በተቋሙ ለነበራቸው ላቅ ያለ አስተዋፅኦም የምስጋና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡