የኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ከሆኑት ክቡር ሰም ፋብሪዚ ጋር ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ውይይት አድርገዋል። ውይይቱም በኢትዮ ቴሌኮም እና በጣሊያን ኩባንያዎች መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር እና በማፋጠን የጋራ የዲጂታል ሽግግር ግቦችን እና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ልማትን ለማሳካት ያለመ ነው።
በተለይም የኩባንያችን “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ ከጣሊያን ተቋማት እና ኩባንያዎች ጋር ያለውን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ በውይይቱም ከአስኮት ኢነርጂ (Ascot Energy) ጋር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የተገመገሙ ሲሆን፣ በተለይም የኃይል አጠቃቀምን ውጤታማነት እና የአረንጓዴ መሠረተ ልማት እንቅስቃሴዎችን ማሳደግ የኩባንያችን ዘላቂ እና ቀልጣፋ የቴሌኮም ኦፕሬሽን ቁልፍ ምሰሶዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚያችን ከክቡር አምባሳደሩ ጋር በቴሌኮም መሠረተ ልማት ላይ የኃይል ጥንካሬን (Resilience)፣ የሥራ ቅልጥፍናን እና የአካባቢ ጥበቃን የሚያሻሽሉ የጋራ ተግባራትን አተገባበር ለማፋጠን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በተጨማሪም ከጣሊያን የልማት ፋይናንስ ተቋም (Cassa Depositi e Prestiti – CDP) ጋር ያለውን ትብብር የገመገሙ ሲሆን፣ ይህም ትላልቅ የዲጂታል መሠረተ ልማት እና ዘላቂ የኃይል ፕሮግራሞችን ጨምሮ ለዋና ዋና የ“ቀጣዩ አድማስ” ስትራቴጂያዊ ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው። ሁለቱም ወገኖች የኢትዮጵያን ሰፊ የዲጂታል ሽግግር አጀንዳ የሚደግፉ ሀብቶችን እና እውቀቶችን ለማሰባሰብ ከሌሎች የጣሊያን ኩባንያዎች እና የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በዚህም ወቅት ክቡር አምባሳደሩ ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ ያለውን የላቀ የለውጥ ሚና አድንቀው፣ በጣሊያን ኢንተርፕራይዞች እና በኢትዮ ቴሌኮም መካከል ጠንካራ አጋርነት እንዲኖር ጣሊያን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። በተለይም ፈጠራን፣ የመሠረተ ልማት ግንባታን እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ተደራሽነትን ለማፋጠን ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊ ስለመሆኑ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኩባንያችን የሀገራችንን ሁለገብ የዲጂታል ሽግግር እና ዘላቂ እድገት ፍላጎት የሚደግፉ ጠንካራ፣ አረንጓዴ እና ለመጻዒ ጊዜ ዝግጁ የሆኑ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ዓለም አቀፍ አጋርነቱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ ዋና ሥራ አስፈፃሚያችን ክቡር አምባሳደሩ በቴክኖሎጂ፣ በመሠረተ ልማት እና በስትራቴጂያዊ ፋይናንስ ረገድ የኢትዮ-ጣሊያን ትብብርን ለማሳደግ ላሳዩት ቀና ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም




