ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀምን መሰረት በማድረግ 47,098 የሚደርሱ ደንበኞች የሞባይል አገልግሎትን ከ3ጂ ወደ 4ጂ በነፃ አሳደገ፡፡ በተጨማሪም ለእነዚሁ ደንበኞች ለሶስት ተከታታይ ወራት በየወሩ 100 ሜጋ ባይት የኢንተርኔት አገልግሎት በነፃ አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ኢትዮ ቴሌኮም 98 ሺህ ለሚደርሱ የ3ጂ ሞባይል አገልግሎት ደንበኞቹ ከህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎታቸውን ወደ 4ጂ እንዲያድግ የሚያደርግ ሲሆን ይህንኑም ደንበኞች በአጭር የፅሁፍ መልዕክት አማካኝነት እንዲያወቁት ያደርጋል፡፡

የ4ጂ ሞባይል አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ ሲሆን ፤ የሞባይል አገልግሎታቸው ወደ 4ጂ እንዲያድግላቸው የተመረጡ ደንበኞች ከሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀማቸው በተጨማሪ የ4ጂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሞባይል ቀፎ ተጠቃሚ መሆናቸው እንደ ቅድመ ሁኔታ ተወስዷል፡፡

ደንበኞች በ4ጂ ሞባይል አገልግሎት ሲጠቀሙ ቀደም ሲል በ3ጂ ሞባይል አገልግሎት ሲጠቀሙበት ከነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት የተሻለ ፍጥነት ያገኛሉ፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ የ4ጂ አገልግሎት የድምፅ፣ የኢንተርኔት እንዲሁም አጭር የፅሁፍ መልዕክት አገልግሎቶች ታሪፍ ከ3ጂ ሞባይል አገልግሎት ታሪፍ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡