ኢትዮ ቴሌኮም በመላ ሃገሪቱ ያሉ የኩባንያው ቤተሰቦች የሚሳተፉበት “የአረንጓዴ አሻራ” የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ያስጀመረ ሲሆን በስድስት የኩባንያው ዞኖችና አስራ ሰባት ሪጅኖች የሚሳተፉበት መርሐ-ግብር ላይ አንድ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴው በይፋ ተጀምሯል፡፡

ዘንድሮ በተቋም ደረጃ ለሶስተኛ ጊዜ የሚከናወነው የክረምት ወራት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ከሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡

ኩባንያው ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመላ ሀገሪቱ በመትከልና ሀገሪቷ የያዘችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመደገፍ የበኩሉን የላቀ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ይህም ተቋሙ ለአካባቢ ጥበቃ ጉልህ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ቴክኖሎጂዎችን፣ ቫውቸር ካርዶችን እና ወረቀት አልባ አሰራሮችን ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር በአካባቢና ተፈጥሮ ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳረፍ ማህበራዊ ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ችግኞችን መትከል ብቻም ሳይሆን የተተከሉ ችግኞች አስፈላጊውን ሁሉ ጥበቃና እንክብካቤ በማረግግ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ማጽደቅ የቻለ ሲሆን ባከናወናቸው የችግኝ ተከላ ዘመቻዎችም ከ4,326 በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በማሳተፍ ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡

ተቋሙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ለችግኝ ተከላ መርሀግብሩ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ያለውን ቁርጠኝነትና ሀላፊነት በተግባር ያሳየ ሲሆን በቀጣይም የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ከማስፋፋት ባሻገር ለማህበረሰባችንና ለሀገራችን ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ማንኛውም ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

                     ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives