ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2011 እስከ ሰኔ 2012 ያለውን የኢትዮ ቴሌኮም የአንድ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ለህዝብ ይፋ ያደረገውን የሦስት ዓመት ስትራቴጂና የ2012 በጀት ዓመት እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ተቋሙን በደንበኞቹና በአጋሮቹ ዘንድ ተመራጭ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተያዙ ስትራቴጂያዊ ግቦችን ለማሳካት መጠነ ሰፊ የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን በዋናነትም የደንበኞች ተሞክሮን ማሻሻልና እርካታን ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ የኦፕሬሽን ልህቀት ማምጣት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ማሳደግ፣ የደንበኞችን አቅም ያገናዘበ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ፣ የሀብት አጠቃቀም ማሻሻልና የፋይናንስ አቅምን ማጎልበት፣ የገጽታ ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን፣ የተቋማችን ሠራተኛና አመራር ስትራቴጂን የመንደፍ፣ የማስፈጸምና የመፈጸም እንዲሁም ውሳኔ የመስጠት አቅምን ማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ኩባንያችን 47.7 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 105.1% በማሳካት የላቀ አፈጻጸም አስመዝግቧል፤ ይህ ውጤት ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ31.4% አድጓል፡፡ ይህን ከፍተኛ እና ከእቅድ በላይ የሆነ ገቢ ማግኘት የተቻለው የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያና የአገልግሎት ጥራትን ለመጨመር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን በመተግበር፣ የ4ጂ አገልግሎትን በመላው አዲስ አበባ እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የ4ጂ አድቫንስድን በተወሰኑ አካባቢዎች በመዘርጋት፣ የባለገመድ ብሮድባንድ አገልግሎት ላይ ሰፊ ማሻሻያዎችና እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ እንዲሁም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች በተጨማሪ ሌሎች እሴት የሚጨምሩ 16 አዳዲስ እና 25 ነባር የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች በማቅረብ ነው፡፡

የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 147.7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዱን 107% በማሳካት የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገበ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ50% እድገት አስመዝግቧል፡፡ በውጭ ምንዛሪ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የቴሌኮም ማጭበርበርን በተለያዩ ስልቶች በመከላከል እና የተቋም ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ቢዝነስ አጋሮቻችን ጋር ያለውን ግኑኝነት ለማሻሻልና ለማጠናከር ሰፊ ሥራዎች በመከናወናቸው ነው፡፡ ገበያው በሚጠይቀው መሠረት አዳዲስ አሰራሮችን መከተል፣የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምጽ ገቢ ድርሻ 49%፣ የዳታና ኢንተርኔት ገቢ ድርሻ 29%፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ገቢ ድርሻ 9%፣ እሴት ከሚጨምሩ አገልግሎቶች (VAS) 9.4% እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች የተገኘው ገቢ ድርሻ 3.6% ይይዛል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ዋና ዋና ክፍያዎች መካከል 11.3 ቢሊዮን ብር ታክስ እና 4 ቢሊዮን ብር ዲቪደንድ ለመንግስት የተከፈለ ሲሆን በቬንደር ፋይናንሲንግ ሞዳሊቲ ለተከናወኑ ፕሮጀክቶች ብድር 10.2 ቢሊዮን ብር ወይም 318.4 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የተፈጸመ ሲሆን እነዚህንና ሌሎች ክፍያዎችን ፈጽሞ ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት በጥሩ የጥሬ ገንዘብ መጠን (Cash Position) ተሸጋግሯል፡፡

በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የደንበኞቻችን ብዛት 46.2 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ሲነጻጸር የ5.8% እድገት አሳይቷል፡፡ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች 44.5 ሚሊዮን፣ የዳታzs እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ 23.8 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ (Fixed Broadband) ደንበኛ 212.2 ሺህ እንዲሁም መደበኛ ስልክ 980 ሺህ ደንበኞች ናቸው፡፡ በበጀት ዓመቱ በባለገመድ ብሮድባንድ አገልግሎት ላይ በተደረጉ የአገልግሎት ማሻሻያዎችና ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ ምክንያት የብሮድባንድ ደንበኞች ቁጥር በ135% ማሳደግ ተችሏል፡፡ በዚህም አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) 46.1% ደርሷል፡፡

ኩባንያችን 16,506 ቋሚ እና 19,959 የኮንትራት ሠራተኞች ያሉት ሲሆን የተቋሙን ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ የተለያዩ የሥልጠና ፕሮግራሞችን በመቅረጽ 10,665 ሠራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የሠራተኛውን ተነሳሽትና የባለቤትነት መንፈስ የሚያሳድጉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት ያህል ሠራተኞችን በተቋሙ ስትራቴጂ ዝግጅትና የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ግብዓት እንዲሰጡ የማድረግ፣ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎችን አቅርቦት ማሻሻል፣ የሥራ ከባቢን አመቺና ደህነንቱን የማረጋገጥ፣ የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመተግበር እንዲሁም በሁሉም የተቋሙ የሥራ ቦታዎች የሠራተኞች ቀን በማክበር የተሻለ የሥራ ከባቢን የሚፈጥሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮ ቴሌኮም ምርትና አገልግሎት ለደንበኞች የሚያደርሱ 249 ሺህ አጋሮች ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ ከቴሌኮም ጋር ተዛማጅ በሆኑ ሥራዎች ተሰማርተው የሥራና የገቢ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ቁጥር ከ287 ሺህ በላይ ደርሰዋል፡፡

ኩባንያችን ለደንበኞቹ ከሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ ለማህበረሰባችን ፋይዳ ባላቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በተቀናጀ መልኩ በሚገባ ተወጥቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ በአይነት፣ በአገልግሎትና በገንዘብ በድምሩ 1.15 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ በመላው ሃገሪቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ ላይ ተሳትፏል፡፡ ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ከ2.1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆችንና ተቋማትን እየተፈታተነ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የተለያዩ እርምጃዎች የወሰደ ሲሆን የቴሌኮም አገልግሎት ለድርጅቶች፣ ለመንግስትና ለማህበረሰቡ እንደዋነኛ የመገናኛና የሥራ ማስኬጃ አማራጭ በመሆኑ አብዛኛው ማህበረሰብ በቴሌኮም አገልግሎት ላይ በመመርኮዝ ከቤቱ ሆኖ ሥራውን ማከናወን፣ ማህበረሰባችን ማህበራዊ ርቀትን ጠብቆ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ማከናወን እንዲችል ለማገዝ ከፍተኛ ቅናሽ ያለው ፓኬጅ ለተጠቃሚዎች ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከፍተኛ ሀብት በመመደብና ትኩረት በመስጠት የጎላ ሚና የተጫወተ ሲሆን የአንድ መቶ ሚሊዮን ብር (100 ሚሊዮን ብር) የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ አንስቶ፣ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የስልክ ጥሪን የኮቪድ-19 መከላከል መልዕክቶች ለማስተላለፍ መጠቀም፣ ማህበረሰቡ ኮቪድን ለመከላከልና መረጃና አስፈላጊ እርዳታ ለማግኘት የሚችልባቸው አጫጭር ቁጥሮች ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት በነጻ የማቅረብ፣ የጤና ሚኒስቴርና የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወረረሽኙን አስመልክቶ በድረ ገጻቸው የሚስተላልፉትን መረጃ በነጻ ማድረስ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በኮቪድ ምክንያት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አካላት የሚሆን የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጮችን የማቅረብ፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካይነት በኮቪድ – 19 ላይ ለሚደረግ ምርምር የገንዘብ አስተዋጽኦ የማድረግ እንዲሁም ከወረርሽኙ ጋር በተገናኘ ትምህርት በመስተጓጎሉ ተማሪዎች የትምህርት መረጃዎችን በነጻ የሚያገኙበት ሁኔታ የማመቻቸትና የመሳሰሉ ተግባራት አከናውኗል፡፡

በበጀት ዓመቱ ኩባንያችን ከገጠሙት ተጋዳሮቶች መካከል፡ የኮቪድ- 19 በዓለም አቀፍና በሀገራችን መከሰት ኩባንያው አገልግሎቱን ለማሻሻል በሚያደርጋቸው የማስፋፊያ ሥራዎችና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንዲሁም አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት እንቅሰቃሴን ገድቧል፡፡ በሌላ በኩል የፋይበርና ኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆረጥ፣ የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የጸጥታ ችግሮችና የቴሌኮም ጣቢያዎች መትከያ ቦታ አቅርቦት መዘግየት በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የኩባንያችን የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም እጅግ የላቀና ለበለጠ ስኬት የሚነሳሳ ሲሆን በተለይም በአሁኑ ወቅት ዓለማችንና ሀገራችንን ከገጠመው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንጻር የቴሌኮም አገልግሎትን ለመስጠትና ለማስፋፋት ካለው ፈታኝ ሁኔታ አንጻር አፈጻጸሙን እጅግ አመርቂ ያደርገዋል፡፡ ይህን የላቀ ውጤት ኩባንያችን ሊያስመዘግብ የቻለው የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ኩባንያውን በደንበኞቹና በአጋሮቹ ተመራጭ ለማድረግ ያሳዩት ቁርጠኝነት እንዲሁም ላቀዷቸው ግቦች መሳካት ያደረጉት ርብርብ በመሆኑ እጅግ የላቀ ምስጋናና አክብሮት ይገባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ለተመዘገበው አመርቂ አፈጻጸም ለደንበኞቻችን፣ ለሥራ አጋሮቻችን እና ለባለድርሻ አካላት ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

 ሐምሌ 23 ቀን 2012

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives