የቴሌኮም አገልግሎት ሂሳብ አከፋፈል ዝርዝር መረጃ

1. በይሙሉ አገልግሎት

  • በአቅራቢያዎ በሚገኝ የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከል ወይም በመላ ሀገሪቱ ይሙሉ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አጋር የንግድ እና የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በአካል በመቅረብ ወርሃዊ የአገልግሎት ሂሳብዎን በቀላሉ መክፈል ይችላሉ፡፡
  • የይሙሉ አገልግሎትን በችርቻሮ ሱቆች፣ ሱፐርማርኬቶች፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ፎቶ ስቱዲዮዎች እና በሌሎች የንግድ እና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ያገኛሉ::
  •  ሂሳብዎን ለመክፈል ከእርስዎ የሚጠበቀው በማዕከላቱ ቀርበው ሂሳብ የሚከፍሉለትን የአገልግሎት ቁጥር ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡
  • ወርሃዊ የአገልግሎት ሂሳብዎን መክፈልዎን የሚገልፅ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ይደርስዎታል፡፡

2. በሞባይል ዋሌት

2.1 ለሲቢኢ (CBE-Birr) ብር አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች

ሀ) በቅድሚያ *847# ላይ በመደወል ወደ ሲቢኢ ብር አገልግሎት ይግቡ

ለ) 3 ቁጥርን በማስገባት “Buy Airtime” የሚለውን ይምረጡ

ሐ) የሲቢኢ ብር አገልግሎት ለሚጠቀሙበት የሞባይል ቁጥር ሂሳብ ለመክፈል 1 ቁጥርን በማስገባት “My phone” የሚለውን ይምረጡ ቀጥሎም የሚከፍሉትን የሂሳብ መጠን        በመጨረሻም የይለፍ ቃልዎን ያስገቡ፡፡

መ) የሚከፍሉት ሂሳብ የሌላን የአገልግሎት ቁጥር ከሆነ 2 ቁጥርን ይምረጡ በመቀጠልም የሚከፍሉለትን የአገልግሎት ቁጥር ያስገቡ (ለምሳሌ 0911xxxxxx) ቀጥሎ የሚከፍሉትን የገንዘብ መጠን በማስገባት ቀጣይ መመሪያውን ይከተሉ፡፡

ሠ) የሚከፍሉትን የብር መጠን እና የአገልግሎት ቁጥር በማረጋገጥ ሂሳብዎን መክፈል ይችላሉ፡፡

3. ከባንክ ሂሳብ ቀጥታ ተቀናሽ በማድረግ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኛ ከሆኑ ወርሃዊ የአገልግሎት ሂሳብዎን የቀጥታ የባንክ ማዘዣ በማቅረብ በሶስትዮሽ ውል መሠረት ከባንክ አካውንትዎ ተቀናሽ በማድረግ መክፈል ይችላሉ፡፡ የቴሌኮም አገልግሎት ክፍያ ከባንክ አካውንትዎ በቀጥታ እንዲቆረጥ ለማድረግ በቅድሚያ ውል በመፈረም ፈቃደኝነትዎን ማረጋገጥ ያለብዎ ሲሆን በየወሩ ከአካውንትዎ የአገልግሎት ሂሳብ ተቀናሽ ሲደረግ ደረሰኝ ይቆረጥልዎታል፡፡

ይህ የክፍያ አማራጭ በተለይ ለዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች የአገልግሎት ሂሳባቸውን በቀላሉ መክፈል የሚችሉበት አሰራር ሲሆን በዚህ የክፍያ አማራጭ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለጉ ፍላጎትዎን የሚገልጽ መልዕክት በኢሜይል አድራሻ:- BOcommunication@ethiotelecom.et ላይ ሲልኩልን ዝርዝር መረጃ የምንሰጥዎ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

4. በቅድመ-ክፍያ የሞባይል ካርድ

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጨማሪ የአገልግሎት ሂሳብ ክፍያውን በሞባይል ዋሌት አማካኝነት በሌሎች ባንኮች እስክንጀምር የቅድመ ክፍያ ሞባይል ካርድን በመጠቀም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በአይ ቪ አር/IVR ወይም በዩ ኤስ ኤስ ዲ/USSD (አጭር ኮድ) አማካኝነት ወርሃዊ የአገልግሎት ሂሳብዎን መክፈል የሚችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

4.1 በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አማካኝነት:-

ሀ. እርስዎ የሚጠቀሙበትን የሞባይል አገልግሎት ሂሳብ ለመክፈል: *በካርዱ ላይ ያለውን ስውር ቁጥር# በመጻፍ ወደ 805 ይላኩ

ለ. የሌላ ቴሌኮም የአገልግሎት/ደንበኛን ሂሳብ ለመክፈል፡ *በካርዱ ላይ ያለውን ስውር ቁጥር*የአገልግሎት ቁጥር# በመጻፍ ወደ 805 ይላኩ

ለምሳሌ:- *በካርዱ ላይ ያለውን ስውር ቁጥር*09xxxxxx# በመጻፍ ወደ 805 ይላኩ

4.2 በአጭር ኮድ (USSD) አማካኝነት:-

ሀ. እርስዎ የሚጠቀሙበትን የሞባይል አገልግሎት ሂሳብ ለመክፈል :- *805*በካርዱ ላይ ያለውን ስውር ቁጥር# በመፃፍ ይደውሉ

ለ. የሌላ ስልክ ቁጥር ወርኃዊ አገልግሎት ሂሳብ ለመክፈል:- *805*በካርዱ ላይ ያለውን ስውር ቁጥር*የሚከፍሉለትን የአገልግሎት ቁጥር# በማስገባት ይደውሉ ወይም *805# ላይ በመደወል ይደውሉ፡፡

ለምሳሌ፡- *805*በካርዱ ላይ ያለውን ስውር ቁጥር*09xxxxxx#በማስገባት ይደውሉ::

4.3. በራስ-አገዝ አገልግሎት (IVR) አማካኝነት:-

ሀ. በመጀመሪያ ክፍያ የሚፈፅሙበትን የቅድመ ክፍያ ሞባይል ካርድ ያዘጋጁ

ለ. በመቀጠል ወደ 903 ደውለው 1 ቁጥርን በመጫን “ሂሳብዎን ለመሙላት” የሚለውን አማራጭ ይምረጡ

ሐ. ለሚደውሉበት የስልክ ቁጥር የአገልግሎት ሂሳብ ለመክፈል 1 ቁጥርን እንዲሁም ለሌላ የስልክ ቁጥር አገልግሎት ሂሳብ ለመክፈል 2 ቁጥርን በመጫን በመመሪያው መሠረት በካርዱ ላይ ያለውን የሚስጥር ቁጥር በማስገባት የአገልግሎት ሂሳብዎን መክፈል ይችላሉ፡፡

ማስታወሻ:-

• በቅድመ-ክፍያ የሞባይል ካርድ ሂሳብ ለመክፈል እንደሚከፍሉት ወርሃዊ የአገልግሎት ሂሳብ መጠን የባለ 1000 ብር፣ 500 ብር፣ 250 ብር፣ 100 ብር፣ 50 ብር እና ሌሎች የቅድመ-ክፍያ ሞባይል ካርዶችን መጠቀም የሚችሉ ሲሆን ከሚከፍሉት የአገልግሎት ሂሳብ መጠን የሚበልጥ ዋጋ ያለው ካርድ በሚሞሉበት ጊዜ ቀሪው ሂሳብ ለቀጣይ ክፍያዎ ተቀማጭ ይደረግልዎታል፡፡

ለምሳሌ ፡ 557 ብር የአገልግሎት ሂሳብ ለመክፈል ባለ 500 ፣ ባለ 50 እና ባለ 10 ብር ካርድ በድምር የ 560 ብር ካርድ ቢሞሉ በእላፊነት የሚከፍሉት 3 ብር ወደ ሚቀጥለው ወር ይተላለፍልዎታል፡፡

• ለእርስዎም ሆነ ለሌላ ደንበኛ የአገልግሎት ሂሳብ ሲከፍሉ ወዲያውኑ የማረጋገጫ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ይደርስዎታል፡፡