ኢትዮ ቴሌኮም በኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር መስመር አጠቃቀም ዙሪያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ህዳር 17 ቀን 2ዐ11 ዓ.ም የማዕቀፍ ስምምነት በዋናው መ/ቤት ተፈራረመ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃይል ለማስተላለፍ የዘረጋውን የኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር /Optical Ground Wire/ ለቴሌኮም አገልግሎቶች እንደ ተጨማሪ አማራጭ የማስተላለፊያ መስመር በመጠቀም አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ እንዲሁም የአገልግሎት መቆራረጥን ለማስቀረት እየሰራ ይገኛል፡፡
OPGW ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ኃይል ተሸካሚ እና ከመሬት በከፍታ የተዘረጋ በመሆኑ መስመሩ ላይ ሰው
ሰራሽ አደጋዎች የማጋጠም ዕድሉ አነስተኛ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በመሬት ውስጥ በዘረጋው የፋይበር መስመር ላይ
በሚደርሱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ የመቆራረጥና የጥራት
መጓደል ችግሮችን ለመፍታት ይህን የኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር መስመር መጠቀም እንደአማራጭ ወስዷል፡፡ በዚህም
በቴሌኮም መስመሮች ላይ ብልሽቶች ወይም የመቆረጥ አደጋዎች ሲያጋጥሙ በዋና ዋና መስመሮች ላይ
የአገልግሎቶች መቆራረጥ ሳያጋጥም ብልሽቶቹ የሚጠገኑበት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም እየተጠቀመበት ያለው የOPGW መስመር ርዝመቱ 3283 ኪሎ ሜትር ሲሆን ዋና
መስመሮችም አዲስ አበባ — ባህርዳር — መተማ፣ አዲስ አበባ — ጅማ፣ አዲስ አበባ — ጋላፊ፣ አዲስ አበባ —
ደሴ — መቀሌ፣ አዲስ አበባ — አምቦ — ጌዶ፣ መቱ — ጋምቤላ፣ አዋሽ — ደወሌን ያጠቃልላሉ፡፡

ይህ የአገልግሎት ስምምነት ከመፈረሙ አስቀድሞ ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ከ2002 ዓ .ም
ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን በወቅቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል በአገልግሎት ክፍያ፣ አገልግሎቱን ከማስፋት አኳያና
በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልውውጦች ሲደረግ የቆየ ቢሆንም አሳሪ የውል ስምምነት አልተፈጸመም ነበር፡፡
በዛሬው ዕለት የሁለቱ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እና የሚመለከታቸው የተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት
OPGW መስመር አጠቃቀም ላይ የረዥም ጊዜ የማዕቀፍ ውል ስምምነት ተፈርሟል፡፡