ኢትዮ ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመጣመር ያዘጋጀውን የቴሌኮም ኢንጅነሪንግ የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራም ሲከታተሉ የነበሩ 37 ሠራተኞቹን ለመጀመሪያ ገዜ አስመረቀ

ኢትዮ ቴሌኮም የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት እንዲያስችለው የተለያዩ ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ ለሰው ኃይል አቅም ግንባታ የተለየ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ፕሮግራሞችን እየተገበረ ሲሆን ከአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር መጋቢት 2009 ዓ/ም የጀመረው የቴሌኮም ኢንጅነሪንግ የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራም አንዱ ነው ፡፡ ይህ የትምህርት ፕሮግራም የኢንዱስትሪውን በፈጣን ሁኔታ ማደግና ተለዋዋጭነትን በሚገባ በመገንዘብ ከእድገቱ የሚገኙ ትሩፋቶችንና መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም ተያይዘው የሚከሰቱ ፈታኝ ሁኔታዎችን በበቂ ዝግጅት መ ምራት የሚችል የሰው ኃይል ለ ማፍራት የታቀደ ነ ው፡፡ በዚህ ፕሮግራም የሚሰጠውን የንድፈ ሃሳብና የተግባር ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ 37 የተቋሙ ሠራተኞች በዛሬው ዕለት (ህዳር 22 ቀን 2ዐ11 ዓ/ም) ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቀዋል፡፡ ከተመራቂዎቹ ውስጥ አስራ ስድስቱ በቴሌኮም ኔትዎርክ ኢንጅነሪንግ እንዲሁም ሃያ አንዱ ደግሞ በቴሌኮም ኢንፎርሜሽን ሲስተም የትምህርት ዘርፍ ሲሆን ከነዚህም መካከል አምስቱ ሴቶች ናቸው ፡፡

ተመራቂ ተማሪዎቹ ከኢንዱስትሪው ጋር ያላቸውን ቁርኝት መጠበቅ እንዲያስችላቸው በሳምንት አንድ ቀን በስራ ገበታቸው ላይ በመገኘት ለተቋሙ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ከመሆኑም በተጨማሪ የመመረቂያ ጥናታቸውም የደንበኛ እርካታን በሚያሻሽሉ እና ሌሎች በተቋሙ በሚታዩ ቁልፍ ችግሮች ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ ተደርጓል ፡፡ በዛሬው ዕለት የተመረቁትን ሳይጨምር በአሁኑ ወቅት 126 የኩባንያው ሠራተኞች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በቀጣይም የፕሮግራሙን ውጤታማነት በመገምገም ተጨማሪ የኩባንያው ሠራተኞችን ለማስተማር እቅድ ተይዟል፡፡