“አካፍሎ የጎደለበት ሰጥቶ የከሰረ የለም” ስለዚህ “ስንሰጥ በደስታ እና በልግስና እንስጥ” ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ

የኢትዮ ቴሌኮም የማኔጅመንት አባላት እሁድ ህዳር 23 ቀን 2011 ዓ/ም የመቄዶንያ አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ጎበኙ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት በማዕከሉ ከሚገኙ አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን ጋር በተደረገው የምሳ ግብዣ ፕሮግራም ላይ ከማዕከሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እስከአሁን ኩባንያው ለማዕከሉ ባደረጋቸው ድጋፎች ዙሪያ ውይይት ያደረገ ሲሆን በእለቱም ለማዕከሉ ህንፃ ግንባታ የሚውል የ10,000,000 ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ከተጠቀሰው የብር ድጋፍ በተጨማሪ በማዕከሉ ድጋፍ የሚደረግላቸው ወገኖች ለኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ በዕለቱ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለማዕከሉ አገልግሎት የዋሉ የአጭር መልዕክት ቁጥሮች ማለትም 8151፣ የድምፅ አገልግሎት ቁጥር 8131 እና 8050 ቋሚ እንዲሆኑ እና የሚሰጡት አገልግሎትም ከወርሃዊ ክፍያ ነፃ እንዲሆን ተወሰኗል፡፡ በተጨማሪም ለማዕከሉ የስራ አገልግሎት የሚውሉ የስልክ ቁጥሮች ወጪም በኢትዮ ቴሌኮም እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡

ለዚሁ ማዕከል በተደረገው የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም ባዘጋጃቸው አጭር የጽሁፍ መልዕክት ቁጥሮች አማካኝነት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከህብረተሰቡ የተሰበሰበውን 57,774,571 ብር ቀደም ሲል ለማዕከሉ ገቢ ማድረጉ የተገለፀ ሲሆን፤ ኢትዮ ቴሌኮም በጉብኝቱ ወቅትም ላለፉት 12 ወራት ከህብረተሰቡ የተሰበሰበ 16,943,594 ብር በተመሳሳይ ሁኔታ ገቢ አድርጓል፡፡ በድምሩ እ.ኤ.አ. ከጥር 2015 ጀምሮ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካኝነት የተሰበሰበ 74,718,165.00 ብር ለማዕከሉ ገቢ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ ይህንን ድጋፍ ለማሰባሰብ ኢትዮ ቴሌኮም 11 ቢሊየን የሚጠጋ አጭር የፅሁፍ መልዕክት አገልግሎት በነፃ ያሰራጨ ሲሆን ይህም በገንዘብ ሲተመን 125,000,000 ብር ነው፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር “አካፍሎ የጎደለበት ሰጥቶ የከሰረ የለም” በማለት በመተጋገዝ እና በመረዳዳት ባህል ውስጥ እጅግ ፈታኝ እና ተራራ የሚመስሉ ችግሮችን ስንተባበር እና ስንተጋገዝ ብሎም ስንደመር በቀላሉ መወጣት እንደሚቻል የመቄዶንያ የአረጋውያን እና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ስራ አስፈፃሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም ላለፉት ሦስት አመታት ለዚሁ ዓላማ ከሕብረተሰቡው የሰበሰበውን ጠቅላላ ገንዘብ ከእያንዳንዱ ኪስ የተዋጣው የአንድ ብር ድምር ሲሆን፤ ይኸውም ገንዘብ ሁለት ሺህ ወገኖችን ከጎዳና አንስቶ መንከባከብ ማስቻሉ መደመር ውስጥ ያለውን ታላቅ ኃይል ያሳያል በማለት ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም ኢትዮ ቴሌኮም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዘርፈ ብዙ የድጋፍ ሥራዎችን በመላው የሃገሪቱ ክፍሎች ለመከወን ዕቅድ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን ለመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ያደረገው ድጋፍም የዚሁ ዕቅድ አካል ከመሆኑም ባሻገር ማዕከሉ የሚያደርገው ታላቅ የሰብዓዊ ሥራ ከኩባንያው እሴቶች ጋር የተሳሰረ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ኢትዮ ቴሌኮም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት አማካኝነት ሕብረተሰቡ ለማዕከሉ በሦስት አመት ጊዜ ውስጥ ያደረገውን ድጋፍ እንዲያውቅ በማድረግ በማዕከሉ ስም ምስጋናውን አስተላልፏል፡፡ ከዚህም ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መረዳት የሚቻለው ዜጎች ሲተባበሩ፣ ሲተጋገዙ፣ ያላቸውን ሲደምሩ እና ሲደመሩ ከባድ የሚመስሉ
ሁኔታዎች ማለፍ እንደሚቻል በጉብኝቱ ወቅት ጠቅሰዋል፡፡ በመጨረሻም ስራ አስፈፃሚዋ “አካፍሎ የጎደለበት ሰጥቶ የከሰረ የለም” ስለዚህ “ስንሰጥ በደስታ እና በልግስና እንስጥ” በሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡