ለወገን ደራሽ ወገን ነው

ኢትዮ ቴሌኮም ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ድጋፍ ማሰባሰቢያ የሚውል አጭር ቁጥር እና

40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

   

6020 ላይ A ብለን በመላክ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን እንርዳ!

ኩባንያችን ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም በህዝብና በመንግስት እየተደረገ ያለውን አገር አቀፍ ጥረት ለማገዝ እንዲያስችል የድጋፍ ማሰባሰቢያ አጭር ቁጥር 6020ን ያዘጋጀ ሲሆን ከዚሁ በተጨማሪ 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

6020 የተዘጋጀው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት መላው ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር እያደረጉ ያለውን የድጋፍ እንቅስቃሴ በተቀናጀ መልክ ለማካሄድ እንደሚረዳ በማሰብ ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያዩ አካላትም አጭር የድጋፍ ቁጥር እንዲዘጋጅ ጥያቄ በማቅረባቸውም ጭምር ነው ፡፡

በመሆኑም መላው ህብረተሰባችን የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመርዳት 6020 ላይ A ብለው በመላክ በአንድ መልእከት የ2 ብር ድጋፍ ማድረግ የሚችል ሲሆን ኩባንያችንም በዚህ መልክ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለፌደራል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚያስረክብ ከመሆኑም በተጨማሪ በአጭር ቁጥሩ አማካኝነት የሚሰበሰበውን ገንዘብ አስመልክቶ ለህብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ይሰጣል ፡፡

በተጨማሪም ከላይ በተገለፀው መሰረት ኩባንያችን ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የለገሰውን የ40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለፌደራል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስረክቧል፡፡ በሌላ በኩል ኩባንያው ከሚያደርገው አስተዋጽዖ በተጨማሪ የተቋሙ ሠራተኞች በሚሠሩባቸው አካባቢዎች ያሉ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍና ማኅበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት በራስ ተነሳሽነት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የገንዘብ መዋጮ እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን ለዚህም ኩባንያው ላቅ ያለ ምስጋናውን በዚህ አጋጣሚ ያቀርባል፡፡

በመሆኑም እርስዎም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም 6020 ላይ A ብለው በመላክ (በአንድ መልዕክት 2 ብር) የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በመርዳት እና ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው በመመለስ ሂደት ላይ በመሳተፍ የበኩልዎን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪያችን እናቀርባለን ፡፡

 

መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም