የሞባይል ካርድ ችርቻሮ ንግድ ላይ ለተሰማራችሁ ባለሱቆች በሙሉ

ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ካርዶችን በችርቻሮ ንግድ ላይ በተሰማሩ አጋር ሱቆች አማካኝነት ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ኩባንያችን አሠራሩን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ በማድረግ አጋር ድርጅቶች የሞባይል ካርዶችን መግዛት፣ ማጓጓዝ እና ማከማቸት ሳያስፈልጋቸው ይሙሉ በተሰኘ ኤሌክትሮኒክ አየር ሰዓት መሙያ ዘዴ አማካኝነት በሞባይል ስልካቸው በቀላሉ መሸጥ የሚያስችላቸውን አገልግሎት በቅርቡ ተግባራዊ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በርካታ አጋር ሱቆችም የይሙሉ አገልግሎትን በመጠቀም የአየር ሰዓት በመሸጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

አሁን ደግሞ ኩባንያችን በይሙሉ አገልግሎት የአየር ሰዓት ለሚሸጡ ባለሱቆች ቀደም ሲል ሲሰጥ ከነበረው የ5 በመቶ መደበኛ ኮሚሽን በተጨማሪ እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ 5 በመቶ ተጨማሪ የማበረታቻ ክፍያ ወይም ቦነስ ማቅረቡን ሲገልፅ በደስታ ነው፡፡
ከዚሁ በተጨማሪ ይሙሉ አገልግሎት ለድህረ ክፍያ ሞባይል ፣መደበኛ ስልክ እንዲሁም የብሮድባንድ አገልግሎት ወርሃዊ ሂሳብ ወይም ቢል መክፈል የሚያስችል በመሆኑ አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች በመስጠት በተመሳሳይ ሁኔታ የኮሚሽን እና የማበረታች ክፍያውን ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
በመሆኑም በይሙሉ አገልግሎት የችርቻሮ ሽያጭ ላይ መሠማራት የምትፈልጉ ድርጅቶች በአቅራቢያችሁ በሚገኙ ወኪል የጅምላ አከፋፋዮች ጋር በመቅረብ እንድትመዘገቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በይሙሉ አገልግሎት የአየር ሰዓት ሲሸጡ የሚያገኟቸው ጥቅሞች

  • ከመደበኛው 5% ኮሚሽን በተጨማሪ እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በይሙሉ አገልግሎት የሞባይል አየር ሰዓት ሲሸጡ 5% ማበረታቻ ክፍያ (Bonus) ያገኛሉ ፡፡
  • የሞባይል ካርዶችን መግዛት፣ ማጓጓዝ እና ማከማቸት ሳይጠበቅብዎ ከወኪል አከፋፋዮቻችን በሚፈልጉት የብር መጠን በሞባይል ስልክዎ አማካኝነት የአየር ሰዓት መግዛት ያስችልዎታል፡፡
  •  ከ5 ብር ጀምሮ (የ5 ብር፣ የ6 ብር፣ የ7 ብር…) በፈለጉት የብር መጠን የአየር ሰዓት መሸጥ ስለሚያስችልዎ ለደንበኞችዎ ሰፊ አማራጭ ማቅረብ ያስችልዎታል፡፡
  • በይለፍ ቃል መዝጋት ስለሚያስችልዎ የሞባይል ስልክዎ ቢጠፋ እንኳ የገዙት የአየር ሰዓት በሌላ አካል ጥቅም ላይ የመዋል ስጋት አይኖርብዎትም፡፡
  •  በይሙሉ አገልግሎት ሽያጭ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች በተጨማሪ ለተጠቃሚ ደንበኞች የ5% ነፃ የአየር ሰዓት ያቀረብን በመሆኑ ከሞባይል ካርድ ይልቅ የይሙሉ አገልግሎት በተጠቃሚዎች ዘንድ ተመራጭ ነው፡፡

ይሙሉ አገልግሎትን ተጠቅመው ለደንበኞች እንዴት የአየር ሰዓት መሸጥ ይችላሉ ?

  • በቅድሚያ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ ወኪል አከፋፋይ በአካል በመቅረብ እና ስልክዎን በማስመዝገብ በሚፈልጉት የብር መጠን የአየር ሰዓት ግዢ ይፈፅሙ፡፡ 
  • በመቀጠል የአየር ሰዓት ለመግዛት የሚፈልግ ደንበኛ ወደ እርሰዎ ሲመጣ አገልግሎቱን ለመስጠት ባስመዘገቡት ስልክ ቁጥር አማካኝነት *922# ይደውሉ ፣ ቀጥሎም የደንበኛውን የስልክ ቁጥር እና የሚሞላውን የብር መጠን በመጠየቅ በቀላሉ ሽያጩን ማከናወን ይችላሉ፡፡
  • ያጩን እንዳከናወኑ የአየር ሰዓቱ በተሳካ ሁኔታ መሞላቱን የሚገልጽ የማረጋገጫ አጭር የጽሑፍ መልእክት ለእርስዎ እና ለደንበኛዎ ይደርሳል፡፡ በአቅራቢያዎ የሚገኙ የይሙሉ አገልግሎት ወኪል አከፋፋዮችን አድራሻ ለማወቅ ድረ-ገጻችንን www.ethiotelecom.et ይጎብኙ፡፡