Enabling all Payment Platforms for Fuel Payment!
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም የሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓትን (Cross-Country Public Transport Service System) የተቀናጀ ነዳጅ አቅርቦት ስርዓት ሶሉሽንን (ENABLING ALL PAYMENT PLATFORMS FOR FUEL PAYMENT) እንዲሁም ሀገር አቀፍ የትራፊክ ቅጣት ማዕከላዊ አስተዳደር ስርዓትን (National Traffic Point Based Penalty Management System) ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
እነዚህም በሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርትና በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ዘልማዳዊ የአሰራር ሂደቶችን ለማዘመንና በነዳጅ አቅርቦትና ግብይት ረገድ ትክክለኛ ዳታ በወቅቱ ለማግኘት፣ ደንበኞች በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አማራጮች መጠቀም እንዲችሉ፣በትራፊክ ቅጣት አስተዳደር ግልጽነት ያለው አሰራርን ለማስፈንና የተገልጋዮችን እንግልት ለማስቀረት የላቀ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረጉት የዲጂታል ሶሉሽኖች፡-
1. የሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓት (Cross-Country Public Transport Service System)
ይህ የዲጂታል ሶሉሽን አገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለማግኘት ያሉ የሥራ ሂደቶች በቀላሉ ለማስተዳደር እና ለማቀላጠፍ የተዘጋጀ ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ሶሉሽን ሲሆን፣ ይህም ለትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ለአገር አቀፍ ትግበራ ከፈቃድ አሰጣጥ እና የህግ ተገዥነት (regulatory compliance) ጀምሮ እስከ ትኬት መቁረጥ እና ዲጂታል ክፍያ ድረስ ወጥ የሆነ ሶሉሽን ለማቅረብ የሚያስችል ነው።
ይህም በማኑዋል የሚፈጸም የትኬት ግዢ ለተጓዦች መዘግየትንና አገልግሎት ለማግኘት የሚባክን ጊዜን ለመቅረፍ፣ የፈቃድ አሰጣጥ ሂደትን ለማሳጠር እንዲሁም ባልተሟሉ ወይም ትክክል ባልሆኑ ሰነዶች ምክንያት የሚባክን ጌዜን ለመቆጠብ፣ የሽያጭ እና የገቢ ሁኔታ ግልጽነትን ለማስፈን፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም ሆነ በተጓዦች ላይ ሊከሰት የሚችል ስርቆትንና ማጭበርበርን ለመከላከል፣የመረጃ አያያዝን ለማዘመንና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እንዲሁም ስለ አውቶቡስ እንቅስቃሴ፣ የትኬት ሽያጭ፣ የተሳፋሪ ብዛት እና የአገልግሎት ሽፋንን አስመልክቶ አስተማማኝ እና ቅጽበታዊ መረጃ ለማግኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
ዲጂታል ሶሉሽኑ በተለይም ነባሩን ማኑዋል/ወረቀት ተኮር የትራንስፖርት ስምሪት አሰራር የፍቃድና የምዝገባ ስርዓት፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ምዝገባና ስምሪትን እንዲሁም የማኑዋል ቲኬት ሕትመትና ክፍያዎችን ዲጂታል በማድረግ የአስተዳደር ወጪን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን፣ ለባለድርሻ አካላት ቅጽበታዊ ክትትል፣ የአሠራር ቁጥጥር እና ሪፖርት ለማድረግ፣ የጉዞ መስመር ዝርጋታና የጊዜ ሰሌዳ ዝግጅትን፣ የመናኸሪያ (የአውቶቡስ ጣቢያ) አስተዳደርን ለማዘመን የሚያስችል ይሆናል፡፡
በተጨማሪም መንገደኞች/ተጓዦች የሞባይል ስልኮቻቸውን በመጠቀም እንግሊዝኛን ጨምሮ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የሀገር አቋራጭ የአውቶቡስ ትኬቶችን በማንኛውም ጊዜና ቦታ ቴሌብርን ጨምሮ በተለያዩ የክፍያ አማራጮች በመቁረጥ/በመግዛትና በቀላሉ ቦታ ለመያዝ እና ለማረጋገጥ ያስችላቸዋል።
2. የተቀናጀ የነዳጅ ክፍያ ስርዓት ሶሉሽን (ENABLING ALL PAYMENT PLATFORMS FOR FUEL PAYMENT)
ይህ የነዳጅ አቅርቦት ስርዓት ሶሉሽን ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት (ሁሉንም ባንኮች፣ ዋሌቶች፣ እና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን) ከማዕከላዊ የነዳጅ አስተዳደር ሥርዓት ጋር የሚያገናኝ አገር አቀፍ የተቀናጀ ነዳጅ አቅርቦት ስርዓት ሶሉሽን ሲሆን፣ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የነዳጅ ማደያዎች በቅንጅት እንዲሰሩና የነዳጅ ግብይቶችን አንድ ወጥ በሆነ አሰራር በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስችል ሶሉሽን ነው፡፡
ይህም ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ለነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ቅጽበታዊ ሪፖርቶችን ለማግኘት፣ የተሻለ የገበያ ቁጥጥር ለማስፈን፣ የአገር አቀፍ የነዳጅ ክምችትን፣ ሥርጭትን እና ሽያጭን በቅርበት በመከታተል ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን በመቅረፍ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠት ጠቀሜታው የላቀ ሲሆን፣ ለነዳጅ ማደያዎች ደግሞ ቴሌብርን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች እና ዋሌቶች የነዳጅ ክፍያዎችን ለማስተናገድ፣ የተሻሻለ እና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሠጣጥን ለማስፈን የሚያስችል ይሆናል፡፡
በተጨማሪም ለአሽከርካሪዎች በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ በማንኛውም የነዳጅ ማደያዎች ቴሌብርን ጨምሮ በተለያዩ የክፍያ አማራጮች ነዳጅ ለመቅዳት የሚያስችል ሲሆን፣ ለፋይናንስ ተቋማት ደግሞ ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢነትን እውን በማድረግ ፈጣን የነዳጅ ገበያ ተደራሽነት በማስፈን እና የአገልግሎት አሰጣጥ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡
3. ሀገር አቀፍ የትራፊክ ቅጣት ማዕከላዊ አስተዳደር ስርዓት (National Traffic Point – Based Penalty Management System)
ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ ሕጎች በተገቢው መንገድ እንዲተገበሩ የሚረዳ ሲሆን፣ በዲጂታል የታገዘ የትራፊክ ቅጣት አስተዳደርን በማስፈን፣ በማዕከል ደረጃ ዳታ የሚመዘገብበትና በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የሆነ የትራፊክ አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችል አሰራር ነው።
በተለይም በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለውን ማኑዋል የትራፊክ ቅጣት አሰራርን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል ለመቀየር እንዲሁም የዲጂታል መዝገብ፣ የተማከለ የትራፊክ ቅጣት ስርዓት፣ የትራፊክ የቅጣት ነጥብ አያያዝ፣ ቅጣቱን ለመፈጸም ያለው ምቹነት፣ ዳታን በመተንተን የመረጃ ውስንነትን እና ውጤታማ ያልሆነ የሀብት አጠቃቀምን ለመቅረፍና ፖሊሲዎችን ለማውጣት የመረጃ እጥረት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
በተጨማሪም በሀገሪቱ የሚገኙ የአሽከርካሪዎችን ሙሉ መረጃዎችን በመመዝገብ፣ የትራፊክ ህግ ጥሰቶችን ለመቆጣጠር እንዲሁም ጤናማ የትራፊክ ፍሰትን እውን ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን፣ ሶሉሽኑ የትራፊክ ቅጣት አስተዳደርና ተፈጻሚነትን ከማሳደግ ባለፈ የክልል ትራንስፖርት ቢሮዎች ተጨማሪ ኢንቨስትመንትና ወጪ ሳያስፈልጋቸው በቴሌክላውድ ታግዘው አሰራራቸውን በማዘመን ለትራንስፖርትና ትራፊክ ዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
የዲጂታል ሶሎሽኑ ተግባራዊ መሆን ለትራፊክ/ትራንስፖርት ቢሮዎች የአሰራር ብቃትንና ግልጽነትን ለመጨመር፣ በመረጃ ላይ ተመስርቶ የትራፊክ ህጎችን ለማሻሻል እና ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲሁም የኦፕሬሽን ወጪዎችን ለመቆጠብ የሚያስችል ሲሆን፣ ለአሽከርካሪዎችም የቅጣት ክፍያዎችን በቀላሉ በመከፈል አገልግሎቱን ለማግኘት የሚያባክኑትን ጊዜ ለመቆጠብ፣ አላስፈላጊ ወከባዎችን ለማስቀረት እና ለትራፊክ አደጋ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
በተጨማሪም ለፌደራል እና ለክልል መንግስታት የትራፊክ ህግ ማስከበር ሂደትን ውጤታማ ለማድረግ፣ አዲስ ሲስተም ለማበልጸግ ተጨማሪ ወጪ ሳያስፈልጋቸው ሶሉሽኑን ለመጠቀም፣ ወጥነት ያለው እና ስታንዳርዱን የጠበቀ የትራፊክ ፖሊሲን ለመተግበር፣ ሪፖርቶችን በቅጽበት ለማግኘት እና ውሳኔ ለመስጠት፣ የላቀ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ አገልግሎቱን በድረ-ገጽ፣ በሞባይል መተግበሪያና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካኝነት ማግኘት ይቻላል፡፡
ኩባንያችን የዲጂታል ፈጠራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል። በመሆኑም ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የቀረቡት ሶሉሽኖች ኢትዮ ቴሌኮም በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ዲጂታል መፍትሄዎች የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ገጽታ ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
ተግባራዊ የተደረጉት ሶሉሽኖች በግል ሶፍትዌር አልሚ ተቋማት የለማ መሆኑ፣ እንዲሁም የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አማራጮች ከኩባንያችን ሥርዓቶችና ከቴሌብር ጋር በኤፒአይ (API) በቀላሉ እንዲዋሀዱ በማድረግ፣ የጋራ የመሥራት አቅምን (interoperability) በማሳደግ የሥራ ፈጠራንና አካታች የዲጂታል ሥነ-ምህዳርን ማጠናከር የቻለ ነው።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም
ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም