የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዘርፍ አመሠራረት በኢትዮጵያ አጭር ታሪካዊ ዳራ

የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዘርፍ አመሠራረት በኢትዮጵያ አጭር ታሪካዊ ዳራ

የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኢትዮጵያ የተጀመረው በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት በ1886 ዓ.ም. ከሐረር ከተማ ወደ ሐገሪቷ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ 477 ኪሎ ሜትር የቴሌፎንና ቴሌግራፍ መስመር በተዘረጋበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫዎች የመገናኛ መስመሮች እየተስፋፉ በመሄዳቸው በርካታ የአገሪቷ ዋና ዋና ከተሞች በኦፕሬተሮች አማካይነት የቴሌኮሙኒኬሽን መገናኛ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ አገልግሎቱም በየከተሞቹ  በተቋቋሙ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች አማካኝነት በሩቅ ቦታ የሚኖሩ ፈላጊንና ተፈላጊን በስልክ በማገናኘት ይሰጥ ነበር፡፡

1886-1934

የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተቋም ስያሜዎች

ከ1886-1934 ዓ.ም. ድረስ በነበረው ወቅት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን በተለያዩ ስያሜዎችና መዋቅሮች ሲጠራና ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሠረት፡-

  • በመጀመሪያ የአገልግሎቱ አስተዳደር በዳግማዊ ምኒሊክ ቤተ-መንግስት አስተዳደር ሥር ሆኖ የኢትዮጵያ የቴሌፎንና የቴሌግራፍ ማዕከላዊ አስተዳደር በሚል መጠሪያ ከ1886 እስከ 1900 ዓ.ም. ድረስ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በወቅቱም ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የፈረንሳዩ ዜጋ ሚስተር ስቴቬኒን የተባሉ ነበሩ፡፡
  • አገልግሎቱ የኢትዮጵያ የፖስታ፣ ቴሌግራፍ እና ቴሌፎን ማዕከላዊ ቢሮ የሚል የስያሜ ለውጥ ተደርጎለት ከ1900 – 1903 ዓ.ም. ድረስ በዚሁ ሲጠራ ቆይቷል፡፡ በዚህ ወቅት ሲተዳደር የነበረው የዳግማዊ ምኒሊክ አማካሪ በነበረው የስዊስ አገር ዜጋ በሆነው አልፍሬድ ኢልግ ነበር፡፡
  • ቀጥሎም አገልግሎቱ የፖስታ፣ የቴሌግራፍ እና ቴሌፎን ሚኒስቴር (ፖቴቴ) ተብሎ በ1903 ዓ.ም. የስያሜ ለውጥ ተደርጎለት ሚስተር ሊዮ ሸፍኖ በተባሉ የፈረንሳይ ዜጋ ሲተዳደር ቆይቷል፡፡ ከዚህም ሰው ቀጥሎ በመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን አስተዳዳሪዎች በልጅ ግዛው በዛብህ፣ በልጅ በየነ ይመር እና ተከታዮቻቸው ሲተዳደር ቆይቷል፡፡

1886-1934

ከኢትዮ-ኢጣሊያ ጦርነት በኋላ የተካሄደ የመልሶ ማቋቋም ሥራ

የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ተሸንፎ አገሪቷ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ እንደገና እንዲቋቋም የተደረገው የፖስታ፣ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ሚኒስቴር  የቴሌፎን፣ የቴሌግራፍና የሬዲዮ መገናኛዎችን የማስተዳደር ተግባር ተረክቦ በመላ አገሪቷ የመገናኛ ኔትወርኩን እንደገና የማቋቋም ተግባር አካሂዷል፡፡  በዚህ የፖስታ፣ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ሚኒስቴር አማካይነት የረጅም መስመር መገናኛዎችን የመጠገን ሥራ ተካሄዷል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ (Imperial Board of Telecommunication of Ethiopia - IBTE) በሚል ስያሜ ጥቅምት 5 ቀን 1945 ዓ.ም ራሱን ችሎ በአዋጅ ቁጥር 131/45 ተቋቋመ፡፡

የቦርዱ ዋና ዓላማ በማቋቋሚያ ቻርተሩ አንቀጽ 5 ላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን መሣሪያዎችን መልሶ ማቋቋም፣ ማስፋፋት፣ መጠገንና መጠበቅ እንዲሁም ትርፍ ለማግኘት ሚያስችል የቴሌኮሙኒኬሽን ሥራ ማካሄድ የሚሉ ነበሩ።

የቴሌኮሙኒኬሽን ቦርዱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የኦፕሬሽናል ጉዳዮችን የሚቆጣጠር የክፍለ ሐገር ጽ/ቤት በማስፈለጉ ጽ/ቤቱ በ1952 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንዲቋቋም ተደርጓል።  በተመሳሳይ ጊዜም የሬዲዮ ዋና ክፍል ከቴክኒክ ዋና ክፍል ተነጥሎ ራሱን ችሎ እንዲደራጅ በመደረጉ የዋና ክፍል ቢሮዎችን ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ እንዲል አድርጎት ነበር።

1934-1945

በደርግ ዘመነ መንግሥት

በደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን በተለያዩ ስያሜዎች ሲጠራ የነበረ ሲሆን በዚህም መሠረት፡-

  • ከጥቅምት ወር 1967 ዓ.ም. እስከ ጥር ወር 1973 ዓ.ም. ድረስ የሶሻሊስት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ድርጅት በሚል ስያሜ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡
  • ከጥር ወር 1973 ዓ.ም - 1983 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ተብሎ ሲጠራ የነበረ ሲሆን ይህም ጊዜ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከአውቶማቲክ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ለውጥ ያደረገበት ወቅት ነበር፡፡

1966-1983

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ

ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉ በአዲስ መልክ እንደገና እንዲዋቀር በማድረጉ ሁለት የተለያዩና ራሳቸውን የቻሉ ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ (ሬጉላቶሪ አካል) እና የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ኦፕሬተር አካል) በሕዳር ወር 1989 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 49/1989 መሠረት እንዲቋቋሙ አደረገ፡፡

ከ1983 - እስከ አሁን ድረስ

የኢትዮ ቴሌኮም አመሠራረት

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት የባለፈውን አምስት (1998 – 2002 ዓ.ም) እቅድ እንዲቀጥል በማድረግ እንዲሁም ለትምህርት፣ ለጤናና ለግብርና ዘርፎች ትኩረት በመስጠት እና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለሀገራችን ልማት ወሳኝ ኃይል መሆኑን በመገንዘብና አገልግሎቱን ለማሻሻል በመወሰን በሀገራችን ቀጣይ እድገት የሚጫወተው ቁልፍ ሚና እንዲጠናከር ካለው ፍላጎት አኳያ ኢትዮ ቴሌኮም ሕዳር 20 ቀን 2003 ዓ.ም እንዲመሠረት አድርጓል፡፡