በአፍሪካ የቴሌኮም አገልግሎትን በማቅረብ ፈር ቀዳጅ የሆነውና ላለፉት 129 ዓመታት በሃገራችን በሰፊው የቴሌኮም አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ታላቅ ሀገርና ህዝብ በማገልገል ላይ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለማሕበረሰባችን ከማስተዋወቅ እና በሰፊው ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የሀገራችን የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እና ሁለገብ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በቁርጠኝነት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት የዘመናችንን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የዲጂታል ሶሉሽኖችን በፍጥነት እያቀረበ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ አቅሞችን አሟጦ በመጠቀም ለሀገራችን ልማትና ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና ያላቸውን ዘርፎች በመለየትና በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ ይበልጥ ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የአስቻይነት ሚናውን በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በዛሬው ዕለትም ደንበኞች ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች የሚጎበኙበትና በተግባር የሚሞክሩበት የኤክስፒሪየንስ ማዕከል በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በይፋ አስመርቋል፡፡ የኤክስፒሪየንስ ማዕከሉ፣ የግለሰብ እና የድርጅት ደንበኞች ምርትና አገልግሎቶችን የሚመለከቱበት፣ አዳዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በተግባር በመሞከር ፈጠራቸውን የሚያነሳሱበትና የቴክኖሎጂ ግኝቶችን የሚመረምሩበት ማዕከል ነው፡፡ማዕከሉ የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ያለፈባቸውን በርካታ ሂደቶች የሚዘክር፣ አሁን ላይ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚያሳይ እንዲሁም የወደፊቱን የቴክኖሎጂ እድገት የሚያመላክት ሲሆን የኢትዮ ቴሌኮምን ታሪካዊ የዕድገት ደረጃዎች የሚተርኩና የሚያስቃኙ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ጨምሮ አሁን ላይ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ልህቀት በሚያሳይ መልክ ተደራጅቷል፡፡

ኤክስፒሪየንስ ማዕከሉ ዘመኑ ያፈራቸውን የተለያዩ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን (cutting-edge technology) በውስጡ አካቶ የያዘና የተደራጀ ሲሆን፣ ለአብነት ያህል እጅግ ፈጣን የ5ጂ ኮኔክቲቪቲ ቨርቹዋል ሪያሊቲ (VR)፣ የፈጠራ ሶሉሽኖችን፣ የስማርት ሆም አውቶሜሽን፣ የቴሌብር ፋይናንሺያል ግብይቶችን፣ የፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ትስስርን (fintech integration)፣ ስማርት የቱሪዝም አገልግሎቶችን፣ የርቀት ታካሚ ክትትልን (remote patient monitoring)፣ የስማርት ግብርና ቴክኒኮችን፣ ስማርት የትምህርትና የትምህርት መሳሪያዎችን፣ ስማርት የማዕድን ልማትን (smart mining practices)፣ የክላውድ እና የዳታ ማዕከል ሶሉሽንስ፣ ፈጣንና ሙሉ ጊዜ የደህንነት ክትትል/ቁጥጥር ሶሉሽን (real-time safety) እንዲሁም በመዝናኛው ዘርፍ በ5ጂ የታገዘ የሙዚቃ መዝናኛ ሶሉሽንን (5G-enabled music streaming) እና በመሳሰሉ አዳዲስ ሶሉሽኖች የተሞላ ማዕከል ነው፡፡

በመሆኑም ለሀገራችን ልማትና ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና ያላቸውን በተለያዩ ዘርፍ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የተቋማቸውን አሰራር በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርታማነታቸውን ማሳደግና ማዘመን የሚችሉበትን ሶሉሽኖች በተግባር የሚፈትሹበትና የሚያዩበትን እድል የሚፈጥር በመሆኑ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን እየተሰራ ላለው ስራ በእጅጉ የሚያግዝ ነው፡፡

ኩባንያችን ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታና ለማህብረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥ እና የኑሮ መሻሻል በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያከናወናቸውና እያበረከታቸው የሚገኙ መጠነሰፊ ፕሮጀክቶችን በተለይም የላቀ የደንበኛ ተሞክሮን እውን የሚያደርጉ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራን የሚያሳድጉ ስራዎችን ማከናወኑን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives