አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም፤ ኩባንያችን የሀገራችንን የግብይት ሥርዓት በዲጂታል በማዘመን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል፣ ሁሉን አቀፍ እና አካታች የሆነ ‘ዘመን ገበያ ‘ የተሰኘ ዘመናዊ የዲጂታል ግብይት ፕላትፎርም በቴሌብር ሱፐርአፕ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ይህ ፕላትፎርም በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች የገበያ ትስስርን በመፍጠር እና ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ፣ ለሀገራዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በአጋርነት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾችን ወደ ዘመን ገበያ በማስገባት፤ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገር ውስጥ ሸማቾች እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን በታላቅ ደስታ ያበስራል፡፡
ይህ ስምምነት የኢንዱስትሪ ፓርክ አምራቾች የኤክስፖርት ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶቻቸውን በስፋትና በቅልጥፍና ተደራሽ እንዲያደርጉ ከማድረግ ባሻገር፤ ግብይቱ በዲጂታል የሚከናወንና ሙሉ በሙሉ በመረጃ በተደገፈ (Data-driven) ዘመናዊ የክምችትና የሎጂስቲክስ አስተዳደር የሚመራ በመሆኑ፣ የኦፕሬሽን ወጪን በእጅጉ ለመቀነስ ያስችላል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ዘመን ገበያ ላይ ለግብይት የሚቀርቡት ዋና ዋና የኢንዱስትሪ ምርቶች፡-
· የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ አልባሳት፣ ጨርቃ ጨርቅ እና ጋርመንት፤
· የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፡ በኢትዮጵያ ሀይላንድ ሌዘር (Highland Leather) የሚታወቁ የቆዳ ውጤቶች፣ ቦርሳዎች እና የፋሽን መለዋወጫዎች፤
· የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ውጤቶች፡ እሴት የተጨመረባቸው የግብርና ምርቶች፣ የቅባት እህሎች፣ ቡና፣ እና የምግብ ምርቶች፤
· ኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኖሎጂ ምርቶች፡ የሞባይል ስልኮች፣ ታብሌቶች፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎች (ቲቪ፣ ፍሪጅ)፣ እና የኤነርጂ ምርቶች፤
· መድሃኒት እና የህክምና ግብዓቶች፡ የመድሃኒት ምርቶች እና የተለያዩ የህክምና መርጃ መሳሪያዎች፤
· የኬሚካል እና የግንባታ ግብዓቶች፡ ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚውሉ ኬሚካሎች፣ ማዳበሪያ እና የግንባታ ማቴሪያሎች፤ እንዲሁም
· ሌሎች የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች፡ የሴራሚክ እና የእንጨት ውጤቶችን ያካተተ ነው።ይህ ስምምነት በዋናነት የሚከተሉትን የትብብር ማዕቀፎች ያካተተ ነው፦
· በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን (IPDC) ስር ያሉ አምራቾችን በዘመን ገበያ የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ላይ በመመዝገብ ማሳተፍ፤
· በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶችን ዲጂታል ሥርዓትን በመጠቀም ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር
· ከመነሻ ትዕዛዝ እስከ ግብይት ፍጻሜ ያለውን የሎጂስቲክስ፣ የትዕዛዝ አስተዳደር እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ፤
· በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥነ ምህዳር ውስጥ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ።
ከዚህም ባሻገር ይህ የትብብር ማዕቀፍ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾችን የዲጂታል ክህሎት እና አቅም በመገንባት፣ ምርቶቻቸውን በዘመን ገበያ በማስተዋወቅ፣ እንዲሁም አስተማማኝ የገበያ ትስስር እና የግብይት መረጃ ልውውጥ ሥርዓትን በመዘርጋት፤ የሀገራችንን የንግድ ሥነ ምህዳር ወደ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ደረጃ ለማሸጋገር የማይተካ ሚና ይጫወታል።
ኩባንያችን በነደፈው “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” መሰረት፤ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ እና አጠቃላይ የንግድ ሥነ ምህዳሩን በማዘመን ይበልጥ አካታችና ተደራሽ ለማድረግ፣ እንዲሁም ለንግዱ ማህበረሰብና ለሸማቾች አስተማማኝና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መፋጠን የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በላቀ ቁርጠኝነት መወጣቱን የሚቀጥል ይሆናል።
ስለ ዘመን ገበያ
ዘመን ገበያ የኢትዮ ቴሌኮምን ሰፊ የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የኢንተርኔት እና የስማርት ስልክ ተደራሽነት እንዲሁም የቴሌብር ሥነ-ምህዳርን በመጠቀም የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅስ ብሔራዊ የዲጂታል መገበያያ ፕላትፎርም ነው። ፕላትፎርሙ የአገር ውስጥ ነጋዴዎችን በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ደንበኞች ጋር በጥሬ ገንዘብ አልባ እና በመረጃ ላይ በተመሠረተ የኢ-ኮሜርስ ሥርዓት በማገናኘት፣ ፈር ቀዳጅ የዲጂታል መፍትሔ ሆኖ ብቅ ብሏል። እ.ኤ.አ. ግንቦት 2025 ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ዘመን ገበያ ከ21 ሚሊዮን በላይ ጉብኝቶችን እና ከ70,000 በላይ ትዕዛዞችን ያስተናገደ ሲሆን፣ ከ460 በላይ ነጋዴዎችን በማቀፍ የሀገራችንን የኢ-ኮሜርስ ዘርፍ በላቀ ፍጥነት እየለወጠ ይገኛል።
ስለ ኢትዮ ቴሌኮም
ኢትዮ ቴሌኮም ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የተቀናጁ የቴሌኮም እና የዲጂታል መፍትሄዎች አቅራቢ ኩባንያ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ1894 ጀምሮ የሀገሪቱን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በመምራት ላይ ይገኛል። ኩባንያው 86.1 ሚሊዮን ደንበኞች እና ከ57.59 ሚሊዮን በላይ የቴሌብር ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፣ ከ10,200 በላይ የሞባይል ማሰራጫ ጣቢያዎችን በመላ ሀገሪቱ የያዘ ሰፊ የኔትወርክ መሰረተ ልማት በመጠቀም፤ ለዜጎች እና ተቋማት አስተማማኝ የኮሙኒኬሽን፣ የዲጂታል መፍትሄዎች እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል።
የማህበራዊ ትስስር ገጾች፡
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/ethiotelecom
ቴሌግራም፡ https://t.me/ethio_telecom
ኤክስ (ትዊተር): https://twitter.com/ethiotelecom
ሊንክዲን፡ https://www.linkedin.com/company/ethio-telecom
ዩቲዩብ፡ https://www.youtube.com/c/EthiotelecomETH
ዌብሳይት፡ https://www.ethiotelecom.et/
ስለ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እ.ኤ.አ. በ2014 የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር ለማፋጠን የተቋቋመ የመንግስት ልማት ድርጅት ነው። ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በስትራቴጂያዊ ቦታዎች የሚገኙ 11 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን እና 2 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስተዳደር ላይ ይገኛል። ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የመሰረተ-ልማት አውታሮችን፣ የለሙ መሬቶችን እና ደረጃቸውን የጠበቁ የምርት ሼዶችን ከማቅረብ በተጨማሪ፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ቀልጣፋ የባለአንድ ማዕከል አገልግሎት በመስጠት ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ለኢንዱስትሪ ዘርፉ መስፋፋት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የማህበራዊ ትስስር ገጾች፡
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/IPDCEthiopiaofficial#
ቴሌግራም፡ https://t.me/ipdcofficial
ኤክስ (ትዊተር): https://twitter.com/ethiopiaipdc
ሊንክዲን፡ https://www.linkedin.com/company/ipdcethiopiaofficial/
ዩቲዩብ፡ https://www.youtube.com/channel/UCkkZlVUiETmETOmn1Qotz2g
ዌብሳይት፡ https://www.ipdc.gov.et/
ኢትዮ ቴሌኮም እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን
ታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም

