በኢትዮ ቴሌኮም እና በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መካከል የፓስፖርት አገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተደረገ

ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረጉን ጉዞ እየገፋበት የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም አዲስ ፓስፖርት የሚያወጡ፣ የሚያሳድሱና ምትክ የሚፈልጉ ደንበኞች ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ የሆነውን የዘመኑን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ቴሌብርን ተጠቅመው በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሆነው የአገልግሎት ክፍያቸውን መፈጸም ይችሉ ዘንድ ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ፈጸመ፡፡

ይህ በዛሬው ዕለት የተደረገው የአጋርነት ስምምነት በዋናነት የኢትዮ ቴሌኮም የቴሌብር አገልግሎትን ከፓስፖርት አገልግሎት ክፍያ አሰራር ጋር በማስተሳሰር በየጊዜው እያደገ የመጣውን የደንበኞች የክፍያ አማራጭ የአገልግሎት ፍላጎት ቀላል እና አስተማማኝ በማድረግ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት፣ ለማሳደስ፣ ለጠፋ ምትክ ለማውጣት እና የተበላሸ እንዲስተካከልላቸው የሚፈልጉ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን ባሉበት ቦታ በቀላሉ መክፈል ያስችላቸዋል፡፡

በተጨማሪም ደንበኞች ለከፈሉት የአገልግሎት ክፍያ ማስረጃው በቅርብ እንዲኖራቸው፣ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣትም ሆነ ለማሳደስ ወደ ኤጀንሲው ሲሄዱ የሚደርሰውን የገንዘብና የጊዜ ብክነት፣ የጉልበት ድካም እና የደላሎች ወከባ በመቀነስ ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ የአገልግሎት ክፍያ አማራጭ ለማቅረብ ያለመ ነው፡፡

የቴሌብር የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ለዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስፋፋት ጉልህ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን አገልግሎቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ 19.95 ሚሊዮን ደንበኞች፣ 82 በላይ ዋና ወኪሎች፣ 69.8 ሺህ ወኪሎች እና 18.8 ሺህ ነጋዴዎች ማፍራት ችሏል፡፡

በተጨማሪም በቴሌብር 20.63 ቢሊዮን ብር የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር የተደረገ ሲሆን ከ12 ባንኮች ጋር ከባንክ ወደ ቴሌብር እና ከ10 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ ገንዘብ ለማስተላለፍ ትስስር መፍጠሩ ለዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ያለውን ከፍተኛ ተመራጭነት ያሳያል፡፡

ኩባንያችን የህብረተሰቡን የተለያዩ የቴሌኮም ፍላጎቶችን ለማሟላት እና ዘመኑ ያፈራቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር በአጋርነት ከሚሰሩ ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር የማህበረሰባችንን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል፣ ለማቅለል ብሎም የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ለማድረግ እንዲሁም በማህበረሰባችን ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬትን፣ የመብራት አገልግሎት፣ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን፣ የውሃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤቶች የወርሃዊ አገልግሎት ክፍያን እንዲሁም የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /ራይድ/ አገልግሎት ክፍያን በቴሌብር ለማከናወን የሚያስችል የጋራ ስምምነትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች የአገልግሎት ክፍያዎቻቸውን በቴሌብር እንዲፈጽሙ የሚያስችል ስምምነት አድርጓል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርአታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርአት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው መፈጸም እንዲችሉ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡

ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives