ኩባንያችን የመጪውን 2015 አዲስ ዓመት መዳረሻ የጳጉሜን 5 ቀናት በመላው የሀገራችን ክፍሎች ከደንበኞቹ ጋር በአገልግሎት ማዕከሎቹ፣ በአውዳመት ገበያ ስፍራዎች፣ በጎዳና ትርኢቶች፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾቹ እንዲሁም በሌሎችም መሰናዶዎች ለማክበር ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን ዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የበጎ አድራጎት ቀን አስመልክቶ በመላው የሀገራችን ክፍሎች ከ19 በላይ በሚሆኑ የበጎ አድራጎት ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ 6,850 ነዋሪዎች ለአዲስ ዓመት መዋያ ወጪ የሚሆን የ5.2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ዛሬ በአዲስ አበባ ተከናወነው መርሃ ግብር በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ በጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል እንዲሁም በሙዳይ የበጎ አድራጎት ማህበር ውስጥ ለሚገኙ 2050 ነዋሪዎች የ2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በኩባንያው ሪጅኖች በሚገኙ 16 የበጎ አድራጎት ተቋማት ውስጥ ለሚገኙ 4,800 ነዎሪዎች ደግሞ የ3.2 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የኩባንያችን ዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ደም በመለገስ የወገኖቻቸውን ውድ ሕይወት የሚታደግ የከበረና ታላቅ የአዲስ ዓመት ስጦታ አበርክተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም እየተሰናበትነው ባለነው የ2014 ዓ.ም በዓይነት፣ በአገልግሎትና በጥሬ ገንዘብ በድምሩ ከ422.6 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለትምህርት፣ ለአካባቢያዊ ጥበቃ፣ ለመንግሥት ፕሮጀክቶች እና ለሰብዓዊ አገልግሎት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በተለይም በበጎ አድራጎት ለተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በዓይነት፣ በጥሬ ገንዘብ፣ በነጻ አጭር ቁጥር መስመሮች እና በቴሌብር ገቢ ማሰባሰብያ ድጋፍ ለመቄዶኒያ አረጋውያን መርጃ ማዕከል፣ ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ ለጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል፣ ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ ለሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር፣ ለኩላሊት ሕመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ለኢትዮጵያ ካንሰር አሶሲየሽን እና ሌሎችም ድርጅቶች ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ኩባንያችን በደንበኞቹ የአኗኗር ዘይቤ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የዲጂታል መፍትሔዎችን፣ ዘመኑ የደረሰበትን የቴሌኮም አገልግሎቶች ከመተግበር እና የአሰራር ሥርዓቶችን ከመዘርጋት እንዲሁም አዳዲስ የቴሌኮም ምርት እና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባሻገር ለህብረተሰባችን አስፈላጊ በሆኑ ማኅበራዊ ድጋፎች ሁሉ ኃላፊነቱን እየተወጣ ሀገራዊ አለኝታነቱን እያረጋገጠ ይቀጥላል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives