ኢትዮ ቴሌኮም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች የበረራ ትኬት ክፍያን በቴሌብር እንዲፈጽሙ የሚያስችል አሰራርን ተግባራዊ አደረገ

በኢትዮ ቴሌኮም እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል የሀገር ውስጥ መንገደኞች የበረራ ትኬት ግዢ ክፍያዎችን በቴሌብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት የተደረገ ሲሆን፣ ይህም የአየር መንገዱ ደንበኞች የጉዞ ትኬት ግዢ ክፍያዎችን በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ በሆነው በቴሌብር እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸው የክፍያ አማራጭ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች በዓመት ውስጥ ከ2.52 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ተጓዦችን ለማስተናገድ በዕቅዱ ይዞ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ከ17.6 ሚሊዮን በላይ ከመድረሱ አኳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደንበኞቹ ቀላል እና አስተማማኝ የክፍያ አማራጭ በማቅረብ እቅዱን ለማሳካት ያስችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሙከራ ደረጃ በቴሌብር የሃገር ውስጥ ትኬት ክፍያን ከጀመረበት ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ 6.67 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የሀገር ውስጥ የበረራ ትኬቶችን በቴሌብር አማካኝነት መሸጥ አስችሎታል፡፡

የቴሌብር አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ከ12.58 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ የገንዘብ ዝውውር ወይም ግብይት ማከናወን የተቻለ ሲሆን ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር (528.4 ሺህ ዶላር) በላይ በስምንት የቴሌብር ዓለም አቀፍ ሀዋላ አጋሮች በኩል ከ34 ሀገራት ገንዘብ መቀበል ተችሏል፡፡

በተጨማሪም የቴሌብር የዲጂታል ግብይት አገልግሎት ተደራሽነት እና የአገልግሎት ሰጪ አጋሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎቱ በ353 የሽያጭ ማዕከላት፣ በ80 ማስተር ኤጀንቶች/ዋና ወኪሎች፣ በ64 ሺህ ወኪሎች እና ከ16 ሺህ በላይ ነጋዴዎች የሚሰጥ ሲሆን ከ12 ባንኮች ጋርም አገልግሎቱን የማስተሳሰር ስራ ተከናውኗል፡፡

የቴሌብር የዲጂታል ግብይት አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገበት ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ የማህበረሰባችን የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴን በማቅለል በኩል ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ተችሏል፡፡ በተለይም የቴሌብር የዲጅታል (ኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር) ግብይት አገልግሎት የማህበረሰባችን የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ተጠቃሚነትን ተሞክሮ ለማሻሻል እና በጥሬ ገንዘብ የሚገበያየው የማህበረሰብ ቁጥር እንዲቀንስ ለማድረግ እንዲሁም ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ እና የአገልግሎት ክፍያቸውን በትክክለኛው ጊዜ ለመሰብሰብ እንዲችሉ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ልዩ ልዩ አነስተኛ የአገልግሎት ክፍያዎችን ከመፈጸም ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ድረስ በቴሌብር ማከናወን መቻሉ ለሀገራችን የዲጂታል ግብይት ስርዓት መፈጠር ጉልህ አበርክቶ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ተቋማት አገልግሎቱን በስፋት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡

የቴሌብር አገልግሎት የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን ጨምሮ ከ52 በላይ የቀጥታ ግብይትን (online merchants) ከሚያከናውኑ፣ ወርሃዊ የአገልግሎት ክፍያን በቴሌብር ከሚቀበሉ እና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡም ከ20 በላይ ከሚሆኑ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የአገልግሎት ክፍያን በቴሌብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ኩባንያችን በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

                                            ኢትዮ ቴሌኮም

                                     ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives