ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2014 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2015 ዓ.ም ያለውን የመጀመሪያ መንፈቅ የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ሲሆን አፈጻጸሙ በኢትዮ ቴሌኮም የሥራ አመራር ቦርድና በከፍተኛ ማኔጅመንት ተገምግሞ የቀረበ ነው፡፡

የቴሌኮም መሠረተ ልማትና አገልግሎት የሀገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ እና ለማሳለጥ አይነተኛ የአስቻይነት ሚና ይጫወታል፡፡ ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል፣የማህበረሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ የታሪፍ ማሻሻያዎች በማድረግ፣ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፊ የፕሮጀክትና የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት እያደገ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ ደንበኞቹን በማርካት ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነው የቴሌኮም ገበያ ብቁና ተመራጭ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን በትጋት እየሰራ ያለ ሀገራዊ የልማት ተቋም ነው፡፡

ኩባንያችን ለቴሌኮም ውድድር ገበያው ብቁ፣ ተወዳዳሪና ተመራጭ መሆን የሚያስችለውን BRIDGE (ድልድይ) የተሰኘ የሶስት አመት ስትራቴጂውን ተግባራዊ ባደረገባቸው ሶስት አመታት፤ የደንበኛን ብዛት በ75.6% ገቢን በ76%፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን በ104% በማሳደግ እንዲሁም የተጣራ ትርፍን በ142% በማሳደግ በስኬት አጠናቆ በአዲሱ በ2015 በጀት አመት፣ በአዲስ ጅማሮ፣ በአዲስ እይታ ከኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር (beyond connectivity) መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ በመሆን የድርጅቶችን እንዲሁም የግለሰቦችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማሳለጥ አካታች እድገት እንዲኖር የማስቻል ራዕይ የሰነቀ ከ2022 እስከ 2025 የሚቆይ LEAD (መሪ) የተሰኘ የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ቀርጾ እ.ኤ.አ ከሐምሌ 01 ቀን 2022 ጀምሮ ለህዝብ በማስተዋወቅ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ይህ የያዝነው በጀት ዓመት የLEAD Growth ስትራቴጂ የመጀመሪያው አመት ሲሆን በመጀመሪያው ስድስት ወራት ውስጥ የአገልግሎታችን ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 70 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ15.1% እድገት ወይም 9.2 ሚሊዮን ጭማሪ የደንበኛ ብዛት እንዲሁም ከእቅድ አንጻር የ98.6% አሳክቷል፡፡ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 67.7 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ (Fixed Broadband) 566.2 ሺህ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 862.2 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 31.3 ሚሊዮን ናቸው፡፡ የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) መጠን 65.7% ሆኗል፡፡

በበጀት አመቱ አጋማሽ 33.8 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 96% አሳክቷል፡፡ ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ19.9% ብልጫ ያለው ሲሆን በብር 5.62 ቢሊዮን ብር እድገት አሳይቷል፡፡ የተገኘው የገቢ ድርሻ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 47.4% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 28% ፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 8.4% እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች የ6.5% የመሰረተ ልማት ኪራይ 2.2% እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 7.5% ድርሻ አላቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 64.8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዱን 90% ያሳካ ነው፡፡

ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 50 አዳዲስ እና 41 ነባር በድምሩ 91 የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች ለማቅረብ በመቻሉ ነው፡፡

በተጨማሪም የኩባንያችን መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማከራየት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ 228 የፕሮጀክት ሥራዎች በማከናወን 5 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የኔትወርክ አቅም የማሳደግ ስራ የተሰራ ሲሆን ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (mission critical)፣ በተመሳሳይ ወቅት (real time) መከናወን ለሚያስፈልጋቸው አገልግሎቶች እና internet of things የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች በተግባር እውን እንዲሆኑ የሚያስችለውን የ5G የሞባይል ቴክኖሎጂ የሙከራ አገልግሎትን በአዳማ ከተማ አስጀምሯል፡፡

ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ የገቢ አማራጮችን ለማስፋት ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት በተጨማሪ ወጪን በአግባቡ የመጠቀም እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስወገድ እና በአጠቃላይ ኩባንያውን ውጤታማና ምርታማ ለማድረግ የሚያስችል የወጪ መቆጠብ ስትራቴጂ (DO2SAVE & cost optimization strategy) በመቅረጽና ተግባራዊ በማድረግ 3.5 ቢሊዮን ብር በላይ የወጭ ቅነሳ በማድረግ የዕቅዱን 134% ማሳካት ችሏል፡፡

የሀገራችንን የድጅታል ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ታስቦ የተጀመረው “የቴሌብር” አገልግሎት 27.2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራትና በስድስት ወራት ውስጥ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ 166.1 ቢሊዮን ብር የግብይት መጠን (Transaction Value) በማንቀሳቀስ የ82.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት ተችሏል፡፡

የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያችን አጋሮችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እስካሁን ድረስ 372 የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከሎች፣ 112 ማስተር ኤጀንቶች፣ 98.8 ሺህ በላይ ኤጀንቶችና 25.5 ሺህ በላይ ነጋዴዎች /Merchants/ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ከ18 ባንኮች ጋር የኢንቴግሬሽን ሥራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን ከ15 ባንኮች ጋር ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር እንዲቻል ተደርጓል፡፡ የቴሌብር ሃዋላ አገልግሎት በማስጀመርና ከዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ጋር በማገናኘት በ44 ሀገራት የሚገኙ ዜጎች በቀላሉ ወደ ሀገርቤት ገንዘብ ማስተላለፍ የሚችሉበት አማራጭ የተፈጠረላቸው ሲሆን ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 719.6 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለመቀበል ተችሏል፡፡

በዚህ መንፈቅ ዓመት ከተተገበሩና የክፍያ ስርዓቶቻቸውን ከቴሌብር ጋር ካስተሳሰርናቸው ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶችና ተቋማት ውስጥ ብሔራዊ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ፣ የዩኒቲ ፓርክና የወዳጅነት ፓርክ ምእራፍ 2 የመግቢያ ትኬቶች፣ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ቢሮ፣ የብሄራዊ ሎቶሪ፣ የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ሲሆኑ አጠቃላይ 214 ተቋማት የክፍያ ስርአታቸውን ከቴሌብር ጋር አስተሳስረዋል፡፡ በቀጣይም ከ127 በላይ የመንግስት አገልግሎቶች የክፍያ ስርዓታቸው ዲጂታል እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ኩባንያችን በቬንደር ፋይናንሲንግ ሞዳሊቲ ላከናወናቸው ፕሮጀክቶች ብድር 3.4 ቢሊዮን ብር ወይም 60.8 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በመፈጸም ከአጋሮቹ ጋር ያለውን መልካም የቢዝነስ ግንኙነት፣ ተዓማኒነት እና አጋርነት ማስቀጠል ችሏል፡፡

የኩባንያችንን የማስፈፀምና የመፈጸም አቅምን በማጎልበት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ ተከታታይነት ያለው ስልጠና በአካል 9 ሺህ በላይ እና በዲጂታል አማራጭ 14 ሺህ በላይ ሠራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የሠራተኛውን ተነሳሽነትና የባለቤትነት መንፈስ የሚያሳድጉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት ያህል ሠራተኞችን በተቋሙ ስትራቴጂ ዝግጅትና የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ግብዓት እንዲሰጡ የማድረግ፣ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎችን አቅርቦት ማሻሻል፣ የሥራ ከባቢን አመቺና ደህነንቱን የማረጋገጥ እንዲሁም የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመተግበር የተሻለ የሥራ ከባቢን የሚፈጥሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ሲሆን በበጀት አመቱ አጋማሽ በዓይነት፣ በአገልግሎትና በገንዘብ በድምሩ 294 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ በመላው ሃገራችን በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ ላይ ተሳትፏል፡፡ ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች 2.9 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን በመንፈቅ ዓመቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል በተለያዩ የሀገራችን ክፍል ባጋጠሙ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የአገልግሎት መቆራረጥ፣ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ ቴሌኮም ማጭበርበር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የአቅርቦት እጥረት እና የስራ ተቋራጮች አቅም ማነስ፣ በተቋም ንብረት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ የገበያ አለመረጋጋት እንዲሁም የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ያስመዘገበው አበረታች አፈጻጸም ለበለጠ ስኬት የሚያነሳሳ ሲሆን በተለይም በወቅቱ ከነበሩ ተግዳሮቶች እና የቴሌኮም አገልግሎትን ለመስጠትና ለማስፋፋት ካለው ፈታኝ እንዲሁም በውድድር ገበያ ውስጥ መሆኑ አፈጻጸሙን እጅግ አመርቂ ያደርገዋል፡፡ ይህ ውጤት የተመዘገበው የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ከኩባንያው አመራር ጋር በመናበብና በመደጋገፍ እንዲሁም የኩባንያችን አመራርና ሠራተኞች የኩባንያችንን ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥና ተመራጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ እንዲሆን ለማድረግ ካላቸው ህልም፣ ለውጤታማነቱ ባሳዩት ቁርጠኝነት እንዲሁም በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በአግባቡ በመወጣት ላቀዷቸው ግቦች መሳካት ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረትና ሰፊ ርብርብ ነው፡፡

በመንፈቅ ዓመቱ ለተመዘገበው አበረታች ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለነበራቸው ደንበኞቻችን፣ የኩባንያችን የስራ አጋሮች፤ የምርትና አገልግሎቶቻችን አከፋፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮቻችን እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችን እናቀርባለን፡፡ በቀጣዩ መንፈቅ ዓመትም ለበጀት ዓመቱ ያቀድናቸውን መጠነ ሰፊ ግቦች ለማሳካት የሚያስችሉን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ የኔትዎርክ ማስፋፊያ ሥራዎችን እንዲሁም አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን በማቅረብ የደንበኞቻችን ፍላጎት ለማርካት የምንተጋ መሆናችንን በአክብሮት እንገልጻለን፡፡

  ጥር 04 ቀን 2015 .

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives