ኢትዮ ቴሌኮም በመላው የሃገራችን ክፍሎች በ509 የራሱ የሽያጭ ማዕከላት እንዲሁም በ134 የወኪል ሽያጭ ማዕከላት (Franchise shops) አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሆኖም ኩባንያው ምርትና አገልግሎቶቹን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እና የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር ያስችለው ዘንድ ዛሬ ሚያዚያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም የኢትዮ ቴሌኮምን ምርት እና አገልግሎቶች በብቸኛ አጋርነት (exclusive strategic partnership) ዋና አከፋፋይ በመሆን ከሚሰሩ 7 ድርጅቶች እና ተቋማት ጋር ስምምነት ፈጽሟል፡፡

በዚህም መሠረት እነዚህ ሃገርአቀፍ አከፋፋዮች ኢትዮ ቴሌኮምን በመወከል የቴሌብር አገልግሎት፣ የሞባይል ሲምካርድ እና የአየር ሰዓት፣ የምትክ ሲም ካርድ አገልግሎቶችን በዋና አከፋፋይነት እንዲሰሩ እንዲሁም የወኪል ሽያጭ ማዕከላትን (Franchise shops) በመክፈት የኩባንያውን ምርት እና አገልግሎት ለደንበኞች እንዲሰጡ ያስችላቸዋል፡፡

በሃገር-አቀፍ ደረጃ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ብቻ የቴሌኮም ምርትና አገልግሎቶችን ለማቅረብ/ለማከፋፈል የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት የተፈራረሙት ድርጅቶች/ተቋማትም ህዳሴ ቴሌኮም አክስዮን ማህበር፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ ናሬድ ጄኔራል ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግል ማህበር፣ ሃይላይት ስቴሽነሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ትሬዲንግ፣ ስማርት ዲጂታል ቴክኖሎጂስ ኃ.የተ.የግል ማህበር፣ ቴሌፖርት ቴክኖሎጂስ ኃ.የተ.የግል ማህበር እና አላሚ ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል እነዚህ ሃገርአቀፍ አከፋፋዮች ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በአጋርነት ሲሰሩ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን በዚህ የብቸኛ አገልግሎት ሰጪነት ስምምነት ቀደም ሲል ይሰጡ ከነበሩት ውስን አገልግሎቶች በተጨማሪ መስኮች በመሠማራት የኩባንያውን ምርቶች ለደንበኞች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችላቸው መልኩ ሃገር-አቀፍ አከፋፋይነት እንደዲሰማሩ ያስችላቸዋል፡፡

በተመሰሳይም በዛሬው እለት በኩባንያው ዞኖች እና ሪጂኖች በብቸኛ አከፋፋይነት የሚሰሩ 13 ድርጅቶች ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከኩባንያው ጋር 48 ሌሎች ድርጅቶች በአከፋፋይነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም የአጠቃላይ የኩባንያው ምርት እና አገልግሎት አከፋፋዮችን ቁጥር 68 የሚያደርሰው ሲሆን በእነዚህ አከፋፋዮች ስር 9,448 ንዑስ አከፋፋዮች እንዲሁም 350,102 ቸርቻሪዎች በአጠቃላይ በሽያጭ ትስስሩ 359,618 ድርጅቶች በአጋርነት አብረው እየሰሩ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

 

                                            ኢትዮ ቴሌኮም

                                    ሚያዚያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives