ካምቴል እና ኢትዮ ቴሌኮም በካሜሩን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን የሚያስችል የኮንትራት ስምምነት ተፈራረሙ

camtel and Et feature photo
Camtel logo
Et logo for PR

ያውንዴ፣ ህዳር 25 2025 – የካሜሩን ቴሌኮሙኒኬሽን (ካምቴል) የካሜሩንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የኮንትራት ስምምነት በይፋ ተፈራረመ። ሁለቱ ኦፕሬተሮች የተፈራረሙት ይህ ታሪካዊ የማስተር ሰርቪስ ስምምነት (Master Service Agreement) የካምቴል ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች እ.ኤ.አ በኤፕሪል 2025 በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተጀመረውና ዕውን የሆነው የትብብር ግንኙነት አካል ነው።

በወቅቱ በነበረው የመጀመሪያ የልምድ ልውውጥ ጉብኝት፣ የካምቴል አመራሮች ኢትዮ ቴሌኮም የ”ዲጂታል ኢትዮጵያሀገራዊ አጀንዳን በማፋጠን ረገድ የተጫወተውን ወሳኝ ሚና በአካል የተመለከቱ ሲሆን፣ ይህ ጉብኝት ኩባንያችን ለግለሰቦች እና ለድርጅቶች በሚያቀርባቸው አዳዲስ ዲጂታል መፍትሄዎች፣ ዓርአያነት ያለው የለውጥ አመራር፣ ጠንካራ የፕሮጀክት አፈፃፀም እና የቢዝነስ ክህሎት በተግባር ለማሳየት የቻለ ነበር።

በዚህ የኩባንያችንና የሀገራችን ስኬት በመነሳሳት፣ ካምቴል በካሜሩን ተመሳሳይ ዲጂታል ስኬቶችን በሀገራቸው ለመተግበር ፍላጎት አሳይቷል። የካምቴል ቀዳሚ ስትራቴጂካዊ ዓላማ የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል መቀየር፣ አካታች የዲጂታል ፋይናንስ መፍትሄዎችን ዕውን ማድረግ እና የገመድ አልባ ኔትወርክ (wireless network) ማዘመንን ያካተተ የዳበረ ብሔራዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ መፍጠር ሲሆን፣ ካምቴልም ይህንን ራዕዩን ለማሳካት ኢትዮ ቴሌኮምን ስትራቴጂያዊ አጋር አድርጎ ለመምረጥ ችሏል።

በዚህ የትብብር ማዕቀፍ ኢትዮ ቴሌኮም የካሜሩንን የለውጥ ጉዞ ለማገዝ እና የካምቴል (CAMTEL) ግቦችን ዕውን እንዲሆኑ ለማገዝ ከፍተኛ የአማካሪነት አገልግሎት እና የልምድ ልውውጥ (cross-immersion) ተሞክሮዎችን በማቅረብ እና ያለውን ልምድ በማካፈል ጭምር በዘርፉ አብሮ የመስራት ዕድልን ያመቻቻል።

ይህ አጋርነት በዋናነት የሚከተሉት ስትራቴጂያዊ ምሰሶዎች ላይ መፍትሔዎችን በመተግበር ላይ ያተኩራል፦

  1. የሞባይል ገንዘብ ኢኖቬሽን (Mobile Money Innovation): የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ በብሉ መኒ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎት በጋራ መስራት፤
  2. ብሄራዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት (Sovereign Infrastructure): የህዝብ አገልግሎቶችን ዲጂታል ማድረግና ብሄራዊ የመንግሥት ክላውድ (Government Cloud) እንዲቋቋም መደገፍ፤
  3. የኔትወርክ መዘመን (Network Modernization): ለላቀ የግንኙነት ጥራት (connectivity) የ4G፣ 5G ኔትወርክን እና አዳዲስ መፍትሄዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ድጋፍ መስጠት፤
  4. ተቋማዊ ለውጥ (Organizational Transformation): በዋናነት የመረጃ ሥርዓቶችን በማዘመን፣ አሰራርን አውቶሜሽን በማድረግ፣ ደንበኛ-ተኮር ባህልን በማጎልበት ረገድ ድጋፍ በማድረግ የካምቴልን (CAMTEL’s) ተቋማዊ ሽግግር መደገፍ፤

ከእነዚህ የአጋርነት ምሰሶዎች ባሻገር፣ ስምምነቱ ተጨማሪ የትብብር ማዕቀፎችን ለመፍጠር ያስችላል። በቀጣይም የትብብር አድማሱን በማስፋት በኢንተርፕራይዝ መፍትሔዎች፣ በዲጂታል የአኗኗር ዘይቤ አገልግሎቶች፣ በኢንተርኮኔክት ማዕቀፎች እና ተጨማሪ ዕሴት ያላቸው አገልግሎቶች (VAS) ላይ ስትራቴጂያዊ ትብብር መፍጠርን የሚያካትት ይሆናል።

በስምምነቱ አማካኝነት ካምቴል (CAMTEL) የካሜሩንን ዲጂታላይዜሽን በማፋጠን አካታች ኢኮኖሚ የመገንባት አቅሙን የሚያጎለብት ሲሆን፤ ይህም በኩባንያችን ‘ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ’ መሰረት ከአፍሪካዊ ኦፕሬተሮች ጋር በአጋርነት የዲጂታል አፍሪካን ጉዞ ለማፋጠን እና ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ይከፍታል።

ህዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም.

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives