ኩባንያችን የኮኔክቲቪቲና የዲጂታል ሶሉሽኖችን ከማቅረብ ባሻገር ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፈ ብዙ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ የበኩሉን መልካም አሻራ እያሳረፈ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይም የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ተጠቃሚነት ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት እና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን መደገፍ፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ ደም ልገሳና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ በስፋት እና በንቃት የሚሳተፍባቸው አበይት ጉዳዮች ናቸው፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በእነዚህ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ በገንዘብ እና በዓይነት በድምሩ 694.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡
በዚህም መሰረት “በበጎነት የአዲስ ዓመት የምገባ ፕሮግራም” በተሰኘው መርሃ ግብር በመላው የሀገራችን ክፍሎች በ28 የበጎ አድራጎት ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ 8,352 አረጋዊያን፣ ህጻናት፣ እናቶች፣ አቅመደካሞች እና አካል ጉዳተኞች አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የማእድ ማጋራት መርሃ ግብር ከ16.7 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ኩባንያችን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ቀን በመላው የሀገራችን ክፍሎች በ26 የበጎ አድራጎት ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ 7,112 አረጋዊያን እና ሴቶች አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለምገባ መርሃ ግብር ከ8.89 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ ቀንም ኩባንያችን በጎነት ለሰብዓዊነት በሚል መርህ ከብሔራዊ የደም ባንክ ጋር በመተባበር በተቋሙ ዋና መ/ቤት፣ በዞን እና በሪጅን ጽ/ቤቶች በአጠቃላይ በ19 ቦታዎች የኩባንያችን በጎ ፈቃደኛ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ደም በመለገስ የወገኖቻቸውን ውድ ሕይወት የሚታደጉበት መርሃግብር አዘጋጅቶ የወገን አለኝታነቱን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም አነስተኛ ገቢ ላላቸው ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በድርቅና በጸጥታ ችግር ምክንያት ለተቸገሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ቀደም ሲል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመለየት ኩባንያችን “ለነገ ተስፋዎች” በሚል መርህ ባዘጋጀው መርሃ ግብር በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ 930 የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ 75,000 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን የመማሪያ ደብተር ከ67.26 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በስጦታ አበርክቷል፡፡ ኩባንያችን እንደ አንድ ሀገራዊ ተቋም የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ በዋናነትም የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ጫና ለመጋራት፣ ተማሪዎች መሰረታዊ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው እና በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ ለማስቻል እንዲሁም ነገ የተሻለ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወሳል፡፡
እንዲሁም ኩባንያችን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አስከፊ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ኩባንያችን 10 ሚሊዮን ብር እንደተቋም እንዲሁም የአጭር ቁጥር እና በቴሌብር ሱፐርአፕ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ሲስተሞችን በአፋጣኝ በማበልጸግ ከደንበኞች ያሰባሰበውን 1.35 ሚሊዮን ብር በድምሩ ከ11.35 ሚሊዮን ብር በላይ በስፍራው በመገኘት ለጎፋ ዞን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ምላሽ ፈንድ አበርክቷል፡፡
ኩባንያችን በደንበኞቹ የአኗኗር ዘይቤ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የዲጂታል አገልግሎቶችን፣ ዘመኑ የደረሰበትን የቴሌኮም አገልግሎቶች ከመተግበር እና የአሰራር ሥርዓቶችን ከመዘርጋት እንዲሁም አዳዲስ የቴሌኮም ምርት እና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባሻገር ለህብረተሰባችን አስፈላጊ በሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሁሉ ድጋፎችን በማድረግ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ሀገራዊ አለኝታነቱን እያረጋገጠ ይቀጥላል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም
ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም