ኩባንያችን የ5G የሞባይል ቴክኖሎጂ የቅድመ-ገበያ ሙከራ አገልግሎቱን በይፋ አስጀመረ!!

በአፍሪካ በቴሌኮም ዘርፍ ቀደምትና ፋና ወጊ የሆነው ኩባንያችን፣ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ዘመኑ ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎች በማስተዋወቅ የሀገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በመደገፍ ከፍተኛ የሆነ የአስቻይነት ሚናውን በመወጣት ላይ ያለ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡

ኩባንያችን የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይን ዕውን ለማድረግ ባለው ቁርጠኝነት የ3ጂ እና 4ጂ ኔትዎርክ በማስፋፋትና 97 በመቶ የቴሌኮም አገልግሎት ሽፋን በማረጋገጥ ያሉንን ቀደምት ቴክኖሎጂዎችን ዘመን አፈራሽ ወደ ሆኑ ቴክኖሎጂዎች በማሳደግና በማሻሻል ላይ ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶችን ወደ ገበያ በማቅረብ፣ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት እንዲሁም የተለያዩ ዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ላይ ይገኛል፡፡

የቴሌኮም አገልግሎቶችን የማዘመንና የማሻሻል ጥረታችን ቀጣይ እርምጃ የሆነውን የ5ጂ የሞባይል ቴክኖሎጂ የሙከራ አገልግሎትን በአዲስ አበባ ከተማ በስድስት ጣቢያዎች ማስጀመራችንን ስንገልጽ በታላቅ ደስታ ነው፡፡ ይህ የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 Gbs የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ሲኖረው፣ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን (Ultra low latency) እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ ወደ 1ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ሲሆን በተጨማሪም በአንድ ካሬ ኪሎሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ዓለማችን የደረሰበት የመጨረሻ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ነው፡፡

5ጂ አገልግሎት በተለይም ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (Mission Critical) እና በተመሳሳይ ወቅት መከናወን የሚፈልጉ አገልግሎቶችን (real time) ለአብነትም የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ህክምና፣ ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ ያለው ሲሆን እንደ አሽከርካሪ-አልባ ተሽከርካሪዎች (self-driving vehicles)፣ Internet of Things የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች በተግባር እውን እንዲሆኑ የሚያስችል አስተማማኝና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነው፡፡

ኩባንያችን ይህንን የ5ጂ ኔትወርክ የቅድመ-ገበያ የሙከራ አገልግሎት በዋና መዲናችን ያስጀመረ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እስከ 150 የ5ጂ ጣቢያዎችን በመትከል በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ተጨማሪ ማስፋፊያ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ኩባንያችን በአሁኑ ሰዓት ያስጀመረው የ5ጂ አገልግሎት የስነ-ምህዳሩን (ecosystem) ዝግጁነት ለመፈተሽ የሚያስችለውን የቅድመ-ገበያ የሙከራ  አገልግሎት ሲሆን አገልግሎቱን ገበያ ላይ ለማዋልና ለማስፋፋት የደንበኞች ዝግጁነትና 5ጂ የመጠቀም ፍላጎት ማደግ፣ 5ጂ መጠቀሚያ መሳሪያዎችና የ5ጂ መጠቀሚያ ቀፎዎች በስፋትና አቅምን ባገናዘበ መልኩ ገበያ ላይ መኖር፣ በሀገራችን ያሉ ኢንዱስትሪዎች 5ጂ አገልግሎትን የመጠቀም ፍላጎትና ዝግጁነት እንዲሁም አጠቃላይ የቴሌኮም ስነ-ምህዳር የእድገት አዝማሚያ ወሳኝነት አለው፡፡

ኩባንያችን ይህንን ቴክኖሎጂ በሀገራችን ዋና ከተማ እንዲሁም የዓለም አቀፍና አህጉራዊ ዲፕሎማቲክ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ እውን ማድረጉ ተመራጭ የቴሌኮም ኦፕሬተር ለመሆን ያለውን ህልም ለማሳካት ከቀረጸው የሦስት ዓመታት የእድገት ስትራቴጂ ጋር የተናበበና በቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ የተያዘ ነው፡፡ ይህን የ5ጂ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ በቅድመ ገበያ ሙከራ ደረጃ ለመጀመር የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽንስ ባለስልጣን ጊዜያዊ የስፔክትረም ፈቃድ በመስጠት የተባበረን ሲሆን ኔትዎርኩን የዘረጋው የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ አጋራችን ሁዋዌ ቴክኖሎጂስ ነው፡፡

5ጂ ኔትዎርክ ደንበኞቻችን ምርጥ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የላቀ ተሞክሮ እንዲኖራቸው የሚያደርግ፣ የኢንተርፕራይዝ ደንበኞቻችን ደግሞ የአሰራር ቅልጥፍናቸውንና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳቸው ይሆናል፡፡

ግንቦት 1 ቀን 2014

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives