ኩባንያችን የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረጉን ጉዞ መጠነ-ሰፊ ስራዎችን በማከናወን እየገፋበት የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደንበኞች የተለያዩ የግብር ክፍያዎችን ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ የሆነውን ቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ተጠቅመው በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሆነው የግብር ክፍያቸውን ያለምንም ውጣውረድ በኦንላይን አገልግሎት እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል፡፡

ይህ በዛሬው ዕለት የተደረገው የአጋርነት ስምምነት በዋናነት ለገቢዎች ሚኒስቴር የገቢ ግብርን እና የግል ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ፣ የፌደራል ታክስ ክፍያዎችን በወቅቱ ለመሰብሰብ እና ለማሳለጥ ከሚኖረው ጉልህ ሚና ባሻገር በየጊዜው እያደገ የመጣውን የግብር ከፋዮች የክፍያ አማራጭ ፍላጎት ቀላል እና አስተማማኝ በማድረግ የቴሌብር ተጠቃሚዎች ከግል ወይም ከድርጅት የቴሌብር አካውንታቸው በቴሌብር የሞባይል መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር *127# በመጠቀም የግብር ክፍያቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ ለመክፈል የሚያስችላቸው ሲሆን፣ በቴሌብር ግብይት የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ከሚፈጽሟቸው ግብይቶች ከሰበስቡት ገንዘብ ላይ ለግብር ክፍያ በቀጥታ መክፈል የሚችሉበት ሁኔታም ተመቻችቶላቸዋል፡፡

በተጨማሪም በቴሌብር እና በገቢዎች ሚኒስቴር የሲስተም ትስስር አማካኝነት የደንበኞች የክፍያ ሁኔታን ወቅታዊ ለማድረግ (update)፣ ክፍያው እንደተፈጸመ ለደንበኛው የክፍያ ክሊራንስ እና ደረሰኝ በወቅቱ ለመስጠት፣ በገቢዎች ሚኒስቴር ሰርቨር ላይ መረጃን ወቅታዊ (update) በማድረግ በመዘግየት ምክንያት በግብር ከፋዩ ላይ የሚደርሰውን ቅጣት ለማስቀረት እና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት የሚኒስቴር መ/ቤቱ ደንበኞች ወደ www.mor.gov.et. በመግባት እና የኤሌክትሮኒክ ታክስ አገልግሎት የሚለውን በመመምረጥ፣ አስፈላጊውን ሂደት ሲጨርሱ ከገቢዎች ሚኒስቴር የሚሰጣቸውን የሰነድ ቁጥር (doucument number) በመጠቀም በቀላሉ ክፍያቸውን በቴሌብር አፕሊኬሽን ወይም በአጭር ቁጥር *127# በመጠቀም የግብር ክፍያ የሚለውን በመምረጥ ክፍያቸውን በመፈጸም የክፍያ ደረሰኝ ወዲያውኑ በኢ-ሜል አድራሻቸው ማግኘት ይችላሉ፡፡

ኩባንያችን በቅርቡ #ቴሌብር መላ – የግለሰብ ደንበኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ወኪሎች የአነስተኛ ብድር አገልግሎት በቴሌብር አካውንታቸው አማካኝነት የሚያገኙበት፣ #ቴሌብር እንደኪሴ የቴሌብር ደንበኞች በአካውንታቸው ላይ ያላቸው ቀሪ የሂሳብ መጠን በቂ ባልሆነበት ጊዜ የሚጠቀሙት እንዲሁም #ቴሌብር ሳንዱቅደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ መጠን የሚታሰብባቸው የቁጠባ ዓይነቶችን የሚጠቀሙበት ሲሆን አገልግሎቶቹን ከዳሸን ባንክ ጋር በአጋርነት ፋይናንስ ለሁሉም በሚል መርህ በማቅረብ የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በቴሌብር አገልግሎት እስከ አሁን ድረስ 28.2 ሚሊዮን ደንበኞችን፣ 112 ዋና ወኪሎችን (Master Agents)፣ 98.8 ሺህ ወኪሎች እና 25.5 ሺህ ነጋዴዎች /Merchants/ ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ በ615 የአገልግሎት ማዕከሎቻችን አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን፡፡ እንዲሁም በቴሌብር ከ263 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት (Transaction Value) የተከናወነ ሲሆን፣ ከ18 ባንኮች ጋር ትስስር (Integration) በማድረግ ከባንክ ወደ ቴሌብር፣ ከ15 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ የገንዘብ ዝውውር እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩልም ከበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የክፍያ ስርአታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ደንበኞቻቸው እፎይታን አጎናጽፏል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርዓት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው እንዲፈጽሙ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡

ጥር 25 ቀን 2015 .

ኢትዮ ቴሌኮ

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives