ኩባንያችን በሚሰጠው አገልግሎት የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ለመደገፍና የአስቻይነት ሚናውን ለመጫወት በየጊዜው አዳዲስ አገልግሎቶችን በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኮኔክቲቪቲ ባሻገር ያሉ የዲጂታል ሶሉሽንስ ላይ ትኩረት በማደረግ ግለሰቦችና ድርጅቶች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ቢዝነሶቻቸውን የበለጠ ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን አገልግሎቱን ለማስፋፋትና ለማዘመን ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረቶችና ሥራዎች ባሻገር ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችና ሥራ ፈጠራን ለማበረታታት ያለመ ኢትዮቴል ኢኖቬሽን ፕሮግራም የሚል ኢኒሼቲቭ ቀርጾ በተለይም የሀገራችን ጀማሪ የዲጂታል እና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ቢዝነሶችንና ባለሙያዎችን የሚያበረታታና የሚያግዝ ፕሮግራሙን ዛሬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ አስጀመረ፡፡

ኢትዮቴል ኢኖቬሽን ፕሮግራም ማንኛውም ጀማሪ ቢዝነስ ሊገጥመው የሚችለውን ወደ ገበያ ዘልቆ የመግባት፣ ደንበኛን የመሳብና የመያዝ እንዲሁም የባለሙያና የገንዘብ እጥረት ተግዳሮቶችን በመፍታት ጅምር የቢዝነስ ሀሳቦችን ወደ ስራ እንዲገቡ ለማብቃት፣ ለማበረታታትና የተጀመሩ ቢዝነሶችን ለማሳደግ ታልሞ በሶስት ምዕራፎች ተከፍሎ የተቀረጸ ፕሮግራም ሲሆን መሰረታዊ ዓላማውም የሀገር በቀል ችግር-ፈቺ ተግባራትን ለማበረታታት፣ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች ለመሳብ፣ ለማነሳሳትና አዳዲስ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ለማገዝ፣ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የፈጠራ ሀሳቦችን እንዲያጎለብቱና አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ወደ ገበያ እንዲያመጡ ለመደገፍ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያ፣ ለቴክኖሎጂ አጋሮች እና ለዘርፉ ተዋንያን የትብብር ከባቢያዊ ሁኔታን በመፍጠር ጥረታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን የማድረግ ጉዞውን ማጠናከር ነው፡፡

ፕሮግራሙ ጀማሪ ቢዝነሶችን የሚያግዝበት የድጋፍ እና ገቢ የመፍጠሪያ ጥቅሎች (Support and Commercialization) ሲኖሩት የድጋፍ ጥቅሉ፣ አሸናፊዎቹ የቴሌኮም ሀብት አቅርቦት፣ የገንዘብና የማቴሪያል፣ የማርኬቲንግ፣ የተለያዩ ስልጠናዎችና የልምድ ልውውጥ ድጋፎች የሚያገኙበት ሲሆን ገቢ የመፍጠሪያ ጥቅሉ የዘርፉን ስነ-ምህዳር በመገንባት ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ወደ ገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንዲሁም የሽርክና ንግድ (Joint Venture) አማራጮች የሚያገኙበትን ሁኔታዎች ያመቻቻል፡፡

ኩባንያችን ዛሬ ላይ ያስጀመረው ከየካቲት 03 እስከ ሚያዚያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም የሚተገበረውን የፕሮግራሙን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን የሚያተኩረው በጀማሪ የክላውድና የሞባይል ፋይናንስ ቢዝነሶች ላይ ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ ተወዳድረው የሚያሸንፉ 100 ተወዳዳሪዎች ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶችና እጥረቶችን የሚፈቱበትና ንግዳቸውን በስኬት የሚያስቀጥሉበት እንዲሁም ለተግባር የቀረቡ ጅምር የፋይናንስና ክላውድ ቢዝነስ ሀሳቦች በፍጥነት ወደ ስራ የሚገቡበት (accelerator) ፕሮግራም ነው፡፡

በዚህ ዙር ተወዳድረው የሚመረጡት 100 አሸናፊዎች ሙያዊ ምክርን ጨምሮ የባለሙያ፣ የገንዘብ እና ማቴሪያል አቅርቦቶችን የሚያገኙ ሲሆን የኩባንያችን አጋር ከሆነው ከሁዋዌ ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር ወደ ቻይና ሀገር ተጉዘው አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመመልከት ልምድ የሚካፈሉበትንም እድል ያመቻቻል፡፡

ኩባንያችን በመቀጠል ከመጋቢት 11 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ሁለተኛውን የፕሮግራሙ ምዕራፍ የሚተገብር ሲሆን ከፋይናንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ባለፈ ዲጀታል ይዘቶች፣ አገልግሎቶች፣ ትንታኔዎች እና መተግበሪያዎች ላይ የሚሰሩ 150 ጀማሪ ቢዝነሶች ላይ የሚያተኩር ይሆናል፡፡

በነሐሴ ወር የሚጀምረው ሶስተኛው የፕሮግራሙ ምዕራፍ ተቋማዊ በሆነ አደረጃጀት በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ ያሉ የቢዝነስ ሀሳቦች የሚጎለብቱበትና ስራ ላይ መዋል እንዲችሉ የሚያደርግ የኢትዮ ቴሌኮም የቴክኖሎጂ ማብቂያ ማዕከል (techhub) እንዲሁም ከምዕራፍ አንድ እና ሁለት የተወሰዱ መልካም ተሞክሮዎችን በመጠቀም ወደ ጥናት፣ ምርምር እና ልማት (R&D) ደረጃ በማሳደግ የሚተገበር ይሆናል፡፡

በኢትዮቴል ኢኖቬሽን ፕሮግራም በመጀመሪያው ምዕራፍ መወዳደር የሚፈልጉ የክላውድ እና የሞባይል ፋይናንስ ጀማሪ ቢዝነሶች በኢሜይል አድራሻችን ethiotelinnovation@ethiotelecom.et ላይ ከየካቲት 03 እስከ መጋቢት 03 ቀን 2015 ዓ.ም ማመልከት የሚችሉ መሆኑን እየገለጽን ለተወዳዳሪዎች በሙሉ መልካም እድልን እንመኛለን፡፡

በቀጣይም ኩባንያችን ፕሮግራሙን ከመቅረጽ እና ከማዘጋጀት በተጨማሪ እንደ ዘርፉ ስነምህዳር ቁልፍ ተዋናይ ከአጋሮች ጋር በመተባበር ተወዳዳሪ የሆነ አገርአቀፍ አቅምን ለመገንባት፣ ፈጠራ እና ቅንጅታዊ ስራን ለማጎልበት፣ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች የተለያዩ ፋሲሊቲዎችን በማቅረብ፣ የስልጠና እና ሌሎች አቅም ማጎልበቻ ድጋፎችን በማድረግ፣ በሀገራችን የዲጂታል ስነምህዳር ዕድገት ላይ መልካም አሻራ በማሳረፍ እና የማህበረሰቡ ችግሮችን የሚቀርፉ ምርትና አገልግሎቶችን በማልማት በአህጉሪቱ የጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ የስበት ማዕከል ለማድረግ በቁርጠኝነት የሚሰራ ይሆናል፡፡

ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives