ኢትዮ ቴሌኮም በመላው የሀገራችን ክፍሎች በተመረጡ ት/ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች የመማሪያ ደብተር እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ተቋማት የገንዘብ ድጋፎችን አደረገ!

ኩባንያችን የኢትዮጵያን ዲጂታል መፃዒ ዕድል በመቅረፅና በአፍሪካ ዘላቂና አካታች ዕድገትን ለማስፋፋት ያለውን ሚና አዲስ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ የሚያስችል “ቀጣዩ አድማስ” ስትራቴጂን በስራ ላይ በማዋል በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህም ጎን ለጎን ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፈ ብዙ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የበኩሉን መልካም አሻራ እያሳረፈ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን “ለነገ ተስፋዎች” የሚል መርሃ ግብር በመቅረጽ እና በየዓመቱ ተግባራዊ በማድረግ ተቋማዊ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በዘላቂነት እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን፣ በዘንድሮው ለነገ ተስፋዎች መርሃ ግብሩም በመላው የሀገራችን ክፍሎች ለሚገኙ እና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን መደገፍን ታሳቢ ያደረገ የመማሪያ ደብተር ድጋፎችን አድርጓል፡፡

በዚህም መሰረት ለ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን “ለነገ ተስፋዎች” በሚል መርህ ባዘጋጀው የመማሪያ ደብተር መርሃ ግብር በአዲስ አበባ እና በሁሉም የኢትዮ ቴሌኮም ሪጅኖች ለሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ 80ሺ ተማሪዎች ከ98.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን ደብተር ድጋፍ መርሃ ግብር አስጀምሯል፡፡

ኩባንያችን የዘንድሮን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት “ለነገ ተስፋዎች” በሚል መርሃ ግብር በመላው የሀገራችን ክፍሎች ለሚገኙ እና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ታሳቢ ያደረገ የመማሪያ ደብተር ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በአጠቃላይ እስከ አሁን በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ 373 ሺህ ተማሪዎች ከ320.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም “በጎነት” የሚል መርሃ ግብር በመቅረጽ እና በየዓመቱ ተግባራዊ በማድረግ ተቋማዊ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በዘላቂነት እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን፣ በዘንድሮው የበጎነት መርሃ ግብሩም በመላው የሀገራችን ክፍሎች ለሚገኙ 39 የበጎ አድራጎት ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዚህም መሰረት በእነዚህ የበጎ አድራጎት ተቋማት ለሚገኙ 13,674 አረጋዊያን፣ ህጻናት፣ እናቶች፣ አቅመደካሞች እና አካል ጉዳተኞች ከ47.8 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በተመሳሳይ የበጎ አድራጎት መርሃ ግብሮች በመላው የሀገራችን ክፍሎች በሚገኙ 117 የበጎ አድራጎት ተቋማት ለሚገኙ 32,700 አረጋዊያን፣ ህጻናት፣ እናቶች፣ አቅመደካሞች እና አካል ጉዳተኞች ከ78.8 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በተመሳሳይ ቀንም የኩባንያችን የማኅበራዊ ኃላፊነታችን አካል የሆነው የደም ልገሳ መርሃግብር በማዘጋጀትና በጎነት ለሰብዓዊነት!በሚል መርህ ከብሔራዊ የደም ባንክ ጋር በመተባበር በተቋሙ ዋና መ/ቤት፣ በዞን እና በሪጅን ጽ/ቤቶች በአጠቃላይ በ19 ቦታዎች የኩባንያችን በጎ ፈቃደኛ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ደም በመለገስ የወገኖቻቸውን ውድ ሕይወት የሚታደጉበት መርሃግብር አዘጋጅቶ የወገን አለኝታነቱን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡ 

ኩባንያችን በደንበኞቹ የአኗኗር ዘይቤ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የዲጂታል አገልግሎቶችን፣ ዘመኑ የደረሰበትን የቴሌኮም አገልግሎቶች ከመተግበር እና የአሰራር ሥርዓቶችን ከመዘርጋት እንዲሁም አዳዲስ የቴሌኮም ምርት እና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባሻገር ለህብረተሰባችን አስፈላጊ በሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሁሉ ድጋፎችን በማድረግ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ሀገራዊ አለኝታነቱን እያረጋገጠ ይቀጥላል፡፡

 

                                                         ኢትዮ ቴሌኮም

                                                   ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives