መንግስት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በርካታ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ የጋራ እድገትን ለማረጋገጥ ከወሰዳቸው ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች መካከል የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ በማቋቋም ዜጎች በመንግስት ልማት ድርጅቶች ውስጥ የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ማድረግ ሲሆን ለዚህም ያወጣቸውን የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿን ለ130 ዓመታት በትጋት ሲያገለግል የቆየው የኢትዮ ቴሌኮምን በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት ከልማት ድርጅትነት ወደ አክሲዮን ማኀበርነት ለመቀየር የሚያስችሉ ተግባራት በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን መመሪያ መሰረት ሲከናወን ቆይቷል፡፡
በዚህም መሰረት የኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ሽያጭ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ በማስጀመር የአክሲዮን ሽያጩን እስከ ታኅሣስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ማከናወኑ ይታወሳል፡፡ በመቀጠልም ውጤቱን ለሚመለከተው የመንግስት አካል እና ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በማቅረብ እና በመገምገም በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የሽያጭ ቀነ-ገደቡን በማራዘም እስከ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ማለትም ለ121 ቀናት (የዕረፍትና የበዓል ቀናትን ጨምሮ) በዲጂታል መንገድ ሲከናወን መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በዚህም መሰረት የተከናወነው የኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ ውጤት በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አካላት ተገምግሞ እንዲሁም በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን (Ethiopian Capital Market Authority) ታይቶ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
በመሆኑም በዛሬው ዕለት ኩባንያችን በመላ ሀገሪቱ የሚኖሩ ዜጎችን በማሳተፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ47 ሺህ በላይ ዜጎችን በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችል ወሳኝ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ መድረሳችንን ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም የባለቤትነት ድርሻ ሽያጭ በዋናነት መንግስት አካታች እና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገትን ለማፋጠን በተለይም በርካታ ዜጎች በሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት በስፋት በማሳተፍ ጠንካራ የካፒታል ገበያ ስርዓት እንዲኖር በማቀድ የአክሲዮን ሽያጩ በዲጂታል መንገድ ፍትሃዊ፣ ግልጽ እና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በስፋት እና በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ በመቻሉ የዲጂታል ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ የበኩሉን ሚና ለመጫወት ተችሏል፡፡
በአክሲዮን ሽያጩ ወቅት በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ተቋማት እና ውጪ የሚኖሩ ባለሀብቶች ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም በቅድሚያ በሀገር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊነት ለማረጋገጥ ታሳቢ በማድረግ ለዜጎች ዝቅተኛ መሸጫ ዋጋ በማስቀመጥ ሲከናወን ቆይቷል፡፡ በተለይም መንግስት የሀገሪቱን ግዙፍ እና አስተማማኝ የሆነውን ኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ለሽያጭ በማቅረብ ዜጎች በመተማመን ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማስቻል በቀጣይም አክሲዮናቸውን ማንቀሳቀስ ወደ ሚችሉበት የሰነደ መዋዕለ ንዋይ (Stock Market) ልምምድ በመግባት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካለ ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡
በዚህም መሰረት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች በስፋት በመሳተፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ ከ47,377 ዜጎች ከ10.7 ሚሊዮን የኢትዮ ቴሌኮም መደበኛ አክሲዮኖች የግዢ በዲጂታል መንገድ በማከናወን ብር 3.2 ቢሊየን የሚጠጋ ሀብት ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡ በቀጣይ ከእያንዳንዱ አመልካች ጋር በሚኖር የቀጥታ ግንኙነት ያልተሟሉ መረጃዎችን የማሟላት ተግባር በማከናወን የተቋማችን ባለቤት የሚሆኑበት ማረጋገጫ የመስጠት ስራ ይከናወናል፡፡
የተሸጡ አክሲዮኖች ድልድል በካፒታል ገበያ ባለስልጣን የማጽደቅ ሂደት ከተከናወነ በኋላ ውጤቱን በይፋ የምናሳውቅ ሲሆን የተደለደሉ አክሲዮኖች በማዕከላዊ የሰነዶች ሙዓለ ነዋዮች ግምጃ ቤት (Central Securities Depository) ይመዘገባሉ፤ ይህም ሂደት እስኪጠናቀቅ ኩባንያችን መረጃዎችን ለባለአክሲዮኖች ደረጃ በደረጃ የሚሰጥ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
የኩባንያችን ባለድርሻ የሚሆኑ ባለአክስዮኖች በቀጣይ በኢትዮጵያ የሰነዶች ሙዓለ ነዋዮች ገበያ አክስዮናቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ ተቋማችንን በገበያው እንዲመዘገብ ቀጣይ ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን ቀሪ አክስዮኖች በተመለከተ ዝርዝር የሽያጭ ሂደቱን በቀጣይ የምናሳውቅ መሆኑን እየገለጽን አሁን አክሲዮን የገዙ ባለድርሻዎችን መብት ባስጠበቀ መልኩ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ይሁንታ በማግኘት በድጋሚ ለገበያ የሚቀርቡ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም.
ኢትዮ ቴሌኮም