ኢትዮ ቴሌኮም እና ሲንቄ ባንክ በአጋርነት በቴሌብር የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን እና የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎትን አስጀመሩ!

በሃገራችን የቴሌኮም እና ዲጂታል አገልግሎቶችን በሰፊው ተደራሽ በማድረግ ታላቅ ሀገርና ሕዝብ በማገልገል ላይ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በተለይም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር መሪ የዲጂታል ሶሉሽን አቅራቢ በመሆን የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የቴክኖሎጂ አቅምን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የፋይናንስ ዘርፉ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝና ስነ ምህዳሩ እንዲጎለብት፣ እንዲሁም ተደራሽነት እና አካታችነቱ እንዲያድግ የአስቻይነት ሚናውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

በተለይም ከ52.5 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉትን እና የተቋማትን የቢዝነስ እንቅስቃሴ በማዘመንና የማህበረሰባችንን የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ እያቀለለ በሚገኘው ቴሌብር አማካኝነት መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ላልሆነው የማህበረሰብ ክፍል ጭምር ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸውን እንዲሁም ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አገልግሎቶችን ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በአጋርነት በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም በሃገራችን ሁለንተናዊ የልማትና የዕድገት ጉዞ ውስጥ አስቻይ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት ኢትዮ ቴሌኮም እና ሲንቄ ባንክ ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣንና ቀላል በሆነ አማራጭ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በቴሌብር እንዲያገኙ እንዲሁም የቴሌኮምና ዲጂታል አገልግሎቶችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ሲም ካርድን ያካተቱ የዲቫይስ ፋይናንሲንግ ለማግኘት የሚያስችሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን በአጋርነት በይፋ አስጀምረዋል፡፡

የአጋርነት ስምምነቱ የሚያካትታቸው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች

የቁጠባ አገልግሎት

  • ደንበኞች በቴሌብር ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ ምጣኔ የሚታሰብባቸው የተንቀሳቃሽ እና የጊዜ ገደብ ተቀማጭ የቁጠባ አገልግሎቶችን በመጠቀም፣ በየትኛውም ቦታ ሆነው ማንኛውንም መጠን ያለው ገንዘብ የሚቆጥቡበት አማራጭ ነው።

እንደራስ አነስተኛ ብድር

  • ግለሰቦች፣ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ወይም በንግድ ሥራ ለተሰማሩ መካከለኛ ተቋማትበቴሌብር በሚያደርጉት የግብይት መጠን ላይ ተመስርቶ እስከ ብር 30,000 ድረስ የአነስተኛ ብድር አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል ሲሆን፣ በዚህም ከአምስት ቀን ጀምሮ እስከ 45 ቀን የሚቆይ ብድር እንዲያገኙ ያስችላል፡፡

የደመወዝ ብድር

  • የኢትዮ ቴሌኮም እናየሲንቄ ባንክ ሰራተኞችን ጨምሮ ወርሃዊ ደመወዛቸው በቴሌብር እና በሲንቄ ባንክ ለሚከፈላቸው የግል እና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ በ14 ወራት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የአምስት ወር ደሞዝ ክፍያ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል አማራጭ ነው። ይህም በዓመት እስከ 1.3 ቢሊየን ብር የሚደርስ የብድር አቅርቦት ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የዲጂታል ፋይናንስ አቅርቦት ፋይዳ

  • የፋይናንስ አገልግሎት በበቂ ሁኔታባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የአርሶ አደር እና አርብቶ አደር የማህበረሰብ ክፍሎች እና አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ችግር ለመቅረፍ ይረዳል፣
  • የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን በማስፋፋት ረገድ ባህልና ቋንቋን መሰረት ባደረጉ ምቹ አማራጮች አማካኝነት በቀላል መንገድ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል።
  • በገጠርም ሆነ በከተማ ለሚኖሩ ዜጎች የፋይናንስ አገልግሎቶችንበቀጥታ በዲጂታል አማራጭ ካሉበት ሆነው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የፋይናንስ ተደራሽነት ክፍተትን ለማጥበብ ያስችላል፤
  • በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ደንበኞችያለዋስትና (Non-Collateral) የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።

የብድር አገልግሎት ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች

ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች/ነጋዴዎችና ወኪሎች አነስተኛ ንግድ/ቢዝነስ እንዲጀምሩ ወይም እንዲያስፋፉ በዋስትና እና ያለዋስትና እስከ ብር 1.2 ሚሊየን የሚደርስ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን በዚህ አገልግሎት በዓመት እስከ ብር 10 ቢሊየን ለደንበኞች ለማቅረብ ታቅዷል፡፡ በዚህም፡-

ያለዋስትናጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የንግድ ስራቸውን እንዲያሳድጉና ተጨማሪ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ያስችላል፤

  • እስከ 30 ሺህ ብር የሚደርስ የአንድ ወርየብድር ጊዜ ያለው አቅርቦት፤
  • እስከ 70 ሺህ ብር የሚደርስየሁለት ወር የክፍያ ጊዜ ያለው የብድር አቅርቦት እንዲሁም
  • እስከ 130 ሺህ ብርየሚደርስ የአምስት ወር የክፍያ ጊዜ ያለው የብድር አቅርቦት። እነዚህ ሁሉ ያለዋስትና የሚገኙ ናቸው።

በሚያቀርቡት ዋስትና፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች/ነጋዴዎችና ወኪሎች የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ለማሻሻል፡-

  • የሶስት ወር የክፍያ ጊዜ ያለው የ300 ሺህ ብርብድር፤
  • የሰባት ወር የክፍያ ጊዜ ያለው የ700 ሺህ ብርብድር፤ እንዲሁም
  • የዘጠኝ ወር የክፍያ ጊዜ ያለው የ2 ሚሊዮን ብርብድር ናቸው።

የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎት (Device Financing)

ኩባንያችን የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚያፋጥን ግዙፍ የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመላ ሀገሪቱ በመገንባት ላይ ሲሆን፣ ይህ መሰረተ ልማት አዳዲስ የዲጂታል እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መደላድል ፈጥሯል። ዜጎች የተዘረጋውን መሠረተ ልማት በመጠቀም የዲጂታል እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል፣ በዲቫይስ ፋይናንሲንግ የስማርት ስልክ ስርጸትን በመጨመር የዲጂታል ዕውቀትን (literacy) ለማሳደግ ስትራቴጂ ነድፎ በመስራት ላይ ይገኛል። ይህ የዲጂታል አገልግሎቶች ተደራሽነት እና አካታችነትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችል፣ ሲም ካርድን ጨምሮ የስማርት ዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎት በዛሬ ዕለት በኢትዮ ቴሌኮም እና በሲንቄ ባንክ መካከል ይፋ ከተደረጉ አገልግሎቶች መካከል አንዱ ነው።

በዚህ መሰረት ኩባንያችን በአመት እስከ 2 ሚሊየን የሚደርሱ የስማርት ስልኮችን በተለያዩ የረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጮች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ለማቅረብ ከተለያዩ የፋይናንስ አጋሮቻችን ጋር በመስራት ላይ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በዛሬው ዕለት ከሲንቄ ባንክ ጋር እስከ 4 ቢሊየን ብር የዲቫይስ ፋይናንሲንግ ስምምነት ላይ በመድረስ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረናል።

አገልግሎቱ በተለይም በግብርና የተሰማሩ ዜጎችን ጨምሮ፣ ሰራተኞች፣ ነጋዴዎችና ወኪሎች የተለያዩ የቴሌኮም መገልገያ መሳሪያዎችን (devices) በረጅም ጊዜ ክፍያ (installment) ከሲም ካርድ ጋር እንዲያገኙ ያስችላል።

የዲቫይስ ፋይናንሲንግ ለአካታችነት ያለው አስተዋጽኦ

የዲቫይስ ፋይናንሲንግ፣ በስማርት ስልኮች ዋጋ ከፍተኛ መሆን ምክንያት የዲጂታል እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማግኘት ላልቻሉ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ እና በረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጮች ስማርት ስልክ እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባሻገር፣ የብሔራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂንና የስማርት ስልኮችን ስርፀት ለማሳደግ እንዲሁም የዲጂታል ክፍተትን ለማጥበብ  አይነተኛ ሚና ይኖረዋል። በተለይም አገልግሎቱ የፋይናንስ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ሳይሆን በቆየባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ የአርሶ እና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን አካታች እና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ኩባንያችን በቀጣይም ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን አጋርነት በይበልጥ በማጠናከር፣ የማህበረሰባችንን የአኗኗር ዘይቤ ሊያሻሽሉና ሊያሳድጉ በሚችሉ የተለያዩ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን እና ሁሉን አካታች የኢኮኖሚ እድገትን እንዲሁም የኢትዮጵያን የዲጂታልና ፋይናንስ አካታችነት ጉዞን የሚያፋጥኑ ፈጠራ የታከለባቸው አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያን ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠን የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

 

ሚያዚያ 18 ቀን 2017 .

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives