ኩባንያችን ከዩጋንዳ ከፍተኛ ልዑክ ጋር በዲጂታል ዘርፍ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ውይይት አደረገ
በካምፓላ ከተማና ሜትሮፖሊታን ጉዳዮች ሚኒስትር ክብርት ሀጃት ሚንሳ ካባንዳ የሚመራ ከፍተኛ ልዑክ በኩባንያችን የጉብኝት እና ስትራቴጂክ ውይይት አካሄደ።
መርሃ ግብሩ የኩባንያችንን የተለያዩ ስማርት መፍትሔዎች እና አካታች ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የምናደርገውን ጥረት ለማሳየት ያስቻለ ነበር።
ልዑካኑ ስማርት ሲቲ፣ ስማርት ግብርና፣ ስማርት ማዕድን፣ ስማርት ትምህርት እንዲሁም ሌሎች ፈጠራዎችን የጎበኙ ሲሆን ከኩባንያችን ጋር የሚደረግ አጋርነት ሀገራዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን ጽኑ እምነት አረጋግጠዋል።
ልዑካኑ በኩባንያችን ኤክስፒሪየንስ ማዕከል፣ የመረጃ ማዕከል፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያ እንዲሁም የስማርት ሲቲ ፕሮጀክቶችን የጎበኙ ሲሆን በመቀጠልም በዋና መሥሪያ ቤታችን ውይይት አድርገዋል።
የኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ኩባንያችን ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባሻገር ዜጎችን፣ የመንግሥት ተቋማትንና የግል ድርጅቶችን ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ለዘላቂ እድገት መመዝገብ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ለመቅረጽ በጋራ የምንሠራበት ጊዜ መሆኑን በማብራራት ተግዳሮቶችን ወደ ዕድሎች በመቀየር፣ የአህጉሪቱን የተፈጥሮ በረከት በመጠቀም፣ በዲጂታል የተገነባች አካታች እና ተወዳዳሪ አህጉርን ለመገንባት በጋራ መስራት እንዳለብን አጽንዖት ሰጥተዋል።
ውይይቱ የቴሌኮምና የዲጂታል መሠረተ ልማትን፣ የዲጂታል ክፍያ፣ የእውቀት ሽግግርን ጨምሮ በሌሎችም የትብብር መስኮች ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህም ለዩጋንዳ የ2040 ራዕይ እንዲሁም የካምፓላን ስማርት ሲቲ እውን ለማድረግ እንደሚረዳ ተገልጿል።
እትዮ ቴሌኮም
ነሀሴ 6- 2017