ኩባንያችን “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” የተሰኘ አዲስ የሶስት አመት ስትራቴጂ እና የ2018 በጀት ዓመት የቢዝነስ እቅድ ይፋ አደረገ!

ይህ በሳይንስ ሙዚየም ለህዝብ ይፋ የተደረገ የኩባንያችን የቀጣዩ ሦስት ዓመታት የስትራቴጂ እቅድ (እ.ኤ.አ ከ2024/25 እስከ 2027/28 እና የ2018 በጀት ዓመት) ዓመታዊ የቢዝነስ እቅድ ነው፡፡

ኩባንያችን እጅግ ተለዋዋጭና ተወዳዳሪ በሆነ የቢዝነስ ከባቢ ውስጥ ተግባራዊ ያደረገው የLEAD የዕድገት ስትራቴጂ (2022-2025) ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት፣ ለፈተና የማይበገር አቅም በመገንባትና በገበያው የመሪነት ሚናውን በማጎልበት በስኬት በማጠናቀቁ የሀገራችን የዲጂታል ምሰሶ ሆኖ እንዲቀጥልና ጠንካራ መሰረት እንዲጥል አስችሎታል።

ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እና ከሌሎች ሀገራዊ የልማት ዕቅዶች ጋር በተጣጣመ መልኩ የተከናወነው የኩባንያችን የሪፎርም ጉዞ፣ በLEAD ስትራቴጂ አማካኝነት ባለፉት ሶስት ዓመታት አስደናቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል። እነዚህ ውጤቶች፣ የቴሌኮም እና የዲጂታል አገልግሎቶች አካታች ሀገራዊ ልማትን በማፋጠን ረገድ ያላቸውን ወሳኝ ሚና ከማረጋገጣቸው ባሻገር፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለንን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያሉ።

ኩባንያችን፣ ከLEAD የዕድገት ስትራቴጂው ባካበተው ልምድና በሀገራዊ ዳሰሳ ጥናቶች ላይ በመመስረት፣ የኢትዮጵያን ዲጂታል መፃዒ ዕድል ለመቅረፅና በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ ዕድገትን ለማስፋፋት ያለውን ሚና በአዲስ መልክ የሚተልመውን “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” (NEXT HORIZON፡ Digital & Beyond 2028 Strategy) የተሰኘ፣ ከቀጣይነት የላቀ፣ ኩባንያችን ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያን ዲጂታል ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ እና በአፍሪካ ዘላቂና አካታች ዕድገትን በማስፋፋት ያለውን ሚና አዲስ መልክ እንዲይዝ የሚያደርግ ስትራቴጂ ይፋ አድርጓል።

የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ ኢትዮ ቴሌኮምን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ፣ በቀጠናው ልዩ እና በዲጂታል የጎለበተ ኩባንያ ለማድረግ ያለመ ሲሆን ይህ ከመደበኛ ቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር ወደ ፕላትፎርሞች፣ ሥነ-ምህዳሮችና መፍትሄዎች በመግባት ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን በማፋጠን፣ በቀጠናውና በዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎችን ለመክፈት እና ኩባንያችንን በአፍሪካ እና ከዚያ ባሻገር ባሉ የቴክኖሎጂ እና ፈጠራ መሪዎች መካከል ለማስቀመጥ ያስችላል::

የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ እ.ኤ.አ ከሐምሌ 2025 እስከ ሰኔ 2028 ያለውን የሶስት ዓመት ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን የቴሌኮም ዘርፍ በፍጥነት እያደገና ተለዋዋጭ በመሆኑ ከወቅቱ ጋር በፍጥነት የሚራመድ ተቋም የመሆን ትልም በመንደፍ ዕቅዱ ቋሚ (Static) ሳይሆን በየወቅቱ በኢንዱስትሪው ላይ የሚታዩ እድገትና

ለውጦች እንዲሁም ከውድድር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንና የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ ‘deliberate’ እና ‘adaptive approach’ በመከተል የተዘጋጀ በመሆኑ ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች ሲለወጡ በድጋሚ ታይቶ እቅዱ በለውጡ መሰረት የሚሻሻል ይሆናል፡፡

ይህ ስትራቴጂ በአራት መርሆች ላይ የተመሰረተውን Balanced Scorecard የተባለውን ማዕቀፍ የሚከተል ነው። እነዚህም፡-

  • ፋይናንስ (Finance)
  • ደንበኛ (Customer)
  • የውስጥ አሰራር ስርዓት (Internal Business Process)
  • ትምህርት እና ዕድገት (Learning and Growth)

ይህ የተቀናጀ አቀራረብ የአሰራር ብቃትን፣ የደንበኛ ትኩረትን፣ የፋይናንስ ዘላቂነትን እና የሰራተኞችን ልማት በማጣመር የኢትዮ ቴሌኮምን የረጅም ጊዜ ራዕይ እውን ለማድረግ ያለመ ነው። በዚህም መሰረት ስትራቴጂያችን፣ ሰው-ተኮር እና ችግር-ፈቺ በሆኑ፣ ሰፊ የስራ እድል በሚፈጥሩ እንዲሁም ዘላቂ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴት በሚያስገኙ ተግባራት ላይ ያተኩራል። ከዚህም በተጨማሪ፣ አካታችና ፍትሃዊ የኮሙኒኬሽንና ዲጂታል አገልግሎቶች ተጠቃሚነትን የምናረጋግጥ ሲሆን፣ የአካባቢያችንን ዘላቂነት መጠበቅ የሁሉም ስራዎቻችን መሰረት ነው።

ስትራቴጂው ሲዘጋጅ የኩባንያችንን ተወዳዳሪነት እና አስተማማኝ እድገት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተቋሙ ላይ ፍላጎትና ተጽዕኖ ሊኖራቸው የሚችሉ የመንግስት የፖሊሲ ሰነዶችን፣ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት ፍላጎትና ተጽዕኖ (የደንበኞች፣ የሠራተኞች፣ የተቆጣጣሪ አካላት፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና የተለያዩ የመንግስት አካላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት) በተጨማሪም በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማሩ ሌሎች ተቋማት ያላቸውን የገበያ እንቅስቃሴና ልምድ፣ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ እድገት ዋና ዋና አዝማሚያዎችና የዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመተንተን፣ የተወዳዳሪ ኩባንያዎችን ስትራቴጂዎች እንዲሁም የኩባንያችን ውስጣዊ ጥንካሬና ውስንነቶችን በመለየት፣ ውጫዊ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶችን በመለየትና በመተንተን የተቋሙን ተጨባጭ አቅምና ለተወዳዳሪነት የሚያበቃውን ተግባራት በመቃኘት የተዘጋጀ እቅድ ነው፡፡

በስትራቴጂው ኩባንያችን ያለውን ጠንካራ ጎኖች ማለትም ያፈራቸውን ከ83 ሚሊዮን በላይ ደንበኞቹን፣ ሰፊ መሠረተ ልማቱን እና የ131 ዓመታት ልምድ ያለው ጠንካራ ብራንዱን በመጠቀም የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለመምራት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መገኘቱን፣ ከቴሌኮም ባሻገር ወደ ፊንቴክ፣ ክላውድ እና ስማርት ሲቲ በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ መስፋፋቱን እንዲሁም በመልካም ዕድሎች፣ የሀገራችን

የዲጂታል አጀንዳ፣ ወጣትና ቴክኖሎጂ-ተኮር የሆነው ህዝብ እንዲሁም እንደ 5G እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ታሳቢ ተደርገዋል።

በተጨማሪም በስትራቴጂያዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030፣ የብሔራዊ ባንክ ስትራቴጂ 2023-26፣ የብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ እና የAI ስትራቴጂዎች ሀገራችን ወደ ዲጂታል ቀዳሚ (Digital First) ኢኮኖሚ እያደረገች ያለው ሽግግር ኢትዮ ቴሌኮምን በመሠረተ ልማት፣ በፊንቴክ፣ እና በዲጂታል ሥነ ምህዳሮች ላይ ከፍ ያለ ሚና እንዲኖረው እንደሚያደርግ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ የቀጠናዊ ትስስር እና ዓለም አቀፍ የንግድ ለውጦች ከፍተኛ የዕድገት ዕድሎችን የሚከፍቱ ሲሆን፣ ነገር ግን የቅድመ ዝግጅት የቁጥጥር ቅንጅትን፣ ስትራቴጂካዊ አጋርነቶችን ማጎልበት እና ተለዋዋጭና ወቅቱን የዋጀ አመራርን የሚጠይቁ መሆኑን ከግምት አስገብቷል፡፡

የቴሌኮም ኢንዱስትሪው አዝማሚያ እንደሚያሳየው የዳታ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች የቴሌኮም ዕድገት ማዕከል ሆነው መቀጠላቸውን ሲሆን ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በዓለም ላይ ዝቅተኛው የግንኙነት (Connectivity) መጠን (ከ29% በታች) ያላቸው መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ይህም ከከፍተኛ የአጠቃቀም እና የሽፋን ክፍተቶች ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም የ4G ሽፋን ወደ 70.8% በማስፋፋት አስደናቂ እድገት ያሳየ ሲሆን ይህም በቀጠናው ገበያ ውስጥ ጠንካራ አቋም/ ቦታ/ እንዲኖረው አስችሎታል። ይህንን እድገት ለማስቀጠል፣ ዘላቂ የመሠረተ ልማት ማልማት፣ የታለሙ የዲጂታል አካታችነት ጥረቶች እና የአገር ውስጥ ይዘት አቅርቦቶች እንደ ቪዲዮ ስትሪሚንግ እና የኦንላይን ላይ ጨዋታዎችን ማጠናከር ተደራሽነትን ለመጨመር እና የዲጂታል ክፍተትን ለማጥበብ ወይም ለመዝጋት ወሳኝ ይሆናሉ።

በዚህ መሰረት በተሻሻለ ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች ላይ የተመሰረተው አዲሱ የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ በፈጠራ፣ አካታችነት፣ ፈተናን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ እና የወደፊት አዳዲስ እድሎችን ለመቅረጽ ያለመ ነው፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ራዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴት (Vision, Mission & Values)

የዚህ ስትራቴጂ ለውጥ ማዕከል የሆነው የተሻሻለው የድርጅታችን ማንነት ሲሆን እነዚህ መሠረታዊ የኩባንያችን ይዘትና ማንነት የሚገልጹ ወሳኝ ነጥቦች እንደሚከተለው ተገልጸዋል፡፡

ራዕይ፡

ለዘመነች እና የዲጂታል ልዕልናን ለተጎናጸፈች ኢትዮጵያ እና ባሻገር መሪ የለውጥ አንቀሳቃሽ ኃይል መሆን

Vision:

‘’To be the Leading Catalyst for a Thriving, Digitally Empowered Ethiopia and Beyond’’

ተልዕኮ፡ ህይወትን ማቅለል እና የኢትዮጵያን ዲጂታል ሽግግር እና ከዚህም ባሻገር አስተማማኝ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶችን፣ ፈጠራ ያላቸው የዲጂታል መፍትሄዎችን እና እንከን የለሽ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ ማህበረሰቦችን፣ የንግድ ድርጅቶችን እና ሀገራትን ከመሠረታዊ ግንኙነት ባሻገር ማብቃት

Mission:

simplifying Lives and accelerating Ethiopia’s Digital Transformation and beyond through delivering reliable communications, innovative digital solutions and seamless financial services that empower communities, businesses and nations far beyond connectivity.

እሴቶች፡

ሰው ተኮር፣ አብሮነት እና ትብብር፣ ቅንነት እና ታማኝነት፣ ፈጠራ፣ የላቀ ብቃት፣ ማህበራዊ ኃላፊነት የሚሰማው እና በጎ ተፅዕኖ መር

Values:

Human- centric, Togetherness and Collaboration, Integrity and Trust, Innovation, Excellence, Socially responsible and impact driven

ስትራቴጂካዊ መስኮች (Strategic Themes)

  1. ዲጂታልቀዳሚ፣ደንበኛተኮር የላቀ ተሞክሮ: የግለሰቦችን፣ የንግድድርጅቶችን እና ማህበረሰቦችንተለዋዋጭ ፍላጎቶች አስቀድሞበመገንዘብ እና ከሚጠበቀውበላይ በሆነ መልኩበግል የተበጀ፣ ተደራሽእና እንከን የለሽተሞክሮዎችን ማቅረብ።
  2. የቴክኖሎጂፈጠራ እና የዲጂታል መፍትሄዎች መሪነት፡ አዳዲስ የእድገት ዕድሎችን ለመክፈትእና ለወደፊት ዝግጁ የሆኑ የዲጂታል መፍትሄዎችን ለማቅረብ በክላውድ፣ በAI፣ በIoT፣ በ5G  እና በተቀናጀየፕላትፎርምሥነ-ምህዳርውስጥ ፈጠራን ማፋጠን።
  3. በAI-የጎለበተ እና በዲጂታል የሚመራ የኦፕሬሽን ልህቀት:ቅልጥፍናን ለመጨመር፣ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም ፈጣንና ብልህ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ አውቶሜሽንን፣ የተራቀቀ ትንታኔንና አስተዋይ ሲስተሞችን መጠቀም።
  4. ፈጠራ ያለው የቢዝነስ ብዝሃነት እና ዘላቂ የእሴት ፈጠራ:አካታች፣ ለውጥን የሚቋቋም እና ዘላቂነት ያለው የቢዝነስዕድገትን ለማረጋገጥ ወደአዳዲስ የኢንዱስትሪ ዘርፎች፣ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎች እና ከፍተኛእምቅ ወዳላቸው ገበያዎችመስፋፋት።
  5. የበቃ፣ ቅልጥፍና ያለው እና ለወደፊት ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል:በየጊዜው በሚለዋወጠው የቢዝነስእና የቴክኖሎጂ ሁኔታውስጥ የላቀ ብቃትእንዲኖራቸው ሰራተኞቻችንን በተራቀቁ የዲጂታል ክህሎቶች፣ የፈጠራ መሳሪያዎች እና የመላመድ ባህል ማስታጠቅ።
  6. ተአማኒ የንግድ ስም፣ ዓላማ መር ተፅዕኖ እና ዘላቂነት ያለው መጪ ጊዜ: የህዝብን አመኔታ ማጠናከር፣ ጥልቅ የባለድርሻ አካላት ትብብር መፍጠር፣እና ለአካባቢ ጥበቃእና ለበጎ የማህበራዊ ለውጥ ቁርጠኝነትን ማሳየት።

ስትራቴጂያዊ ግቦች (Strategic Goals)

  1. የደንበኛእርካታ እና ተሞክሮ ማላቅ
  2. የቢዝነስ ብዝሃነትን፣ አዲስ የእድገት ምንጭ እና ቀጠናዊ መስፋፋት
  3. የአሰራር ልህቀትን እና የወጪ ቅነሳን ማሳካት
  4. ከፍተኛ የEBITDA መጠን ማሳካት እና ማስቀጠል
  5. የሰራተኛን እርካታን ማሳደግ እና ቀልጣፋ፣ ከፍተኛ አፈጻጸም ያለው ቡድን መገንባት
  6. የገበያ መሪነት

ስትራቴጂያዊ ዓላማ (Startegic Objectives)

ይህ ስትራቴጂ የኩባንያችንን፣ የሀገራችንን እና ከዚያም ባሻገር ያለውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሚና ለማጠናከር ያለመ ሲሆን ትኩረቱን የደንበኞችን ተሞክሮ በማሻሻል፣ ኔትወርኮችን በማዘመን እና ዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋፋት፣ በአስተማማኝ የመረጃ ደህንነት፣ የገቢ ምንጮችን በማስፋፋት፣ የሰው ኃይልን በማጎልበት እና የአሰራር ብቃትን በማሳደግ፣ የመሪነት ቦታውን በማስጠበቅ፣ ቴሌብርን በማሳደግ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የሚጠቀሙ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት እና ዘላቂነት ባላቸው አጋርነቶችና በአካባቢያዊ እና ማህበራዊ ኃላፊነት ላይ ትኩረት በማድረግ ለደንበኞቹ፣ ለባለአክሲዮኖቹ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ዘላቂ እሴት መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም የ2025/26–2027/28 ስትራቴጂ የኩባንያውን ሚና ለኢትዮጵያ ዲጂታል ሽግግር እንደ አቀጣጣይ ለማጠናከር በጋራ የሚያግዙ አስራ ዘጠኝ ስትራቴጂካዊ ዓላማዎችን አስቀምጧል። ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች የደንበኞች ተሞክሮን ማሳደግ፣ ኔትወርኮችን ዘመናዊ ማድረግ እና የዲጂታል አገልግሎቶችን ማስፋፋት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ይህም እንከን የለሽ እና ግላዊ የሆነ የዲጂታል ጉዞን ማቅረብ፣ የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻል፣ የ4ጂ/5ጂ እና የፋይበር ኔትወርኮችን ማስፋፋት፣ እንዲሁም በጠንካራ የመረጃ ግላዊነት እና ደህንነት አሰራሮች የደንበኞችን እምነት ማረጋገጥን ያጠቃልላል። በእነዚህ ዘርፎች ላይ በማተኮር ኩባንያው ታማኝነትን ለማጠናከር፣ የንቁ ደንበኞች ቁጥሩን ለማሳደግ እና ተወዳዳሪነትን ለማግኘት ይጥራል።

ስትራቴጂው በቴክኖሎጂ አመራር፣ በብዝሃነት እና በኦፕሬሽናል ልህቀት ላይም ትኩረት ያደርጋል። ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌብርን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን በማሳደግ፣ ኢ-ኮሜርስ እና የዲጂታል አኗኗር አገልግሎቶችን በማሻሻል፣ እና ለድርጅቶች የተበጁ መፍትሄዎችን በማቅረብ ከግንኙነት ባሻገር ለመሄድ አቅዷል። በተመሳሳይ ጊዜ፣ በሰው ሰራሽ እውቀት (AI) የሚመሩ አውቶሜሽኖች፣ የዲጂታል የአሰራር ስርዓቶችን፣ የላቁ የአቅርቦት ሰንሰለቶች እና ዘመናዊ ትንተናዎች በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ወጪዎችን ለመቀነስ እና ቅልጥፍናን ለማሻሻል ይተጋል። እነዚህ ጥረቶች ዘላቂ እድገትና ትርፋማነትን ለማረጋገጥ ከዲሲፕሊን የፋይናንስ አስተዳደር፣ ብልህ የካፒታል ወጪ (CAPEX) አስተዳደር እና ንብረትን ወደ ገንዘብ መቀየር  (monetization) ጋርተጣምረዋል።

ስትራቴጂው የሰው ኃይልን፣ ሽርክናዎችን እና የዘላቂነትንአስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደርጋል።በዲጂታል የሰለጠነ እና ለወደፊት ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይልን መገንባት፣ በብቃት ላይ የተመሰረተ የድርጅታዊ ባህልን ማጎልበት እና የሰራተኞችን ተሳትፎ ማጠናከር የለውጡ ማዕከላዊ አንቀሳቃሾች ናቸው። የረጅም ጊዜ እምነትን ለመገንባት ለአካባቢ፣ ለማህበረሰብ እና ለተቋማዊ  የስነ ምግባራዊ መርሆች (ESG) እና ንቁ የማህበረሰብ ተሳትፎ ቁርጠኛ ነው። የስርዓተ-ምህዳር ሽርክናዎችን በማጠናከር፣ ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር በትብብር በመስራት እና ተገዢነትን በማክበር፣ ኩባንያችን የመቋቋም አቅምን ለማረጋገጥ፣ የገቢ ምንጮችን ለማስፋት እና ለደንበኞቹ፣ ለአክሲዮን ባለቤቶች እና ለሰፊው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዘላቂ እሴት ለማቅረብ ተዘጋጅቷል።

ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች (Strategic Priorities)

ኩባንያችን በቀጣዩ አድማስ- ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር ስትራቴጂው በርካታ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ወይም (Strategic Priorities) የለየ ሲሆን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች አስቀምጧቸዋል እነሱም፡- ዲጂታል ትራንስፎሜሽን፣ አካታችነትን እና አቅም ማጎልበትን፣ የደንበኞችን ተሞክሮ ማሻሻል፣ የቢዝነስ ብዝሃነት፣

ቀጠናዊ ተሳትፎ እና ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ማጠናከር፣ ብቃት ያለውና ለወደፊት ዝግጁ የሆነ በዲጂታል የጎለበተ ሰራተኛ እና ባህል መፍጠር የሚሉ ናቸው፡፡

አራቱ ዋና ዋና ክፍሎች በሚከተሉት ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ተከፍለዋል፦ በኔትወርክና ሲስተም ልህቀት ላይ መሪነትን ማስቀጠል፣ ዘመናዊና ለወደፊት ዝግጁ የሆነ የኔትዎርክና ሲስተም መሠረተ ልማት መገንባት፣ የኦፕሬሽን ልህቀት፣ ተገቢነት ያለው ኢንቨስትመንትና የሀብት አጠቃቀም፣ የኃይል ውጤታማነት እና አረንጓዴ መሰረተ ልማት፣ የፕላትፎርም ኢኮኖሚና በፈጠራ ላይ የተመሰረቱ የፊንቴክ መፍትሄዎች፣ በኢንተርፕራይዝና ዘርፍ መፍትሄዎች ላይ መሪነቱን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ መፍጠር፣ በምርምርና ልማት፣ በቴክኖሎጂ ትግበራና ለገበያ ማቅረብ ላይ ማተኮር፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ቢግ ዳታ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና የኦፕሬሽን አውቶሜሽን፣ ፈጠራ ያላቸው ምርቶች፣ አገልግሎቶች እና የደንበኛ መጠቀሚያ መሳሪያዎች ስርጸትን ማሳደግ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና የቴክኖሎጂ ሥነ-ምህዳር ትብብር ላይ መስራት፣ የገበያ መሪነትና የብራንድ መታመን፣ የቁጥጥር ደንቦችን ማክበርና ከባለድርሻ አካላት ጋር መተባበር፣ የሳይበር ደህንነትና የመረጃ ግላዊነት፣ ስትራቴጂያዊ አጋርነት እና የስነምህዳር ልማት፣ ለፈተና የማይበገር የፋይናንስ አቅም እና ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ፣ የዘላቂነት፣ የአካባቢ፣ ማህበራዊና አስተዳደር (ESG) ኃላፊነት ላይ የተመሰረተ ዕድገት ማምጣት የሚሉ ናቸው። እነዚህ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የአፈጻጸም፣ የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች፣ የሀብት ማሰባሰብ እና የአፈጻጸም ክትትልን የሚመሩ ይሆናል፡፡

የቀጣዩ አድማስ (NEXT HORIZON) ሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ኢኒሼቲቮች

የኢትዮ ቴሌኮም የ2024/25–2027/28 ስትራቴጂያዊ ዕቅዶች በመሠረተ ልማት እና በዲጂታል መፍትሄዎች አመራር ላይ ያተኮሩ ናቸው። ዕቅዱ የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ ሽፋን ወደ 85 በመቶ በማሳደግ፣ በ550 አዳዲስ ከተሞች 4ጂ በመዘርጋት እንዲሁም 322 የገጠር ጣቢያዎችን ጨምሮ 1,228 አዳዲስ የሞባይል ሳይቶችን በመገንባት የሀገር አቀፍ ግንኙነትን ከፍ ለማድረግ ቅድሚያ ይሰጣል። እነዚህ ጥረቶች የደንበኝነት አቅምን ከፍ በማድረግ፣ Massive MIMO እና የቤት ውስጥ መፍትሄዎችን (indoor solutions) በመዘርጋት የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ይረዳሉ።

ከዚህ ጋር በተጓዳኝ፣ ኩባንያው ዋናውን ኔትወርክ በማዘመን፣ ስፔክትረም በመቀየር እና በገጠር የቴሌኮም መሠረተ ልማት በመገንባት ግንኙነትን እያሰፋ ነው። በተጨማሪም፣ የፋይበር ዝርጋታን በስፋት በማከናወን የኦዲኤን (ODN) ዝርጋታን፣ ፋይበር-ቱ-ታወርን እና የኮፐር ኔትወርክን ሙሉ በሙሉ በፋይበር የመተካት ስራ ይሰራል። እነዚህ ተግባራት በሜትሮ እና ባክቦን ኔትወርኮች ማሻሻያ የተደገፉ

ሲሆን፣ ጠንካራ የሪንግ ፕሮቴክሽን እና በጂአይኤስ (GIS) የሚመራ ማኔጅመንት ተግባራዊ በማድረግ የመደበኛ እና የሞባይል ብሮድባንድ አገልግሎቶችን ያጠናክራል።

ከኔትወርክ ማስፋፊያ በተጨማሪ፣ ኩባንያው በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በቀጣይ ትውልድ ፕላትፎርሞች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስት እያደረገ ነው። ይህ ኢንቨስትመንት ሞዱላር፣ ኤጅ እና ሃይፐርስኬል ዳታ ሴንተሮችን፣ በዘመናዊ የኮምፒዩት እና ማከማቻ አቅም የክላውድ አገልግሎት ማስፋፊያን እና እንደ AI-SON እና ዲጂታል ትዊን ፕላትፎርሞች ያሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አፈጻጸምን ለማሳደግ ያለመ ነው። እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ለኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የዳታ፣ የኢንተርፕራይዝ እና የሀገራዊ ፕሮጀክቶች ፍላጎት መደገፍ የሚችል፣ መጠነ ሰፊ፣ አስተማማኝ እና ከኃይል ብክነት የጸዳ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር መፍጠር ያስችላሉ።

የስትራቴጂው መሠረታዊ አካል ዘላቂነት እና የድርጅታዊ አቅም ግንባታ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም በየዓመቱ ከ500 እስከ 1,000 የሚደርሱ ጣቢያዎችን ወደ የፀሐይ ኃይል እና የኤሌክትሪክ ፍርግርግ በመቀየር፣ የነዳጅ ፍጆታን ከ16 በመቶ በላይ በመቀነስ እና የካርበን ልቀትን በመቀነስ በአረንጓዴ የኃይል ሽግግር ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በተመሳሳይ፣ የኩባንያው ዕቅዶች በደንበኛ ተኮር የዲጂታል ልምዶች፣ ለወደፊት ዝግጁ በሆነ የሰው ኃይል ልማት፣ እና በዘላቂ ሀገራዊ ተጽዕኖ ላይ የተመሠረተ አስተማማኝ ብራንድ በመገንባት ላይ ያተኩራሉ። እነዚህ ጥረቶች ኢትዮ ቴሌኮምን የዲጂታል ተደራሽነትን በማፋጠን፣ ተወዳዳሪነትን በማጠናከር እና የኢትዮጵያን ዲጂታል ሽግግር ዋና አንቀሳቃሽ በመሆን ያለውን ሚና ለማሳካት ያስችሉታል።

2018 በጀት ዓመት ለማከናወን የታቀዱ ዋና ዋና ግቦች

የሞባይል ኔትዎርክ ማስፋፋትና ማሻሻል

ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ኔትዎርክ ለማስፋፋት እና ለማሻሻል ሰፊ ዕቅዶችን የያዘ ሲሆን ይህም የ4G አገልግሎት 2,270 የ4G ጣቢያዎችን በመጨመር  የህዝብ ሽፋን ወደ 85% በማሳደግ 550 ተጨማሪ ከተሞችን ያካተተ ይሆናል። እንደ Massive MIMO እና Indoor solutions ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአገልግሎት ጥራትን ያሻሽላል። የ5G አገልግሎት በ10 ተጨማሪ ከተሞች ለመዘርጋት ታቀደ ሲሆን የ5G ጣቢያዎች ቁጥር አሁን ካለበት 315 ወደ 490 ለማሳደግ ታቅዷል። 1,228 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ለመገንባት የታቀደ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 322 የሚሆኑት በገጠር የሚተከሉ ናቸው፡፡ በዚህም 7.6 ሚሊዮን አዲስ የሞባይል አቅም በማከል አጠቃላይ የሞባይል ኔትዎርክ አቅሙን ወደ 112.4 ሚሊዮን ለማድረስ አቅዷል።

የፋይበር፣ የብሮድባንድ ኔትዎርክ እና የኃይል መሠረተ ልማት

በፋይበር ኔትዎርክ ግንባታ ዘርፍ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ለኦፕቲካል ዲስትሪቡሽን ኔትወርክ (ODN) አቅሙን በ900K ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 115K አዲስ ግንባታ እንዲሁም 785ሺህ ደግሞ የኮፐር መስመርን በፋይበር በመተካት የሚሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም 320,000 ደንበኞችን ከኮፐር ወደ ፋይበር ኔትዎርክ የሚዛወሩ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ በዋና ዋና ከተሞች ለሚገኙ 1112 የሞባይል ጣቢያዎች በፋይበር ማገናኘት፣ 2000 ኪሎ ሜትር ተጨማሪ የሜትሮ ፋይበር ዝርጋታ ለማከናወን እና 356 አዳዲስ FBB (OLT) መሳሪያዎችን ለመግጠም ታቅዷል።

የሞባይል ታወሮችን በፋይበር ማገናኘት (Fiber to the Tower)፡ አዲስ አበባ አሁን ያለው ሽፋን 92% ሲሆን፣ ተጨማሪ 6% በመጨመር ወደ 98% ለማድረስ፣ ዋና ዋና የክልል ከተሞች፡ አሁን ያለው ሽፋን 46% ሲሆን፣ ተጨማሪ 44% በመጨመር ወደ 90% ለማድረስ ታቅዷል። Massive MIMO አሁን ያሉት ሳይቶች 304 ሲሆኑ፣ ተጨማሪ 525 ሳይቶችን ለማሳደግ ታቅዷል።

የዲጂታል መሠረተ ልማት እና ሌሎች አገልግሎቶች

በአይሲቲ መሠረተ ልማት ላይም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለማድረግ የታቀደ ሲሆን የዳታ ማዕከል አቅም በ192 ራክ በማሳደግ፣ 1.536MW የIT load እና 8,064 ሰርቨሮችን ለመጨመር እቅድ ተይዟል። በተጨማሪም፣ 1100 ኪሎ ሜትር Backbone ፋይበር መዘርጋት፣ የኃይል ምንጭ ለ500 ሳይቶች ወደ አረንጓዴ ኃይል መቀየር፣ የዓለም አቀፍ ጌትዌይ (IGW) አቅምን በ350 Gbps ማሳደግ፣ የCache አቅምን በ600 Gbps ማሳደግ እና የክላውድ አገልግሎትን በ40 ሺህ vCPU፣ 4.5PB Object Storage እና 6PB Enterprise Storage ማሻሻል የታቀደ ነው። እንዲሁም 2.5 ሚሊዮን ተጨማሪ የደንበኛ መጠቀሚያ መሣሪያ (Devices) ለማቅረብ ታቅዷል፡፡

የደንበኛ እድገት እቅድ

ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት የደንበኞቹን ብዛት በ6% በመጨመር 88 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን በሞባይል ድምጽ 6% በመጨመር 85.4 ሚሊዮን፣ በሞባይል ዳታና ኢንተርኔት በ13.3% በመጨመር 52.8 ሚሊዮን እንዲሁም የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኛ በ23% በመጨመር 1 ሚሊዮን በማድረስ አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት መጠንን 77.2% ለማድረስ ታቅዷል፡፡

የሞባይል ብሮድባንድ በተለይም የ4ጂ ሽፋን ከ71% ወደ 85% በማሳደግ እና የ5ጂ አገልግሎት በማስፋፋት ለ1.8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል አቅም ይገነባል፡፡ በረጅም ጊዜ ክፍያ የዲቫይስ አቅርቦት፣ በጥቅል ቅናሾች እና በገጠር ተኮር ዘመቻዎች አማካኝነት ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን፣ ይህም

የሞባይል ዳታ አጠቃቀም ከሞባይል ደንበኞች ውስጥ 61% ደንበኞች የብሮድባንድ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል፡፡ የ4ጂ ኢንተርኔት አማካይ ፍጥነት (throughput) ወደ 8.78mb/s ለማድረስ ታቅዷል፡፡

በመደበኛ ብሮድባንድ አገልግሎት የGPON አቅምን ወደ 1.9 ሚሊዮን በማሳደግ በኮፐር የሚጠቀሙ 320,000 መስመሮችን ወደ ፋይበር ለመቀየር ታቅዷል፡፡ የመኖሪያ ቤት የደንበኝነት ምዝገባዎች በ128,000፣ የንግድ ድርጅት ደግሞ በ32,000 ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን በተለየ መልኩ በSME፣ በድርጅትና በመንግስት መፍትሄዎች በመደገፍ እንዲሁም ቀላል የሆኑ ጥቅሎች እና የተጣመሩ የመደበኛ ብሮድባንድና ሞባይል ፓኬጆችን ለማቅረብ  ታቅዷል፡፡

የቴሌብር ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛትን 62.5 ሚሊዮን ለማድረስ ከመታቀዱ ባሻገር የንቁ ደንበኞች ምጣኔን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ሲሆን በዚህም የ30 ቀናት ንቁ ደንበኞች ምጣኔ ከ14.5% ወደ 20.5% እና የ90 ቀናት ምጣኔ ከ22.6% ወደ 32% ለማሳደግ ታቅዷል፡፡

እንዲሁም በሥነ ምህዳሩ ዕድገት በነጋዴዎች (merchant) በማኅበራዊ አገልግሎት ክፍያዎች ዲጂታላይዜሽን፣ በብሔራዊ መታወቂያ ትስስር እና በጌሚፊኬሽን አማካኝነት አጠቃቀምንና ዘላቂነትን ለማሳደግ እንዲሁም በወጣቶች ላይ ያተኮሩ ዘመቻዎች፣ የገጠር የቴሌብር ወኪሎችን ለማብዛት፣ አጠቃቀምና የአቅም ማሻሻያ ፕሮግራሞች በመተግበር የቴሌብር አገልግሎት ተደራሽነትና አጠቃቀም የማሳደግ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

የገቢ እቅድ

ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢውን 235.8 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ያቀደ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ45.6% ጭማሪ አለው፡፡ ከዋናው የቴሌኮም አገልግሎቶች በ133 ቢሊዮን ብር ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን፣ ወደ 40% የሚጠጋው ገቢ ደግሞ ከመደበኛ ቴሌኮም ባሻገር ካሉ የቢዝነስ ሥራዎች ለማግኘት ታቅዷል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም የገቢ ምንጭ ከዋና እና አዳዲስ የንግድ ዘርፎች የተዋቀረ ሲሆን ከታቀደው ገቢ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የዳታ እና የኢንተርኔት አገልግሎት 23.8% ሲሆን በመቀጠል የድምፅ አገልግሎት 23.2% ድርሻ አለው። ዓለም አቀፍ አገልግሎቶች 8.9%፣ የደንበኞች መጠቀሚያ መሣሪያ ሽያጭ 11.5% ገቢ ያስገኛል። አዳዲስ የእድገት ዘርፎችም ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው የታቀደ ሲሆን በዚህም የኢንተርፕራይዝ አገልግሎቶች 10.2%፣ የተጨማሪ እሴት አገልግሎቶች (VAS) 7.6%፣ እንዲሁም ቴሌብር 3.6% ድርሻ ይይዛል። የመሠረተ ልማት መጋራት 2.2% ድርሻ ሲኖረው ሌሎች አገልግሎቶች ደግሞ 9% ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡

የቴሌብር እቅድ

የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር በ14% በማሳደግ 62.5 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን የግብይት መጠኑም ወደ 4.43 ትሪሊዮን ብር ወይም በ86% ለማሳደግ እና የግብይት ብዛቱ ወደ 1.94 ቢሊዮን ወይም በ83% ለማሳደግ ታቅዷል። ከቴሌብር የሚገኘው ገቢ ወደ 8.5 ቢሊዮን ብር ወይም በ93.9% ለማሳደግ እንዲሁም የንግድ አጋሮች ቁጥርን ወደ 444.6 ሺህ ወይም በ43% እና ወኪሎችን ወደ 432.9 ሺህ ወይም 35% በማሳደግ የቴሌብርን ስነ-ምህዳር ለማጠናከር ታቅዷል።

ምርትና አገልግሎቶች

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 327 ምርትና አገልግሎቶች እንዲሁም ከ3.5 ሚሊዮን በላይ የደንበኛ መጠቀሚያ መሣሪያዎች ወደ ገበያ በማቅረብ አጠቃላይ ገቢውም ወደ 235.8 ቢሊዮን ብር ወይም ካለፈው በጀት ዓመት በ45.6% ለማሳደግ እቅድ ተይዟል። በዓለም አቀፍ አገልግሎቶች በመሠረተ ልማት መጋራት፣ በገንዘብ ዝውውር እና በኮል ትራንዚት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በ6% በማደግ ወደ 225.9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል።

የፋይናንስ ዕቅድ

ገቢን ከመጨመርና የገቢ ምንጮችን ከማስፋፋት ባሻገር የተጠናከረ የወጭ ቁጠባ ሥርዓትን በመተግበር EBITDA 47.7% እንዲሁም የኩባንያችን ከታክስ በፊት የሚያገኘውን ትርፍ 76 ቢሊዮን ብር በማድረስ ካለፈው ዓመት የ260% እድገት ለማስመዝገብ የታቀደ ሲሆን የትርፍ ህዳጉ 22.6% ለማድረስ በእቅድ ተይዟል፡፡ በበጀት ዓመቱ በቀጥታና ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስ ብር 70.9 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከትርፍ ክፍፍል (ዲቪደንድ) 35.4 ቢሊዮን ብር ፈሰስ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

ባጠቃላይ በበጀት አመቱ በሚያደርገው የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ኢንቨስትመንቶች አጠቃላይ ሀብቱን ከ332 ቢሊየን ብር ወደ 501 ቢሊየን ብር ለማሳደግ ታቅዷል፡፡

የቀጣዩ አድማስ (Next Horizon) የሶስት አመት ስትራቴጂ ቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያዎች

በቀጣዩ አድማስ – ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር የሶስት ዓመት ስትራቴጂ ማብቂያ አጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 100 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሰሆን የሞባይል ድምጽ እና ብሮድባንድ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በማደግ የዲጂታል ተደራሽነትን የሚያሰፉ ሲሆን በተለይም የሞባይል ብሮድባንድ ተጠቃሚዎች ወደ 67.3 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኞች ደግሞ ወደ 1.6 ሚሊዮን ይደርሳሉ።

በስትራቴጂ ዘመኑ ማጠናቀቂያ የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር በ36.8% በማደግ 75 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን የግብይት መጠኑም ወደ 21.3 ትሪሊዮን ብር (+334%) እና የግብይት ብዛቱ ወደ 10.4 ቢሊዮን (+439%) ለማሳደግ ታቅዷል። ከቴሌብር የሚገኘው ገቢ ወደ 49.1 ቢሊዮን ብር (+568%) ለማሳደግ እንዲሁም የንግድ አጋሮች ቁጥርን ወደ 960.6 ሺህ (+209%) እና ወኪሎችን ወደ 840 ሺህ (+162%) በማሳደግ የቴሌብርን ስነ-ምህዳር ለማጠናከር ታቅዷል።

በአጠቃላይ በሶስት ዓመታት ውስጥ 842.3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት የታቀደ ሲሆን ከቀደመው ስትራቴጂ ዘመን ገቢ 154% አድገት ያለው ነው፡፡ ይህ የገቢ እድገት ዕድገት ከቴሌኮም፣ ከቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር ከፊንቴክ፣ ከደንበኛ መጠቀሚያ መሳሪያዎች ሽያጭ፣ ከኤንተርፕራይዝ ሶሉሽኖች እና ከሌሎች አገልግሎቶች የሚመነጭ ይሆናል። የውጭ ምንዛሪ ገቢም ወደ 976 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማሳደግ ታቅዷል፡፡ በስትራቴጂ ዘመኑ በሚያደርገው የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ኢንቨስትመንቶች የኩባንያችን አጠቃላይ ሀብት  851 ቢሊየን ብር ለማድረስ ታቅዷል፡፡  ኩባንያችን ለሀገራችን ኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ ከመወጣት አኳያ ከአገልግሎቱ ባሻገር በሦስቱ ዓመታት ውስጥ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስ በድምሩ 253 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የትርፍ ድርሻ ክፍያ (ዲቪደንድ) በመፈጸም በድምሩ 111.3 ቢሊዮን ብር ለመንግስት ፈሰስ ለማድረግ ታቅዷል።

ታሳቢዎች (Assumptions)

ከቴሌኮም ገበያ ሪፎርም ጋር በተያያዘ ሁለገብ (በቴሌኮም፣ በዲጂታል አገልግሎትና በፊንቴክ አገልግሎቶች) የገበያ ውድድር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። እ.አ.አ በ2026/27 ሦስተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር ወደ ገበያ ሊቀላቀል ይችላል ተብሎ የታሰበ ሲሆን፣ ተጨማሪ ISPs ወደ ገበያው መቀላቀል፣ የመሠረተ ልማት ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ፈቃድ ማግኘት፣ አዲስ የሳተላይት ብሮድባንድ አቅራቢዎች እና ተጨማሪ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ኦፕሬተሮች ወደ ገበያው ሊገቡ ይችላሉ በሚል እሳቤ ተወስዷል። እነዚህ ለውጦች በዋጋ እና ከአንድ ደንበኛ በአማካይ የሚገኘው ገቢ (ARPU)

ላይ ጫና የመፍጠር፣ የገበያ ድርሻ ሊያሳጡ እና የደንበኞችን የፍልሰት ስጋት ሊጨምሩ ይችላሉ። ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞችን ታማኝነት ማሳደግ፣ በተለየ መልኩ የአገልግሎት ጥራት ማረጋገጥ፣ በጥቅል አገልግሎቶች (bundling)፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ (SME/enterprise) መፍትሄዎች፣ ለገጠር ተስማሚ የሆኑ ጥቅሎች እና ፈጠራ ባላቸው የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ላይ ማተኮር አለበት። በተመሳሳይ ጊዜ፣ እየተለዋወጡ ያሉት የቁጥጥር መስፈርቶች እንደ SMP (በገበያ ላይ ጉልህ ድርሻ ከመያዝ ጋር በተገናኘ የሚኖሩ አሰገዳጅ የቁጥጥር ስርዓት) እና ከተወዳዳሪ ጋር

በሚኖር የድምጽ ትራፊክ አገልግሎት ጋር በተገናኘ የሚኖር የዋጋ ታሪፍ (MTR) ትግበራ፣ ጥብቅ የሆነ የጥራት ደረጃ፣ የፍሪኩዌንሲ (spectrum) እና የቁጥር (numbering) አጠቃቀም፣ የዳታ ጥበቃ እና የደንበኛ እርካታ ግቦች፣ ቅጣቶችን ለማስወገድ እና መልካም ስምን ለመጠበቅ ከደንብ አውጭዎች ጋር ቀድሞ መገናኘትን፣ ደንብን በጥራት መከተልን እና በሥራ ላይ ፈጣን መሆንን ይጠይቃሉ።

እንደ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የብር የመግዛት አቅም መቀነስ እና የውጭ ምንዛሪ ያሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎች የሥራ ማስኬጃ እና የካፒታል ኢንቨስትመንት አቅምን ይጎዳሉ። ይህ በፋይናንስ ላይ ጠበቅ ያለ አሰራርን የሚያስገድድ ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ የገንዘብ ምንጮችን መፈለግን፣ ግብዓቶችን ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች መግዛትን እና የወጪ ቁጠባና ቅነሳ ማድረግን ይጠይቃል። የቀጠናዊ ጂኦፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እና የሀገር ውስጥ ግጭቶች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና የአገልግሎት ቀጣይነት ላይ ስጋት ይፈጥራሉ። ይህ ደግሞ ጠንካራ የአደጋ ጊዜ እቅድ (contingency planning)፣ የአቅራቢዎች ብዝሃነት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራትን አስፈላጊ ያደርገዋል። በተመሳሳይ ጊዜ እንደ ቀጠናዊ የቴሌኮም ግንኙነት (regional connectivity)፣ የንግድ ኮሪደሮች እና ድንበር ዘለል ዲጂታል መፍትሄዎች ባሉ መስኮች ሰፋፊ እድሎች አሉ። እነዚህንም እንደ ሮሚንግ ስምምነቶች፣ የመሠረተ ልማት መጋራት እና የጋራ የዲጂታል ፕሮጀክቶች አማካኝነት መጠቀም ይቻላል። እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ ዳታ ሳይንስ (data science) እና የሳይበር ደህንነት (cybersecurity) ባሉ ዘመናዊ ክህሎቶች ላይ እየጨመረ የመጣው ፍላጎት የዘርፉን ዲጂታል ሽግግር ለማረጋገጥ ቁልፍና ተሰጥዖ ያላቸውን ሰራተኞችን የመሳብ፣ የማሰልጠን እና የማቆየት ስትራቴጂዎችን መተግበር ይፈልጋል።

የስጋት ማቅለያ ስትራቴጂዎች 

የኢትዮ ቴሌኮም የቢዝነስ እንቅስቃሴ ውስብስብ እና ባለብዙ ገፅታ ባላቸው ስጋቶች የተከበበ ሲሆን፣ እነዚህም ስትራቴጂካዊ፣ ኦፕሬሽናል፣ ፋይናንሳዊ፣ የቁጥጥር እና የቴክኖሎጂ ዘርፎችን ያካትታሉ። እነዚህ ስጋቶች የቢዝነስ ቀጣይነትን የማደናቀፍ፣ ተወዳዳሪነትን የማዳከም እና የኩባንያውን የረዥም ጊዜ ፈተናን የመቋቋም አቅም የመጉዳት አቅም አላቸው።

ዋና ዋናዎቹ ውጫዊ ስጋቶች እንደ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የብድር ተጋላጭነት ያሉ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ሲሆኑ ከእነዚህም በተጨማሪ የቁጥጥር ገደቦች እና የውድድር ገበያ  ናቸው።የመሠረተ ልማት መቆራረጥ፣ የኃይል አቅርቦት መዛባት፣ የሳይበር ደህንነት ስጋቶች እና የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ የመሳሰሉ ኦፕሬሽናል፣ ቴክኖሎጂያዊና የሰለጠነ ሰው ኃይል ችግሮች ይስተዋላሉ።

እነዚህን ስጋቶች ለመቋቋም ገቢን በማስፋፋት፣ መሠረተ ልማትን በማዘመን፣ የአስተዳደር ስርዓትን በማጠናከር እና በሰው ኃይል እና በደንበኞች ግንኙነት ላይ ያተኮሩ ቅድመ ዝግጅት ስልቶችን መተግበር ያስፈልጋል። በመጨረሻም፣ ስኬት የሚረጋገጠው በስርዓት በተመራ አፈጻጸም፣ ከሬጉላቶሪ አካላት ጋር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ እና ለወደፊት ፈተናዎች ዝግጁ በሆነ የሰው ኃይል አቅም በመጠቀም ነው። ይህም በየጊዜው በሚለዋወጠው የቢዝነስ ከባቢ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል እና ለፈተና የማይበገር አቅምን ለማጠናከር ወሳኝ ነው።

ሴክተር ዘለል የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች እቅድ 

በጾታ እኩልነት ረገድ ፡- ሴቶች በስራ ቦታቸው ላይ የሚያጋጥማቸውን አሳሳቢ ችግሮች በመለየት ተግባራዊ መፍትሔ የመስጠት፣ በተቋሙ ውስጥ Gender mainstreaming ተግባራዊ ማድረግ፣ ለሴት ሰራተኞች የስራና የግል ህይወት ማመጣጠንን፣ የአቅም ግንባታ ስልጠና ማመቻቸት እንዲሁም ፓናል ውይይቶች ማዘጋጀት እንዲሁም ጤና፣ የማስ ስፖርትና ሌሎች ማህበራዊ ተሳትፎ ማሳደግ፡፡

የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት: የካርበን ልቀትን በመቀነስ፣ ዘላቂ የኃይል ምንጮችን (Green Energy) በመጠቀም፣ ለኤሌክትሪክ መኪኖች የኃይል መሙያ አገልግሎት በማቅረብ እና የኔትወርክ ቁሳቁሶችን በኃላፊነት ስሜት በማስተዳደር ላይ ያተኩራል። በተጨማሪም፣ የሰራተኞችንና ማህበረሰቡን ተሳትፎ በማበረታታት አረንጓዴ የስራ ባህልን እናዳብራለን፤ ቴክኖሎጂያችንም ለዘመናዊና ለአካባቢ ተስማሚ ከተሞች (Smart Cities) ግንባታ ወሳኝ ተሳትፎ ለማድረግ ያስችላል።

በጎ አድራጎት ተግባራት፡ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን በፋይናንስና በቴክኖሎጂ በማገዝ አቅማቸውን እናጎለብታለን፤ እንዲሁም ሰራተኞቻችንን በደም ልገሳ እና እንደ ኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ላሉ ተቋማት በሚደረግ የገቢ ማሰባሰብ በማስተባበር የማህበረሰብ ተሳትፏችንን እናጠናክራለን። በተጨማሪም፣ በኤች.አይ.ቪ መከላከልና ድጋፍ ላይ በማተኮር ለሰራተኞቻችንና ለማህበረሰቡ ጤና ከሚመለከታቸው ጋር እንሰራለን።

ይህ ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ዲጂታል ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ እና በአፍሪካ ዘላቂና አካታች ዕድገትን በማስፋፋት ያለውን ሚና በአዲስ መልክ የሚቀርፅ ወሳኝ ፍኖተ-ካርታ በመሆኑ ለስኬቱ የኩባንያችን ማኔጅመንትና ሠራተኞች ቁርጠኛና ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጽን የደንበኞቻችን፣ ተቆጣጣሪ አካላት፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ የቢዝነስ አጋሮች፣ ባለድርሻ አካላት እና ሚዲያዎች አብሮነት በመተማመን አዲሱን የስትራቴጂ ዘመን  በአዲስ ጅማሮ፣ አዲስ ተስፋና እይታ በይፋ ያስጀመርን መሆኑን በደስታ እንገልጻለን፡፡

ነሐሴ 2017 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives