የኢትዮ ቴሌኮም 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት

ይህ ሪፖርት የአዲሱን “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” ዘመን ከሐምሌ 2017 እስከ ታህሳስ 2018 ያለውን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡

ኩባንያችን የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን፣ የዲጂታል አካታችነትን፣ የሥራ እድል ፈጠራን፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ለሀገራችን ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም ኩባንያው በአህጉራዊ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳደግ ያለመ “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” (Next Horizon: Digital & Beyond 2028 Strategy) ቀርፆ እየተገበረ ይገኛል።

በዚህም በየጊዜው የሚለዋወጠውን ቴክኖሎጂ በፍጥነት በመላመድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ፣ በቀጠናው ልዩ እና በዲጂታል የጎለበተ ኩባንያ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎችን በመክፈት ከትሩፋቱም ለመቋደስ የሚያስችል ሥራዎችን ለማከናወን ሁሉንም የኩባንያ ማህበረሰብ በማቀናጀት በከፍተኛ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ስትራቴጂውን እየተገበረ ይገኛል፡፡

ስትራቴጂ ከሀገራዊው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ራዕይ ጋር የተጣጣመ ሲሆን፤ ይህም ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን፣ የዲጂታል መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ፣ በቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚጫወተውን ሚና ያጠናክረዋል።

ኩባንያችን በቴሌኮም መሠረተ-ልማት፣ በዲጂታል መድረኮች እና በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ላይ የሚያደርገውን ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት በማጠናከር የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማሻሻል፣ የንግዱን ማህበረሰብና የመንግሥት ተቋማትን ለመደገፍ እንዲሁም ንቁ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር መሠረትን ለማጽናት በትጋት እየሠራ ይገኛል።

በተጨማሪም ኩባንያችን አገልግሎቱን ወደ ተለያዩ ዲጂታል ፕላትፎርሞች፣ ስነ-ምህዳሮች እና የኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽኖች በማስፋት ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችን የሚደግፉ ተግባራትን በቁርጠኝነት እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር በቀጠናው እና አለምአቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ አዳዲስ እድሎችን በመፍጠር፣ ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት በማቅረብ እና አህጉራዊ ትብብርን በማጎልበት የዲጂታል አፍሪካን ጉዞ ለማፋጠን እና በቀጠናው ተምሳሌት ለመሆን እየሰራ ይገኛል።

ኩባንያችን የዲጂታል ክፍተን በማጥበብ የዜጎችን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል፣ የኢንተርፕራይዞችን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የዲጂታል አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማስፋፋት የአገራችንን የኢኮኖሚ እድገት ለማነቃቃት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በዚህም የቴሌኮም መሰረተ ልማትንና የዲጂታል መፍትሄዎችን በማቅረብና በመጠቀም የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት እና በማዘመን ዲጂታል ከባቢን ከመፍጠር አኳያ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

የቴሌኮምና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያ

 ኩባንያችን የሀገራችንን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያፋጥን ዲጂታል ከባቢን ለመፍጠር፣ በስትራቴጂው መሠረት የቴሌኮም ዘርፉን ይበልጥ በማዘመን አገልግሎቱን ለማስፋፋት እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እንዲሁም የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማሻሻል እና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘመኑን ያማከለ ወቅታዊ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ  እየተገበረ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ፡- የዳታ ትራፊክ እድገትን መሠረት ያደረገ የ4G እና 5G ኔትዎርክ አቅምና ሽፋን ማሳደጊያ፣ የባክሃውልና ትራንስፖርት ኔትወርክ አቅም ማሳደጊያ፣ የመደበኛ ብሮድባንድ አቅም ማሳደጊያ፣ የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያ፣ የክላውድ አገልግሎት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ የአሰራር ስርዓቶች፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ የአሰራር ደጋፊ ሲስተሞች (Operation support) እና የኮርፖሬት ሶልዩሽንስ፣ የሴኩሪቲ ሶልዩሽንስ እና የተለያዩ የሲቪል ግንባታ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

 የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ስራዎች

 ኩባንያችን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ባከናወነው መጠነ ሰፊ የፕሮጀክት ስራ 278 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን ገንብቶ ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 130 ያህሉ (ወይም 47 በመቶው) የገጠር አካባቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የገጠር ሞባይል ጣቢያዎች ናቸው። በዚህም አጠቃላይ የጣቢያዎችን ቁጥር 10,288 በማድረስ የዕቅዱን 98.5% ለማሳካት ያስቻለ ሲሆን፣ የኔትወርክ አቅምን በ3.21 ሚሊዮን በማሳደግ አጠቃላይ ደንበኞችን የመሸከም አቅም ወደ 108 ሚሊዮን ከፍ እንዲል በማድረግ አፈጻጸሙ 101% ሆኗል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ውስጥ በተከናወኑ የኔትወርክ ማስፋፊያ ስራዎች 133 አዳዲስ ከተሞች የ4G LTE አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የ4G ተጠቃሚ ከተሞችን ቁጥር ወደ 1,069 በማሳደግ የ4G የሕዝብ ቁጥር ሽፋንን 74% እንዲሁም የቆዳ ሽፋንን (Geographical Coverage) 27.6% ማድረስ ተችሏል፡፡

በተለይም የገጠር ሳይቶችን ቁጥር በመጨመር፣ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ተደራሽ ባልነበረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማህበረሰቦችን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚው እንዲቀላቀሉ አድርጓል። ይህም ሁሉም ዜጎች ከድምፅ አገልግሎት ባለፈ ወደ ዲጂታል እና ዲጂታል ፋይናንስ፣ የመንግስት አገልግሎቶች እና ለሌሎች የቴክኖሎጂ አማራጮች እንዲሸጋገሩ አመቺ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ የኢንተርኔት ፍጥነትና የአገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል አስችሏል።

የገጠር ሞባይል አገልግሎት

 ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ባልደረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች የዲጂታል መካተትን (Digital Inclusion) ለማረጋገጥና የገጠር ነዋሪዎችን ከዲጂታሉ ዓለም ጋር ለማቀላቀል ሰፊ የማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ በ9 ክልሎችና102 ወረዳዎች ውስጥ 130 የገጠር ሞባይል ጣቢያዎችን በመገንባት 332 ቀበሌዎችንና መንደሮችን የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በዚህም 761,027 ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፤ ጣቢያዎቹ የተገነቡባቸው አካባቢዎችም በአማካይ ከከተሞች በ23.76 ኪ.ሜ፣ እንዲሁም ከሌሎች የሞባይል ጣቢያዎች በ18.77 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የማስፋፊያ ሥራው ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ ያሳያል።

የባክቦን ኔትወርክ፣ የኢንተርኔት ጌትዌይ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ

ባለፉት ስድስት ወራት በባክቦን ኔትወርክ ማስፋፊያ ረገድ 377.7 ኪ.ሜ አዲስ የፋይበር ዝርጋታ ተከናውኗል። ይህም OPGWን ጨምሮ አጠቃላይ የባክቦን ፋይበር ርዝመቱን 23,026.7 ኪ.ሜ አድርሶታል። ይህ የማስፋፊያ ስራ የኔትወርኩን አማራጭ መስመሮች (Redundancy) በማብዛት እና ጥንካሬውን (Resilience) በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ከደንበኞች የዳታ አጠቃቀም መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ለማስተናገድ እንዲቻል፣ በግማሽ ዓመቱ በcache አማካኝነት የዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መውጫ (IGW) አቅም በ500 Gbps እንዲያድግ ተደርጓል። ይህም አጠቃላይ የኢንተርኔት መውጫ አቅሙን 3 Tbps አድርሶታል። ይህ ሰፊ አቅም የተገነባው የኩባንያውን የውጭ ምንዛሬ ወጪ ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ ሲሆን፣ ከጠቅላላ አቅሙ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው (1,762 Gbps) ዳታ ትራፊክን በአገር ውስጥ በማቆየት የCache አቅምን በመፍጠር የተከናወነ ነው፡፡

በተጨማሪም በ13 የዳታ ማዕከላት እና የኮር ሳይቶች ላይ የIP Core እና IGW ራውተሮችን የማዘመን ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ይህም የአንድ መስመር የመሸከም አቅምን ወደ 800G  እንዲሁም የስሎት አቅምን ወደ 3.2T ከፍ አድርጓል። በዚህም አጠቃላይ የIP Core አቅም 97 Tbps ደርሷል።

የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ

 የኔትወርክ አገልግሎት ጥራትን (Quality of Service) ለማረጋገጥ 152 ጄነሬተሮች እና 101 አዳዲስ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ሳይቶች የተተከሉ ሲሆን፣ የ264 የሶላር ሳይቶች አቅም የማሳደግ ስራ ተከናውኗል። ይህም የኩባንያውን አጠቃላይ የፀሐይ ኃይል ማመንጨት አቅም 30MW peak አድርሶታል። በተጨማሪም አገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የ61 ኪ.ሜ የባክቦን ፋይበር ጥገና እና እድሳት በመከናወኑ፣ ደንበኞች አስተማማኝ እና ፈጣን የኔትወርክ ተሞክሮ እንዲኖራቸው አስችሏል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ 3 እጅግ ፈጣን (Super-fast) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች የተገነቡ ሲሆን፣ እነዚህ ጣቢያዎች በአንድ ጊዜ በድምሩ 40 ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም አላቸው።

ይህም እስካሁን በኩባንያችን የተገነቡትን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያ ጣቢያዎች ቁጥር ወደ 5 ከፍ ያደረገው ሲሆን፣ በአጠቃላይ 72 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ እጅግ ዘመናዊና ፈጣን በሆነ ቴክኖሎጂ (Ultra-fast and Super-fast) የመሙላት አቅም ፈጥሯል። ይህ ተግባር የመንግስትን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲና አቅጣጫ ከመደገፍ ባሻገር፣ በሀገራችን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀምና ሽግግር (EV Adoption) በከፍተኛ ፍጥነት እንዲፋጠን የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

የፊክስድ ኔትወርክ አቅምንና ጥራት ማሳደግ

የደንበኞችን የፊክስድ ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ከፍተኛ ፍላጎት ለማርካት፣ የፋይበር ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የኔትዎርኩን ጥራት እና አቅም ለማሳደግ በስድስት ወራቱ ተጨማሪ 254.3 ሺ የኦፕቲካል ዲስትሪቢውሽን ኔትወርክ (ODN) አቅም የተገነባ ሲሆን፣ በዚህም አጠቃላይ የODN አቅማችንን 1.21 ሚሊዮን በማድረስ የዕቅዱን 124% ማሳካት ተችሏል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ከትላልቅ ኢንተርፕራይዝ፣ ከተማ መስተዳድሮች እና የመንግስት ተቋማት ጋር በተደረገው ስምምነት የCCTV የፋይበር ዝርጋታ 306 ኪ.ሜ ለማከናወን ታቅዶ በስፔሻል ፕሮጀክት በአጠቃላይ 519 ኪ.ሜ ዝርጋታ ተከናውኗል፡፡

የፋይበር ብሮድባንድ ኔትወርክ መሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ ሲሆን፣ በአዲስ የፋይበር ብሮድባንድ ኔትወርክ ሽፋን (Green Field) ፕሮጀክት ስር 31,474 የደንበኛ ቤቶችን ለማገናኘት ታቅዶ አፈጻጸሙ 32,948 (105%) ሆኗል። ይህ ስኬት የተገኘው ለስራው የሚያስፈልጉ የኦፕቲካል ዲስትሪቡሽን ኔትወርክ (ODN) እቃዎች በቬንደር ፋይናንስ አማራጭ በፍጥነት ለማቅረብ በመቻሉ ነው። በተጨማሪም፣ የነባር የኮፐር ደንበኞችን ወደ ፋይበር ለመቀየር በተያዘው Copper Switch-Off ፕሮጀክት በስድስት ወራቱ 228.5 ሺ ደንበኛ ማስተናገድ አቅም ያለው ODN ኔትወርክ በመገንባት አገልግሎት ላይ ለማዋል ታቅዶ 221.3 ሺ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው ODN ኔትወርክ የተገነባ ሲሆን አፈፃጸሙ 97% ሆኗል። ይህ ፕሮጀክት የነባር ደንበኞችን የአገልግሎት ጥራት ችግር ለመፍታት እና በልማት የተጎዱ የኮፐር ኔትወርኮች ባለባቸው አካባቢዎች አገልግሎትን በፍጥነት ለማስጀመር ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። በዚህም በስድስት ወራቱ 32,600 ደንበኞች ከኮፕር ወደ ፋይበር ማዞር የተቻለ ሲሆን ይህም አጠቃላይ ወደ ፋይበር የተዛወሩትን ደንበኞች ብዛት 68,661 አድርሶታል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን 173 አዳዲስ OLT መሣሪያዎች የተተከሉ ሲሆን፣ አጠቃላይ የOLTን ብዛት ወደ 833 ከፍ አድርጎታል። በከተሞች ያለውን የፋይበር ኔትወርክ ሽፋን ለማሳደግ በተከናወነው የሜትሮ ፋይበር ማስፋፊያ፣ በግማሽ ዓመቱ 253 ኪ.ሜ ዝርጋታ ተከናውኖ አጠቃላይ የሜትሮ ፋይበር ርዝመት 14,593 ኪ.ሜ ደርሷል። ከዚህ ውስጥ 234 ኪ.ሜ የሚሆነው ለFTTT (Fiber to the Tower) ዝርጋታ የዋለ ሲሆን፣ ይህም የሞባይል  backhaul ኔትወርክ አቅማችንን በማሳደግ ለ5G እና ለወደፊት የማስፋፊያ ስራዎች ዝግጁ እንዲሆን አድርጎታል።

የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን ማሳደግና ማሻሻል

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም ለማሳደግና ለማሻሻል ዘመኑ የደረሰባቸውንና የተሻሻለ የአገልግሎት ጥራት በማምጣት ምርጥ የደንበኛ ተሞክሮን በማረጋገጥ፣ ቀጣይነት ያለው የቢዝነስ እድገት እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማምጣት ችሏል። በዚህም አጠቃላይ ለማህበረሰቡ አኗኗር እና ለኢንተርፕራይዝ ድርጅቶች የአሰራር ቅልጥፍና ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሰፊው ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ለደንበኞች ፈጣንና ምቹ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉና አሰራርን በእጅጉ የሚያዘምኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡

ከነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ፡- የOSS Cloud ትግበራ፣ NGBSS SNS ማሻሻያና ደንበኛ የማስተናገድ አቅም ወደ 110 ሚሊዮን ማሳደጊያ፣ የTeleCloud እና Private Cloud፣ Disaster Recovery (DR) ማስፋፊያ፣ የአዲስ E-Commerce Platform ግንባታ፣ DNS System Upgrade Solution፣ Webhosting Upgrade and Migration፣ Authentication, Authorization & Accounting (AAA) ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የዳታ ሴንተር እና የክላውድ አገልግሎት

የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይን እውን ከማድረግ አንጻር በተሰሩ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የዳታ ሴንተር እና የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሰረት በማድረግ የዳታ ሴንተር አቅማችንን ወደ 5 MW IT Load ፣ 624 IT Rack እና 28,848 U ደርሷል።

የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው እና ተቋማት አሰራራቸውን ዲጂታላይዝ እንዲያደርጉ የሚያስችለው የክላውድ ኢንፍራስትራክቸር ማስፋፊያ ስራዎች የተተገበሩ ሲሆን በዚህም በ elastic compute 31,616 vCPU፣ storage 4.5 PB እንዲሁም ኢንተርፕራይዝ ስቶሬጅ 3 PB የዳታ ሴንተር አቅም መገንባት ተችሏል፡፡

የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች

የሞባይል አገልግሎት ጥራትን ከማሳደግ አንፃር በተከናወኑ ተግባራት የሞባይል የኔትወርክ መገኘት መጠን (NAR) 95.7 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 93.7 በመቶ አፈጻጸሙ በአማካይ 97.9 በመቶ ሆኗል፡፡

በተጨማሪም በስድስት ወራቱ በ5 ቀን ውስጥ የፊክስድ ብሮድባንድ አዲስ መስመርን ማስገባት 79.5 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 81.7 በመቶ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ በአማካይ 102.8 በመቶ ሆኗል፡፡ እንዲሁም የፊክስድ ብሮድባንድ ዳታ ብልሽት ጥገና በ3 ቀን ውስጥ 62.5 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 51.3 በመቶ ሲሆን አፈጻጸሙ 82 በመቶ ሆኗል፡፡

የሞባይል የጥሪ ስኬት መጠን (CSSR) 98% ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 95.6% ሲሆን አፈጻጸሙ በአማካይ 97.6% ሆኗል፡፡ የ4G MBB ፍጥነት 8.2 Mbp ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 6.9 Mbps ሆኗል፡፡ በአማካይ የብሮድባንድ አገልግሎት ፓኬት ሎስ (packet loss) ደግሞ 0.32% በመሆኑ ከታቀደው 0.35% የተሻለ አፈጻጸም አሳይቷል።

የኔትወርክ ትራፊክ አፈጻጸም

በስድስት ወራቱ 92.38 ቢሊየን ደቂቃ የሞባይል የድምፅ ጥሪ፤ 440.18 ሚሊዮን ደቂቃ ወደ አገር ውስጥ የተደረገ ዓለም አቀፍ የድምፅ ጥሪ ተከናውኗል። እንዲሁም 26.6 ቢሊየን አጭር የጽሁፍ መልዕክት፣ 942.52 ቢሊዮን ሜጋ ባይት የሞባይል ዳታ ትራፊክ ተመዝግቧል፡፡ ይህ አፈፃፀም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፡ በሞባይል ድምፅ ጥሪ የ10.6% ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የተደረገ ጥሪ በ12.8% ጭማሪ አሳይቷል፣ በአጭር መልእክት የ44% እና በሞባይል ዳታ የ46.8% እድገት አስመዝግቧል፡፡

በሁሉም የትራፊክ ዓይነቶች እድገት የተመዘገበ ሲሆን፣ የዳታ ትራፊክ አፈፃፀም የላቀ እድገት አሳይቷል፡፡ አፈፃፀሙ ከፍ ያለው የዳታ ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥርና የዳታ አጠቃቀም ባህሪ መጨመር፣ ተጨማሪ የኔትዎርክ መሰረተ ልማቶች በተለይም የ4ጂ ኔትዎርክ መስፋፋት፣ አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶች ወደ ገበያ መውጣታቸው፤ ተከታታይ የሆነ የኔትዎርክ ማትባት ስራዎች መሰራታቸው፣ የዋጋ ተመጣጣኝነትን ለደንበኞቹ ከማረጋገጥ አንፃር የተደረገው የደንበኞችን የመግዛት አቅም ያማከለ የፓኬጅ አማራጮችን ማቅረብ መቻሉ እንዲሁም ከአጋሮች ጋር ያለው ትብብር ማደጉ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

ምርትና አገልግሎቶችን ከማሳደግ አንጻር

በግማሽ ዓመቱ 81 አዳዲስ74 ማሻሻያ የተደረገባቸዉ፣ እና 49 ፕሮሞሽን የተደረገባቸው 204 ምርትና አገልግሎቶች ለገበያ ቀርቧል፡፡ በስድስት ወራቱ 83 ምርትና አገልግሎቶች ለግለሰብ ደንበኞች 30 ቢዝነስ ኮኔክቲቪቲ፣ 27 የዲጂታልና ላይፍ ስታይል አገልግሎቶችና መፍትሄዎች11 የክላውድና የኢንተርፕራይዝ መፍትሔዎች፣ 13 አለም አቀፍ የንግድ ገቢን ለመጨመር እና አጋርነትን ከመጠቀም አንጻር የቀረቡ ምርትና አገልግሎቶች እና 40 የቴሌብር ምርትና አገልግሎቶች ለገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡

ከቀረቡት የክላውድና የዲጂታል መፍትሔዎች ውስጥ ለትምህርት፣ ለትራንስፖርት እና ለፋይናንስ ቁልፍ ዘርፎች ቴለርድ ፍሊት ማኔጅመንት ሶሉሽን የሚሆኑ መፍትሔዎች ይገኙበታል። በተጨማሪም የተለያዩ አዳዲስ 231.9 ሺህ የቴሌኮምና የዲጂታል አገልግሎት መገልገያ ዲቫይሶች ለገበያ የቀረቡ ሲሆን በግማሽ አመቱ 389.9 ሺህ ለደንበኞች ተሸጧል፡፡

ኩባንያችን የዲጂታል አካታችነትን እውን ለማድረግ የሚያስችሉና ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ በክላውድ ላይ የተመሰረቱ ዘኔክሰስ ስማርት ዲቫይሶችን እና የክላውድ ዎርክስፔስ መፍትሄዎችን እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ አቅርቧል፡፡ ይህም ኩባንያችን ባለፉት ዓመታት የዘረጋቸውን የቴሌኮምና ዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በስማርት ስልኮች ውድነት ምክንያት መጠቀም ያልቻሉና ከዲጂታል ኢኮኖሚው ተገልለው የነበሩ ማህበረሰቦችን ለማካተት ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡

ኢንተርፕራይዝ ሶሉሽንስ

በኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽን ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ 3.4 ቢሊዮን ብር ገቢ በማመንጨት 48.5 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል። በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 9.45 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 31 የፕሮጀክት ኮንትራቶች የተፈረሙ ሲሆን ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ድረስ 21.07 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 65 የፕሮጀክት ኮንትራቶች ተፈርመዋል፡፡

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ውስጥ በሂደት ላይ ያሉትን ጨምሮ 346 የሚደርሱ ሶሊዩሽኖች በመበልጸግ ላይ ሲሆኑ 126ቱ አፕሊኬሽን/ፕላትፎርም፣63ቱ ቨርቲካል ሶልዩሽን፣35ቱ ስማርት ካምፓስ ሶልዩሽን፣34ቱ ኔትወርክ ሶልዩሽን፣29ኙ ሴኪዩሪቲ ሶልዩሽን፣30ው ኢነርጂ ሶልዩሽን፣12ቱ ስማርት ሲቲ ሶልዩሽን እና 17 አፊስ ሶሊዩሽኖች ናቸው፡፡አሁን ላይ ያሉበትን ሁኔታ ስንመለከት 80ው በደንበኞች ግምገማ ላይ፣61ዱ ያለቁ፣87ቱ አዲስ የበለጸጉ፣49ኙ ፕሮፖዛል ዝግጅት ላይ፣ 36ቱ የኮንትራት ፊርማ ሂደት ላይ፣14ቱ የማጽደቅ ሂድትን እየተጠባበቁ ያሉ፣ 16ቱ በሰነድ አደረጃጀት ላይ ያሉ እና 3 ደግሞ ኮንትራታቸው የተቋረጠ ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ አኳያ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ሲሆን፣ በተለይም ስማርት ሲቲ፣ ስማርት ካምፓስ፣ የመንግስት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ (e-government)፣ እና የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለተለያዩ የክልልና የፌዴራል ተቋማት በማቅረብ ላይ ይገኛል።

የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትና አጋሮቻችን

በስድስት ወራቱ 112 ተጨማሪ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የተጨመሩ ሲሆን በአጠቃላይ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ብዛትን 1,150 ማድረስ ተችሏል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 582 በፍራንቻይዝ፣ 437 በኩባንያችን ባለቤትነት እና 131 በኢንዳይሬክት ቻናል አጋሮች የተያዙ ማዕከላት ናቸው። ማዕከላቱ የተከፈቱት ከዚህ በፊት ምንም አይነት የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ያልነበራቸው ከተሞች ላይ እና ከፍተኛ የተጠቃሚ ፍሰት ባለባቸው አካባቢዎች ነው። ይህም ለደንበኞች ይበልጥ ተደራሽ መሆን ከማስቻሉም በላይ በውድድር ገበያው ላይ በሁሉም ቦታዎች ላይ በቅርበት በመገኘት ተመራጭ የሽያጭ ቻናል መፍጠር ተችሏል።

ኩባንያችን በተገበረው ዲስትሪቢውሽን ስትራቴጂ መሰረት 59 ዋና አከፋፋዮች 65.2 ሺ ንዑስ አከፋፋዮች፣ እንዲሁም 383.9 ሺ ቸርቻሪዎች በሽያጭ ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም አጠቃላይ የአጋሮችን ቁጥር ወደ 449.3 ማሳደግ ተችሏል፡፡

የደንበኛ ቁጥር

በአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቻችን ብዛት 87.1 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ከእቅድ አንጻር አፈጻጸሙ 101.5% ሆኗል:: ከዚህም ውስጥ 3.93 ሚሊዮን በስድስት ወር የተጨምሩ ናቸው፡፡ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ6.56 ሚሊዮን ወይም የ8.1% እድገት አሳይቷል፡፡ በስድስት ወራቱ የ90 ቀናት ንቁ የሞባይል ተጠቃሚዎችን ብዛት በ2.4 ሚሊዮን በመጨመር 69.1 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል፡፡

ደንበኞች በአገልግሎት አይነት

በአገልግሎት አይነት ሲታይ በስድስት ወራቱ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 8.1% በመጨመር 84 ሚሊዮን፣ የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 12.7% በመጨመር 49 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ 19.2% በመጨመር 934.7 ሺ እንዲሁም በደንበኞች ፍላጎት ወደ ኢንተርኔት ግንኙነት አማራጮች መቀየር ምክንያት የመደበኛ ስልክ የድምፅ ደንበኞች ብዛት በ6.2% ቀንሶ 718.3 ሺ ደርሷል፡፡ በእነዚህ አገልግሎቶች የቴሌኮም አገልግሎት ስርጸት (teledensity) መጠን 77.1% ማድረስ ተችሏል፡፡

በስድስት ወራቱ በአጠቃላይ 10.2 ሚሊዮን የአገልግሎት ሽያጭ የተከናወነ ሲሆን፣ ከእቅድ ጋር ሲነጻጸር የ112% አፈጻጸም ሲኖረው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10.1% ጭማሪ አለው፡፡

የገቢ አፈጻጸም

በስድስት ወራቱ የገቢ አፈጻጸም 85.02  ቢሊዮን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን የእቅዱን 81.1% ማሳካት ተችሏል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ 37%  ጭማሪን አሳይቷል፡፡  በስድስት ወር የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 30.4% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 28.3%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 9.7%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች የ9.7%፣ የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሳሪያዎች ሽያጭ 3.8%፣ የመሰረተ ልማት ኪራይ 2.6%፣ ቴሌብር 4.9%፣ ኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽን 4%፣ ናሽናል ኢንተርኮኔክሽን 0.8%፣ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 5.9% ድርሻ አላቸው፡፡

ለገቢው ዕድገት የደንበኞች ቁጥር መጨመር፣ በደንበኛ አጠቃቀም እድገት የትራፊክ መጨመር፣ የ4ጂ ኔትወርክ አቅም መጨመር እና መሻሻል፣ የመሰረት ልማት መስፋፋት፣ የአዳዲስ የምርት እና አገልግሎቶች አቅርቦት፣ ከአጋሮች ጋር ያለው የትብብር እድገት፣ እና የውስጥ አሰራር መዳበር፣ የሰራተኞች እና የአመራር የአቅም መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሪ እጥረት የዲቫይስ እና የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽን የገቢ አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

የውጭ ምንዛሪ ግኝት

በስድስት ወራቱ የውጭ ምንዛሪ ከማመንጨት አንፃር በተከናወኑ ተግባራት በአጠቃላይ 88.19 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ይህም የእቅዱን 83% አሳክቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ 69 ሚሊዮን ዶላር ከአለም አቀፍ አገልግሎት የተገኘ ገቢ፣ 3.16 ሚሊዮን ዶላር ከመሰረተ ልማት ማጋራት ኪራይ (Infrastracture sharing) የተገኘ ገቢ ሲሆን በቴሌብር አለም አቀፍ የሀዋላ አገልግሎት አማካኝነት ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ከ 16.02 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት የዕቅዱን 79% ለማሳካት ተችሏል፡፡ የአለም አቀፍ አገልግሎት ገቢው ከባለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ4.6 ሚሊዮን ዶላር (7.2%) ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የወጪ ቁጠባ ባህልን ማጎልበት

ኩባንያችን የወጪ ቁጠባ ባህልን ለማጎልበት የሀብት አስተዳደር እና ወጪ ቅነሳ ፕሮግራምን ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በዚህም በስድስት ወራቱ ከ 4.15 ቢሊዮን ብር በላይ የወጪ ቁጠባ በማድረግ የዕቅዱን 129% ማሳካት ተችሏል፡፡ ለዚህ ስኬት አስተዋፆ ያበረከቱት ቁልፍ ጉዳዮች ውጤታማ የሀብት አጠቃቀም ስልቶች መተግበር፣ ከአጋር አካላት ጋር መተባበር እና የዕለት ተዕለት ተግባራትን ዲጂታል ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው። ከወጪ ቁጠባ ሥራዎች ባሻገር የገቢ ምንጮችን በማበራከት ለተቋሙ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ እና ቦታ በማከራየት በአጠቃላይ ከ 89.9 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት ተችሏል፡፡ ይህም አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች እና ተረፈ-ምርቶች በወቅቱ በመወገዳቸው ከቦታ ኪራይ የተገኘ ተጨማሪ ገቢን ያካትታል፡፡

የፋይናንስ ግቦች አፈፃፀም

የፋይናንስ መግለጫዎች (Unaudited statement of profit or loss)

በስድስት ወራቱ ኩባንያው ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት የኔትወርክ መሰረተ ልማት ለመገንባት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ለማስረጽ እና ግንባር ቀደም የዲጂታል ሶሉሽን አቅራቢ ሆኖ ለመዝለቅ እንዲያስችለው ለካፒታል ፕሮጀክት በጀት 52.92 ቢሊዮን ብር እና ለመደበኛ በጀት 62.92 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበ ሲሆን ከተያዘው በጀት ውስጥ የመደበኛ በጀት 67.75% (42.63 ቢሊዮን ብር) እንዲሁም የካፒታል በጀት 33% (17.44 ቢሊዮን ብር) ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

ኩባንያችን የፋይናንሱን ጤንነት ለማረጋገጥ በዘረጋው የአሰራር ስርአት መሰረት የሂሳብ ሪፖርቱን በአለም አቀፍ የሂሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ስርአት (IFRS Based Financial report) መሰረት በማዘጋጀት፤ በውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ እስከ 2017 በጀት ዓመት እንከን አልባ (Unqualified) መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን የ2018 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ሂሳብ ምርመራ በሂደት ላይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር እንደ የደንበኛ ቁጥር፤ እለታዊ ገቢንና እለታዊ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት ያሉትን ቁልፍ አፈጻጸም መለኪያዎች በየዕለቱ ጥብቅ ክትትል ያደርጋል፡፡

በስድስት ወራቱ ገቢን በማሳደግና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በመከተል ትርፋማነቱን ለማጠናከር ባቀደው መሠረት ያልተጣራ ትርፍ (EBITDA) 42.36 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ ያልተጣራ ትርፍ ህዳግ መጠን 49.8% አስመዝግቧል፡፡ በተጨማሪም በስድስት ወራቱ ውስጥ 35.6 ቢሊዮን ብር ታክስ ለመንግስት ገቢ ተደርጓል፡፡

ቴሌብር ለአካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ

 የኅብረተሰቡን ሕይወት በማቅለል እና የሀገራችንን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ በማሳለጥ እንዲሁም በዲጂታል ፋይናንስ አካታችነት ሥር ነቀል ለውጥ በማምጣት ረገድ ኩባንያችን የቴሌብር አገልግሎትን በማቅረቡ ለአካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በዚህም የመደበኛ ባንክ አገልግሎት የተደራሽነት ክፍተት በመሙላት ዜጎች በቀላሉ በራስ አገዝ ወይም በአቅራቢያቸው በሚገኙ ወኪሎች እና በመላ ሀገራችን በሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አማካይነት የዲጂታል ፋይናንስ እና የሞባይል መኒ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል ላይ ይገኛል። በአጠቃላይ የቴሌብር አገልግሎት ዜጎች ደኅንነቱ በተጠበቀ፣ ቀላል እና ምቹ በሆነ መንገድ ዘርፈ ብዙ የዲጂታል መፍትሄዎች እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች እንዲያኙ በማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ትሩፋት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ምቹ መደላድል ፈጥሮላቸዋል።

የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር

 በግማሽ ዓመቱ 4.69 ሚሊዮን ተጨማሪ የቴሌብር ደንበኞች በመመዝገብ አጠቃላይ የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር 58.61 ሚሊዮን በማድረስ የእቅዱን 99.4% አሳክቷል፡፡ አፈፃጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 51.54 ሚሊዮን አንጻር የ13.7% እድገት አለው፡፡ የመንግስት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ፣ ከብዙ ድርጅቶች ጋር የተደረገው ውህደት፣ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ፣ ብዙ ምርትና አገልግሎት ለገበያ መቅረቡ፣ ለተጠቃሚ ምቹ የሆነ ሱፐር አፕ መልማቱ፣ የደንበኛ ምዝገባ ማበረታቻ ፣ የ127 የጥሪ ማዕከል መዘመኑ ፣ የራስ አገዝ አገልግሎት መመዝገቢያ አማራጭ መተግበሩ፣ የደንበኞችን ቁጥር መሰረት ያደረጉ የሲስተም ማስፋፊያዎች እና ማሻሻያዎች መተግበራቸው የደንበኞች ቁጥር እንዲጨምር አስችሏል።

ኩባንያችን በስድስት ወራቱ ከቴሌብር አገልግሎት 4.1 ቢሊዮን ብር ገቢ በማግኘት የእቅዱን 109.1% አሳክቷል፡፡ የገቢው ዕድገት የተመዘገበው የነባር የአገልግሎት ክፍያዎች የዋጋ ክለሳ እንዲሁም በነጻ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን ክፍያ ማስጀመር ፣ ከቴሌብር ወደ ቴሌብር ገንዘብ የመላክ መጠን ማደጉ፣ ከባንኮች እና ከሌሎች ተቋማት ጋር የተደረገ የአገልግሎት ትስስር በማደጉ፣ የተበላሹ የቴሌብር የብድር አገልግሎት ገቢ መሰብሰብ መቻሉ እንዲሁም የደንበኞች፣ የነጋዴዎችና የወኪሎች ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ነው፡፡

የቴሌብር ግብይት

በስድስት ወራቱ 1.94 ትሪሊዮን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር በቴሌብር የተከናወነ ሲሆን አገልግሎቱ ከተጀመረ ጀምሮ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ 6.88 ትሪሊየን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ተችሏል፡፡ ይህም በሀገራችን የገንዘብ ዝውውርን ዲጂታላይዝ ከማድረግ ባሻገር የፋይናንስ አገልግሎቶችን በእጅጉ አካታችና ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል፡፡

የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያችን አጋሮች ቁጥር ለማሳደግ እንዲሁም ቴሌብርን ተጠቅመው የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዚህም 175 ዋና ወኪሎች፣ 383.4 ወኪሎች እና 363.3 ሺ ነጋዴዎች የቴሌብር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወኪሎች ደንበኛ መመዝገብ፣ ገንዘብ ወጪ እና ገቢ ማድረግ፣ የአየር ሰዓት መሸጥ እና የቢል ክፍያዎችን መፈጸም እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ከ 30 ባንኮች ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ከቴሌብር ወደ ባንክ በቀላሉ ገንዘብ ማዘዋወር ተችሏል፡፡

የቴሌብር የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት

ቴሌብር አገልግሎት ለማህበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ አነስተኛ የቁጠባ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ከባንኮች ጋር በመተባበር ቀርበዋል። በግማሽ አመቱ 4.27 ሚሊዮን ደንበኞች 8.62 ቢሊዮን ብር አነስተኛ ብድር ያገኙ ሲሆን 1.24 ሚሊዮን ደንበኞች ከ8.68 ቢሊዮን ብር በላይ በቴሌብር ቆጥበዋል፡

የዘመን ገበያ (ኢኮሜርስ) አፈጻጸም

የሀገራችንን የግብይት ሥርዓት በማዘመን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ኩባንያችን ዘመን ገበያ የተሰኘ የዲጂታል ግብይት ፐላትፎርም (ኢኮሜርስ) በሥራ ላይ ማዋሉ ይታወቃል:: የዘመን ገበያን ተደራሽነትና ተቀባይነትን ከማሳደግ አንጻር የዕቃ ማድረሻ ዋጋ ላይ ማስተካከያ በማድረግ፣ በዓላትን ታሳቢ ያደረገ የዕቃ የማድረሻ ክፍያን ነፃ በማድረግ እና የእቃ ዋጋ ላይ ቅናሽ በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ የዘመን ገበያ ተጠቃሚዎችን እና የዲጂታል ግብይት ልምምድን በእጅጉ ማነቃቃት ተችሏል፡፡ በተለይም አብዛኛው ማህበረሰብ የሚጠቀምባቸውን የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እና በተሳለጠ መንገድ ለማህበረሰቡ ማድረስ እንደሚቻል እንዲሁም አምራቾች ምርቶቻቸውን በተሻለ አማራጭ ለማህበረሰቡ ማቅረብ እንደሚችሉ አመላካች ሆኗል።

ይህም ባለፉት ሰባት ወራት  506 አምራቾችና የንግድ ድርጅቶች 14,529 ምርቶችን እንዲያስተዋውቁና እንዲሸጡ ማድረግ በመቻሉ ከ33.3 ሚሊዮን በላይ የገጽ ጎብኚዎች የኢኮሜርስ ገበያውን የተመለከቱ  ሲሆን በ42,400 የግዢ  ትዕዛዞች 163,300 ምርቶችን ግብይት አከናውነዋል፡፡ በኢኮሜርስ ገበያው በንግዱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከብር 158.9 ሚሊዮን በላይ  የሚያወጣ የግብይት እንቅስቃሴ ተደርጎበታል፡፡

የሰው ኃይል አቅም ግንባታ

 የኩባንያችንን ተወዳዳሪነትና ቀጣይነት ያለውን እድገት ለማስቀጠል የሚችል በአመለካከት፣ በክህሎትና በእውቀት የዳበረ፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን የሚላመድ እና ለወደፊት ዝግጁ የሆነ የሰው ሀብት  ከመፍጠር አኳያ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ሲሆን፣ ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል የስልጠና ፕሮግራሞችን በመቅረጽ በራስ ኃይል ወይም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ስልጠና መስጠት ነው፡፡ በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የሰራተኞችን አቅም ለማሳደግ 23,963 ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን፣ ለ9,306 ሰራተኞች በአካል፣ በቨርቹዋል እና በቅንጅት እንዲሁም ለ14,657 ሰራተኞች በዲጂታል ፕላትፎርም የተሰጡ ናቸው፡፡

ኩባንያችን የሴት ሠራተኞችን ወደ አመራር ለማምጣት ስትራቴጂ ነድፎ በተግባር በመተርጎም ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ተግባራት ውስጥ የሴት አመራሮች ቁጥር ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት ያህል የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት የማካሄድ በጥናቱ መሠረት በቴክኒካል እና በኮሜርሻል ዘርፍ ላሉ ሴት የስራ አመራሮች አቅምን የሚያሳድግ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የአደረጃጀት ለውጥና የሥራ ክፍሎች ሪፎርም ሲደረግ ሴቶችን ወደ ኃላፈነት የማሳደግ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በሌላ በኩል የኩባንያችንን ምርታማነት ለማሳደግ እና አዳዲስ የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችና ቢዝነስ ሞደሎችን በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም አዳዲስ እድሎችን ለመጠቀም እና ፈተናዎችን ለመቋቋም ብሎም ወደ እድል ለመቀየር የሚያስችል ወቅታዊ የአደረጃጀት ማሻሻያ እና የሰው ኃይል ምደባ ሥራዎችን በቀጣይነት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የገቢ እና ሥራ እድል ፈጠራ

 ኩባንያችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥነ-ምህዳርን በመገንባት ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተውን ቁልፍ የአስቻይነት ሚና ከመወጣት ጎን ለጎን፣ ለዜጎች ዘላቂ የሥራ እና የገቢ ዕድል በመፍጠር ሀገራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛል። በዚህም መሠረት፣ በቋሚና በጊዜያዊ ቅጥር ለተሰማሩ 44,031 ሠራተኞች ከሚፈጠሩት ቀጥተኛ የሥራ ዕድሎች ባሻገር፤ በምርትና አገልግሎት አከፋፋይነት እና በቴሌብር ወኪልነት  449,273፣ በሀገር ውስጥ አቅራቢነት (Local Suppliers)  1,648፣ በቫስ (VAS) አጋርነት ለ 1,203፣ በፈቃድ/ፍራንቻይዝ አጋርነት ለ 140 እንዲሁም በአለም አቀፍ አጋርነት  668 አጋሮች በሰፊ የሥራ ዘርፎች የሥራና የገቢ ዕድል እንዲፈጠር አስችሏል።

በአጠቃላይ በዕድገት ስትራቴጂ ዘመን በጥበቃ፣ በኔትዎርክ ዝርጋታ፣ በጥገና፣ በትራፊክ ቁጥጥር፣ በኮንስትራክሽን ስራ፣ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ እና በሦስተኛ ወገን በኩል በተፈጠሩ ቋሚና በጊዜያዊ የሥራ መደቦች እንዲሁም በመደበኛ እና በቴሌብር ምርትና አገልግሎት አከፋፋይነትና አጋርነት ሥራዎች፤ በድምሩ በሥነ-ምህዳሩ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ 1.3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራና የገቢ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህም ኩባንያችን ከ 497 ሺህ በላይ የሥራ ስምምነቶች (Agreements) በማድረግ የኢኮኖሚ አቅምን በማጎልበት ረገድ ያለውን ሚና ያሳያል።

የሳይበር ደህንነት

ኩባንያችን በፍጥነት እያደገ ለሚገኝ የዲጂታል አገልግሎት የሳይበር ጥቃት ትልቅ ተግዳሮት በመሆኑ ችግሩን በተጠናከረ መልኩ መከላከል እንዲቻል የኩባንያችንን የሰው ሃይል አቅምን በመገንባት፣ የአሰራር ሂደትን በማዘመን እና እጅግ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ የተሞከሩበትን ጥቃቶች በመመከት የኩባንያችንን ዋና ዋና አሴቶች ሊገጥማቸው ከነበሩ የዳታ መመዝበር፣ የአገልግሎት መቋረጥ እና የገቢ ብክነትን መከላከል ተችሏል፡፡ ሁሉንም ጥቃቶች ያለምንም ጉዳት መመከት የተቻለው 24/7 የሳይበር ደህንነት ቁጥጥር ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ፣ የኩባንያውን ዋና ዋና ሲስተሞችን ደህንነት በጠበቀ ሁኔታ ለማስተዳደር ቴክኖሎጂን ያማከለ የሲስተሞች የመግቢያ ፈቃድ አሠጣጥ መተግበሩ እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የጥቃት ሙከራዎችን አስቀድሞ መለየት መቻሉን በዋነኛነት መጥቀስ ይቻላል።

በገቢ ብክነት ቅነሳ ረገድም ኩባንያችን ቀጣይነት ያላቸው የክትትልና እርምጃ የመውሰድ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ ከማጭበርበር የሚባክነውን ከገቢ 0.15% በታች ለማድረስ ታቅዶ ወደ 0.13% ዝቅ በማድረግ ከ115% በላይ ስኬት አሳይቷል። ይህ የተገኘው የማጭበርበር ባህሪያትን በመረዳት፣ አስቀድሞ በመከላከል፣ የማያቋርጥ ትንተናና ክትትል በማድረግ ነው።

ከመረጃ ደህንነትና ማጭበርበር ጋር በተያያዙ የደንበኛ ቅሬታዎች ላይ ምላሽ የመስጠት ፍጥነት ወደ 2.1 ሰዓታት ዝቅ በማድረግ 23,578 ቅሬታዎችን በወቅቱ ለመፍታት ተችሏል። ከባለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከነበረው 2.28 ሰአት ጋር ሲነፃፀር መሻሻል አሳይቷል፡፡ በኔትዎርክና ሲስተም አቅም ማሳደግ ረገድ፣ የደህንነት ሲስተሞችን የመገኘት መጠን (Availability) በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ፣ የተለያዩ የጥገና ማስተካከያ ስራዎች እና የሲስተም ማሻሻያዎች የሲስተሞችን አቅም እና ተደራሽነት በማሳደግ እየጨመረ የመጣውን የመረጃ መጠንና የሳይበር ስጋቶችን በብቃት መቋቋም ተችሏል።

በቴሌኮም መሠረተ ልማት አጠባበቅ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ ውይይት የተደረገ ሲሆን ጉዳትን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ ተቀናጅቶ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ እያጋጠሙ ያሉትን የመሰረተ ልማት ጉዳቶችን ለመቅረፍ ለ 471 ሺ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የጸጥታ አካላትና በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት አመራር አካላት በቴሌኮም መሠረተ ልማት አጠባበቅ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተከናውኗል፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት

ኩባንያችን የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የCSR ስራዎችን በተደራጀ ሁኔታ በማቀድ የሀገርን እና የዜጎችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ከዘላቂ የልማት ግቦች (SDGs) ጋር የተንሰላሰለ እና በጥናት የተደገፈ ተግባራት በመላ ሀገሪቱ እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም በዋነኛነት የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግን፣ የዲጂታል ግንዛቤን ክፍተትን ማጥበብን፣ አካታችነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ልማት ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢያዊ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡

በግማሽ ዓመቱ በዓይነት 74.9 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በገንዘብ 308.5 ሚሊዮን ብር በድምሩ 383.46 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ የተደረገ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ለትምህርት 117.55 ሚሊዮን ብር፣ ለጤና 9.66 ሚሊዮን ብር፣ ለሰብአዊ 81.62 ሚሊዮን ብር፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአረንጓዴ ልማትና ማስዋብ 19.87 ሚሊዮን ብር እና ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች 154.79 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ኩባንያችን የአካባቢ ብክለትን በመከላከልና ለማህበረሰባችን ንጹህ እና ለኑሮ ተስማሚ አካባቢን በመፍጠር ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት እና እድገት ባለው ቁርጠኝነት የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲካሄድ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ቁርጠኝነት በማሳየት የኩባንያችንን ሰራተኞችና አጋሮቻችንን በማሳተፍ በመላው አገሪቱ ችግኞች እንዲተከሉ አድርጓል፡፡

ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየት የ1.16 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታ እና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አፈጻጸም

የኢትዮጵያን የዲጂታል ዕድገት ለማቀላጠፍ የዲጂታል መታወቂያ ወሳኝ እንደመሆኑ ኩባንያችን የምዝገባ እና ህትመት ሂደቱን በመላ ሀገሪቱ የማፋጠንና የማስፋፋት ሥራን በልዩ ትኩረት ማከናወኑን አጠናክሮ በማስቀጠል የተሰጠውን ሀገራዊ ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡ በዚህም የምዝገባ ሥራውን ተደራሽ ለማድረግ ከ 3500 በላይ የመመዝገቢያ መሣሪያዎችን በመጠቀም በመላው የአገሪቱ ክፍሎች ማለትም በ 12 ክልሎች፣ በ2 ከተማ አስተዳደሮች፣ በ 119 ዞኖች፣ በ 867 ወረዳዎች እንዲሁም ከ 1120 በላይ ከተሞች ላይ ተደራሽ በመሆን ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል፡፡

የምዝገባ ሥራው የተሳለጠ እንዲሆን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ ያማከለ ለማድረግ የመዝጋቢ ባለሙያዎች ቅጥር ከሁሉም የክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመቀናጀት እና የአካባቢውን ተወላጆች በማካተት ሰፊ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም ከ 3200 በላይ ሠራተኞችን በመቅጠር፣ አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት፣ ተገቢውን የአቅርቦት ሥራ በማከናወን እና በየጊዜው የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ቋሚ የሆነ የቴክኒካል እና የድጋፍ ሰጭ ቡድን በማቋቋም ያልተቋረጠ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በዚህም እንደሀገር ከተመዘገቡት 32 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም 22 ሚሊዮን ዜጎችን በመመዝገብ የአጠቃላዩን ምዝገባ 69% ያከናወነ ሲሆን በባለፈው ግማሽ የበጀት ዓመት አፈፃፀም እንደሀገር ከተመዘገቡት 12 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም 10.8 ሚሊዮን ዜጎችን በመመዝገብ የአጠቃላዩን ምዝገባ 90% በማከናወን የአንበሳውን ድርሻ ይዟል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞችን ፍላጎት ባማከለ መልኩ እና በአገልግሎቱ ላይ መተማመንን ለመፍጠር እንዲቻል 24 የመታወቂያ ህትመት መሣሪያዎችን በስራ ላይ በማዋል እና ከ340 በላይ ማከፋፈያ ቦታዎች በማዘጋጀት እና ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የስርጭት ሂደቱን በሲስተም በመደገፍ በአሁኑ ሰዓት 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የታተመ መታወቂያ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት ማቅረብ (Oversea Operation)

ኩባንያችን “Next Horizon: Digital and Beyond 2028” ዕቅዱ ውስጥ አንደኛው ግብ ከሀገር ውጭ ወጥቶ መስራትና በአፍሪካ የዲጂታል ሶሉሽን መሪ ተቋም መሆንን ያካትታል፡፡ በዚህም መሠረት በተለያዩ አገራቶች ከሚገኙ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት በርካታ የቢዝነስ ግንኙነቶችን እያከናወነ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ አንዱ በካሜሮን ሀገር ከሚገኘውና በመንግስት ሥር ከሚተዳደረው ካምቴል (CAMTEL) ከተባለው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ጋር ነው፡፡

የዚህ አጋርነት መነሻ ኢትዮ ቴሌኮም ራሱን ከመደበኛ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ወደ ቴክኖሎጂ ኩባንያ (TechCo) ለመለወጥ የነደፈው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ሲሆን፣ በተለይም የዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽነትን ማስፋፋት፣ ከመደበኛ የድምፅና ዳታ ግንኙነት ባለፈ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የዲጂታል ፕላትፎርሞች ማቅረብ እና የቴሌብርን (telebirr) ስኬታማ ሥነ ምህዳር መሠረት በማድረግ የፋይናንስ፣ የማኅበራዊ እና የመንግስት አገልግሎቶችን ማቀናጀትን ያካተተ ነው፡፡

ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሄ  እርምጃዎች

በግማሽ ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ዋና ዋና ተግዳሮቶች አጋጥመዋል፡፡ በተለይም የፋይናንስ እጥረት፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት፣ የገበያ ዋጋ መለዋወጥና ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ በልማት ሥራ፣ በአደጋ፣ በጸጥታ ችግሮች፣ በኬብል ስርቆት እና በቴሌኮም መሠረተ ልማት ላይ የደረሱ ጉዳቶች፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥና የነዳጅ እጥረት ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ እነዚህን ተግዳሮቶች ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የፋይናንስ አማራጮች በማፈላለግ፣ ከፌዴራል እና ክልል የመንግሥት አካላት ጋር በቅርበት በመሥራት መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ተደርጓል፡፡

ለተመዘገበው ስኬት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ጉዳዮች

ኩባንያችን ላስመዘገበው ስኬት የጠራ ራዕይ ያለው አመራር እና ቀልጣፋ አስተዳደር፣ የሰራተኞች ቁርጠኝነትና መናበብ፣ ውጤታማ የፕሮጀክት አመራር እና አፈጻጸም፣ተቋማዊ ቅልጥፍና እና ውጤታማ ስትራቴጂ፣ ጠንካራ ሽርክናዎች እና የባለድርሻ አካላት አስተዳደር፣ የደንበኞቻችን ከእኛ ጋር የመቆየት ፍላጎት፣ የኩባንያችን ማህበራዊ ኃላፊነት እና መልካም ዝና፣ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ባላቸው ቴክኖሎጂዎችና ፕላትፎርሞች ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶችና ትግበራዎች እንዲሁም የፋይናንስ ዘላቂነት እና የወጪ ቁጠባ ስራዎች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

እውቅና እና ሽልማት

ኩባንያችን ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ እውቅናዎችን እና ሽልማቶችን ያገኘ ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹም፡

  • የኢትዮ ቴሌኮም የዳይሬክተሮች ቦርድ ለኩባንያችን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ላሳዩት የላቀ አመራር እና ጠንካራ ቁርጠኝነት እና በድርጅታችን የለውጥ ጉዞ ስኬት እውቅና ሰጥቷቸዋል።
  • ዘመን ገበያ በዲጂታል ንግድ (ኢ-ኮሜርስ) ዘርፍ ላስመዘገበው የላቀ አፈጻጸም ከኢትዮጵያ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፍተኛ እውቅናና ሽልማት ተበርክቶለታል።
  • ኩባንያችን የግድቡን መጠናቀቅ ተከትሎ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ላለፉት ዓመታት ለ“የይቻላል ተምሳሌትባደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ የሞባይል ተጠቃሚዎች በ8100-A እና 8120 አጭር መልእክት በመላክ ደስታቸውን እንዲገልጹ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ መላው ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን እንዲያሳርፉ በማስቻሉ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡
  • PCI DSS (የክፍያ ካርድ ኢንዱስትሪ የደህንነት ስታንዳርድ):-የPCI DSS የብቃት ማረጋገጫ መታደስ የኢትዮ ቴሌኮምን የፋይናንስ ሥርዓት በተለይም የቴሌብርን እና የሌሎች ዲጂታል ክፍያዎችን አስተማማኝነት የሚያጠናክር ትልቅ ስኬት ነው። ተቋሙ እነዚህን ጥብቅ ዓለም አቀፍ የደህንነት መስፈርቶች በማሟላቱ፣ ደንበኞች ስስ (Sensitve) ለሆኑ የፋይናንስ መረጃዎቻቸው ከፍተኛ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ይሰጣል፤ ይህም ከክፍያ ጋር የተያያዙ ስጋቶችን በማስቀረት ሙሉ የደንበኛ እምነትን ይገነባል።
  • በኢትዮጵያ ውስጥ የGSMA ሞባይል መኒ ሰርቲፊኬት ያገኘ የመጀመሪያ እና ብቸኛ ኩባንያ ስንሆን፣ ይህም ሰርቲፊኬሽን በልዩ ሁኔታ ለሞባይል መኒ አገልግሎቶች የተነደፈ ብቸኛው ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ነው፡፡ በመጀመርያ መንፈቅ ዓመት 280 የሚሆኑ የግምገማ መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ አሟልተናል፡፡ ይህም በአገሪቱ የዲጂታል ፋይናንሽያል አገልግሎት ገበያ ውስጥ ያለንን ተወዳዳሪነትና ተቀባይነት በከፍተኛ ደረጃ ያጠናክራል።

በመጨረሻም በግማሽ ዓመቱ የተመዘገበው ስኬት የጋራ ርብርብ ውጤት በመሆኑ ለውድ የኩባንያችን ቤተሰቦች፤ ለክቡራን ደንበኞቻችን እንዲሁም ስትራቴጂያዊ አጋሮቻችን ለሆናችሁ አከፋፋዮች፣ አቅራቢዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና ለመላው ባለድርሻ አካላት ልባዊ ምስጋናችን እያቀረብን የጀመርነውን የሃገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አጠናክረን በመቀጠል ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ እናረጋግጣለን።

 

ኢትዮ ቴሌኮም

ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives