ኢትዮ ቴሌኮም እና አዋሽ ባንክ በቴሌብር “ጥላ” የተሰኘ ያለዋስትና (non-collateral) የዲጂታል ፋይናንስ እና የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎቶችን አስጀመሩ!

የቴሌኮም እና ዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ ታላቅ ሀገርና ሕዝብ በማገልገል ላይ የሚገኘው ኩባንያችን፣ በሀገራችን ሁሉን አቀፍ የኮሙኒኬሽን እና የዲጂታል ጉዞ የሚያበረክተውን ቁልፍ ሚና አጠናክሮ በመቀጠል፣ ከመደበኛ የቴሌኮም ግንኙነት ባሻገር በዲጂታል ሶሉሽኖችና ዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ ጉልህ ሚና በመጫወት ለሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መፋጠን የበኩሉን በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም ኩባንያችን በቴሌብር ዲጂታል አገልግሎት 57.59 ሚሊዮን ደንበኞችን ከማፍራት ባሻገር አገልግሎቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለማህበረሰባችን ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አነስተኛ የዲጂታል ያለዋስትና ብድርና የቁጠባ አገልግሎቶችን ከአጋር ባንኮች ጋር በመተባበር በግንባር ቀደምነት በማስተዋወቅ ለ15 ሚሊዮን ደንበኞች ከ31.6 ቢሊዮን ብር በላይ የዲጂታል ብድር አገልግሎት አቅርቧል፡፡ እንዲሁም ከ4.71 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ከ30.3 ቢሊዮን ብር በላይ በቴሌብር ለመቆጠብ እንዲችሉ አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን በ“ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከ2028 ባሻገር ስትራቴጂ” የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ከአጋር አካላት ጋር በስፋት ለማቅረብ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣ በኢትዮጵያ የግል ባንክ ታሪክ ፈር ቀዳጅ ከሆነው አዋሽ ባንክ ጋር በመተባበር፣ “ጥላ” የተሰኘ ያለዋስትና ብድር እንዲሁም በረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጭ የስማርት ስልክ ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ማስጀመሩን በደስታ ያበስራል።

ጥላ” አነስተኛ ያለዋስትና (non-Collateral) የብድር እና የቁጠባ አገልግሎት፤ በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ የግለሰብ ደንበኞች፣ ደመወዛቸው በቴሌብር እና በአዋሽ ባንክ የሚከፈላቸው የግል እና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች እንዲሁም አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች/ነጋዴዎች፤ የቴሌብር አገልግሎቶች ተጠቃሚ በመሆናቸው ብቻ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በሚታገዝ የብድር ቀመር ስሌት (Credit Score) የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡

በጋራ ይፋ የተደረጉት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች የሚከተሉት ሲሆኑ ለእነዚህም የብድር አገልግሎቶች በዓመት በጠቅላለው ከ2 ቢሊየን ብር በላይ የሚደርስ የብድር አቅርቦት ስምምነት ተደርጓል፡፡

  1. የቁጠባ አገልግሎት

 ይህ አገልግሎት ደንበኞች በቴሌብር አማካኝነት ከወለድ ነጻ (non-interest bearing) ወይም የወለድ ምጣኔ የሚታሰብባቸው (interest bearing) የቁጠባ አማራጮችን በመጠቀም፣ በየትኛውም ቦታ ሆነው ማንኛውንም መጠን ያለው ገንዘብ እንዲቆጥቡ የሚያስችል አማራጭ ነው።

  1. የግለሰብ ደንበኛ ብድር አገልግሎት

ይህ አገልግሎት የግለሰብ ደንበኞች በቴሌብር በሚያደርጉት የግብይት መጠን ላይ ተመስርቶ እስከ 16,000 ብር የሚደርስ የአነስተኛ ብድር (personal micro credit) አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፣

  • በ15 ቀን የክፍያ ጊዜ የሚመለስ እስከ 5,000 ብር የሚደርስ ብድር
  • በ40 ቀን የክፍያ ጊዜ ውስጥ የሚመለስ እስከ 12,000 ብር የሚደርስ ብድር እንዲሁም
  • በ75 ቀን የክፍያ ጊዜ ውስጥ የሚመለስ እስከ 16,000 ብር የሚደርስ ብድርን ያለዋስትና በማቅረብ የአነስተኛ ብድር አገልግሎቶችን ባሉበት ሆነው በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላል።
  1. የሠራተኞች የደመወዝ ብድር

የኢትዮ ቴሌኮም እና የአዋሽ ባንክ ሰራተኞችን ጨምሮ ወርሃዊ ደመወዛቸው በቴሌብር እና በአዋሽ ባንክ ለሚከፈላቸው የግል እና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ በ16 ወራት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የስድስት ወር ደመወዛቸውን እስከ 1 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል አማራጭ ነው።

  1. ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የሚቀርብ ብድር

አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች/ነጋዴዎች እንዲሁም ወኪሎች አነስተኛ ንግድ/ቢዝነስ እንዲጀምሩ ወይም እንዲያስፋፉ እና ተጨማሪ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ የሚያስችል ያለዋስትና የሚቀርብ የአነስተኛ ብድር ሲሆን፣ በቴሌብር በሚያደርጉት የግብይት መጠን ላይ ተመስርቶ ፡-

  • እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ የአንድ ወር የብድር ጊዜ ያለው አቅርቦት፤
  • እስከ 90 ሺህ ብር የሚደርስ የሶስት ወር የክፍያ ጊዜ ያለው የብድር አቅርቦት፣ እንዲሁም
  • እስከ 150 ሺህ ብር የሚደርስ የስድስት ወር የክፍያ ጊዜ ያለው የብድር አቅርቦት ያለዋስትና የሚያገኙ ይሆናል።
  1. የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎት 

ኩባንያችን ከአዋሽ ባንክ ጋር ስማርት ስልኮችን በተለያዩ የረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጮች ለዜጎች ለማቅረብ የዲቫይስ ፋይናንሲንግ ስምምነት ላይ በመድረስ፣ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። አገልግሎቱ በተለይም በግብርና የተሰማሩ ዜጎችን ጨምሮ፤ ሰራተኞች፣ ነጋዴዎችና ወኪሎች የተለያዩ የቴሌኮም መገልገያ መሳሪያዎችን (devices) በረጅም ጊዜ ክፍያ (installment) ከሲም ካርድ ጋር እንዲያገኙ ያስችላል።

የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎት፣ በስማርት ስልኮች ዋጋ ከፍተኛ መሆን ምክንያት የዲጂታል እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማግኘት ላልቻሉ ዜጎች፣ በተመጣጣኝ ዋጋ እና በረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጮች ስማርት ስልክ እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባሻገር፤ አገልግሎቱ የፋይናንስ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ሳይሆን በቆየባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖረው የአርሶ እና አርብቶ አደር ማህበረሰብ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን አካታች እና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

  1. ያለካርድ ገንዘብ ማውጣት እና የስኩል ፔይ

ለደንበኞች የተሻለ ተሞክሮ እና ሞቾት ለመፍጠር በማለም ቴሌብርን ብቻ ተጠቅመው ከአዋሽ ባንክ ኤቲኤም (ATM) በቀላሉ ገንዘብ ማውጣት የሚችሉበት አሰራር ላለፉት ጥቂት ወራት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ እስከ አሁን በአጠቃላይ ከ 92.6 ሺህ በላይ በተደረገ የገንዘብ እንቅስቃሴ (transactions) ከ 97.3 ሚሊዮን ብር በላይ በአገልግሎቱ ወጪ (withdraw) ማድረግ ተችሏል፡፡ እንዲሁም በቴሌብር ሱፐርአፕ አዋሽ ባንክ “ስኩል ፔይ”ን (School Pay) በማካተት የትምህርት ቤት ክፍያዎችን ለማከናወን የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

ኩባንያችን የስማርት ስልክ ስርጸትን በመጨመር የዲጂታል እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማሳደግ በማቀድ፣ በቅርቡ “ዘኔክሰስ” የተሰኙ ክላውድን መሰረት ያደረጉ ስማርት ዲቫይሶችን በቅናሽ ዋጋ ያቀረበ ሲሆን፤ በቀጣይም ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን አጋርነትም በማስፋት የአጠቃቀም ክፍተትን ለማጥበብ የሚያስችሉ የዲጂታል ፋይናንስ እና ዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ፣ አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።

 

ኢትዮ ቴሌኮም እና አዋሽ ባንክ

ህዳር 11 ቀን 2018 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives