teleStream: SMART Streaming Powered by Ethiopia’s Digital Backbone!
ኩባንያችን የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን፣ የዲጂታል አካታችነትን፣ የሥራ እድል ፈጠራን፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ለሀገራችን ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም ኩባንያችን በአህጉራዊ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳደግ ያለመ “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” ቀርጾ እየተገበረ ይገኛል።
በተለይም በየጊዜው የሚለዋወጠውን ቴክኖሎጂ በፍጥነት በመላመድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ፣ ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር በሀገራችን እና ከዚያም ባሻገር ፈጠራ የታከለባቸው ዲጂታል ሶሉሽን እና የቴሌብር ፋይናንስ አገልግሎት ፈር ቀዳጅነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚው አዳዲስ ዕድሎችን በመክፈት ሁሉንም የማህብረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን በስፋት በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን የዚህ ስትራቴጂ አካል የሆነ፣ የሀገራችንን የሚዲያ ስነ-ምህዳር በእጅጉ የሚቀይር “ቴሌስትሪም” የተሰኘ በኢንተርኔት የሚሰራ የይዘት ስትሪሚንግ አገልግሎት እንዲሁም የመደበኛ ብሮድባንድ አገልግሎት አሰጣጥን ሙሉ በሙሉ የሚያዘምን የፊክስድ ብሮድባንድ (ዋይ ፋይ) አገልግሎት “ንክኪ-አልባ ዲጂታል አሰራር” ይፋ ማድረጉን ሲገልጽ በታላቅ ደስታ ነው፡፡
- የሀገራችንን የሚዲያ ስነ-ምህዳር በእጅጉ የሚቀይረውን የ“ቴሌስትሪም” (teleStream) አገልግሎት
ኩባንያችን ያሉትን ዘመናዊ የፋይበር፣ የ4ጂ እና የ5ጂ የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማቶች፣ የቴሌ ክላውድ እንዲሁም የቴሌብር ዲጂታልና የክፍያ ስነ-ምህዳር እንደ አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም በዛሬው ዕለት ተግባራዊ ያደረገው የ“ቴሌስትሪም” አገልግሎት፤ የዜጎችን የዲጂታል አኗኗር ዘይቤ ከማዘመን ባለፈ ለተጠቃሚዎች የላቀ የቴክኖሎጂ ተሞክሮን የሚያበረክትና የሀገራችንን የሚዲያና መዝናኛ ስነ-ምህዳር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።
የቴሌስትሪም አገልግሎት፤ በኩባንያችን የፋይበር እና የቴሌ ክላውድ መሰረተ ልማት የሚቀርብ በመሆኑ፤ ዝቅተኛ መዘግየት (low latency) እና እጅግ የላቀ የስርጭት ጥራት ያለው ሲሆን፤ ተጠቃሚዎች ያለ ሳተላይት ዲሽ ጥራት ያላቸው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ይዘቶችን በቤታቸው ባለው የብሮድባንድ ኢንተርኔት ዋይ ፋይ (Wi-Fi) በቀላሉ እንዲመለከቱ ያስችላል። ይህም የአየር ሁኔታ ሳይበግረው ጥራቱን የጠበቀና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲገኝ ያደርጋል።
በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የቀጥታ ስርጭት ቻናሎችን እና ከ350 በላይ በፍላጎት የሚታዩ ቪዲዮዎችን የያዘው የቴሌስትሪም አገልግሎት፤ በመደበኛ ብሮድባንድ፣ በሲም ካርድ እንዲሁም የ‘Set Top Box’ (STB) መሣሪያን በመጠቀም የስትሪሚንግ አገልግሎት ከማቅረብ ባሻገር፣ ስማርት ያልሆኑ ቴሌቪዥኖችን ወደ ስማርትነት በመቀየር ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህም ዘመናዊ የዲጂታል መዝናኛን ለእያንዳንዱ ቤት ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
ቴሌስትሪም ለሀገራችን የሚዲያና የመዝናኛ ስነ-ምህዳር ተዋንያን አዲስ የዕድገት አድማስ የከፈተ ሲሆን፤ በዚህም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ የፕሮዳክሽን ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የፊልም አዘጋጆችና ተዋንያን እንዲሁም በትምህርት፣ በጤና እና በማህበረሰብ እሴት ግንባታ ላይ የሚሰሩ አካላት የሀገራችንን ብሄራዊ እሴት የጠበቁ ይዘቶቻቸውን በስፋት ተደራሽ የሚያደርጉበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሰፊ ስትራቴጂያዊ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።
አገልግሎቱ በሀገራችን እስካሁን የነበረውን የሳተላይት ዲሽ ጥገኝነት የሚቀይርና እጅግ የላቀ አማራጭ ይዞ የመጣ ሲሆን፤ ስርጭቶችን በአገር ውስጥ በሚገኘው የኩባንያችን ቴሌ ክላውድ በማስተናገድ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ዜናዎችን፣ የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራሞችን፣ ትምህርታዊ ይዘቶችን፣ ፖድካስቶችን እና ፊልሞችን ያለ ምስል መቆራረጥ ለማስተላለፍ ያስችላል። በተለይም የሀገራችንን ባህል፣ እሴትና ስነ-ምግባር መሰረት ያደረጉ ይዘቶችን ለኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ተደራሽ ያደርጋል።
የቴሌስትሪም አገልግሎት ለግለሰቦች፣ ለቢዝነስ ተቋማት እና ለሀገር የሚሰጣቸው ዘርፈ-ብዙ ፋይዳዎች በዋናነት በሚከተሉት አምስት ነጥቦች፡-
- ለግለሰቦችና ለቤተሰቦች
አገልግሎቱ ለግለሰቦችና ለቤተሰቦች እጅግ የላቀ የዲጂታል መዝናኛ ተሞክሮን የሚያበረክት ሲሆን፤ በኩባንያችን ዘመናዊ የፋይበር መሰረተ ልማት የሚቀርብ በመሆኑ ተጠቃሚዎች በማንኛውም የአየር ሁኔታ የማይበገረውን እጅግ ጥራት ያለው እስከ 4K የሚደርስ የሚደርስ የምስል ስርጭት በቤታቸው ባለው ዋይ ፋይ ኢንተርኔት በቀላልና ምቹ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡
በተጨማሪም የሀገራችንን ባህል፣ እሴትና ስነ-ምግባር መሰረት ያደረጉና ለቤተሰብ የሚመጥኑ፣ ለልጆች የሚሆኑ አስተማሪ ይዘቶችን፣ ፊልሞችንና መዝናኛዎችን ከታመነ የይዘት ምንጭ ጋር የሚያቀርብ ሲሆን፤ የወላጆች ቁጥጥር ሥርዓት መካተቱ አገልግሎቱን አስተማማኝና ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
- ለሚዲያ ተቋማትና ለፈጠራ ባለሙያዎች
አገልግሎቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለሳተላይት ኪራይ የሚከፍሉትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት በሀገር ውስጥ መሰረተ-ልማት ስርጭታቸውን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል፡፡ ለፊልም ባለሙያዎች፣ ለጸሃፊዎችና ለተዋንያን ደግሞ ስራዎቻቸውን በቀጥታ ለሚሊዮን ተመልካቾች የሚያቀርቡበትና ገቢ የሚያገኙበት ምቹ መድረክ ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም ይዘት አቅራቢዎች በቴሌስትሪም ስራዎቻቸውን በፍጥነት በነጻም ሆነ በክፍያ ለተመልካች ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን፤ ለማስታወቂያ ድርጅቶችና ብራንዶችም ለታለመለት ተጠቃሚ የሚደርሱ (Targeted Ads) ማስታወቂያዎችን ለማስተላለፍ አዲስ እድል ይፈጥራል፡፡
- ለቢዝነስ ተቋማት እና ለሆቴሎች
ለቢዝነስ ተቋማት እና ኢንተርፕራይዞች፣ በተለይም ለሆቴሎች እና ለእንግዳ ማረፊያዎች ቴሌስትሪም እጅግ ተመራጭና ዘመናዊ መፍትሄ ነው፡፡ ሆቴሎች ለዓለም አቀፍ እና ለአገር ውስጥ እንግዶቻቸው ከፍተኛ ጥራት ያለው የመዝናኛ ተሞክሮ ማቅረብ እንዲችሉ የሚረዳ ሲሆን፤ ይህም በእንግዳ መቀበያ ቦታዎች፣ በመኝታ ክፍሎች እና በሎቢዎች አስተማማኝና ከፍተኛ ፍጥነት ካለው ኢንተርኔት እና ከቴሌ ክላውድ (telecloud) ደህንነት ጋር የተሳሰረ የመረጃ ስርጭት እንዲኖር ያስችላል፡፡
- ለመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት
አገልግሎቱ ለመንግስት ተቋማት፣ ለትምህርትና ለጤና ዘርፎች ሰፊ ጠቀሜታ ያለው የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለትምህርታዊ ቪዲዮዎች ስርጭት የላቀ አቅም ከመፍጠሩም በላይ በሆስፒታሎች ውስጥ ለታካሚዎች ግንዛቤ ማስጨበጫና መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ያገለግላል፡፡ በተጨማሪም መንግስታዊ ተቋማት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የግብርና፣ የጤና እና ሌሎች ስራዎቻቸውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ በማድረግ ለማህበረሰባዊ እድገት የላቀ ሚና እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል፡፡
- ለስማርት ሲቲ እና ሀገራዊ የዲጂታል ሉዓላዊነት
ቴሌስትሪም የሳተላይት ዲሾችን በማስቀረት ለዘመናዊ የከተማ ውበትና ለስማርት ሲቲ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከመሆኑ ባሻገር፤ ይዘቶችን በአገር ውስጥ የቴሌ ክላውድ መሰረተ-ልማት በማስተናገድ ከውጭ ሀገር የሳተላይት አቅራቢዎች ጥገኝነት በመቀነስ ሀገራችን በመረጃ ፍሰቷ ላይ የዲጂታል ሉዓላዊነት (Digital Sovereignty) እንዲኖራት ያግዛል፡፡ በተጨማሪም በአገር ውስጥ በዲጂታል መሰረተ-ልማት አማካኝነት ይዘቶችን በማሰራጨት በዘርፉ በርካታ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩና የሀገራችን ዲጂታል ምህዳር ይበልጥ እንዲጎለብት ያደርጋል።
- በፋይበር መሰረተ ልማትና በዲጂታል አሰራር የዘመነው ዋይ ፋይ አገልግሎት
ኩባንያችን ኢትዮ ቴሌኮም 14,413 ኪ.ሜ የሜትሮ ፋይበር እና 1.2 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የፋይበር ኔትወርክን ከመገንባት ባሻገር የመደበኛ ብሮድባንድ አገልግሎቱን ለማዘመን ነባሩን የኮፐር ኔትወርክ በዘመናዊ የፋይበር ኔትወርክ የመተካት (Copper switch-off) ፕሮጀክት በስፋት ተግባራዊ በማድረግ እስካሁን ከ79 ሺህ በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ለዕለት ተዕለት ሥራዎችና ለላቁ ሲስተሞች የሚፈለገውን ከፍተኛ ፍጥነት በማረጋገጥ ደንበኞች አሠራራቸውን እንዲያቀላጥፉ አስችሏቸዋል፡፡
ኩባንያችን ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት በቀጥታ ደንበኛው እስከሚፈልግበት ክፍል ድረስ ለማቅረብ የሚያስችለውን የ“ፋይበር ቱ ዘሩም” (FTTR) አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ይህም ለቢሮና ለመኖሪያ ቤቶች እጅግ አስተማማኝ፣ እንደ ክላውድ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ስማርት ሆም ላሉ የላቁ የዲጂታል አገልግሎቶች ምቹ ሁኔታን እንዲሁም እጅግ ዝቅተኛ መዘግየት (Ultra-low latency) ያለውንና ጥራት ያለው ኢንተርኔት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ያደርጋል፡፡
በተጨማሪም ኩባንያችን የመደበኛ ኢንተርኔት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የሚያስችል የዲጂታል ሲስተም (Operation Support System) ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን ይህ ስርዓት የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን “ንክኪ-አልባ” (Zero-touch) በማድረግ የደንበኞችን ተሞክሮ በእጅጉ ያሻሽላል፡፡ ይህም የኩባንያችን “የቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂን እውን ለማድረግና የአገልግሎት ጥራትን በላቀ ደረጃ ለማስጠበቅ የሚያስችል ሁሉን-አቀፍ የዲጂታል ሲስተም ነው፡፡
ደንበኞች ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መሄድ ሳይጠበቅባቸው በቴሌብር ሱፐርአፕ አማካኝነት አዲስ የዋይፋይ ወይም የጥምር አገልግሎት ጥያቄዎችንና የብልሽት ምዝገባን በዲጂታል ማከናወን ይችላሉ። በመልክዓ ምድራዊ መረጃ ሥርዓት (Web-GIS) እና በንክኪ-አልባ (Zero-touch) ቴክኖሎጂ የታገዘው ይህ ሲስተም፤ ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ሲሆን፣ ለአገልግሎቱም የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (National ID/Fayda) እና የቴሌብር አካውንት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ ሁሉን አቀፍ የብሮድባንድ እና ቴሌስትሪም አገልግሎቶች ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍቱና ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሚጥሉ ሲሆን ኩባንያችን ዘመናዊ የዲጂታል መፍትሄዎችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን የዲጂታል አኗኗር ዘይቤ ከመቀየር ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የዲጂታል 2030 ራዕይ ወደ ተጨባጭ ስኬት የሚያሸጋግር ነው፡፡
ክቡራን እና ክቡራት ደንበኞቻችን፤ ቴሌስትሪም አገልግሎትን ከብሮድባንድ ኢንተርኔት ጋር በጥምር በቴሌብር ሱፐርአፕ ዘመን ገበያ ወይም በአቅራቢያዎ በሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላችን በልዩ ቅናሽ፤ እንዲሁም ዘመናዊውን የዋይ ፋይ አገልግሎታችንን በቴሌብር ሱፐርአፕ ‘ቴሌ-ኦንላይን ፊክስድ ሰርቪስ’ ሚኒአፕ እንዲያገኙ እንጋብዛለን።
ኢትዮ ቴሌኮም
የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም



