ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ግሩፕ ከፍተኛ አቅም ያለው ድንበር ተሻጋሪ “መልቲ-ቴራቢት” የኦፕቲካል ፋይበር መሠረተ ልማትን ለመዘርጋት የሚያስችል ታሪካዊ የሦስትዮሽ ስትራቴጂያዊ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል። ይህ ስምምነት በ”ሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ” (Horizon Fiber Initiative) አማካኝነት የቀጣናውን ዲጂታል ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ትልቅ ስኬት ነው።
ስምምነቱ በዋናነት በጅቡቲ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የባሕር ውስጥ ኬብል ማረፊያ ጣቢያዎችን በኢትዮጵያ በኩል በማሳለፍ ከሱዳን ማረፊያ ጣቢያዎች ጋር የሚያገናኝ አስተማማኝ የየብስ ላይ የፋይበር መስመር (corridor) ለመዘርጋት የሚያስችል ይሆናል፡፡ ይህ አዲስ የፋይቨር መስመር ዝርጋታ ምሥራቅ አፍሪካን ከዓለም አቀፍ ዲጂታል ኔትዎርኮች ጋር በማገናኘት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና በቀጠናው የተለያዩ አማራጭ የኮኔክቲቪቲ መስመሮችን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ የዓለም አቀፍ የባንድዊድዝ (bandwidth) አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ፣ የኔትወርክ አስተማማኝነትንና ተለዋጭ መስመሮችን (redundancy) ለማጠናከር እንዲሁም በቀጣናው እያደገ የመጣውን የዳታ፣ የክላውድ አገልግሎቶች፣ የየከፍተኛ የዳታ ማዕከል (hyperscale) ኮኔክቲቪቲ፣ የዲጂታል ፕላትፎርሞች እና የድንበር ተሻጋሪ ዳታ ፍሰት ፍላጎቶችን ለበበቂ ሁኔታ ለማሟላት ታሳቢ ያደረገ ነው። በተጨማሪም ይህ ኢኒሼቲቭ እንደ ክላውድ አጠቃቀም፣ ፊንቴክ (fintech)፣ ዲጂታል ግብይት (e-commerce)፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ የመረጃ ስርጭት እና የድርጅቶች ዲጂታላይዜሽን ባሉ ዘርፎች የሚመራውን የአፍሪካ ፈጣን የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገት በቀጥታ ለመደገፍ የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
ይህ የትብብር ማዕቀፍ ለኢትዮ ቴሌኮም “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂ ስኬት ተጨማሪ አስቻይ እድሎችን የፈጠረ ሲሆን፣ ኩባንያው ከሀገር ውስጥ ኦፕሬተርነት ባለፈ በቀጠናው በዲጂታል ኮኔክቲቪቲ እና በመሠረተ ልማት መሪ የቴሌኮም ኦፕሬተር ለመሆን ያለውን የላቀ ፍላጎት ይበልጥ ለማጠናከር ያስችላል። በዚህ የሆራይዘን ፋይበር (Horizon Fiber) ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ የዲጂታል ትራንዚት የስበት ማዕከል እንድትሆን አስቻይ መደላድሎችን ከመፍጠሩም ባሻገር፣ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ እንደ ክላውድ (Cloud)፣ ዳታ ሴንተር፣ ኢንተርፕራይዝ መፍትሄዎች እና ድንበር ተሻጋሪ የዲጂታል ንግድ ላሉ የላቁ የዲጂታል አገልግሎቶች መሠረት ለመጣል ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
በዚህ ስትራቴጂያዊ የትብብር ማዕቀፍ አማካኝነት ሦስቱ ኦፕሬተሮች ያላቸውን እምቅ የመሠረተ ልማት ሀብቶች፣ የቴክኒክ ክህሎቶች እና ሥራን የመፈጸም አቅም በመጠቀም የሚከተሉትን ዋና ዋና አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
- መልቲ-ቴራቢት” የኦፕቲካል ፋይበር አቅም፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ከፍተኛ የዳታ ፍላጎት ለማሟላት፣
- ከፍተኛ ጥራት ያለው (Carrier-grade)፣ ዝቅተኛ የኢንተርኔት መዘግየት ያለው ዓለም አቀፍ ኮኔክቲቪቲ (low-latency international connectivity)፡ ለክላውድ እና ለከፍተኛ የዳታ ማዕከል አገልግሎቶች፣
- አማራጭ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ድንበር ተሻጋሪ የኮኔክቲቪቲ መስመሮች፡ የቀጣናውን የመሠረተ ልማት ጥንካሬ ለማረጋገጥ፣
- የላቀ ጥራት ያለው አስተማማኝ አገልግሎት፡ ለኦፕሬተሮች፣ ለኢንተርፕራይዞች፣ ለዲጂታል ይዘት አቅራቢዎች እና ለከፍተኛ የዳታ ማዕከል አገልግሎት አቅራቢዎች፣
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቴሌኮም ኦፕሬተሮቹ ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች፤ የሆራይዘን ፋይበር ኢንሼቲቭ (Horizon Fiber Initiative) ስምምነቱ የቀጣናዊ ትብብርን፣ በፈጠራ ላይ የተመሰረተ አጋርነትን እና አካታች የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የጋራ ራዕይ የሚያንፀባርቅ ስለመሆኑ አፅንዖት በመስጠት ገልጸዋል። ይህ ኢንሼቲቭ ጠንካራ የኮሙኒኬሽን መሠረተ-ልማት ለመገንባት ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፣ ስምምነቱ የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥን፣ ዲጂታል አካታችነትን የሚያረጋግጥ እንዲሁም ቀጣናውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና እምነት የሚጣልበት የዲጂታል ኢኮኖሚ መዳረሻ ኮሪደር ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
ይህ ትብብር እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 3 ቀን 2024 በአዲስ አበባ የተፈረመውን ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እና ደህንነቱ የተጠበቀ አማራጭ ዓለም አቀፍ የመገናኛ መስመር የመዘርጋትን ስትራቴጂያዊ አስፈላጊነት እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡ የጋራ መግባቢያ ስምምነቱ ከተፈረመ ጊዜ ጀምሮ ሦስቱ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ኢንሼቲቩን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስፈልጉ የቴክኒክ እና የንግድ ማዕቀፎችን በጋራ ያዘጋጁ ሲሆን፣ ኢንሼቲቩ አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ በመግባቢያ ስምምነቱ ወቅት የነበሩ የጋራ ፍላጎቶች እና ተጨባጭ የአፈፃፀም ውጤት መሆኑን ያሳያል።
ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ ቀይ ባሕርን በሦስት አገሮች በኩል በማገናኘት እና ከፍተኛ አስተማማኝነት ያለው የየብስ ላይ የፋይበር መስመር በማቅረብ፣ አፍሪካን ከአፍሪካ ጋር የሚያስተሳስር ፈርቀዳጅ የትብብር ማዕቀፍ ነው። ይህም የአፍሪካ ኦፕሬተሮች ተጨባጭ የኮኔክቲቪቲ ተግዳሮቶችን በጋራ እንዴት መፍታት እንደሚችሉ የሚያሳይ ሲሆን፣ ለአፍሪካ ዲጂታል እድገት፣ ቀጣናዊ ትብብር እና የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ድጋፍ በመስጠት እንዲሁም ለመፃኢ ጊዜ ዝግጁ የሆነ የተቀናጀ ዲጂታል መሠረተ-ልማት ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ የትብብር ማዕቀፍ ነው።
ስለ ኢትዮ ቴሌኮም
ኢትዮ ቴሌኮም የአፍሪካ ግንባር ቀደም እና የተቀናጀ የቴሌኮም እንዲሁም የዲጂታል ሶሉሽኖች አቅራቢ ግዙፍ ተቋም ሲሆን፣ ከ1894 ዓ.ም ጀምሮ የሀገሪቱን የኮሙኒኬሽን ጉዞ በግንባር ቀደምትነት እየመራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በ87.1 ሚሊዮን የደንበኞች ቁጥር እና ከ58.61 ሚሊዮን በላይ የቴሌብር ተጠቃሚዎች ያሉት ኩባንያችን፣ ከ10,288 በላይ የሞባይል ጣቢያዎችን ያካተተ ሰፊ የኔትወርክ መሠረተ ልማት በመዘርጋት አካታች እና ተደራሽ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር እየፈጠረ ይገኛል።
ኩባንያችን “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” በሚል ስትራቴጂ በመመራት፣ ከመሠረታዊ የኮኔክቲቪቲ አገልግሎቶች ባለፈ የላቁ የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖችን፣ የዳታ ማዕከል፣ ፐብሊክ ክላውድ (Public Cloud)፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ ፊንቴክ (FinTech) እና ኢ-ኮሜርስን ያካተቱ ዘመናዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ ነው።
ኩባንያችን የቀጠናው ግዙፍ ኦፕሬተር እንደመሆኑ መጠን፣ ቀጠናዊ አጋርነትን ለማጠናከር አሻራውን ከድንበር ባሻገር በንቃት እያስፋፋ ይገኛል። በተለይም የ“ዲጂታል አፍሪካ” ጉዞን ለማፋጠን፣ ስኬታማ የሆኑ የዲጂታል ፋይናንስ እና የመሠረተ ልማት ተሞክሮዎቹን በስትራቴጂያዊ ትብብሮች አማካኝነት ለጎረቤት ሀገራት በማጋራት ላይ ነው።
ይከተሉን
- ፌስቡክ:https://www.facebook.com/ethiotelecom
- ኤክስ:https://twitter.com/ethiotelecom
- ሊንክዲኢን: https://www.linkedin.com/company/ethio-telecom
- ዩቲዩብ:https://www.youtube.com/c/EthiotelecomETH
ይጎብኙን
ስለ ጅቡቲ ቴሌኮም
የጅቡቲ ሪፐብሊክ የገነባቻቸው ዘመናዊና ጥራት ያላቸው የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማቶች ሀገሪቱ ቀጠናዊ የቴሌኮሙኒኬሽን ማዕከል እንድትሆን አስችለዋታል። ይህ ስኬት የጅቡቲን የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ በአቅምም ሆነ በትስስር ጥንካሬ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቴክኖሎጂ ሥነ-ምህዳሮች ተርታ ያሰልፈዋል። የኔትወርክ መሠረተ ልማቱ በተለይም የንግድ፣ የባንክ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ እያፋጠነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት የጅቡቲ ቴሌኮም (Djibouti Telecom SA) እንደ ምስራቅ አፍሪካ የባሕር ሥር ሲስተም (EASSy)፣ የአውሮፓ-ሕንድ ጌትዌይ (EIG)፣ ሲኮም (SEACOM)፣ SEAME-WE3 እና የአደን-ጅቡቲ የባሕር ሥር ኬብሎች ባሉ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች አማካኝነት እንደ ዋነኛ የቴሌኮሙኒኬሽን ማዕከል (Hub) ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ስለ ሱዳቴል
ሱዳቴል ቴሌኮም ግሩፕ (Sudatel Telecom Group) በሱዳን እና በመላው አፍሪካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን እያገለገለ የሚገኝ የሕዝብ አክሲዮን ማኅበር (Public Joint Stock Company) ሲሆን፣ በቀጠናው ግንባር ቀደም ከሆኑ የኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) አቅራቢዎች አንዱ ነው። እ.ኤ.አ. በ1993 ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሱዳቴል ከብሔራዊ ቴሌኮም ኦፕሬተርነት ወደ ቀጠናዊ መሪነት ያደገ ሲሆን፤ በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ስኬታማ የፕራይቬታይዜሽን ሂደት በማከናወን ረገድ እንደ አርአያነት የሚጠቀስ አንጋፋ ተቋም ነው።
ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ግሩፕ
ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም




