ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከዳሽን ባንክ እና ኤታ ሶሉሽንስ በአጋርነት በመስተንግዶ (Hospitality)፣ በአስመጪና ላኪ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና ችርቻሮ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ድርጅቶችና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በእጅጉ የሚያዘምን እና የደንበኞችን የግብይት ተሞክሮና የአገልግሎት እርካታ በእጅጉ የሚጨምር “ዙሪያ” የተሰኘ የኢ.አር.ፒ (ERP)፣ የፒ.ኦ.ኤስ (POS) እና ካሽ ሬጂስተር (Cash Register) አገልግሎቶችን በአንድ ላይ ለመስጠት የሚያስችል የቢዝነስ አውቶሜሽ ሶሉሽን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህ “ዙሪያ” የተሰኘው ሶሉሽን ፈጣን የቢዝነስ ግብይትን፣ ግልጽ አሰራርን፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ከወረቀት ገንዘብ ንክኪ የጸዳ የቢዝነስ ግብይትን በመተግበር ከገንዘብ ንክኪ የጸዳ ማህበረሰብ (cashless society) ለመፍጠር እና የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በአገር በቀል አቅም በልፅጎ ከአገሪቱ የንግድ ድባብ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የቀረበ እና ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት የቢዝነስ ሶሉሽን ነው፡፡
በተጨማሪም “ዙሪያ” የቢዝነስ ሶሉሽን ሁሉንም የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ካርዶች መቀበል የሚችል፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ኮሚሽን ዕውቅና የተሰጠው የሂሳብ ምዝገባ አገልግሎት የሚሰጥ እንዲሁም ነጋዴዎች የሚያንቀሳቅሱትን ሃብት በቀላሉ ለማስተዳደር እና ማንኛውንም የክፍያ መረጃዎች በአንድ ያካተተ ደረሰኝ ለማግኘት የሚያስችል ነው፡፡
“ዙሪያ” የቢዝነስ ሶሉሽን ሶስቱ ተቋማት የየድርሻቸውን ከፍተኛ ሚና የተወጡበትና ታሪካዊ ትብብር ያደረጉበት የሀገራችን ፈርቀዳጅ የቢዝነስ ሶሉሽን ነው፡፡ በዚህም ኤታ ሶሉሽንስ (ETTA Solutions) ይህንን የተቀናጀ እና ለሀገራችን አዲስ ምዕራፍ የከፈተ የቢዝነስ ሶሉሽን ያበለጸገ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን የላቀ ሶሉሽን አስተማማኝ በሆነው እና ለተለያዩ ተቋማት የላቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው በቴሌክላውድ (TeleCloud) መሠረተ ልማት ከማስተናገድ (platform hosting) ባሻገር ከ54 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉትን የቴሌብር የክፍያ ስርዓትን በመጠቀም እንዲሁም አጠቃላይ በንግዱ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች የማስተዋወቅና የማሰራጨት ሚናውን የሚወጣ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም ለሀገራችን አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም የሆነው ዳሸን ባንክ ደግሞ ለዚህ አገልግሎት የሚውለውን ማሽን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ከማመቻቸት ባለፈ ለአገልግሎት አቅራቢ ደንበኞች “አሁን ይግዙ ቀስ ብለው ይክፈሉ” የሚል የፋይናስ አቅርቦት ለማመቻቸት እና ከዳሸን ባንክ የክፍያ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር ለደንበኞች ቀላል የክፍያ አማራጭ የሚያመቻች ይሆናል፡፡
“ዙሪያ” የዲጂታል ቢዝነስ አውቶሜሽን፣ የERP ሲስተምን ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ መጫን የሚያስችል ሲሆን፣ በክላውድ የታገዘ አሰራርን አንድ ላይ አሟልቶ የያዘ ከመሆኑ ባሻገር ከቢዝነስ እድገት ጋር አብሮ ሊሰፋ (scalable) የሚችል በመሆኑ፣ ነጋዴዎች/አገልግሎት አቅራቢዎች ከአንድ ቅርንጫፍ ምዝገባ ጀምሮ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን እንደየፍላጎታቸው መጠን በፈለጉት ጊዜ ሌሎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በቀላሉ ወደ ሶሉሽኑ ማካተት ይችላሉ።
ሶስቱ ተቋማት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ10,000 ለሚበልጡ ነጋዴዎች ዘመናዊ የዲጂታል ሶሉሽኖችን በማቅረብ የስራ ቅልጥፍናና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም አገልግሎታቸውን ይበልጥ እንዲጎለብት የማድረግ ተግባር በጋራ የሚያከናውኑ ይሆናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ደንበኞች ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎቱን በ www.zoorya.et ማግኘት የሚችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም፣ ዳሽን ባንክ እና ኤታ ሶሉሽንስ
ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም.