የ2017 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም እና የመሪ ዕድገት የሦስት ዓመታት ስትራቴጂ ማጠቃለያ አፈጻጸም!

ይህ በሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም ለህዝብ ይፋ የተደረገ ከሐምሌ 2016 እስከ ሰኔ 2017 በጀት ዓመት ያለውን የሥራ አፈጻጸም እና የመሪ ዕድገት ስትራቴጂ የሶስት ዓመታት አፈጻጸም ሪፖርት ነው፡፡

ኩባንያችን በሀገራችን ኢኮኖሚና የማህበረሰባችንን ሁለንተናዊ እድገት እንዲሁም በዜጎች ኑሮ መሻሻል ላይ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደመሆኑ ፈጣንና ተለዋዋጭ ከሆነው የቢዝነስ ፍላጎት ጋር በማጣጣም ለደንበኞቹ የሚያቀርበውን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት በመስራት የሀገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ የሚቀይሩ እና ተቋማዊ አሰራሮችን የሚያዘምኑ አካታች ለውጦችን እውን ለማድረግ ዘርፈ-ብዙ የዲጂታል እና የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን ማስፋፊያ እና ማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በውድድር ገበያው ውስጥ ተመራጭ አገልግሎት ሰጪ ተቋም በመሆን በሁሉም መስክ የመሪነት ሚና መጫወት የሚያስችል የሦስት ዓመት መሪ የእድገት ስትራቴጂ ቀርፆ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን በስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎቹ ከመደበኛው የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባለፈ አዳዲስ የዲጂታል መፍትሄዎችንና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በስፋት በማቅረብ፣ የተቋማትን አሰራር ቅልጥፍናና ምርታማነትን የሚያሳድጉ እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ዘርፎች አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማስታጠቅ ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ዲጂታል ሥነ-ምህዳር ውስጥ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችሉ ቁልፍ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

በተለይም የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽን አገልግሎታችን ከፍተኛ ዕድገትና ተጨባጭ ተጽእኖ በማሳየት ተቋማዊ ዘመናዊነትን አፋጥኗል፣ የኢኮኖሚ ብቃትን አሳድጓል፣ እንዲሁም የኩባንያችንን በሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ ያለውን ቁልፍ የአስቻይነት ሚና አጠናክሮ ቀጥሏል።

ይህ ሪፖርት 2017 በጀት ዓመት የመሪ ዕድገት ስትራቴጂ ማጠናቀቂያ በመሆኑ፣ ከበጀት ዓመቱ በተጨማሪ በሶስቱ ዓመታት የስትራቴጂ ዘመን የተከናወኑ አበይት ክንውኖችን ማለትም የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ በማሻሻል፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን በማሳደግ፣ የገቢ ምንጮችን በማስፋፋት እና የኦፕሬሽን ልህቀትን በማምጣት፣ የኔትወርክና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን አቅም በማሳደግ፣ ፈጠራን የተላበሱ ሶሉሽኖችና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ በኩባንያችን የተመዘገቡ አፈጻጸሞችን ይዳስሳል።

በተጨማሪም ኩባንያችን ከማክሮ ኢኮኖሚ ለውጦች ጋር የሚጣጣሙ መፍትሄዎችን በመተግበር ዘላቂ እድገትን በማስቀጠል ያመጣቸው ውጤቶች፣ የቴሌኮም ማጭበርበርን በመከላከል የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን ደህንነት በማረጋገጥ፣ የሰው ኃይልን አቅም በማጎልበት፣ በሥራ ፈጠራ እና ማህበራዊ ኃላፊነት ረገድ ያከናወናቸው ቁልፍ ተግባራት እና በአጠቃላይ በስትራቴጂ ዘመኑ ማብቂያ የዲጂታል ኢትዮጵያን ትራንስፎርሜሽን እውን በማድረግ ረገድ ያስመዘገባቸውን ተጨባጭ ውጤቶችን ያቀርባል፡፡

የቴሌኮምና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያ

ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎትን ለማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል፣ በሀገር ደረጃ የታቀደውን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማገዝ እንዲሁም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ወቅታዊ ስትራቴጂ እቅድ በመንደፍ እና በመከለስ እየተገበረ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ፡- የዳታ ትራፊክ እድገትን መሠረት ያደረገ የ3G፣ 4G እና 5G ኔትዎርክ አቅምና ሽፋን ማሳደጊያ፣ የባክሃውልና ትራንስፖርት ኔትወርክ አቅም ማሳደጊያ፣ የመደበኛ ብሮድባንድ አቅም ማሳደጊያ፣ የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያ፣ የክላውድ አገልግሎት፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ የኦፕሬሽንስ ሰፖርት እና የኮርፖሬት ሶልዩሽንስ፣ የሴኩሪቲ ሶልዩሽንስ እና የተለያዩ የሲቪል ግንባታ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ስራዎች

 ኩባንያችን የአገልግሎቱን ጥራት እና ተደራሽነት እንዲሁም የደንበኞችን ተሞክሮ ለማሻሻል እና የኔትወርክ ሽፋን እና አቅምን በማሳደግና በማሻሻል በበጀት ዓመቱ 1,683 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን ገንብቶ  አገልገሎት ላይ አውሏል፡፡ ከተገነቡት 1,683 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ውስጥ 836ቱ ወይም 49.6% የገጠር ሞባይል ጣቢያዎች ሲሆኑ ይህም የኩባንያችንን በገጠር የኔትወርክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው፡፡

በተጨማሪም 512 ተጨማሪ ከተሞች ላይ LTE አገልግሎትን በማስፋፋት አጠቃላይ የ4G LTE ተጠቃሚ የሆኑ ከተሞችና ወረዳዎችን ቁጥር 936 አድርሶታል፡፣ እንዲሁም 5Gን በ16 ተጨማሪ ከተሞች በማስፋፋት አጠቃላይ  የ5G ከተሞችን ቁጥር ወደ 26 ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ በ212 ተጨማሪ ጣቢያዎች ላይ Massive MIMO የተሰኘ የገመድ አልባ ኔትወርኮችን የስፔክትረም  ቅልጥፍና  እና የዳታ ፍጥነት ለማሻሻል  በብዛት ያላችን አንቴናዎች የሚጠቀም የሞባይል ቴክኖሎጂን በማስፋፋት አጠቃላይ Massive MIMO የተተገበረባቸውን ጣቢያዎች ወደ 306 በማድረስ የኔትወርክ አቅምንና የደንበኞችን ተሞክሮ የማሻሻል ፣ የ4G እና 5G የኮር ኔትወርክ በማስፋፋት፣ የሞባይል ዳታና ተያያዥ አገልግሎቶችን ተደራሽነት እንዲሁም የአገልግሎት ጥራት በማሳደግ አገር አቀፍ የቴሌኮምና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን አጠናክሯል።  

በዚህም በበጀት አመቱ ብቻ የ4G ኔትወርክ የህዝብ ሽፋንን ከ37.5% ወደ 70.8% ማድረስ የተቻለ ሲሆን በተለይም በደቡብ ደቡብ ምዕራብ (SSWR) እና በደቡብ ደቡብ ምሥራቅ (SSER) ሪጅኖች በልዩ ሁኔታ በተካሄዱ መጠነ ሰፊ የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች አማካይነት 18.8 ሚሊዮን ተጨማሪ የሞባይል ደንበኞች ለማስተናገድ አቅም ያለው ኔትዎርክ በመገንባት አጠቃላይ የሞባይል ኔትዎርክ አቅምን ከ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ ከነበረው 86.1 ሚሊዮን ወደ 104.8 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም የኔትዎርክ የህዝብ ሽፋን (Mobile Network Population Coverage) 99.4% የደረሰ እንዲሁም የኔትዎርክ የቆዳ ሽፋን (Geographical Coverage) ሽፋን 86.5% ደርሷል፡፡

የገጠር ሞባይል አገልግሎት

 ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው የገጠር ቀበሌዎች እና መንደሮች የገጠር ሞባይል አገልግሎት በመገንባት የገጠር ማህበረሰባችንን የቴሌኮም፣ የዲጂታል ሶሉሽኖችን እና የፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለማድረግ እና ኢፍትሐዊ የዲጂታል አገልግሎት ስብጥር በማጥበብ ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በበጀት ዓመቱ በ12 ሪጅኖች፣ በ459  ወረዳዎችና በ2,388 ቀበሌዎች 836 አዳዲስ የገጠር ሞባይል ሳይቶች በመገንባት 5.9 ሚሊዮን የገጠር ነዋሪዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በማድረግ  አካታችነትን ከማረጋገጥ አንጻር አስደማሚ ሥራ አከናውኗል፡፡ እነኚህ ስፍራዎች በአቅራቢያው ከሚገኙ የሞባይል ጣቢያዎች በአማካይ ከ10 እስከ 14 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኙ የነበሩ ናቸው፡፡

የትራንስፖርት ኔትወርክ እና  የኃይል አቅርቦት

በባክቦን ኔትዎርክ ለሚሰጡ የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶች የሚሆኑ እና ለኔትዎርክ ጥራት መሻሻል የሚያግዙ የኦፕቲካል ፓች ኮርድ ዝርጋታዎች የኦፕቲካል ሞጁል እና ፖርቶችን ከኦዲኤፍ ጋር የማገናኘት ስራ በተለያዩ ሳይቶች በስፋት ተሰርቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ በተከናወነው የባክቦን ፋይበር ዝርጋታ 686.16 ኪ.ሜ የተጠናቀቀ ሲሆን የOPGWን ጨምሮ አጠቃላይ የተዘረጋው 22,673.1 ኪ.ሜ ደርሷል፡፡ በዚህም የኔትወርክ አቅማችንን ከማጠናከር ባለፈ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት ምቹ መደላድል  ፈጥሯል፡፡

የሀይል አቅርቦት ጋር በተገናኘ በተያዘው የበጀት ዓመት ለ2,400 የLTE እና 5G ሳይቶች የኃይል ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን በተጨማሪም በ141 ሳይቶች አማራጭ የፀሐይ ኃይል (solar) ተተክሏል።   በአጠቃላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለ4,700 ሳይቶች የኃይል ማሻሻያ ሲደረግ፣ በ199 ሳይቶች የፀሐይ ኃይል አቅርቦት ስራ ተከናውኗል።

በተመሳሳይ በዚሁ በጀት ዓመት 66 የአዳዲስ ጄኔሬተሮች ገጠማ ስራ የተከናወነ ሲሆን 193 ጄኔሬተሮች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በድምሩ 491 አዳዲስ ጄኔሬተሮች በመትከል እና 289 ጄኔሬተሮች ጥገና በማከናወን  የአገልግሎት አሰጣጥ ቀጣይነትን ማረጋገጥ እና የደንበኞችን ተሞክሮ ማሻሻል ተችሏል።

 የፊክስድ ኔትወርክ ማስፋፊያ ስራዎች

 በበጀት ዓመቱ የፋይበር ኔትወርክ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ የኔትዎርክ ጥራትን እና አቅምን ለማሻሻል ተጨማሪ 305,894 የኦፕቲካል ዲስትሪቢውሽን ኔትወርክ (ODN) አቅም የተገነባ ሲሆን በዚህም የODN አቅማችንን 951,982 ማድረስ ተችሏል፡፡

ለሀገራችን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ሀገራዊ ልማት መፋጠን ጉልህ ሚና ያለውን የመደበኛ ብሮድባንድ አገልግሎት ከኮፐር ኔትወርክ ወደ ፋይበር ኔትወርክ የመቀየር “የኮፐር ስዊች ኦፍ ኢኒሼቲቭ” በማስቀጠል 35,701 ደንበኞች ወደ ፋይበር የተዘዋወሩ ሲሆን 24,123 ደንበኞች በዚህ በጀት ዓመት ብቻ የተዘዋወሩ ናቸው፡፡

በበጀት ዓመቱ ለተከናወኑ አዳዲስ የኦዲኤን ኔትወርክ ግንባታዎች እና የኮፐር ስዊች ኦፍ ኢንሼቲቭን ለመደገፍ 233 የፋይበር አክሰስ ኔትወርክ እቃዎች (OLTs) ተተክለው አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡

በዚህ በጀት ዓመት በአጠቃላይ በአዲስ አበባ 301 እንዲሁም በክልሎች 357 የሞባይል ጣቢያዎችን በፋይበር የማገናኘት ስራ (ፋይበር ቱ ዘ ተታወር (FTTT)) የተከናወነ ሲሆን ይህም በአዲስ አበባ ያለውን አጠቃላይ የFTTT ጣቢያዎች ቁጥር 1,342፣ በክልሎች ደግሞ 1,049 ማድረስ ተችሏል፡፡ ከFTTT የፋይበር ዝርጋታ በተጨማሪ የሞባይል አገልግሎት ጥራት እና  አስተማማኝነት ለማሻሻል የሚያግዝ የ216 ኪሎ ሜትር የሜትሮ ፋይበር ሪንግ ፕሮቴክሽን (ring protection) ዝርጋታ ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ 1,785 ኪሎ ሜትር የሜትሮ ፋይበር ተገንብቷል፣ በዚህም አጠቃላይ የሜትሮ ፋይበር ኔትወርክን 14,340 ኪሎ ሜትር ማድረስ አስችሏል።

ለስማርት ከተማ (Smart City)፣ ለሲቲ ኔት (City Net) እና ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በዚህ በጀት ዓመት የ529 ኪሎ ሜትር የፋይበር ኔትወርክ ዝርጋታ ስራ የተከናወነ ሲሆን ይህም ባለፉት ሶስት ዓመታት የተዘረጋውን አጠቃላይ የፋይበር ኔትወርክ መጠን 2,066 ኪሎ ሜትር አድርሶታል።

የአገልግሎት ጥራትን (QoS) ለማሳደግ እና የደንበኞችን ተሞክሮ ለማሻሻል 89 ኪሎ ሜትር የሜትሮ ፋይበር ሪሃብልቴሽን ስራ የተከናወነ ሲሆን በመንገድ እና ኮሪደር ልማት ምክንያት 274 የMSAG እና MSAN ሳጥኖች የደንበኞች አገልግሎት ላይ የጎላ መስተጓጎል ሳይገጥም ከግንባታ ወሰን ውጪ የማዘዋወር ስራ ተሰርቷል፡፡

ኢንተርናሽናል ጌትዌይ International Gateway (IGW) capacity

በታሪፍ ቅናሽ እና የዳታ አጠቃቀም መሻሻልና መጨመርን ተከትሎ የመጣውን ከፍተኛ መጠን ያለውን የዳታ ትራፊክ ለማስተናገድ እንዲቻል የዓለም አቀፍ ኢንተርኔት ማስተላለፊያ አቅምን የማሻሻልና የማሳደግ ስራ በማከናወን በበጀት ዓመቱ በ840 Gbps በመጨመር አጠቃላይ የIGW አቅምን 2.48Tbps ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህም የደንበኛን ተሞክሮ  በላቀ ሁኔታ ለማሻሻል በሀገር ውስጥ የተገነባውን የሜታ፣ የኔትፍሊክስ፣ የቲክ ቶክ እና ሌሎችም አለም አቀፍ የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ፕላትፎርሞች 1,242 Gbps የCache አቅምን ያካተተ ነው፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም ማሳደግና ማሻሻል

 ኩባንያችን ዘመኑ የደረሰባቸውንና በአጠቃላይ ለማህበረሰቡ አኗኗር እና ለኢንተርፕራይዝ ድርጅቶች የአሰራር ቅልጥፍና ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን የዲጂታል  ቴክኖሎጂ ውጤቶች በሰፊው ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህን  አገልግሎቶች በብቃት ለማቅረብ የሚያግዙ የኦፐሬሽን ደጋፊ ሲስተሞች (OSS Cloud) ትግበራ፣ የቀጣይ ትውልድ ቢዝነስ ደጋፊ ሲስተሞች (NGBSS SNS) ማሻሻያ፣ ደንበኛ የማስተናገድ አቅም ከ80 ሚሊየን ወደ 110 ሚሊዮን ማሳደጊያ፣ የTeleCloud እና Private Cloud፣ የመጠባበቂ ወይንም ከአዳጋ የማገገሚያ አቅምን ማስፋፊያ (Disaster Recovery-DR) የአዲስ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሲስተም (E-Commerce Platform) ግንባታ፣ በኢንተርኔት ላይ ያሉ ኮምፒውተሮችን፣ አገልግሎቶችን እና ሌሎች የኢንተርኔት ፕሮቶኮል ኔትወርክ ሀብቶችን ለመሰየም የሚያስችሉ ሲስተሞችን (DNS System) የማሻሻል ፣ የድረ-ገጽ ማስተናገጃ (Web hosting) ሲስተሞችን የማሻሻል እና የሽግግር ስራዎች ፣ ተደራሽነት ለመቆጣጠር፣ ደንቦችን ለማስፈጸም እና አጠቃቀምን ለመከታተል የሚያግዙ የአገልግሎቶች እና ፕሮቶኮሎችን (Authentication, Authorization & Accounting (AAA)) የማዘመን ስራዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የዳታ ሴንተር እና የክላውድ አገልግሎት

የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይን እውን ከማድረግ አንጻር በተሰሩ ስራዎች መነሻነት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የዳታ ሴንተር እና የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሰረት በማድረግ በበጀት ዓመቱ የዳታ ሴንተር አቅማችንን ወደ 5 MW IT Load ፣ 624 IT Rack እና 26,208 U ማሳደግ ተችሏል።

ተቋማት አሰራራቸውን ዲጂታላይዝ እንዲያደርጉ የሚያስችል የክላውድ ኢንፍራስትራክቸር ማስፋፊያ ስራ የተተገበረ ሲሆን በዚህም በ elastic compute 31,616 vCPU፣ storage 4.5 PB እንዲሁም ኢንተርፕራይዝ ስቶሬጅ 3 PB የዳታ ሴንተር አቅም መገንባት ተችሏል፡፡

የአገልግሎት ጥራት ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች

የሞባይል አገልግሎት ጥራትን ከማሳደግ አንፃር በተከናወኑ ተግባራት የሞባይል የኔትወርክ መገኘት መጠን (NAR) 95.8 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 95.1 በመቶ አፈጻጸሙ በአማካይ 99.4 በመቶ ሆኗል፡፡ 

የኔትወርክ ትራፊክ እድገት

በበጀት ዓመቱ 172 ቢሊየን ደቂቃ የሞባይል የድምፅ ጥሪ፤ 810.5 ሚሊዮን ደቂቃ ዓለም አቀፍ የድምፅ ጥሪ ወደ አገር ውስጥ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም 39.5 ቢሊየን አጭር የጽሁፍ መልዕክት፣ 1.43 ትሪልዮን ሜጋ ባይት የሞባይል ዳታ ትራፊክ ተመዝግቧል፡፡

ይህ አፈፃፀም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፡ በሞባይል ድምፅ ጥሪ የ6.9% እድገት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የተደረገ ጥሪ በ30% መቀነስ አሳይቷል፣ በአጭር መልእክት የ54.7% እና በሞባይል ዳታ የ52.8% እድገት አስመዝግቧል፡፡

የዳታ ትራፊክ አፈፃፀሙን በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው የደንበኞች ቁጥር እና የዳታ አጠቃቀም ባህሪ ማደግ፣ ተጨማሪ የኔትዎርክ መሰረተ ልማቶች መዘርጋት፣ አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶች ወደ ገበያ መውጣት፤ ተከታታይ የሆነ የኔትዎርክ ማትባት ስራዎች መሰራት፣ የዋጋ ተመጣጣኝነትን ለደንበኞቹ ከማረጋገጥ አንፃር ከ2018 ጀምሮ የተደረገው ተከታታይነት ያለው የዋጋ ቅናሽ እንዲሁም ከአጋሮች ጋር ያለው ትብብር ማደግ ናቸው።

ምርትና አገልግሎቶችን ማሳደግ

በበጀት ዓመቱ የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማርካት እንዲሁም አዳዲስ የገቢ ምንጮችን በማስፋት በአጠቃላይ 365 ምርትና አገልግሎቶች ለገበያ ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 134 አዳዲስ 157 ማሻሻያ የተደረገባቸው እና 74 ፕሮሞሽናል ምርት እና አገልግሎቶች ናቸው።

በበጀት ዓመቱ 93 ምርትና አገልግሎቶች ለግለሰብ ደንበኞች እንዲሁም 76 የኢንተርፕራይዝ ኮኔክቲቪቲ፣ 47 ዲጂታል ላይፍ ስታይል አገልግሎቶች ፣ 53 የክላውድና የዲጂታል መፍትሔዎች፣ 59 የቴሌብር ምርትና አገልግሎቶች እና 37 ዓለም አቀፍ አገልግሎቶች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ እንዲሁም 856.5 ሺ የቴሌኮምና የዲጂታል አገልግሎት መገልገያ ዲቫይሶች ቀርበዋል፡፡

ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ ባሻገር የቴሌ ክላውድ አገልግሎቶችን በማስጀመር ለተቋማት የኮምፒውቲንግ፣ የመረጃ ቋት እና የመጠባበቂያ መረጃ ቋት መፍትሄዎችን አቅርቧል። ከ650 በላይ የመንግስትና የግል ተቋማት የቴሌ ክላውድ አገልግሎቶችን በመጠቀም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመረጃ ማዕከላት ግንባታዎችን በማስቀረት ኩባንያዎቹ በዋና ተልዕኳቸው ላይ እንዲያተኩሩ እና ሀገራዊ የመረጃ ደህንነትን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት

በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተደራሽነት በማሳደግ 1,038 ማድረስ የተቻለ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 553 በፍራንቻይዝ፣ 443 በኩባንያችን ባለቤትነት እና 42  በኢንዳይሬክት ቻናል አጋሮች የተያዙ ማዕከላት ናቸው። ኩባንያችን በተገበረው ዲስትሪቢውሽን ስትራቴጂ መሰረት 107 ዋና አከፋፋዮች እና የቨርችዋል ቶፕአፕ አከፋፋዮች ፤12.7  ንዑስ አከፋፋዮች፣ እንዲሁም 291.1  ቸርቻሪዎች በሽያጭ ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም አጠቃላይ የአጋሮችን ቁጥር ወደ 303.9 ሺ ማሳደግ ተችሏል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ  

ኩባንያችን ወደ ውድድር ገበያው ከመግባቱ አስቀድሞ የዋጋ ተመጣጣኝነትን ለደንበኞቹ ከማረጋገጥ አንፃር ከ2018 ጀምሮ ተከታታይነት ያለው የዋጋ ቅናሽ ሲያደርግ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ይህም የደንበኞችን ቁጥር እና የቴሌኮም አገልግሎት አጠቃቀም ከመጨመርም ባለፈ ለሀገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ 

በበጀት ዓመቱ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጪ ምንዛሪ ተመን ፖሊሲ መውጣቱን ተከትሎ ኩባንያችን የቴክኖሎጂ ግብአቶችን በከፍተኛ ወጪ በውጭ ምንዛሪ የሚያስገባ እንደመሆኑ ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በተፈለገው  መጠን  ማከናወን እንዲቻል በተወሰኑ ምርትና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ማስተካከያ አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ የተደረገው የዋጋ ማሻሻያ የደንበኞችን የመክፈል አቅም ከግምት ያስገባና አብዛኛው ደንበኛ የሚጠቀምባቸውን 22 የሞባይል ምርትና አገልግሎቶች/ጥቅሎች ምንም አይነት የዋጋ ማሻሻያ ሳይደረግባቸው እንዲቀጥል ያደረገ ነው፡፡

የደንበኛ ቁጥር

ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ ጉልህ እድገት በማስመዝገብ፣ አጠቃላይ የደንበኞቻችን ቁጥር 83.2 ሚሊዮን  ለማድረስ የቻለ ሲሆን ይህም ከታቀደው አንጻር 100.2% የሆነ ስኬታማ አፈጻጸም ነው። ይህ አዎንታዊ ውጤት ከባለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር  4.84 ሚሊዮን ደንበኞች ወይም የ 6.2% እድገት ያሳያል። 

ደንበኞች በአገልግሎት አይነት

የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 24.5% በመጨመር 80.3 ሚሊዮን፣ የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 82% በመጨመር 46.6 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኞች 67.2% በመጨመር 847.1 ሺ የደረሱ ሲሆን፣ በደንበኛ ፍላጎት መቀየር ምክንያት የመደበኛ ስልክ የድምፅ ደንበኞች ብዛት በ18.4% ቀንሶ 722.1 ሺ ደርሷል፡፡ በእነዚህ  አገልግሎቶች አማካይነት የቴሌኮም አገልግሎት ስርጸት (teledensity) መጠን 10% በማደግ ከ 63.3% ወደ 73.7% ማድረስ ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 19.1 ሚሊዮን የአገልግሎት ሽያጭ የተከናወነ ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ0.4% ጭማሪ እንዲሁም ከእቅድ አንጻር እጅግ የላቀ የ106% አፈጻጸም አለው፡፡

የገቢ አፈጻጸም

ኩባንያችን ገቢን ከማሳደግ አንጻር የተለያዩ የቢዝነስ አማራጮችን በመተግበር የደንበኛን ቁጥር የማሳደግና የማቆየት ስራዎች በመስራት፣ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸውን መሠረተ ልማቶች በማስፋፋትና በማጠናከር እንዲሁም በማከራየት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የማግኘት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በተሰራው ረቂቅ የሂሳብ ሪፖርት መሰረት አጠቃላይ 162 ቢሊዮን ብር ገቢ  በማስገኘት የእቅዱን 99% አሳክቷል፡፡ በበጀት አመቱ የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ72.9% እድገት አሳይቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ 193.1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአለም አቀፍ አገልግሎት የተገኘ ሲሆን የእቅዱን 101.8% አሳክቷል፡፡ የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 28.6% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 22.7% ዓለም አቀፍ ገቢ 12.9%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች የ7.6% የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሳሪያዎች ሽያጭ 5.4% የመሰረተ ልማት ኪራይ 2.2% ቴሌብር 2.7% ኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽን 6.2% እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 11.7% ድርሻ አላቸው፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝት

 በበጀት ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ከማመንጨት አንፃር በተከናወኑ ተግባራት በአጠቃላይ 213.6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዳችንን 84.3% ያሳካ ነው። ከባለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ15.44 ሚሊየን ዶላር (የ7.8%) ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ 193.11 ሚሊዮን ዶላር ከአለም አቀፍ አገልግሎት የተገኘ ገቢ (66.6 ሚሊዮን ዶላር ከኢንተርናሽናል ትራንዚት ትራፊክ የተገኘ ነው፣ ከመሰረተ ልማት ማጋራት ኪራይ (Infrastracture sharing) 5.62 ሚሊዮን ዶላር ገቢ፣ ሲሆን በቴሌብር አለም አቀፍ የሀዋላ አገልግሎት አማካኝነት ከውጪ ሀገራት ከ14.42 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ችሏል፡፡ በባለፉት ሶስት አመታት በአጠቃላይ 575.76 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል፡፡

የወጪ ቁጠባ ባህልን ማጎልበት

ኩባንያችን ገቢን ከማሳደግ በተጨማሪ ውጤታማና ምርታማ የሚያደርጉ የወጪ ቁጠባ ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተተገበሩ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ከ11.3 ቢሊዮን ብር በላይ የወጪ ቁጠባ በማድረግ የዕቅዱን 151% ማሳካት ተችሏል፡፡ ለዚህ ስኬት አስተዋፆ ያበረከቱት ቁልፍ ጉዳዮች ውጤታማ የሀብት አጠቃቀም ስልቶች መተግበር፣ ከአጋር አካላት ጋር መተባበር እና የእለት ተእለት ተግባራትን ዲጂታላይዝ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው።

በበጀት ዓመቱ ከወጪ ቁጠባ ሥራዎች ባሻገር የገቢ ምንጮችን በማበራከት ለተቋሙ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ እና ከቢሮ ኪራይ በአጠቃላይ ከ 230.02 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡

የፋይናንስ ግቦች አፈፃፀም 

የፋይናንስ መግለጫዎች (Unaudited Statement of Profit or Loss)

ኩባንያችን የፋይናንሱን ጤንነት ለማረጋገጥ በዘረጋው ቀልጣፋ የአሰራር ስርአት መሰረት እስከ 2016 በጀት አመት ድረስ ያለውን የሂሳብ ሪፖርት በአለም አቀፍ የሂሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ስርአት (IFRS Based Financial report) መሰረት በማዘጋጀት፤ በውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ እንከን አልባ (Unqualified) መሆኑ ተረጋግጧል። ከዚህ ባሻገር እንደ የደንበኛ ቁጥር፤ እለታዊ ገቢንና እለታዊ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት ያሉትን ቁልፍ አፈጻጸም መለኪያዎች በየዕለቱ ጥብቅ ክትትል ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የ2017 በጀት አመት ግማሽ አመት ኢንትሪም ኦዲቱ የተጠናቀቀ ሲሆን አመታዊ የሂሳብ ሪፖርቱ ኦዲት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

የበጀት ዓመቱ የኩባንያችን የፋይናንስ አፈጻጸም ከውጪ ምንዛሬ ኪሳራ ውጪ በሚታይበት ጊዜ ጠንካራ የገቢ እድገትን እና ትርፋማነትን የሚያሳይ ሲሆን ገቢን በማሳደግና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በመከተል ትርፋማነቱን ለማጠናከር ባቀደው መሠረት ያልተጣራ ትርፍ (EBITDA) 76 ቢሊዮን ብር በማድረስ የእቅዱን 104% አሳክቷል፡፡ ይህም ከባለፈው በጀት አመት ከነበረው 41.2 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ የ34.8 ቢሊዮን ብር ጭማሬ ወይም የ84% እድገት አሳይቷል፡፡

ቴሌብር ለአካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ 

 ቴሌብር በዲጂታል የፋይናንስ አካታችነት ዘርፍ ሥር-ነቀል ለውጥ በማምጣት፣ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ በማቅለል፣ የተቋማትን የአሰራር ቅልጥፍና በማሳደግ እና የሃገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ በማፋጠን ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ኩባንያችን የቴሌብር አገልግሎት በማቅረቡ የዲጂታል ግብይት የገንዘብ ልውውጡን ፈጣን፣ ቀላል እና አስተማማኝ  በማድረግ cashlite society መፍጠር ከማስቻሉም በላይ የመደበኛ ባንክ አገልግሎት የተደራሽነትን ክፍተት በመሙላት ዜጎች በቀላሉ በራስ አገዝ ወይም በአቅራቢያቸው በሚገኙ ወኪሎች እና በመላ ሀገራችን በሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አማካይነት የዲጂታል ፋይናንስ እና የሞባይል መኒ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል ላይ ይገኛል። 

የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር

 በበጀት ዓመቱ 7.29 ሚሊዮን ተጨማሪ የቴሌብር ደንበኞች በመመዝገብ አጠቃላይ የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር 54.84 ሚሊዮን በማድረስ የእቅዱን 99.7% ያሳካ ሲሆን ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ15.3% እድገት አሳይቷል።

በሀገራችን ለዲጂታል ስነ-ምህዳር እድገት እየተሰጠ ያለው ትኩረት፣ ከብዙ ተቋማት ጋር ያደረግነው ትብብር፣ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ፣ ለተጠቃሚ ምቹ የሆነ ሱፐርአፕ መልማቱ እና የ127 የጥሪ ማዕከል መዘመኑ ለደንበኞች ቁጥር መጨመር ካስቻሉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያችንን አጋሮች ቁጥር ለማሳደግ እንዲሁም ቴሌብርን ተጠቅመው የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዚህም በበጀት ዓመቱ 108.3 ሺ አዳዲስ ወኪሎች፣ 13 ዋና ወኪሎች እና 117.4 ሺ ነጋዴዎችን በመመዝገብ ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ አጠቃላይ ወኪሎችን ወደ 320.3 ሺ ዋና ወኪሎችን ወደ 170፣ ነጋዴዎችን ወደ 310.1 ሺ ማድረስ ተችሏል፡፡

 የቴሌብር ግብይት

በበጀት ዓመቱ 2.38 ትሪሊዮን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር በቴሌብር በማከናወን የእቅዱን 116.9% ያሳካ ሲሆን አጠቃላይ አመታዊ የግብይት መጠኑ (Transaction Volume) 1.06 ቢሊዮን ነው፡፡ አገልግሎቱ ከተጀመረ ጀምሮ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ 4.93 ትሪሊየን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ማንቀሳቀስ የተቻለ ሲሆን አጠቃላይ የአራት አመታት የግብይት መጠኑ 1.98 ቢሊዮን ነው፡፡

የቴሌብር የደንበኞች አጠቃላይ ዓመታዊ የግብይት ዋጋ 1.66 ትሪሊዮን ብር መሆኑን ያሳያል። ከዚህ ውስጥ፣ ከባንክ ወደ ቴሌብር ማስተላለፍ፣ የጅምላ ክፍያዎች እና በዓለም አቀፍ የሓዋላ አገልግሎቶች የሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦች ያሉ ዲጂታል ገቢዎች (Digital In) 27.1% ድርሻ ሲኖራቸው፤ ከቴሌብር ወደ ባንክ ማስተላለፍ፣ የአየር ሰዓት መሙላት እና የፍጆታ ክፍያዎች ያሉ ዲጂታል ወጪዎች (Digital Out) 18.9% ይይዛሉ። ለነጋዴ የሚከፈሉ ክፍያዎች እና እርስ በእርስ የሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦች (P2P) የመሳሰሉ የገንዘብ ዝውውሮች (Circulating) ደግሞ 35.8% ድርሻ አላቸው።

ይህ መረጃ ሚዛናዊ ፣ ጤናማ እና በዲጂታል የሚመራ የግብይት ሥነ-ምህዳርን ያንፀባርቃል። በከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ፣ በቴሌብር የሚከወን ከፍተኛ ድርሻ ያለው የንግድ ግብይት እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው መስተጋብር (interoperability)ቴሌብር የሀገራችንን የዲጂታል ፋይናንስ ትራንስፎርሜሽን ዘዋሪ ቁልፍ ሞተር መሆኑን በተጨባጭ ያሳያል።

በጂ.ኤስ.ኤም.ኤ (GSMA) ዓለም አቀፍ የሞባይል መኒ ሪፖርት (ሚያዝያ 2025) መሠረት፣ የገንዘብ ዝውውር (Circulating) በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም የሞባይል ገንዘብ አፈጻጸም መለኪያ ሲሆን፣ ከጠቅላላ የዋጋ መጠን 28% ይይዛል።  ቴሌብር ይህንን መለኪያ በማለፍ፣ በ2024/25 የገንዘብ ዝውውር ግብይቶቹ ከጠቅላላ የግብይት ዋጋው 35.8% በመድረስ አስደናቂ አፈጻጸም አስመዝግቧል። 

የቴሌብር የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት አፈጻጸም

ቴሌብር አገልግሎት ለማህበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ አነስተኛ የቁጠባ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ከባንኮች ጋር በመተባበር ቀርበዋል። በበጀት አመቱ 6.88 ሚሊዮን ደንበኞች ከ13.22 ቢሊዮን ብር በላይ አነስተኛ  ብደር ሲያገኙ ከ1.77 ሚሊዮን ደንበኞች 11.24 ቢሊዮን ብር የዲጂታል ቁጠባ አከናውነዋል፡፡

በአጠቃላይ የቴሌብር አገልግሎት ከጀመረበት አንስቶ በአራት አመታት ውስጥ ከ11.92 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ከ25.8 ቢሊዮን ብር በላይ አነስተኛ ብድር ሲያገኙ፣ በ3.91 ሚሊዮን ደንበኞች 24.59 ቢሊዮን ብር በላይ የዲጂታል ቁጠባ ተከናውኗል፡፡ እነዚህ ስኬቶች ቁጥሮች ብቻ ሳይሆኑ ተለውጠው ያለፉ ህይወቶችን፣ በድል የታለፉ መሰናክሎችን፣ እንዲሁም ይበልጥ አካታችና ፍትሃዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት የዲጂታል ፋይናንስ ያለውን አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያመላክቱ ናቸው።

የቴሌብር ሱፐርአፕ

ከ8 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ከ68 በላይ ሚኒአፖችን አካቷል። ዘመን ገበያ የተሰኘ ልዩ ሀገር አቀፍ የዲጂታል ኢኮሜርስ ፕላትፎርም በመፍጠር በንግድ ሥነ ምህዳሩ ላይ መነቃቃት እና የዲጂታል ግብይቶችን ማሳደግ እንዲሁም የስራ እድል መፍጠር ተችሏል።

የሰው ኃይል አቅም ግንባታ

 የኩባንያውን ውድ ሀብት የሆነውን የሰው ኃይል በእውቀት፣ በክህሎትና በላቀ የሥራ ሥነ-ምግባር በማነጽ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥራ ተከናውኗል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ለ54.9ሺህ ሰራተኞች ተከታታይ ሥልጠናዎችን መስጠት ተችሏል (አንድ ሰራተኛ ከአንድ በላይ ስልጠና ሲወስድ ድግግሞሹ ይቆጠራል)። ከዚህ በተጨማሪ ልዩ የሙያ ብቃትን በሚያረጋግጡ 60 የሰርተፊኬሽን ፕሮግራሞች 487 ባለሙያዎችን ሰርቲፋይ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ከሊንክድ-ኢን ጋር በተደረገ ስትራቴጂካዊ ስምምነት መሠረት 85% የሚሆኑ ሠራተኞች ከሙያቸው ጋር የተጣጣሙ የኦንላይን ሥልጠናዎችን በስፋት በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በተመቻቸው ነጻ የስልጠና እድል፣ 936 የኩባንያችን ሰራተኞች 1,828 የምስክር ወረቀት ለማግኘት ችለዋል፡፡ በተጨማሪም ኩባንያችን ለመርሃ ግብሩ ተሳታፊ 484,274 ኢትዮጵያውያን ነጻ114.45 GB ኢንተርኔት ያቀረበ ሲሆን የተደረገው ድጋፍ በአጠቃላይ ብር 21,737,830 ይደርሳል።

ኩባንያችን የሴት ሠራተኞችን ወደ አመራር ለማምጣት ስትራቴጂ ነድፎ በተግባር በመተርጎም ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ጥረት በቅርቡ በተደረጉ የዳይሬክተሮች ምደባ የሴቶችን ድርሻ ከ4% ወደ 13% በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ይህንን ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል ሰራተኞችን ያሳተፈ የዳሰሳ ጥናት ተከናውኗል፡፡ በበጀት ዓመቱ በዋና ሥራ አስፈጻሚያችን የተመሩ ተከታታይ ስትራቴጂያዊ አውደ ጥናቶች የተካሄዱ ሲሆን እነዚህም የፕሮጀክት አፈጻጸምን በማሻሻል፣ በሀብት አጠቃቀም፣ በአሰራር ሥርዓት ማሻሻያ፣ በደንበኞች ተሞክሮ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖች፣ በምርት እና አገልግሎቶች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡

የገቢ እና ሥራ እድል ፈጠራ

 ኩባንያችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥነ-ምህዳርን በመገንባት ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተውን ቁልፍ የአስቻይነት ሚና ከመወጣት ጎን ለጎን፣ ለዜጎች ዘላቂ የሥራ እና የገቢ ዕድል በመፍጠር ሀገራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛል። በዚህም መሠረት፣ በቋሚና በጊዜያዊ ቅጥር ከሚፈጠሩት ቀጥተኛ የሥራ ዕድሎች ባሻገር፣ በምርትና አገልግሎት አከፋፋይነት፣ በተለያዩ የአጋርነት ሞዴሎች እና በመሳሰሉት ሰፊ የሥራ ዘርፎች ለአያሌ ዜጎች የሥራና የገቢ ዕድል እንዲፈጠር አስችሏል።

በዕድገት ስትራቴጂ ዘመን በጥበቃ፣ በኔትዎርክ ዝርጋታ፣ በጥገና፣ በትራፊክ ቁጥጥር፣ በኮንስትራክሽን ስራ፣ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባብ እና በሦስተኛ ወገን በኩል በተፈጠሩ ቋሚና በጊዜያዊ የሥራ መደቦች እንዲሁም በመደበኛ እና በቴሌብር ምርትና አገልግሎት አከፋፋይነት፣ በአጋርነት ሥራዎች ከ 1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራና የገቢ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

የሳይበር ደህንነት

ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅምን በመገንባት፣ የተቀላጠፈ የአሰራር ሂደትን በመዘርጋት እና ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችን በመተግበር፣ ከ461,152 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በላቀ ብቃት በመመከት ሊደርሱ ይችሉ የነበሩ የዳታ ምዝበራን፣ የአገልግሎት መቋረጥን እና የገቢ ብክነትን ሙሉ በሙሉ መከላከል ችሏል።

ለዚህ ስኬት፣ ቀን ከሌት የሚሰራ የሳይበር ደኅንነት ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱ፣ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን አስቀድሞ የመለየትና የመከላከል አቅም መገንባቱ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከመቀመርና እንደ ISO 27001 ያሉ የተገዥነት መስፈርቶችን (Compliance Standards) በጥብቅ በመተግበር ሊከሰቱ የሚችሉ ሥጋቶችን የመቀነስ ስትራቴጂ መተግበሩ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

በሌላ በኩል የኢንፎርሜሽን ሴኩሪቲ አገልግሎትን በመስጠት ገቢን ማስፋት እና ማሳደግ የተቻለ ሲሆን  የደህንነት መስፈርቶችን አሟልቶ አገልግሎቱን ማቅረብ ተችሏል፡፡ በዚህም የSSL ሰርተፊኬት አገልግሎቶችን ለበርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ትምህርት ተቋማት በማቅረብ፣ የ IP ደህንነት VPNን ለስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ማቅረብ ተችሏል፡፡

በLEAD  Growth ስትራቴጂ ዘመን ኩባንያችን ISO 27001:2022፣ PCI DSS እና Cloud Security Alliance (CSA) የተሰኙ አለም አቀፍ የጥራትና የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬቶችን ለቴሌብር እና ለቴሌክላውድ አገልግሎቶች ያገኘ ሲሆን ይህም  ኩባንያችን አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በማቅረብ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ለማሳካት ያለውን ተቋማዊ ብቃት በተግባር ያሳያል።

ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት

ኩባንያችን የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ቁልፍ የማኅበራዊ ልማት ዘርፎች ማለትም በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ ይገኛል። በዚህም መሠረት በበጀት ዓመቱ በዓይነት 264.1 ሚሊዮን ብር፣ በገንዘብ 186.1 ሚሊዮን ብር በድምሩ 450.23 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ ያደረገ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ለትምህርት 134.68 ሚሊዮን ብር፣ ለጤና 17.68 ሚሊዮን ብር፣ ለሰብአዊ 135.77 ሚሊዮን ብር፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአረንጓዴ ልማትና ማስዋብ 16.75 ሚሊዮን ብር እና ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች 145.35 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ኩባንያችን የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሰራተኞችና አጋሮቻችንን በማሳተፍ በመላው አገሪቱ ችግኞች እንዲተከሉ ያደረገ ሲሆን በበጀት ዓመቱም በ6ኛው ዙር በ105 ጣቢያዎች ከ446 ሺ በላይ ችግኞች በመትከል ማህበራዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል። በተጨማሪም ሠራተኞቻችን የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የ3.4 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግና ለአካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከተለዩ ወሳኝ ምሰሶዎች አንዱ የሆነውን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራምን ስኬት ለማረጋገጥ፣ ኩባንያችን የተሰጠውን ሀገራዊ ኃላፊነት በመወጣት የምዝገባ እና ህትመት ሂደቱን በመላ ሀገሪቱ የማፋጠንና የማስፋፋት ሥራን በልዩ ትኩረት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ለዚህም 2,000 የባዮሜትሪክ መመዝገቢያ ማሽኖች በመግዛት እና ተጨማሪ 1,500 ማሽኖችን ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽ/ቤት በውሰት በማግኘት፣ አስፈላጊውን ሀብት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማሟላት ምዝገባው በ12 ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በ575 የሽያጭ ማዕከሎቻችን እንዲሁም በ769 ከተሞች፣ በ104 ዞኖች እና በ670 ወረዳዎች ላይ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በአጠቃላይ በ 16 የህትመት ቦታዎች በ270 መቀበያ ማዕከሎች ማለትም በአዲስ አበባ በሁሉም ዞኖች በ 7 ቦታዎች እንዲሁም በሪጅን በ 9 ቦታዎች እየተተገበረ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን የ11 ሚሊዮን ደንበኞች ምዝገባ የተካሄደ ሲሆን፣ ለ9.7 ሚሊዮን ደንበኞች የፋይዳ ቁጥራቸውን እንዲያውቁ ተደርጓል፤ በበጀት ዓመቱ 10.4 ሚሊዮን ዜጎችን በመመዝገብ ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ 2.94 ቢሊዮን ብር ማግኘት የተቻለ ሲሆን በአሁን ወቅት ዕለታዊ የምዝገባ ምጠና በአማካይ 70 ሺ ማድረስ ተችሏል፡፡

በመሪ ዕድገት የሦስት ዓመታት ስትራቴጂ (2022-2025) የተገኙ አበይት ስኬቶች!

የLEAD  Growth 2025 ስትራቴጂ ኩባንያችን ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድር ገበያው ኦፕሬት ያደረገበትና ልምድ የቀሰመበት እንዲሁም በውድድር ገበያው ውስጥ የመሪነት ደረጃውን ጠብቆ እንዲቆይ ያስቻለ ወሳኝ ምዕራፍ ነበር። ይህ ስትራቴጂ በተለይ ኩባንያችን ከመሠረታዊ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር መሪ የዲጂታል ሶሉሹን አቅራቢ የመሆን ራዕይን ሰንቆ መጠነ ሰፊ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ያስፋፋበት፣ የፋይናንስ ዘላቂነት ለማረጋገጥ አዳዲስ የቢዝነስ ዘርፍችን ያስተዋወቀበት፣ የቴሌብር የሞባይል ገንዝብ አገልግሎቱን በእጅጉ  ያሳደገበት እና ከባንኮች ጋር በአጋርነት ባስጀመራቸው የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ አገልግሎቶች የፋይናንስ አካታችነትን ያረጋገጠበት፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ላይ የተካተቱ ዋና ዋና ግቦች በማሳካት ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውንነት ያለውን ቁርጠኝነት ያጸናበት፣ የ4ጂ LTE እና የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ እንዲሁም የገጠር ተደራሽነትን ለማረጋገጥ (Rural Connectivity) የማስፋፊያ ስራዎችን በስፋት በማከናወን እና የሀገሪቱን ኔትወርክ ሽፋን በእጅጉ በማሳደግ የዲጂታል አካታችነትን ያረጋገጠበት፣ አዳዲስ ደንበኛ ተኮር የሆኑና ጊዜውን የዋጁ የቴክኖሎጂ ምርት እና አገልግሎቶችን የማስተዋወቅ እና አዋጭነትን የማረጋገጥ ስራዎች የተሰሩበት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ዘመናዊ ቀፎችን በማቅረብ የስማርት ቀፎ ስርጸትን ማሳደግ የተቻለበት፣ የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ቁልፍ የማኅበራዊ ልማት ዘርፎች በተለይም በአረንጓዴ ልማት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የብራንዱን ተቀባይነት ያሳደገበት፣ በየጊዜው የደንበኞች ዕርካታ ዳሰሳን በገለልተኛ ወገን በማከናወን የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት የተጋበት፣ ለሸማቹም ሆነ ለነጋዴው ማህበረሰብ ምቹ እና ቀልጣፋ የሆነ ዘመን የተሰኘ የዲጂታል ግብይት /Ecommerce/ ፕላትፎርም ያስተዋወቀበት እንዲሁም በደንበኛ ቁጥር እና በገቢ ዕድገት አስተማማኝ ዕድገት ያስመዘገበበት ወሳኝ የስኬት ምዕራፍ ሆኖ ተጠናቋል።

በመሪ (LEAD Growth) የሶስት አመት የእድገት ስትራቴጂ ውስጥ በተወሰዱ ስትራቴጂክ እርምጃዎች በቴሌኮምና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያዎች ተጨማሪ የ35.2 ሚሊዮን የሞባይል ኔትዎርክ ደንበኞች የማስተናገድ አቅም በመገንባት በBRIDGE ስትራቴጂ የነበረውን 69.6 ሚሊዮን አቅም ወደ 104.8 ሚሊዮን ማድረስ የተቻለ ሲሆን አጠቃላይ 2,514 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች በመገንባት በBRIDGE ስትራቴጂ 7,496 የነበረውን የሞባይል ጣቢያ ብዛት 10,010 ማድረስ ተችሏል፡፡

በዚህም በ”BRIDGE ስትራቴጂ የነበረውን 99.1% የኔትወርክ የህዝብ ሽፋን (Mobile Network Population Coverage) በ0.3% በማሳደግ 99.4% ማድረስ የተቻለ ሲሆን የኔትዎርክ የቆዳ ሽፋን (Geographical Coverage) በ1.1% በማሳደግ  ከ85.4% ወደ 86.5% ማድረስ ተችሏል፡፡

በተለይም የ4G የህዝብ ሽፋንን (Population Coverage) ለማሳደግ በተደረገ አስደናቂ ርብርብ በስትራቴጂ ዘመኑ  871 ተጨማሪ ከተሞችን የ4G አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል አጠቃላይ 936 ከተሞች የ4G አገልገሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም 4G የህዝብ ሽፋን (Population Coverage ከ19.9% ወደ 70.8% ማሳደግ የተቻለ ሲሆን የቆዳ ሽፋንን (Geographical Coverage) ከ1.44% ወደ 21.06% ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም የ5G አገልግሎት የሚሰጡ የሞባይል ጣቢያዎችን ወደ 315 ጣቢያዎች በማስፋፋት እና Massive MIMOን በመተግበር ኩባንያችን በኔትዎርክ ማስፋፋትና ማዘመን መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የደንበኞችን የአገልግሎት አጠቃቀም እድገት አዝማሚያ ስንመለከት በሞባይል ዳታና ኢንተርኔት አገልግሎት የታየው እድገት በድምጽ አገልግሎት ከታየው እድገት አንጻር ሲታይ ከድምጽ አገልግሎት ወደ ብሮድባንድ አገልግሎት ተጠቃሚነት ያለውን ሽግግር አመላካች ሲሆን ይህም ሀገራችን እያደረገች ላለችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የማህበረሰባችንን የኑሮ ዘይቤ ለውጥ የሚያሳይ እና ተቋማችንም መጪውን ጊዜ ያማከለ (future ready) ስትራቴጂ መተግበሩን ማሳያ ነው፡፡

በሌላ በኩል የገጠር ማህበረሰባችንን የዲጂታል ሶሉሽን እና ፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ባደረግነው ጥረት በBRIDGE ስትራቴጂ በ11 ሪጅኖች የነበረውን 77 የገጠር ሞባይል ሳይቶች ብዛት በLEAD Growth ስትራቴጂ በ12 ሪጅኖች ወደ 954 በማሳደግ በ529 ወረዳዎች፣ በ2,677 ቀበሌዎች የሚኖሩ 6.5 ሚሊዮን ነዋሪዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

በፊክስድ ኔትወርክ አገልግሎት 724.2ሺ የኦፕቲካል ዲስትሪቢውሽን ኔትወርክ (ODN) አቅም በመገንባት በBRIDGE ስትራቴጂ የመጨረሻ ዘመን የነበረው 228 ሺ የኦፕቲካል ዲስትሪቢውሽን ኔትወርክ አቅም ወደ 952 ሺ ማሳደግ ተችሏል፡፡

በLEAD Growth ስትራቴጂ አጠቃላይ 2,099.34 ኪ.ሜ. የባክቦን ፋይበር ዝርጋታ የተከናወነ ሲሆን በዚህም OPGWን ጨምሮ አጠቃላይ የተዘረጋውን የባክቦን ፋይበር ርዝመት መጠን 22,673.1 ኪ.ሜ ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም የሜትሮ ፋይበር 14,240 ኪ.ሜ ደርሷል።

በሦስት አመት ውስጥ 452.7 ቢሊየን ደቂቃ የሞባይል የድምፅ ጥሪ፤ 2.76 ቢሊየን ደቂቃ ወደ አገር ውስጥ የተደረገ ዓለም አቀፍ የድምፅ ጥሪ፣ 77.69 ቢሊየን የአጭር የጽሁፍ መልዕክት፣ እንዲሁም 2.96 ትሪልዮን ሜጋ ባይት የሞባይል ዳታ ትራፊክ ተመዝግቧል፡፡ ከBRIDGE ስትራቴጂ ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የድምጽ ጥሪ 107.6%፣ ወደ አገር ውስጥ የተደረገ ዓለም አቀፍ የድምፅ ጥሪ 10.7% የአገር ውስጥ አጭር የጽሁፍ መልዕክት 261.2% እንዲሁም የሞባይል ዳታ ትራፊክ 446.2% እድገት አሳይቷል፡፡

የዳታ ትራፊክ አፈፃፀሙን በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው የደንበኞች ቁጥር እና የዳታ አጠቃቀም ባህሪ ማደግ፣ ተጨማሪ የኔትዎርክ መሰረተ ልማቶች መዘርጋት፣ አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶች ወደ ገበያ መውጣት፤ ተከታታይ የሆነ የኔትዎርክ ማትባት ስራዎች መሰራት፣ የዋጋ ተመጣጣኝነትን ለደንበኞቹ ከማረጋገጥ አንፃር ከ2018 ጀምሮ የተደረገው ተከታታይነት ያለው የዋጋ ቅናሽ እንዲሁም ከአጋሮች ጋር ያለው ትብብር ማደግ ናቸው።

የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የዳታ ሴንተር እና የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሰረት በማድረግ በስትራቴጂ ዘመኑ 3 MW IT Load ፣ 384 IT Rack እና 16128 U ተጨማሪ አቅም በመገንባት አጠቃላይ የዳታ ሴንተር አቅማችንን ወደ 5 MW IT Load ፣ 624 IT Rack እና 26,208 U ማሳደግ የተቻለ ሲሆን የክላውድ ኢንፍራስትራክቸር ማስፋፊያ ስራዎችን በመተግበር በelastic compute 31,616 vCPU፣ storage 4.5 PB እንዲሁም ኢንተርፕራይዝ ስቶሬጅ 3 PB የዳታ ሴንተር አቅም በመገንባት ከ650 በላይ የመንግስት እና የግል ተቋማት አሰራራቸውን ዲጂታላይዝ እንዲያደርጉ አስችሏል፡፡

በአጠቃላይ የስትራቴጂው ዘመን 838 ምርትና አገልግሎት ለገበያ ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 432 አዳዲስ እና 359 ማሻሻያ የተደረገባቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የሚሰጡ፣ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አካታች የዲጂታል መፍትሄዎችን የሚያረጋግጡ ምርትና አገልግሎቶችን ማቅረብ ተችሏል። ይህም በBRIDGE ስትራቴጂ ወቅት ከነበረው 275 ምርትና አገልግሎት ጋር ሲነፃጸር በ 3 እጥፍ የሚጠጋ ምርትና አገልግሎት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ያሳያል።

የአገልግሎቶቻችንን ተደራሽነት ለመሳደግ በስትራቴጂ ዘመኑ 386 ተጨማሪ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የተከፈቱ ሲሆን በBRIDGE ስትራቴጂ የነበሩትን 652 የአገልግሎት መስጫ ማእከላት ብዛት ወደ 1,038 ማድረስ ተችሏል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተልማት ማስፋፊያዎች በመስራት16.6 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት የደንበኞቻችን ቁጥር 83.2 ሚሊዮን  ለማድረስ የተቻለ ሲሆን ከቀደመው የBRIDGE ስትራቴጂ የመጨረሻ ዓመት አፈጻጸም አንጻር የ24.9% እድገት  አስመዝግቧል። የስማርት ፎን ስርጸት በBRIDGE ስትራቴጂ መጨረሻ 36.3% የነበረ ሲሆን፣ ኩባንያችን ባቀረባቸው የተለያዩ ተደራሽ የስማርትፎን አማራጮች አማካኝነት በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ የስርጸት መጠኑን 41% ወይም 33 ሚሊዮን ለማድረስ ተችሏል።

በአጠቃላይ በLEAD ስትራቴጂ ዘመን 331.5 ቢሊየን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን ይህም ገቢ ከBRIDGE ስትራቴጂ ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ100% እድገት አለው፡፡ ባለፉት ሦስት አመታት ለገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካደረጉት ስትራቴጂክ እርምጃዎች መካከል የቴሌብር ፋይናንሻል አገልግሎት መጀመሩ፣ የናሽናል ኢንተርኮኔክሽን ትራፊክ መጨመሩ፣ የመሰረተ ልማት ማከራየት፣ ከ900 በላይ የሞባይል ጣቢያዎች መልሶ በማቋቋም ወደ ስራ መግባታቸው፣ ወደ አገር ውስጥ የተደረጉ የዓለም አቀፍ ጥሪ ገቢ መጨመር፣ የኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽን በስፋት መተግበሩ፣ የ4G እና 5G የሞባይል ኔትዎርክ ማስፋፊያ መደረጉ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ኩባንያችን ላለፉት አራት ዓመታት የወጪ ቁጠባ ባህልን ለማጎልበት የሀብት አስተዳደር እና ወጪ ቅነሳ ፕሮግራምን ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት 22.4 ቢሊዮን ብር ወጪ በመቆጠብ የዕቅዱን 131 በመቶ አፈፃፀም አሳይቷል፡፡ በተመሳሳይ በሦስት ዓመቱ አዳዲስ የገቢ አማራጮች በመፍጠር እና ኮር ቢዝነሱን ለመደገፍ በተሰሩ ሥራዎች 729.8 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡

ባለፉት አመታት በተደረጉ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ኢንቨስትመንቶች የኩባንያችን አጠቃላይ ሀብት ከ215 ቢሊየን ብር ወደ 329 ቢሊየን ብር ያደገ ሲሆን የተጣራ ሀብቱ ደግሞ ከ7 ቢሊየን ወደ 115 ቢሊየን አድጓል፡፡

ቴሌብር የዲጂታል የክፍያ ስርዓቱን ቀላል ፈጣን ምቹና አስተማማኝ በማድረግ cashlite society መፍጠር የቻለ ሲሆን በሊድ የስትራቴጂ ዘመን ተጨማሪ 33.9 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት   የተጠቃሚዎቹን ቁጥር 54.84 ሚሊዮን ያደረሰ ሲሆን ከBRIDGE ስትራቴጂ የመጨረሻ ዓመት ከነበረው 20.94 ሚሊዮን አንጻር የ161.9% እድገት አለው፡፡

አጠቃላይ በቴሌብር የተከናወነ የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር በ2021/22 ከነበረው 24.67 ቢሊየን ብር ወደ 2.38 ትሪሊዮን ብር ያደገ ሲሆን የግብይት መጠኑም ከ85.07 ሚሊዮን ወደ 1.06 ቢሊየን አድጓል፡፡

በአጠቃላይ የቴሌብር አገልግሎት ከጀመረበት አንስቶ በአራት አመታት ውስጥ ከ11.92 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ከ25.8 ቢሊዮን ብር በላይ አነስተኛ ብድር ሲያገኙ፣ 3.91 ሚሊዮን ደንበኞች 24.59 ቢሊዮን ብር በላይ የዲጂታል ቁጠባ አከናውነዋል፡፡ እነዚህ ስኬቶች ቁጥሮች ብቻ ሳይሆኑ ተለውጠው ያለፉ ህይወቶችን፣ በድል የታለፉ መሰናክሎችን፣ እንዲሁም ይበልጥ አካታችና ፍትሃዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት የዲጂታል ፋይናንስ ያለውን አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያመላክቱ ናቸው።

የሊድ ስትራቴጂ ካስገኛቸው ትሩፋቶች አንዱ የተለምዶውን የግብይት ሥርዓት በማዘመን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ዘመን ገበያን የተሰኘ የዲጂታል ገበያ ሲሆን ይህም በተለይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን (MSMEs) ጨምሮ የምርትና አገልግሎት አቅራቢዎችን ከሸማቾች ጋር በማገናኘት አዲስ የገበያ ዕድል የሚፈጥርና በዲጂታል ኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የዲጂታል የገበያ መፍትሔ ነው።

በሊድ ስትራቴጂ ማጠናቀቂያ በጀት ዓመት ሁለት አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ተተክለው  አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን እነዚህ ጣቢያዎች እጅግ በጣም ፈጣን (super-fast) እና ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው (ultra-fast) ኃይል መሙያዎችን የያዙ ሲሆን፣ የ1000 KW አጠቃላይ አቅም አላቸው። ጣቢያዎቹ በአንድ ጊዜ 32 መኪናዎችን መሙላት የሚችሉ ሲሆን፣ ለአረንጓዴ የትራንስፖርት (green mobility) ተነሳሽነቶች ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። እስከ በጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ድረስ እነዚህ ጣቢያዎች 73 ሺ ለሚጠጉ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሰጡ ሲሆን ፣ 2.6 ሚሊዮን ኪግ የሚጠጋ የካርቦን ልቀት ቅነሳ ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ተችሏል።

በሌላ በኩል ኩባንያችን በስትራቴጂ ዘመኑ የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ቁልፍ የማኅበራዊ ልማት ዘርፎች በተለይም በአረንጓዴ ልማት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የብራንዱን ተቀባይነት ያሳደገበት ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢያዊ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ልማትና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በድምሩ 1.58 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡

ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች

 በበጀት ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ዋና ዋና ተግዳሮቶች የነበሩ ሲሆን በማክሮ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ምክንያት የብር የመግዛት አቅም መዳከም፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በልማት ሥራ፣ በአደጋ፣ በጸጥታ ችግሮች፣ በኬብል ስርቆት እና በቴሌኮም መሠረተ ልማት ላይ የደረሱ ጉዳቶች፣ የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች የአቅም ውስንነት፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥና የነዳጅ እጥረት ዋነኞቹ ነበሩ፡፡

 በተጨማሪም የዲጂታል ፋይናንስ ቴሌብር አገልግሎትን በተመለከተ፣ ከዲጂታል ዝውውሮች ጋር የተያያዙ የማጭበርበር እንቅስቃሴዎች፣ የባንክ ፈንድ አቅርቦት ላይ ያሉ ገደቦች፣ የደንበኞችን መረጃ (KYC) ለማረጋገጥ የሚያስችል ሀገራዊ አሰራር አለመተግበር፣ የዓለም አቀፍ ትራፊክ መቀነስ ተጽዕኖ አሳድረዋል፡፡

 እነዚህን ተግዳሮቶች ከፌዴራል እና ክልል የመንግሥት አካላት ጋር በቅርበት በመሥራትና አንዳንድ የቴሌኮም ግብዓቶችን ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች በመሸፈን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል፡፡ በተለይም ከህግ አውጪ አካላት ጋር በተደረጉ ውይይቶች ውጤት እየተገኘ ሲሆን፣ ደንበኞችን ከማጭበርበር ለመጠበቅ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች በስፋት ተካሂደዋል፡፡ እንዲሁም አዳዲስ የዓለም አቀፍ ትራፊክ ማሳደጊያ ስልቶችን በመከተል አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡

ለተመዘገበው ስኬት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ጉዳዮች 

ኩባንያችን ላስመዘገበው ስኬት ራዕይ ያለው አመራር እና ቀልጣፋ አስተዳደር፣ የሰራተኞች ቁርጠኝነትና መናበብ፣ ውጤታማ የፕሮጀክት አመራር እና አፈጻጸም፣ተቋማዊ ቅልጥፍና እና ውጤታማ ስትራቴጂ፣ ጠንካራ ሽርክናዎች እና የባለድርሻ አካላት አስተዳደር፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ደንበኞች ያገናዘበ የዋጋ ተመጣጣኝነት፣ የደንበኞቻችን ከእኛ ጋር የመቆየት ፍላጎት፣ የኩባንያችን ማህበራዊ ኃላፊነት እና መልካም ዝና፣ ስትራቴጂክ ፋይዳ ባላቸው ቴክኖሎጂዎችና ፕላትፎርሞች ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶችና ትግበራዎች እንዲሁም የፋይናንስ ዘላቂነት እና የወጪ ቁጠባ ስራዎች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

እውቅና እና ሽልማት

ባለፉት ሶስት ዓመታት ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት እና አበርክቶዎች፣ በተጎናጸፍናቸው ስኬቶች ኩባንያችን እና ዋና ስራ አስፈፃሚያችን ከፍተኛ እውቅናዎችን እና በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል።  ከተጠቃሽ ዕውቅናዎች መካከል፦

  1. በ2016 ቀዳሚ ግብር ከፋይ በመሆናችን የፕላቲነም ደረጃ እንዲሁም ከ2013-2016 ለአራት ተከታታይ ዓመታት ቀዳሚ ግብር ከፋይ በመሆናችን ልዩ ሽልማቶችን አግኝቷል፤
  2. በዓለም አቀፍ ደረጃ ላገኘነው ስኬት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት አግኝቷል፣
  3. ኩባንያችን ሁለንተናዊ የደንበኞች ተሞክሮን ለማሻሻል ላደረገው ጥረት ዱባይ ላይ በተካሄደው የGITEX 2023 ኤክስፖ ከAVAYA ኩባንያ እውቅና አግኝቷል፣
  4. ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያ ጣቢያዎችን በመገንባት፣ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ እና ለአረንጓዴ አሻራ ያደረግነውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ አረንጓዴ ሽልማት 2025 እውቅና አግኝቷል፣  ይህም የአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኝነታችንን አረጋግጧል።
  5. ቴሌብር ምርጥ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በመባል በጁኒፐር ሪሰርች የወርቅ ሽልማት ያገኘ ሲሆን እንዲሁም የስነ-ምህዳር አሸናፊ (Eco System Champion) በመሆኑ የስትራይድ ሽልማት 2024 ዕውቅና አግኝቷል።
  6. በ15ኛው ዓመታዊ የAfrica’s Best Brands Award የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ውስጥ በጣም ተወዳጅ የንግድ ምልክት በመባል እንዲሁም ለህብረተሰቡ እና ለአካባቢው መልካም ስራ በመስራት በሁለት ዘርፍ እውቅና ተሰጥቶናል።
  7. ዋና ሥራ አስፈፃሚ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና ከመቶ መሪዎች መካከል  ከፍተኛ ወጣት የአፍሪካ መሪ ተብለው በቀዳሚነት በፎርብስ አፍሪካ እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን በዚሁ የስትራቴጂ ዘመን በጣም የተከበሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች ሽልማትንም /Most Respected CEO’s Award/ ተቀብለዋል። 
  8. በተፅዕኖ ፈጣሪነት፣ ውጤት ተኮር አመራር እና የተረጋገጠ የስኬት ታሪክን ከግንዛቤ በማስገባት ዋና ሥራ አስፈፃሚያችን  በGSMA የዳይሬክተሮች ቦርድ ለሁለተኛ የአገልግሎት ዘመን የተመረጡ ሲሆን በተጨማሪም በGSMA ፋውንዴሽን ቦርድ ተሹመዋል።

በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ እና በስትራቴጂ ዘመኑ የተመዘገበው ታላቅ ስኬት የጋራ ርብርብ ውጤት በመሆኑ ለውድ የኩባንያችን ቤተሰብ፤ ለክቡራን ደንበኞቻችን፤ እንዲሁም ስትራቴጂካዊ አጋሮቻችን ለሆናችሁ አከፋፋዮች፣ አቅራቢዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና ለመላው ባለድርሻ አካላት ልባዊ ምስጋናችን እያቀረብን የጀመርነውን የሃገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አጠናክረን በመቀጠል ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ እናረጋግጣለን።

ኢትዮ ቴሌኮም

ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on reddit
Share on pinterest
Share on tumblr
Share on whatsapp

Follow Us

Recent Posts

Archives