ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስትራቴጂዎች የ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርኮችን በከፍተኛ ደረጃ በማስፋፋት የኔትወርክ ተደራሽነትን በዘላቂነት ሲያረጋግጥ የነበር መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በዚህም በሀገሪቱ የ4ጂ ህዝብ ሽፋን 71% በማድረስ አስደናቂ የሽፋን ምዕራፍ ላይ በብቃት ደርሷል።
በዚህ ስኬታማ ውጤት ላይ በመመስረት ኩባንያችን በ “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከ2028 ባሻገር ስትራቴጂ” በከፍተኛ የስማርት ዲቫይሶች ዋጋ ምክንያት የተከሰተውን የአጠቃቀም ክፍተት (usage gap) ላይ አተኩሮ በመስራት ላይ ይገኛል። ይህንን ስማርት ዲቫይሶች ዋጋ ተመጣጣኝ ያለመሆን ችግር ለመፍታት እና የተዘረጋውን ሰፊ የኔትወርክ መሠረተ ልማት በመጠቀም የዲጂታል ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እና ሁሉም ዜጋ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተካታች እንዲሆን ለማበረታታት ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸውን ክላውድን መሠረት ያደረጉ ዘኔክሰስ የተሰኙ ስማርት ዲቫይሶች የሞባይል ስልኮች፣ ታብሌቶች፣ ዴስክቶፖች፣ ላፕቶፖች፣ ቲን ክላየንት (thin clients) እና የክላውድ ዎርክስፔስ መፍትሔዎችን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
በኢትዮጵያና በሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የስማርት ስልክ አጠቃቀም ክፍተት መፍትሔ
በተለይ በሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የቴሌኮም መሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ቢሆንም በርካታ ማህበረሰቦች በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ከዲጂታል ተጠቃሚነት የተገለሉ ሲሆን እነሱም የስማርት ስልኮች ከፍተኛ ዋጋ ውድነት እና ውስን የዲጂታል እውቀትና ክህሎት መኖር ናቸው።
በተመሳሳይ በሀገራችን የ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርኮች በስፋት ቢዘረጉም አብዛኛው ዜጋ የዲጂታል ሥነ ምህዳሩ የፈጠረውን መልካም እድሎች በአግባቡ መጠቀም ሳይችል አሁንም መሰረታዊ የ2ጂ/3ጂ ስልክ አገልግሎቶችን ብቻ በመጠቀም ላይ ይገኛል። በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ60% በላይ የሚሆኑት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ የሞባይል ተጠቃሚዎች የኔትወርክ ሽፋን ያለበት አካባቢ የሚኖሩ ቢሆንም የስማርት ስልኮችን መግዛት ባለመቻላቸው ወይም በዲጂታል ክህሎት ማነስ ምክንያት ከዲጂታል አገልግሎቶች ተገልለው ይገኛሉ።
ይህ “የአጠቃቀም ክፍተት” የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን ለማፋጠን ካሉብን ተግዳሮቶች መካከል ዋነኛው ሲሆን አካታች እና ተደራሽ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉ እንደ የዲጂታል ክፍያ፣ ኢ-ትምህርት፣ የጤና አፕሊኬሽኖች፣ የግብርና ፕላትፎርሞች እና ኢ-ጋቨርንመንት የመሳሰሉ ቁልፍ አገልግሎቶችን እንዳይገኙ እንቅፋት ይፈጥራል።
ዘኔክሰስ፡ የአጠቃቀም ክፍተትን ለመሙላት የተዘጋጀ መፍትሔ!
የኢትዮ ቴሌኮም ዘኔክሰስ የተዘጋጀው ይህን የአጠቃቀም ክፍተት ለመሙላት በተለይ በማሰብ ሲሆን ብራንዱ ሰውን ማዕከል ያደረገ እና በቴሌክላውድ (teleCloud) የሚሰራና የሚከተሉት መፍትሄዎች ያሉት ነው፡-
- የፕሮሰሲንግ አቅምን ወደ ቴሌክላውድ (teleCloud) በማዘዋወር የዲቫይሶችን ዋጋ ተመጣጣኝ ያደርጋል፣
- ለተጠቃሚ ምቹ የሆኑ (keypad + touchscreen) በመጠቀም የተጠቃሚዎችን ልምድ ያቀላል፣
- ለገጠራማ እና አነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ላላቸው አካባቢዎች ረጅም የባትሪ ዕድሜ አለው፣
- በተገጠመ የቴሌስቶሬጅ (teleStorage) አማካኝነት የፋይል ማከማቻ ገደቦችን ያስወግዳል፣
- እንደ ቴሌብር፣ የትምህርት ይዘት፣ ሚዲያዎች ያሉ ወሳኝ አፕሊኬሽኖችን ተጭኖባቸዋል፣
- ከሁሉም በላይ ደግሞ የመጀመሪያ ጊዜ ተጠቃሚዎች በቀላሉ አገልግሎቶችን እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡
ዘኔክሰስ ስማርት ስልክ ላይ የሚገኙ ወሳኝ መተግበሪያዎችን በክላውድ አማካይነት በማቅረብ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የዲጂታል ተጠቃሚነት ተግዳሮት የሆነውን የዋጋ ውድነት በዘላቂነት በመፍታት የDigital-First ማኅበረሰቦችን እውን ለማድረግ ያስችላል።
የዘኔክሰስ ዓላማ
የዜንኤክሰስ ዋና ዓላማ የዓለምን ወደ ቅድሚያ-ዲጂታል እውነታ በማምጣት ስማርትና በክላውድ የሚሰሩ ተመጣጣኝና ተደራሽ መሣሪያዎችን በማቅረብ ሀገራትን፣ ማኅበረሰቦችን፣ ኢንተርፕራይዞች እና ግለሰቦችን ማብቃት ነው፡፡
የዘኔክሰስ ቃል ኪዳን
የሃርድዌርን፣ ሶፍትዌርን፣ የክላውድ መሰረተ ልማትንና የአገር አቀፍ የኔትወርክ ግንኙነትን ያለምንም እንከን በሚያስተሳስሩ ፈጠራዎችን በተሞላባቸው በክላውድ ላይ ተመስርተው በተሰሩ መሣሪያዎች የዲጂታል ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ ነው።
ዘኔክሰስ በተመጣጣኝ ዋጋ የኔትወርክ ግንኙነትን፣ የክላውድ አገልግሎቶችንና ምርታማነትን፣ ትምህርትን እና ዕድገትን የሚያፋጥኑ መተግበሪያዎችን በማቅረብ ትምህርትን፣ ግብርናን፣ ጤናን፣ ንግድንና ከዚህም ባሻገር ያሉትን ዘርፎች ያዘምናል።
ዘኔክሰስ: አካታችነትን ማጎልበት፤ ተደራሽነትን እንደገና መወሰን፤ ለወደፊቱ ብርታት መሆን!
ኩባንያችን የዲጂታል ክፍተትን መቅረፍ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያነቃቃና የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ዘይቤ እንደሚያሻሽል በመገንዘብ የዲጂታልና የክላውድ ቴክኖሎጂዎችን ለሁሉም በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን ያስፋፋ ሲሆን 936 ከተሞችን በ4ጂ በማገናኘት የህዝብ ሽፋን 71% በማድረስ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም 5ጂ በ26 ከተሞች ዘርግቷል፡፡ እንዲሁም “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከ2028 ባሻገር ስትራቴጂ” ማጠናቀቂያ 99% 4ጂ ኤልቲኢ ሽፋን ለማድረስ ያቀደ በመሆኑ ይህ ኢኒሼቲቭ አገልግሎቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የስማርት ስልኮች ዋጋ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ያስችላል።
በዚህም መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም ዘኔክሰስ ዲቫይሶችን እንደ ከመደበኛዎቹ ስማርት ስልኮች አነንጻር በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለተጠቃሚዎች አስፈላጊ የሆኑ የስማርት ስልክ አገልግሎቶችን በሙሉ ይሰጣል። ይህንንም የበለጠ ለማሳደግና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የዲጂታልና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ክላውድን መሰረት ባደረገው ዘኔክሰስ ላይ ቴሌብርን አካትቶ አቅርቧል።
ይህ ኢኒሼቲቭ የዲጂታል ልዩነትን በመቅረፍ እና የአጠቃቀም ክፍተትን በመሙላት እንዲሁም ወደ ተግዳሮቶችን በመቀነስ የዲቫይስ አቅርቦትን በማሳደግ፣ የደንበኞችን የዳታ አጠቃቀም ልምድ፣ የክላውድ አገልግሎት አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነትን ከፍ በማድረግና ከግለሰቦች እስከ ኢንተርፕራይዞች አስተማማኝ የሆነ የዲጂታል ተሞክሮ ለማስፋት እንዲሁም የክላውድ ዎርክስፔስ መፍትሔዎች ድርጅቶች በዲጂታል አሰራራቸውን የሚቀይሩበት አስቻይ ሁኔታ ፈጥረዋል።
ዘኔክሰስ በተመጣጣኝ ዋጋ ክላውድን በመጠቀም የሚሰራ፣ አስተማማኝ የስማርት ሞባይል ስልክ ገጽታ ያለው ሲሆን የክላውድ ኮምፒውቲንግ አቅምን በመካተት የዋጋ ተመጣጣኝነትን ያረጋግጣል። ይህ ፈጠራ የታከለበት ዲቫይስ ተጠቃሚዎች ውድ የሆኑ ስማርት ስልኮችን ሳያስፈልጋቸው አስፈላጊ መሣሪያዎችን፣ ቴሌብር አገልግሎቶችን፣ የቴሌክላውድ ማከማቻ እና የአኗኗር ዘይቤ መተግበሪያዎችን እንዲያገኙ በማድረግ የዲጂታል ልዩነትን ለመቅረፍ ይረዳል።
ይፋ የተደረጉት ስማርት ዲቫይሶች ዘኔክሰስ 127 ላይት (znexus 127 Lite)፣ ዘኔክሰስ 131 ላይት (znexus 131 Lite) እና ዘኔክሰስ 2028 ላይት (znexus 2028 Lite) ሞዴሎች ሲሆኑ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ፣ ፌስቡክ፣ ጌሞች፣ አጫጭር ፊልሞች እና ዜናዎች የመሳሰሉ መተግበሪያዎች በክላውድ በማቅረብ ተጠቃሚዎች በቀላሉ የስማርት ስልክ (smartphone-lite) ተሞክሮ እንዲያገኙ ያስችላሉ።
ዘኔክሰስ በክላውድ ላይ የተመሰረተ እና ስማርት ስልኮች የሚሰጡትን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የስልክ አይነት ሲሆን፣ በተለይም አሁን ያሉ እና አዲስ የፊቸር ስልክ ተጠቃሚዎች፣ የቴሌብር ደንበኞች፣ ተማሪዎች፣ የገጠር ማህበረሰቦች፣ በእድሜ የገፉ ደንበኞች እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ቀላል፣ የተቀናጀ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ረዘም ላለ ጊዜ የሞባይል ቀፎዎችን መጠቀም ለሚሹ ደንበኞች ሁነኛ አማራጭ ነው። በተጨማሪም ባለ 4ጂ ኤል.ቲ.ኢ ኮኔክቲቪቲ፣ ረጅም የባትሪ አገልግሎት ዕድሜ፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ቴሌክላውድ ስቶሬጅ እና የተዋሃደ የፊት ገጽን (consolidated homepage) ከዘጠኝ-ግሪድ (9-grid) ማሰሻ ጋር በማጣመር ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ላይ ለማግኘት የሚያስችል ነው።
ቴሌስቶሬጅ (TeleStorage) በዘኔክሰስ ውስጥ የተካተተ የግል ክላውድ ስቶሬጅ አገልግሎት ሲሆን፣ ምስሎችን፣ ፋይሎችን፣ ቪዲዮዎችን እና ድምፆችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀመጥ፣ በቀላሉ አዲስ ማህደሮችን ለመፍጠር፣ ፋይሎችን በየፈርጁ ለማስቀመጥ እንዲሁም ለተጠቃሚዎች በማንኛውም ጊዜ በቀላሉ እንዲጠቀሙ ለማድረግ በሚያስችል መንገድ የተዘጋጀ ነው፡፡ ቴሌስቶሬጅ የዘኔክሰስ ተጠቃሚዎች ፋይሎቻቸውን በቴሌክላውድ እንዲያስቀምጡ በማስቻል በስልክ ዳታ ለማስቀመጥ ያለውን የስቶሬጅ ውስንነት በመቅረፍ ስልክ መጥፋት ወይም መበላሸት ላይ የሚነሱ ስጋቶችን ለማስወገድ እንዲሁም የዲጂታል ይዘቶችን (digital contents) በፊቸር ስልካቸው (basic feature phone) አማካኝነት እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው፡፡
ዘኔክሰስ ክላውድ ወርክስፔስ ሶሉሽን: ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ሊሰፋ የሚችል እና ተለዋዋጭ
የክላውድ ወርክስፔስ ሶሉሽን ቢዝነሶችን፣ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ቨርቹዋል ዴስክቶፖችን እና አፕሊኬሽኖችን ከማንኛውም ዲቫይስ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ሲሆን፣ ይህም የአይ.ቲ ወጪዎችን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ይህ ሶሉሽን የሚቀርበው በዘኔክሰስ ፓድስ (PADs)፣ ላፕቶፖች እና ቲን ክሊያንትስ (thin clients) ማለትም ዘኔክሰስ R2025 Rise-Cloud Tab፣ ዘኔክሰስ E2025 ፕሮ ክላውድ ላፕቶፕ፣ ዘኔክሰስ E131 ፕሮ ክላውድ ላፕቶፕ እና ዘኔክሰስ E2025 አልትራ ቲን ክሊያንትስ (ultra thin clients thin client) አማካኝነት ነው።
ዋና ዋና ጥቅሞች፡
- የዳታ ደህንነት፡ አስተማማኝ ስቶሬጅ እና ፕሮሰሲንግ በክላውድ ውስጥ መኖር፣
- ሊያድግ የሚችልበት ሪሶርስ፡ ድርጅቶች ሲያድጉ፣ ሪሶርሳቸውን በቀላሉ ለማስፋፋት፣
- ወጪ ቆጣቢነት፡ “በተጠቀምንበት በመጠን ለመክፈል” (Pay-as-you-go) የሚያስችል በመሆኑ የካፒታል ወጪዎችን ይቀንሳል፣
- በራሱ ጊዜ ማዘመን እና መረጃዎችን ማስቀመጥ፣ የአይ.ቲ ማኔጅመንትን ለማቅለል እና የቢዝነስ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ፣
- ከፍተኛ ደህንነት፡ ለከፍተኛ ጥበቃ ባለ ብዙ ሽፋን ኢንክሪፕሽን እና የመዳረሻ ቁጥጥር (access control) ያለው መሆኑ የሚሉ ናቸው፡፡
ኩባንያችን ዲቫይሶችን፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትን፣ ቴሌብርን፣ የክላውድ ስቶሬጅ (cloud storage) እና ሶሉሽኖችን ለግለሰቦች እና ለኢንተርፕራይዞች በአንድ ወጥ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በጥቅል የሚያቀርብ ሲሆን፣ ይህ የተቀናጀ ጥቅል ደንበኞች ስለ ሃርድዌር፣ ኮኔክቲቪቲ ወይም የዳታ ደህንነት ሳይጨነቁ እንከን የለሽ የማኔጅመንት ተሞክሮ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ይህም ተጠቃሚዎች እና ድርጅቶች ዲጂታል አገልግሎቶችን የሚጠቀሙበትን መንገድ በእጅጉ ለመለወጥ እና ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ኩባንያችን፣ ከግል ኮሙኒኬሽን ጀምሮ እስከ ኢንተርፕራይዝ ኮምፒዩቲንግ ድረስ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት በአንድ ወጥ፣ አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ በሆነ የክላውድ ስነ-ምህዳር በኩል የሚያቀርብ ሲሆን፣ ሶሉሽኖቹ በሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ ትልቅ እምርታን የሚያበረክቱ ናቸው፡፡ ዲቫይሶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በክላውድ የተደገፈ የኮምፒዩቲንግ አገልግሎትን ከማቅረብ ባለፈ፣ ቁልፍ ለሆኑ ዘርፎች ደህንነቱ የተጠበቀ ዳታ ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን፣ ይህም ኩባንያችን ለደንበኞቹ በተመጣጣኝ ዋጋ አስተማማኝ የዲጂታል ሶሉሽኖችን ለማቅረብ ያለውን ጽኑ ፍላጎትና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
ኩባንያችን ዘኔክሰስ እና ክላውድ ወርክስፔስ ሶሉሽኖችን ተግባራዊ በማድረግ በአጠቃላይ የሀገራችን እና ከዚያም ባሻገር የዲጂታል ተደራሽነትን እና ኢኮኖሚ እድገትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለውን ስትራቴጂያዊ ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ በቀጣይም ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ዲቫይሶች በማቅረብ ግለሰቦች፣ ቢዝነሶች እና ማህበረሰቦቻች በአለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እያደረግን ያለውን ከፍተኛ ርብርብ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም
ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ.ም