ኢትዮ ቴሌኮምና ጅቡቲ ቴሌኮም የቀጠናውን ዲጂታል ሽግግር ለማፋጠን ያለመ ስትራቴጂያዊ ውይይት አካሄዱ
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና የጅቡቲ ቴሌኮም ዳይሬክተር ጀነራል መሀመድ አሰዌ የሁለቱን ኩባንያዎች የረጅም ጊዜ አጋርነት ለማጠናከር እንዲሁም በዲጂታል ሥነ-ምህዳር አዳዲስ ዕድሎችን ለመፈለግ ተስማምተዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል የተፈረመውን ሆራይዘን የፋይበር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ማፋጠን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጌትዌይ፣ ኔትወርክ፣ ቴሌብር፣ የኢንተርፕራይዝ፣ የሮሚንግ እና ሌሎች አገልግሎቶች ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት የ “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” ስትራቴጂ በአህጉሪቱ ዲጂታል ተደራሽነትን፣ ፈጠራንና ዘላቂ እድገትን የሚያፋጥኑ ጠንካራ አጋርነቶችን በመፍጠር የህዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በደንበኞች፣ ቴሌብር፣ ኢ-ኮሜርስ፣ አለም አቀፍ አገልግሎቶች፣ መሰረተ ልማት የተገኙ ስኬቶችን ያብራሩ ሲሆን የአፍሪካን ዲጂታል ሽግግር ለማፋጠን በፋይበር ቀጠናውን ትስስር ማጠናከር ላይም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጅቡቲ ቴሌኮም ዳይሬክተር ጀነራል በበኩላቸው ለአጋርነቱ ያላቸውን ጠንካራ ቁርጠኝነት በማረጋገጥ በአፍሪካ ኦፕሬተሮች መካከል ስትራቴጂያዊ ትብብርን ለማጠናከር አርአያ ለመሆን ቃል ገብተዋል።
አክለውም እያደገ የመጣውን የአለም አቀፍ ፍላጎት ለማርካት ያላቸውን አቅም የገለጹ ሲሆን፣ የቴሌብር ፈጣን እድገትን በማድነቅ ለወደፊቱ ድንበር ተሸጋሪ የዲጂታል ፋይናንስ ለማድረግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አመልክተዋል።
ኩባንያችን የዲጂታል ዕድገት ተደራሽ ለማድረግ የጋራ ራዕይ በመቅረጽ የአፍሪካ ዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ ቀዳሚ አንቀሳቃሾች ለመሆን ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም