ኩባንያችን በረጅም ዘመን አገልግሎቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎን ለማረጋገጥ፣ ለማብቃት እንዲሁም በየደረጃው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል ማኀበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ከማሕበረሰቡ ጋር አብሮ የዘለቀ የሃገር አለኝታ መሆኑ ይታወቃል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ47ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን/ ማርች 8ን የዲጂታል አካታችነት ለፆታ እኩልነት በሚል መሪ ቃል አክብሯል፡፡

ኩባንያችን የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ባከበረበት ወቅትም የአፍሪካ መዲናና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም የቱሪስት መስህብ እየሆነች የመጣችውን አዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች ውበትና ገጽታ እንዲፈካ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ ምቹና ጽዱ ትሆን ዘንድ በጽዳት ሥራ ላይ ለተሰማሩ እና የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ከ122 ወረዳዎች የተውጣጡ 353 ጀግና ሴት የጽዳት ሠራተኞች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ ስልኮችን ለእያንዳንዳቸው በስጦታ በማበርከት በዕለት ተዕለት ኑሮ እና ተግባራትን ለመከወን በዘመናችን ግድ እያለ የመጣውን የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ በተለይም ሽልማቱ ሴቶች የዲጂታል ቴክኖሎጂና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንዲሁም የዲጂታል ኢኮኖሚ ተካታችነትንና እኩልነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ኩባንያችን የ2015 ዓ.ም ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ እስከ 25% ቅናሽ የተደረገበት ለ2 ቀናት የሚቆይ የሴቶች ጥቅል ያዘጋጀ ሲሆን ጥቅሉን ከተጨማሪ 10% ስጦታ ጋር በቴሌብር እንዲሁም በማይ ኢትዮቴል እና በ*999# ማቅረቡን በደስታ ይገልጻል፡፡

ሴቶችን ማካተትና ማብቃት የኩባንያችን አንዱ እሴት እና መገለጫ በመሆኑ፣ የዛሬውን ሳይጨምር ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ ሴቶች የመረጃ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመደገፍ 54.4 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ከ70 ሺህ በላይ የሞባይል ቀፎዎችን ያበረከተ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመትም ዓለምአቀፍን የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በእቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ት/ቤት ለሚማሩ ለ480 ሴት ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የሚሆን የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ እንዲሁም በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 10 ሴት ተማሪዎች ደግሞ የታብሌት ሽልማት አበርክቷል፡፡

በተጨማሪም ሴት መምህራንን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደግፈው በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ለመደገፍ 50 ላፕቶና 200 ዘመናዊ የስልክ ቀፎ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሴት መምህራን ሽልማት መስጠቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ሃገራችንን ለ129 ዓመታት በቁርጠኝነት በማገልገል ላይ የሚገኘው ኩባንያችን፣ የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ለመደገፍና የአስቻይነት ሚናውን ለመጫወት በየጊዜው አዳዲስ አገልግሎቶችን ከማቅረብ ባሻገር ማህበረሰባችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በመቅረጽ፣ የዲጂታል ሶሉሽንስ አገልግሎቶችን በማስፋፋት፣ ሃገራዊና ማህበራዊ የጣምራ ሃላፊነቱን በመወጣት በተለይም የሴቶችን ተሳትፎ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣ ሴቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን በቀላሉ እንዲተገብሩ በማገዝ እና የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች ተቋዳሽ እንዲሆኑ በማድረግ ራሳቸውንም ሆነ ማህበረሰባቸውን እንዲጠቅሙ የበኩሉን አሰተዋጽኦ ማበርከቱን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

                         

                            ኢትዮ ቴሌኮም

                       የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives